በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን 3 ለ 1 አሸነፈ


በ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጋቢት 17/2005 ዓ.ም በይርጋለምና አርባ ምንጭ ሁለት ጨዋታዎች ተካሂደዋል፡፡
ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ 3 ለ 1 ተሸንፏል፡፡
ሙሉዓለም ጥላሁን ለኢትዮጵያ ቡና 2 ግቦችን በማስቆጠር ወደ ግብ ማግባቱ ሲመለስ ለብሄራዊ ቡድን የመጠራት ዕድለ ያገኘውን ኤፍሬም አሻሞ ቀሪዋን ግብ ለክለቡ በስሙ አስመዝግቧል፡፡
የሲዳማ ቡናን ብቸኛ ግብ ከመረብ ያገናኘው የቀድሞ የሙገር ሲሚንቶ አጥቂ ሚካዔል ጆርጅ ነው፡፡
በአርባምንጭ ከተማ አርባምንጭ ከነማ ከኢትዮጵያ መድህን ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ ባዶ ለባዶ ተጠናቋል፡፡
ውጤቶቹን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን እና የግብ ክፍያውን ከሀዋሳ እኩል በማድረስ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡ሲዳማ ቡና በ14 ነጥብ ባለበት 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
አንድ ነጥብ ያገኘው ኢትዮጵያ መድህን ከ8 ወደ 5ኛ ከፍ ያለ ሲሆን አርባምንጭ ከነማ ግን በ16 ነጥብ ባለበት 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ዛሬ መጋቢት 18/2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታድየም በ11 ሰዓት ተኩል ላይ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያ ውሀ ስራዎች እና ሙገር ሲሚንቶ ይጫወታሉ፡፡
በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሴቶች ጥሎ ማለፍ እግር ኳስ ውድድር ደደቢትና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለፍፃሜ ማለፋቸውን አረጋገጡ፡፡
የግማሽ ፍፃሜው የመልስ ጨዋታ መጋቢት 17/2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታድየም የተደረገ ሲሆን ደደቢት ሲዳማ ቡናን፣ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ኢትዮጵያ መድህንን 6 ለ 1 በሆነ ተመሳሳይ ውጤት አሸንፈዋል፡፡
10 ሰዓት ላይ አስቀድሞ በተጀመረው የደደቢትና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ስድስቱንም የደደቢት ግቦች በሁለት ተጫዋቾች ብቻ ተመዝግቧል፡፡
ብርቱካን ገ/ክርስቶስ እና ሰናይት ባሩዳ ሶስት ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ መስራት ችለዋል፡፡
ይርጋለም ላይ በተከናወነው የመጀመሪያ ጨዋታ ደደቢት 1 ለ 0 በሆነ በጠባብ ውጤት አሸንፎ የነበረ ሲሆን በ7 ለ 1 አጠቃላይ ውጤትም ለፍፃሜ መድረስ ችሏል፡፡
12 ሰዓት ላይ የተጀመረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ መድህን ጨዋታም በተመሳሳይ 6 ለ 1 የግብ ልዩነት ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት የተለያዩ ተጫዋቾች ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡
ለኢትዮጵያ መድህን ሰርካለም አሊ ብቸኛ ግብ አስገኝታለች ፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ11 ለ 1 አጠቃላይ ውጤት ነው ከደደቢት ጋር ለፍፃሜ የደረሰው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር