የሃዋሳ ከተማ አሰተዳደር ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ፡፡

አዋሳ የካቲት 27/2005 የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ስድስት ወራት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አስታወቁ ። የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ191 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ ከንቲባው አቶ ዮናስ ዮሰፍ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ገቢዉ የተሰበሰበዉ ቀጥታና ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች፣ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎትና ከሌሎች ገቢዎች ነዉ ። በከተማው የገቢ አስተዳደር ስራዎችን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ የታክስ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ በመደረጉ የተሰበሰበው ገቢ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል ። ገቢዉ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ191 ሚሊዮን 252 ሺህ 029 ብር ብልጫ እንዳለው አስታዉቀዋል ። በከተማ አስተዳደሩ ተቀርፆ እየተተገበረ ያለው የታክስ ማሻሻያ ፕሮግራም፣ አዳዲስ ግብር ከፋዮች ወደ ታክስ ስርዓቱ መግባታቸውና ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ግዴታውን በአግባቡ መወጣት መጀመሩ ለገቢው ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል። በግማሽ በጀት ዓመቱ የግብር ከፋዩን ቁጥር ለማሳደግ አመራሩ፣ ባለሙያውና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት በደረጃ ሀ እና ለ 1ሺህ 564 ግብር ከፋዮች ወደ ግብር ስርዓቱ መግባታቸውን የገለጹት አቶ ዮናስ እነዚህ ግብር ከፋዮች ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣት ጀምረዋል ብለዋል ። በተጨማሪ በከተማ አስተዳደሩ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን መጠቀም ያለባቸው ግብር ከፋዮች መሳሪያውን ገዝተው እንዲጠቀሙና የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ ጤናማና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን 1ሺህ 177 የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖችን ለግብር ከፋዩ ህብረተሰብ እንዲሸጥ መደረጉን ገልጠዋል ። በቀጣይ በከተማው የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የመረጃ ቴክኖሎጂ ስራን ለማጠናከር ከክልሉ ገቢዎች ባለስልጣንና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን የግብር፣ የአከራይ ተከራይ፣ የደረጃ ሀ፣ ለ፣ ና ሐ ፣ የመሬት እና ሌሎች መረጃዎች በዘመናዊ መልክ በኮምፒውተር የማደራጀት ስራዎች መከናወናቸውንም አቶ ዮናስ አስታዉቀዋል ።http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=6079&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር