በደኢህዴን መሪነት የክልሉ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ጎልብቷል

አዋሳ፤ መጋቢት 10/2005/ዋኢማ/ - በደኢህዴን መሪነት የደቡብ ክልል ሕዝቦች በፈቃዳቸው የመሰረቱት ክልላዊ መስተጋብርና አንድነት በሀገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት መስክ ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲጎለብት ጠንካራ መሰረት መጣሉን የደኢህዴንና ኢህአዴግ ሊቀመንበር ገለጹ።

የደኢህዴንና ኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የደኢህዴን 8ኛ ጉባኤ ትናንት በሀዋሳ ከተማ ሲጀመር እንደገለጹት፤ በክልሉ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል የነበረው መስተጋብር በጋራ መልማትና አስተማማኝ ሰላም የማረጋገጥ ፍላጎት በመሆኑ ጠንካራ ክልል እንዲመሰርቱ አስችሏል።

ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሏቸው የታሪክ የስነ-ልቦናና የተለያዩ መስተጋብሮቻቸው በአንድነት በመሰረቱት ክልል በደኢህዴን አመራር ልዩነታችን ውበታችን አንድነታችን ጥንካሬያችን ሆኖ በተሃድሶ መስመር ላገኘነው ድልና ለተመዘገበው ፈጣን ልማት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

እስከ ደኢህዴን ሰባተኛ ጉባኤ በክልሉ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት የባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡ 7ኛው የድርጅቱ ጉባኤ ተከታታይ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ይህንን ዕድገት በማስቀጠል የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ማምጣት እንዳለበት ወስኖ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

ደኢህዴን የተከተለው መስመር ተከታታይና ፈጣን ልማትን ከማረጋገጥ ባሻገር የክልሉ ህዝቦች ከልማቱ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል የሚያረጋግጥ መሆኑን በተግባር እንዳስመሰከረ አቶ ኃይለማሪያም አስታውቀዋል።

ደኢህዴን የክልሉን ህዝቦች ከዳር እስከዳር የማንቀሳቀስ ብቃቱን በመጠቀም ልማትን ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲ በህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረጉን አስረድተዋል።

ንቅናቄው በህዝቡ ተሳትፎ ላይ በመመስረት መልካም አስተዳደር ለማስፈን ያደረገው ጥረት ውጤት ያስመዘገበበትና የተሃድሶው መስመር በልማት በሰላምና ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መስክ ተከታታይና ከፍተኛ ድሎችን ለመጎናጸፍ ያስቻለ ነው ብለዋል።

የክልሉ ህዝቦች በፈቃዳቸው የመሰረቱት ዴሞክራሲያዊ ክልላዊ መስተጋብርና አንድነት ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች አቅም መጎልበት ጠንካራ መሰረት ከመጣል ባሻገር የጋራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንዳስቻለ ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል።

8ኛው የድርጅቱ ጉባኤ የውይይት ነጥብ በሁሉም መስኮች የተገኘው ድል በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በተቀመጠው መሰረት ለውጥ ያልመጣበትን ምክንያት በማወቅ ላይ በማድረግ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ለይቶ በማስቀመጥና ለዕቅዱ ስኬት ርብርብ የሚደረግበት አቅጣጫ ማስቀመጥ ላይ መሆን እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

የደኢህዴን 8ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በሶስት ቀናት ቆይታው በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ የተከናወኑ ስራዎች ላይ በማተኮር በቀጣይ የሚያከናውናቸውን አቅጣጫዎች ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘገባ ያስረዳል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር