የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከአለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዋሳ መጋቢት 05/2005 በምርምር፣ በመማር ማስተማርና በህብረተሰብ አገልግሎት በአለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን ከተለያዩ አለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአሜሪካ ከሚገኘው ኬንታኪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለው የጋራ መግባቢያ ሰነድ ትናንት ተፈራርሟል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና ማርከቲንግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬከተር አቶ መልሰው ደጀነ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ጥራቱና ብቃቱ የተረጋገጠ ፍትሃዊና ተገቢነት ያለው የትምህርት፣ የምርምርና የህብረተሰብ አገልግሎት በመስጠት በአገርና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ በዩኒቨርሲቲ የሚሰጠውን ትምህርት በጥናትና በፈጠራ ስራ በማስደገፍ፣ህብረተሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍና አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር የተገኘውን ውጤት በአግባቡ ለመጠቀም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው ትምህርት ከኢኮኖሚ ፖሊሲው ጋር በማናበብ በኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ ገብተው በንቃት በመሳተፍ የተጀመረውን ዕድገት ማስቀጠል የሚችል ዜጋ ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዛሬውን ጨምሮ ከ30 በላይ በአፍሪካ ፣በአውሮፓና አሜሪካ ከሚገኙ አለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጥናትና ምርምር፣ በትምህርትና ስልጠና፣ በህብረተሰብ አገልግሎና በመምህራን ልማት ተባብሮ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት መፈራረሙን ጠቁመዋል፡፡ በዚሁም በርካታ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተለይ መምህራን የአጭር ፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስልጠና መውሰዳቸውንና የተወሰኑም አሁንም በመከታተል ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ የዛሬው ስምምነት የዚሁ መርሀ ግብር አንዱ አካል መሆኑን የገለጹት አቶ መልሰው ኬንታኪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በውሃ ብዝሀ ህይወት ላይ የካበተ ልምድ ያለው ተቋም በመሆኑ ሃዋሳ ዪኑቨርሲቲ በሃዋሳ ሀይቅ ዙሪያ ሂደው የጥናትና ምርምር ስራ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና ሶስተኛ ድግሪ ፕሮግራሞች ከ31 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ አቶ መልሰው አስታውስው ከነዚህም መካከል 7 ሺህ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ብለዋል፡፡ የኬንታኪ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት ፕሮፌሰር ሜሪ ሲያስ በበኩላቸው የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለመስራት ያለውን ፍላጎትና ተሳሽነትን በማድነቅ በመምህራን ልማት፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በውሃ ብዝሀ ህይወት ላይ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ በማስተባበር በሙሉ አቅምና ዕውቀታቸው ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸው ገልፀዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=6309&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር