ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት ዘርፍ ዕድገት ብታሳይም ከዝቅተኛው ጎራ አልወጣችም


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ባለፈው ዓርብ እዚህ ይፋ ያደረገው የዚህ ዓመት የሰብዓዊ ልማት ሪፖርት፣ የደቡባዊው ንፍቅ ትንሳዔን የሚያበስር ነበር፡፡
ስያሜውን ‹‹The Rise of the South›› በማለት የሰየመውን ሪፖርቱን ይፋ ሲያደርግ፣ የሩቅ ምሥራቅ አገሮችና ላቲኖቹ የዓለምን ሚዛን ወደራሳቸው እንዳጋደሉት በመተንተን ነው፡፡

እያደጉ ካሉ አገሮች ቻይና፣ ብራዚልና ህንድ የዓለምን የዕድገትና የኢኮኖሚ ሒደት ወደራሳቸው እንዲዘነብል ከማድረግ አልፈው፣ በሰብዓዊ ልማት ዘርፎች ቀዳሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ልማት ፕሮግራሙ ይፋ አድርጓል፡፡ ያደጉት አገሮችን ሰሜናውያኑ እያለ የጠራቸው ይህ ሪፖርት፣ ባሉበት እየሮጡ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡

ሪፖርቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፋ ከተደረገ በኋላ በማግስቱ እዚህ ሲለቀቅ በኢትዮጵያ የዩኤንዲፒ ቋሚ ተወካይና የተመድ አስተባባሪ ኡውጂን ኦውሱ እንዳስታወቁት፣ የዓለም የኃይል ሚዛን ወደደቡብ ንፍቅ አዘንብሏል፡፡ በተለይ ቻይና፣ ብራዚልና ህንድ ከነብርነት በላይ የሚፈናጠር ኢኮኖሚ በመገንባታቸው ሳቢያ የኃይል ሚዛኑን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ ተነግሮላቸዋል፡፡ ቻይና ያስዘመገበችው የመጠባበቂያ ክምችት ከሦስት ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ በሌላ በኩል እንደፈረንሳይ ያለው አገር የመጠባበቂያ ክምችቱ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሆኖ መመዝገቡ፣ ለታዳጊዎቹ ደቡባውያን ፈርጣማነት አመላካች ነው፡፡

እንዲህ በኢኮኖሚም፣ በሰብዓዊ ልማትም የሚገሰግሱት ታዳጊ አገሮች ቢያንስ የአንድ ቢሊዮን ሕዝባቸው ድምፅ በአግባቡ እንደማይደመጥ፣ በዓለም መድረኮችም ዘንድ በአግባቡ እንዳልተወከለ ኦውሱ ይናገራሉ፡፡ ለደቡቦቹ ሕዝቦች እንደድሮው የሚቀጥል ነገር ያለ አይመስልም ያሉት ተወካዩ፣ ቻይና ብራዚልና ህንድ ያስመዘገቡት ለውጥ፣ በሰሜን አሜሪካና በሰሜን አውሮፓ ለአንድ ሺሕ ዓመታት ተይዞ የቆየውን የኢኮኖሚ የበላይነት የሰበረ እንደሆነ በማመልከት ነበር፡፡ በዚሁ ሳያበቃም በ40 ያህል የዓለም ዝቅተኛ አገሮች የሰብዓዊ ልማት መሻሻሎች መታየታቸውን በዘንድሮው ሪፖርት የተቃኘ ሲሆን ውጤቱ ሊመጣ የቻለውም አብዛኞቹ አገሮች፣ ሕዝባቸው ላይ ኢንቨስት ማድረግን እየለመዱ በመምጣቸው ነው ተብሏል፡፡

 በንግድ፣ በምርት አቅርቦት፣ መካከለኛ ገቢ ባለው ሕዝብ ቁጥር ብዛት እያሻቀቡ፣ ዓለምን ከኋላ ማስከተል የጀመሩት የደቡብ ንቅፍ አገሮች፣ እ.ኤ.አ. በ2020 ከሚኖረውና 3.2 ቢሊዮን ከሚደርሰው መካከለኛ ገቢ ያለው ሕዝብ ቁጥር ውስጥ ከግማሽ በላዩን የሚያቅፉት የእስያ ፓስፊክ አገሮች ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ፣ ከሰሐራ በታች ያሉት የአፍሪካ አገሮች ግን ምንም እንኳ የማይናቅ ቁጥር የሚያስመዘግብ ሕዝባቸው ወደመካከለኛ ገቢ ክልሉ የሚወጣጣ ቢሆንም ቁጥሩ ከ57 ሚሊዮን ሕዝብ እንደማይበልጥ አስፍሯል፡፡ በሌሎች ግምቶች ደግሞ የአፍሪካ መካከለኛ ገቢ አስመዝጋቢ ሕዝብ ቁጥር ከ300 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ (በነገራችን ላይ መካከለኛ ገቢ ያለው ሰው ማለት በቀን ከ10 እስከ 100 ዶላር የሚያገኝ ወይም ወጪ ማድረግ የሚችል እንደሆነ ሪፖርቱ አትቷል)

ሦስቶቹ አገሮች (ቻይና፣ ብራዚልና ህንድ) በርካታ ሚሊዮኖቻቸውን ከድህነት ማጥ እንዳወጡ ሲነገርላቸው፣ በአፍሪካም በተለይ ከሰሐራ በታች፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ 14 አገሮች ላስመዘገቡት የሰብዓዊ ልማት መሻሻል ከእነዚህ አገሮች ጋር ሲያካሂዱ የቆዩት የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ እንዲሁም የልማት ትብብር ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1992 ቻይና ከሰሐራ በታች ከሚገኙ አገሮች ጋር የነበራት የንግድ ግንኙነት መጠን አንድ ቢሊዮን ዶላር ብቻ ያስመዘገበ ነበር፡፡ በ2011 ግን መጠኑ ወደ140 ቢሊዮን ዶላር አሻቅቧል፡፡

በሁለት አሥርት ውስጥ እንዲህ የተወረወረው የንግድ ግንኙነት፣ በተለይ እ.ኤ.አ ከ2000 ጀምሮ ኢትዮጵያና 13ቱ አፍሪካውያን ላሳዩት ዕድገት አስተዋጽኦ ቢያደረግም አሁንም ድረስ ግን አገሮቹ ከዝቅተኛው የሰብዓዊ ልማት ውጤት ኬላ ሊያልፉ አልቻሉም፡፡ ሆኖም ከፍተኛ ውጤት አስመዝጋቢዎች መሆናቸው በተመድ ሪፖርት ተረጋግጦላቸዋል፡፡ አንጎላ፣ ኢትዮጵያ፣ ሞሪሺየስ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳና ሴራሊዮን ከ14ቱ አገሮች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከኡጋንዳ ቀጥላ ሁለተኛዋ ከፍተኛ ውጤት አስመዝጋቢ አገር ናት ተብላለች፡፡ ከዓለም አገሮች ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ በ2012 በሰብዓዊ ልማት ከፍተኛ ውጤት አስመዝጋቢ ተብላለች፡፡  

ሰብዓዊ ልማት በጤና፣ በትምህርት፣ በኑሮ መሻሻል፣ በገቢ ማደግ፣ በምግብ መሻሻል በሕይወት ረጅም ጊዜ መቆየት ሳቢያና በመሳሰሉት ለውጦች የሰው ልጆች የሚያሳዩት ልማት ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢኮኖሚ ዕድገት የሚመዘንበት መሣርያ ነው፡፡ ሆኖም በአሁን ወቅት ዩኤንዲፒ፣ በሦስት ዋና ዋና መለኪያዎች ላይ አተኩሯል፡፡ ረዥምና ጤናማ ሕይወት፣ የዕውቀት ግብይትና በሕይወት የመቆያ ዕድሜ መጠንን ዋና መመዘኛዎቹ አድርጓል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት እስካሁን በዋናነት የሚሰላው ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገትን መሠረት በማድረግ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ ግን ሰብዓዊ ልማትም የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያ እንዲሆን መደረጉን ተከትሎ የአገሮች ኢኮኖሚ መገምገሚያ መሳርያ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ምንም እንኳ በአፍሪካ የሚታየው የሰብዓዊ ልማት ለውጥ ያን ያህል የሚያስጨበጭብ ባይሆንም ለውጥ እንደሚታይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም አሳውቋል፡፡ አሁንም ድረስ በዝቅተኛው እርከን ላይ እያሉ፣ ያስመዘገቡት ዕድገትና ለውጥ ከዓለም ቀዳሚ እንደሆኑ ከሚነገርላቸው አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ዝቅተኛው የሰብዓዊ ልማት ደረጃን ባታልፍም፣ በዘንድሮው የሰብዓዊ ልማት ሪፖርት መሠረት ከዓለም ሦስተኛዋ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛዋ ተብላለች፡፡

187 አገሮች ከተነጻጸሩበት የዘንድሮው የዓለም ሰብዓዊ ልማት ሪፖርት አኳያ ኢትዮጵያ የምትገኘው፣ በ173ኛው ደረጃ ላይ ነው፡፡ ሆኖም በ12 ዓመት ውስጥ የ44 በመቶ ዕድገት፣ ወይም በየዓመቱ በአማካይ የ3.1 ከመቶ ውጤት በማስመዝገብ እዚህ መድረሷ ቢነገርም፣ አምና ከነበራት ደረጃ ግን ቢያንስ በአንድ ቀንሳ ከ172ተኛነት ወደ 173ተኛ ዝቅ ማለቷን ሪፖርቱ አመለክቷል፡፡ ይህንን ዓይነት ልዩነት ለንጽጽር መጠቀም ወደተሳሳተ ድምዳሜ ይወስዳችኋል የሚለው ዩኤንዲፒ፣ በየዓመቱ የስሌትና የአሠራር ለውጥ እንደሚያደረግ፣ በአሃዞችና በስታቲስቲክስ መረጃዎች ሳቢያ ለውጦች ስለሚደረጉ የአምናው ከዘንድሮው ለንጽጽር መዋል የለበትም ይለናል፡፡

በኢትዮጵያ የአንድ ሰው በአማካይ የሕይወት ዘመን ዕድሜው 59.7 ዓመት እንደሆነ የሚገልጸው ይህ ሪፖርት፣ በ30 ዓመታት ውስጥ የ16 ዓመት ገደማ ጭማሪ እንደታየ ይገልጻል፡፡ ይኸውም ሰው ከተወለደ ጀምሮ፣ በዚህች ምድር በሕይወት የሚቆይበት ጊዜ እየተራዘመ እንደመጣ ለማሳየት ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ልማት ውጤት ዕድገት አሳይቷል ቢባልም ከዝቅተኛው እርከን ሊያስወጣት እንዳልቻለ የሚያመለክተው ይህ ሪፖርት፣ በዕድሜ ዘመን ቆይታ፣ በትምህርት እንዲሁም በገቢ እኩልነት አለመጣጣም ሳቢያም አሁንም ከዝቅተኞች፣ ዝቅተኛውን ደረጃ እንድትይዝ አስገድዷታል፡፡

ዩኤንዲፒ፣ እንደአዲስ አሠራር ባካተተው የሰብዓዊ ልማት ጠቋሚ መመዘኛ ውስጥ አገሮች የሚያስመዘግቡት ለውጥ እኩልነት የማይታይበት ከሆነና፣ የሰፋ ልዩነት የሚመዘገብ ከሆነ ያንን የሚያመዛዝንበት መስፈርትም አስቀምጧል፡፡ የሰብዓዊ ልማት ጠቋሚውን በተስተካከለው መመዘኛ መሠረት ሲታይም፣ በኢትዮጵያ የገቢ አለመመጣጠን በመኖሩ ምክንያት በሰብዓዊ ልማት ታስዘመግብ ትችል ከነበረው መጠን የ20.8 ከመቶ ውጤት እንድታጣ ሆኗል፡፡ መንግሥት የገቢ አለመመጣጠን መጠኑ (በድሃውና በሀብታሙ መካከል ያለው ልዩነት) እየጠበበ ነው ቢልም፣ ዩኤንዲፒ የሚታየው ክፍተት አገሪቱ ካስመዘገበችው የሰብዓዊ ልማት ውጤት ላይ ተቀናሽ እንዲደረግባት ያደረጋት ይኸው የገቢ ልዩነት መሆኑን አመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የሚታየው በሕይወት የመቆየት የዕድሜ መጠንም እንዲሁ በሀብታምና በድሃው መካከል ክፍተት የሚያሳይ በመሆኑ ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ዘንድሮ ካስመዘገበችው ውጤት ላይ የ38.3 በመቶ ውጤት አሳጥቷታል፡፡ በትምህርትም እንዲሁ ነው፡፡ በተማረውና ባልተማረው መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት እንደዚሁ ውጤት የሚያስቀንስ ሆኖ ስለተገኘ የ35.4 ከመቶ ውጤት እንድታጣ አድርጓታል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ታገኝ ይገባት ከነበረው ውጤት ላይ የ32 በመቶ ውጤት አጥታለች፡፡ ይኸውም የገቢ፣ የትምህርትና በሕይወት የመቆያ ዕድሜ መጠን ላይ አለመመጣጠንና ሰፊ ልዩነት የሚታይ መሆኑን በማመላከት ነው፡፡ 

ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ከስምንቱ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ውስጥ ስድስቱን ልታሳካ እንደምትችል ኦውሱ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በትህምርትና በጤና ዘርፎች ያስመዘገችው ዕድገት ከዕርዳታ በሚገኝ ገንዘብ ከሆነና ዕርዳታውን የሚሰጡት ደግሞ ሰሜናውያኑ አገሮች ከሆኑ ዘንዳ፣ ለውጡ ችግር ውስጥ አይገባም ወይ የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው፣ በዩኤንዲፒ የኢኮኖሚ ጉዳይ አማካሪው ሳሙኤል ብዋሊያ ሲመልሱ፣ ምንም እንኳ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የሰብዓዊ ልማት ፕሮግራሞች የለጋሽ እጆች ቢበረክቱባቸውም፣ መንግሥት የሚሰበስበው የአገር ውስጥ ገቢ እያደገ በመምጣቱ ችግር አይሆንም፣ የሚሰበስበው ታክስና ግብር በራሱ አቅም የሰብዓዊ ልማት ሥራዎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያችለው ነው የሚል ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/business-and-economy/item/1163-%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%89%A0%E1%88%B0%E1%89%A5%E1%8B%93%E1%8B%8A-%E1%88%8D%E1%88%9B%E1%89%B5-%E1%8B%98%E1%88%AD%E1%8D%8D-%E1%8B%95%E1%8B%B5%E1%8C%88%E1%89%B5-%E1%89%A5%E1%89%B3%E1%88%B3%E1%8B%AD%E1%88%9D-%E1%8A%A8%E1%8B%9D%E1%89%85%E1%89%B0%E1%8A%9B%E1%8B%8D-%E1%8C%8E%E1%88%AB-%E1%8A%A0%E1%88%8D%E1%8B%88%E1%8C%A3%E1%89%BD%E1%88%9D

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር