በደቡብ ክልል ሐሰተኛ የብቃት ማረጋገጫ አቅራቢዎች ተበራክተዋል


ከተለያዩ ተቋማት በመመረቅ ሥራ ለመቀጠር ወሳኝ ለሆነው የብቃት ማረጋገጫ ሐሰተኛ ማስረጃ የሚያቀርቡ ግለሰቦች እየበዙ መሆናቸውን፣ አንዳንድ ቀጣሪ ድርጅቶች ሲገልጹ፣ የደቡብ ክልል ልቀት ማዕከል ችግሩን ለመቅረፍ ድረ ገጽ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
በተደጋጋሚ ምዘናውን ወስደው ብቁ መሆን ያልቻሉ በቢዝነስና በጤና ዘርፎች በተለይም የደረጃ ሦስትና አራት ዲፕሎማ የተወሰኑ ተመራቂዎች ነን የሚሉ፣ ሐሰተኛውን ሰነድ በማሠራት መጠቀም እንደ አማራጭ መውሰዳቸውን ድርጅቶቹ ጠቁመው፣ ትክክለኛውንና ሐሰተኛውን ለመለየት መቸገራቸውን ይናገራሉ፡፡


የደቡብ ክልል የልቀት ማዕከል በበኩሉ ሐሰተኛ የብቃት ማረጋገጫ ለሥራ ውድድር የሚያቀርቡ ግለሰቦች መኖራቸውን አምኖ፣ በርካታ ቀጣሪ መሥርያ ቤቶች እንዲጣራላቸው በሚልኩት ጥያቄ መሠረት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሐሰተኛ ማስረጃዎችን አጣርቶ ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቁን አስረድቷል፡፡ 



በትምህርት፣ በቢዝነስ፣ በጤናና በሌሎች ተያያዥ የትምህርት ዘርፎች ለመጠርጠር አስቸጋሪ የሆኑ የምዘና ብቃት ማረጋጫዎች እንደሚቀርቡና ለማዕከሉ ካልተላከ በስተቀር መለየት ከባድ እንደሆነ በሐዋሳ ከተማ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ ቀጣሪ ተቋማት ይገልጻሉ፡፡ “ለሥራ ቅጥር ማስታወቂያ አውጥተን ካልተጠራጠርን መለየት የማይቻሉ የሲኦሲ መረጃዎች ይቀርባሉ፡፡ ሐሰተኛ መሆናቸውን ማዕከሉ አጣርቶ ሲልክልን ብቻ ነው ምናውቀው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ችግሮቹን ካየን በኋላ ስንቀጥር ወደ ማዕከሉ ለመላክ ተገደናል፤” በማለት የሚናገሩት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአንድ የግል ድርጅት አስተዳደር ኃላፊ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አስቸኳይ ቅጥር ለማድረግ እንኳ እምነት ማጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ 



“ለሦስትና ለአራት ዓመታት በአግባቡ የሠለጠነ ባለሙያ የምዘና ፈተናውን እንዴት ማለፍ ይሳነዋል?” ብለው የሚጠይቁት በማስተማር ሥራ ላይ የተሠማሩት መምህር ደረጀ በቀለ ናቸው፡፡ ምዘናውን ወስደው ብቁ ያልሆኑት ባለሙያዎች አንድም ብቁ ሳይሆኑ ነው ከተቋሙ የወጡት፡፡ አሊያም የሠለጠኑበት ተቋም ብቁ አይደለም ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሐሰተኛ ማስረጃ ፍለጋ የሚሄዱት ቁጥር መበራከት ምንም ሊገርም አይገባም በማለት ያብራራሉ፡፡ 



በተመሳሳይ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ትምህርት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እየሠሩ የሚገኙትና ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ መምህር፣ የብቃት ምዘናውን የሚያልፉት ቁጥር ማነስ የትምህርት ጥራት ያለበትን ሁኔታ ያሳያል ይላሉ፡፡ “ብቃት ከተማሪው፣ ከተቋሙ፣ ከሥልጠናው ሥርዓትና ከተቋሙ የሰው ኃይል ዝግጁነት ጋር የሚያያዝ ነው፤” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ 



የደቡብ ክልል የልቀት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ዳና ስለጉዳዩ ተጠይቀው፣ የብቃት ምዘናውን ወስደው ብቁ የሚሆኑት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከ25 በመቶ እንደማይበልጡና በዚህ ዓመት አጋማሽ ወደ 36 በመቶ ከፍ ማድረግ እንደተቻለ ይገልጻሉ፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት 45,117 ባለሙያዎች ተመዝነው 11,279 ያህሉ ብቻ ብቁ እንደሆኑ፣ ይህም በመቶኛ ሲሰላ 25 በመቶ እንደሆነ ያብራሩት አቶ ሳሙኤል፣ ሐሰተኛ የብቃት ማስረጃዎችን ማጣራት ተጨማሪ ሥራ እንደሆነባቸው ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡ ከታህሳስ 2004 ዓ.ም ጀምሮ ከቀረቡት 1,560 የብቃት ማረጋገጫ ሰነዶች መካከል 675 ያህሉ ሐሰተኛ መሆናቸውን በማረጋገጥ ለጠያቂ መሥሪያ ቤቶች ማሳወቃቸውንም አስረድተዋል፡፡ 



ሐሰተኛ መረጃዎችን ካጣሩ በኋላ ስለተወሰዱት ዕርምጃዎች ተጠይቀው አቶ ሳሙኤል ሲመልሱ፣ “ለሚመለከተው የፖሊስ አካል አቅርበን ከክትትል ማነስ የተነሳ ግለሰቦቹ ወደ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ ከዞንና ከወረዳ የሚላኩትን በራሳቸው መንገድ ዕርምጃ እንዲወስዱ ከማሳወቅ ባለፈ መከታተል የምንችልበት አሠራር የለንም፤” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በተለይ በጤናው ዘርፍ የሚቀርቡ ሐሰተኛ የብቃት ማረጋገጫዎች መበራከታቸውንና ጉዳዩ በክልል ደረጃ አሳሳቢ በመሆኑ፣ የክልሉ ጤና ቢሮ ከተለያዩ የግል ተቋማት የተመረቁ የጤና ባለሙያዎችን እንደገና ለዘጠኝ ወራት በራሱ ወጪ አሠልጥኖ የብቃት ምዘና እንዲወስዱ እያዘጋጀ መሆኑን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 



የብቃት ማረጋገጫ ምዘና በደቡብ ክልል በቢዝነስና ጤና ዘርፍ መሰጠት የተጀመረው በ2001 ዓ.ም መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅትም ያለውን የብቃት ማነስ ችግርና የሐሰተኛ መረጃ አቅራቢዎችን ቁጥር ለመቀነስ በቅርቡ ይፋ የሚደረግ ድረ ገጽ ማዘጋጀታቸውን የማዕከሉ ኃላፊ አስታውቀዋል፡፡ አንድ ባለሙያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመዝኖ ብቁ ካልሆነ ለሁለተኛ ጊዜ እጥፍ ክፍያ ከፍሎ የሚመዘን መሆኑን፣ ለሦስተኛና ለመጨረሻ ጊዜ ተመዝኖ ብቃት ከሌለው ድጋሚ ፈተናውን መውሰድ አይችልም ብለዋል፡፡ በአማካይ እንደየትምህርቱ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመፈተን እስከ 300 ብር እንደሚከፈል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በአስፋው ብርሃኑ፣ ልዩ ዘጋቢ ከሐዋሳ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር