«የጊዳቦ መስኖ ግድብ ግንባታ በተያዘው ዓመት ይጠናቀቃል»-ኢንጂነር ብሥራት ደምሴ የጊዳቦ መስኖ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት የሥራ ሂደት ባለቤት



በአካባቢው እዚህም እዚያ ዛፎች ቁጥቋጦዎች በብዛት ይታያሉ። አልፎ አልፎ ከሚታዩ መለስተኛ ኮረብታዎች በስተቀር አካባቢው ሜዳማ ነው። በስፍራው ባሉት ሁለት መለስተኛ ኮረብታዎች መካከል የጊዳቦ ወንዝ ሰንጥቆ ያልፋል። በእዚህ ሥፍራ የጊዳቦ የመስኖ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል። ትልልቅ ገልባጭ ተሽከርካሪዎች ያለፋታ አሸዋ ያራግፋሉ። አፈር ይጭናሉ፤ ጠጠር ይደፋሉ። ኤክስካቫተሮች፣ ሎደሮችና ሌሎች ማሽነሪዎች በየሥፍራው ይቆፍራሉ። ይጠርጋሉ። ያስተካክላሉ። ይደመድማሉ።
ሠራተኞች በሥራ ተጠምደዋል። ከፊሎቹ አርማታ ይሞላሉ። የተወሰኑት ማሽነሪዎችን በማንቀሳቀስ ለሥራው የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ያቀርባሉ። ሁሉም ሠራተኞች የአካባቢው ሙቀት ሳይበግራቸው ጥድፊያ ላይ ናቸው። በጊዳቦ የመስኖ ግድብ ግንባታ ለማፋጠን 24 ሰዓት ሥራው አይቋረጥም። በሌሊት በየሥፍራው ያሉት ትልልቅ ፓውዛዎች ጨለማውን ገፈው ብርሃን አላብሰው ታል። በሌሊቱ ግማሾቹ ሠራተኞች ሲያርፉ ቀሪዎቹ ሌሊቱን በሙሉ ሲሰሩ ያነጋሉ።
የጊዳቦ የመስኖ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለቤትነት በአማካሪው የውሃ ሥራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት እና በውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ተቋራጭነት በኦሮሚያና በደቡብ አጐራባች ክልሎች ውስጥ ከ13ሺ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት የሚገነባ ፕሮጀክት ነው። ግድቡ የሚገነባው በጊዳቦ ወንዝ ላይ ነው። ፕሮጀክቱ መንግሥት በመደበው ከ258 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተገነባ ይገኛል።
ይህ ፕሮጀክት ከተጀመረ ከሁለት ዓመት በላይ እንደሆነው የሚገልጹት በውሃ ሥራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት የፕሮጀክቱ አማካሪ መሐንዲስ ኃላፊ ኢንጂነር ብርሃኑ ውቤ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት በፕሮጀክት ግንባታው የግድብ፣ የትርፍ ውሃ ማስወገጃ የተያዘ ውሃ መጥለፊያ ማማ፣ የወንዝ ውሃ ማስቀየሻ የመስኖ ውሃ ወደ ዋናው ቦይ መውሰጃ ቱቦ የሚያካትት ነው። በተጨማሪም የጐርፍ ውሃ መከላከያ ግንባታዎችን ያጠቃልላል።
ፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ካለበት ጊዜ አኳያ ዘግይቷል። የፕሮጀክቱ አማካሪ ግን ለመዘግየቱ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ ባይ ናቸው። ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል ደግሞ የግድቡን የማልማት አቅም ለመጨመር ሲባል የዲዛይን ለውጥ መደረጉ፣ በቁፋሮ ጊዜ የከርሰ ምድር ውሃ በቅርብ ርቀት አለማጋጠሙ፣ ለሥራው ተመጣጣኝ የግንባታ መሣሪያዎች አደረጃጀትና በቂ የግንባታ ግብአቶች በወቅቱ አለመቅረባቸው እና ረጅም ጊዜ የቆየ የዝናብ ወራት ማጋጠሙን በዋናነት ይጠቅሳሉ።
ይሁንና በአሁኑ ጊዜ እነዚህን ችግሮች መፍታት በመቻሉ የግድቡ ግንባታ በመፋጠን ላይ ነው። በተለይ ተቋራጩ ተመጣጣኝ የግንባታ መሣሪያ ዎችና የግንባታ ግብአቶችን በወቅቱ እንዲያሟላ በመደረጉ፤ ለአፈጻጸም መሻሻል ከጥቅምት ወር 2005 .ም ጀምሮ 24 ሰዓት ሥራው መሠራቱ እና የሰው ኃይል አደረጃጀትን ማስተካከል በመቻሉ፤ የግንባታ ሂደቱን ለማፋጠን የተወሰዱት እርምጃዎች መፍትሄ እያስገኙ መሆኑን ነው ያመለከቱት። በአሁኑ ጊዜም አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 43 በመቶ ደርሷል።
አማካሪ መሐንዲሱ ድርጅት የግድብ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጥራት እንዲከናወን የማድረግ ኃላፊነት አለበት። ይህን ድርሻውን በሚገባ እየተወጣ ይገኛል ይላሉ። ፕሮጀክቱ እስከአሁን ከ200በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ይህም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ከመፍጠሩ በላይ ሠራተኞቹ ሙያና ልምድ እንዲቀስሙ ዕድል ይፈጥራል።
ግድቡ ሁለት ተራራዎችን የሚያገናኝ ነው። ይህም ከ350 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ግድብ ይሆናል ያሉን ደግሞ በውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የጊዳቦ የመስኖ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት የሥራ ሂደት ባለቤት ኢንጂነር ብሥራት ደምሴ ናቸው። እርሳቸውም በግድቡ ግንባታ ወቅት ያልተጠበቁ ሁኔታዎች በማጋጠማቸው ግንባታው መዘግየቱን አልሸሸጉም። ይሁን እንጂ ላጋጠሙ ችግሮች መፍትሄ በመፈለግና በመቋቋም በተከናወነው ሥራ የግድቡን መሠረት ወደታች 13 ሜትር በመቆፈር የነበረውን አፈር በማውጣት በሌላ አፈር መተካት መቻሉን ያመለክታሉ። የትርፍ ውሃ ማስተንፈሻ ሥራውም ከ12ሺ ሜትሪክ ኩብ በላይ ኮንክሪት ሙሌት ሥራም ማከናወን ተችሏል።
በተጨማሪም ግድቡን ለመሥራት እንዲያመች ወንዙን አቅጣጫ የማስቀየር ሥራ ተሰርቷል። እነዚህ ሥራዎችን ማጠናቀቅ በመቻሉም በተያዘው ዓመት መጨረሻ አጠቃላይ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ርብርብ በመደረግ ላይ ነው ይላሉ። እስከአሁን የተሠራውም ከአጠቃላይ ግንባታው 43 በመቶ ነው። ከእዚህ አኳያ እንዴት በአንድ ዓመት ሊጠናቀቅ ይችላልየሚል ጥያቄ አቅርበንላቸው፤ አቶ ብሥራት ሲመልሱ በግድብ ግንባታ ብዙ ጊዜ የሚፈጀው መሠረቱ ነው። «የመሠረት ሥራውን አሁን ጨርሰናል። ቀሪው ሥራ የሚሆነው የግድቡን ሙሌት ይሆናል። ይህ ደግሞ የግብአትና የማሽነሪ አቅርቦት ካለ ብዙ ጊዜ የሚፈጅ ሥራ አይደለም። በእዚህ ላይ ቀንና ለሊት በመሥራት ላይ ስለሆንን በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል የሚል እምነት አለኝ» ብለዋል።
እንደ ኢንጂነር ብሥራት ገለጻ፤ የጊዳቦ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 66 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም ይኖረዋል። ውሃው አራት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ወደ ኋላ የሚተኛ ይሆናል። ይህም የአካባቢው ሰዎች ዓሣ በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል። በሁለቱ አጎራባች ክልሎች ማለትም በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች የሚገኙ አርብቶ አደሮችና ኢንቨስተሮችም በመስኖ ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረግ ይሆናል።
ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ለምታደርገው ጥረት አንዱ ማሳያ ነው። በተለይ አካባቢው አርብቶ አደር የሚኖርበት በመሆኑ አርብቶ አደሩ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ኑሮውን ከመግፋት ይልቅ በአንድ ቦታ ሰፍሮ የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖርና ከከብት እርባታ ጐን ለጐንም የእርሻ ሥራውን እንዲጀምር የሚደረግ ፕሮጀክት ነው። በእዚህ አካባቢ ኢንቨስተሮች መኖራቸው ደግሞ መስኖ በመጠቀም ገበያ ተኮር ምርቶችን በዓመት ሁለት ጊዜ አምርቶ ወደ ውጪ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ ያስችላል።
መንግሥት የውሃ ሀብቱን በአግባቡ በመጠቀም ኢትዮጵያ ከተመጽዋችነት እንድትላቀቅ ብሎም የብልጽግና ማማ ላይ እንድትወጣ በሀገሪቱ በአራቱም ማዕዘናት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ይገኛል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ዋና ዓላማቸው ደግሞ የኅብረተሰቡን ኑሮ ማሻሻልና ሀገሪቱን ለማሳደግ ያለሙ ናቸው። በእዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የኅብረተሰቡ ኑሮ እየተሻሻለ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎችም ፕሮጀክቶቹ በሚፈጥሩት የሥራ ዕድል በብዙ መልኩ ተጠቃሚ ናቸው።
ወጣት በላይ አበበ በእዚሁ አካባቢ ፈንታሌ ወረዳ ቀበሌ 03 ነዋሪ ነው። የጊዳቦ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት መጀመሩ ለእሱም ሆነ ለአካባቢው ነዋሪዎች ብዙ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ይናገራል። በፕሮጀክቱ ተቀጥሮ መሥራት ከጀመረ ዘጠኝ ወራትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ዘጠኝ ወራቶች በቀን በአናፂነት ሙያ ከሚከፈለው 65 ብር በላይ አዳዲስ ነገሮችን ማየትና መቅሰም መቻሉን ይገልጻል።
ይህም በቀጣይ በተለያዩ ፕሮጀክቶች በምሠራበት ጊዜ የተሻለ ሥራ መሥራት ያስችለኛል ነው ያለው። ፕሮጀክቱም ለአካባቢው ነዋሪዎች በፈጠረው የሥራ ዕድል በሚያገኙት ገቢ ተጠቃሚ ከመሆን ጐን ለጐን ሙያ ቀስመው እንዲወጡ የሚያደርግ የሙያ ትምህርት ቤት መሆኑን ይናገራል። እንደ በላይ ሁሉ ብዙ የአካባቢው ወጣቶች በተለያዩ ሥራዎች ተሰማርተው ሙያ እየቀሰሙ መሆኑን ከተመለከትነው ተረድተናል።
ይህንኑ አቶ ዳንኤል መንገሻ ያረጋግጥልናል። በጓንጓ ወረዳ ሰሚሮ ቀበሌ በከብት እርባታና አልፎ አልፎ በእርሻ ሲተዳደር ቆይቷል። ሁለት ልጆቹን ለማስተማር ከእርሻና ከብት እርባታ ከሚያገኘው ገቢ በተጨማሪ ሌላ ገቢ ለማግኘት ሲል ወደ ፕሮጀክቱ በመምጣት በአናፂ ረዳትነት መቀጠሩን ነግሮናል። በእዚህም ገቢ ከማገኘቱ ባሻገር የአናፂነት ሙያ መማር ችሏል። ሙያውም የወደፊት ኑሮውን ለማሻሻል የሚረዳው እንደሆነ እምነት አለው።
የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ ምን ታደርጋለህብለን አቶ ዳንኤልን ጠየቅነው። እኔ አርሶ አደር ነኝ፤ ግድቡ ለመስኖ ሥራ ስለሚውል በመስኖ የማልማት ዕቅድ አለኝ። ከእዚህ ጐን ለጐንም ከፕሮጀክቱ በተማርኩት የአናፂነት ሙያ በመሰማራት ኑሮዬን ለማሻሻል እሠራለሁ ብሏል።
እንደ ወጣት በላይና አቶ ዳንኤል ሁሉ በፕሮጀክቱ የሚሠሩ ከ200 በላይ ሠራተኞችም የወደፊት ኑሮአቸውን ለማሻሻል ፕሮጀክቱ የሙያ ስንቅ አስቋጥሯቸዋል። በቀጣይ ወደ ልማቱ ሲገባ የጥቅሙ ተካፋይ ይሆናሉ። እንደነዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ከሚያስገኙት ጥቅም ባሻገር በግንባታ ሂደት ላይ እያሉም ጭምር ለአካባቢው ነዋሪ የገቢ ምንጭና የሙያ ትምህርት ቤት መሆን የሚችሉ ማዕከል ናቸው። ከአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ ለእዚህ ሃሣብ ማጠናከሪያ የምትሆነን ወጣት ሲሳይ ናስር ናት።
ይህች ወጣት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የውሃ ሀብትና መስኖ ምህንድስና ተማሪ ነች። እሷና ስድስት የትምርት ቤት ባልደረቦቿ በመስኖ ምህንድስና የተግባር ልምምድ ለማድረግ ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው የጊዳቦ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት መምጣታቸውን ነግራናለች። በፕሮጀክቱ ላይ ከሁለት ወር በላይ መቆየታቸውን ትገልጻለች። በእዚህ ጊዜ ውስጥም በዩኒቨርሲቲው በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የተማሩትን በተግባር ማየታቸውን ትናገራለች። ይህም ክህሎታችን ይበልጥ እንዲዳብር ያደርጋል ባይ ናት።
በቀጣይም ትምህርቱን አጠናቅቀው ወደ ሥራ በሚገቡበት ጊዜ መደናገርን ያስቀራል። በተሻለ ዕውቀትና ክህሎት ሙያን በአግባቡ ለመሥራት የሚያስችል ዕድልን የሚፈጥር ነው ብላናለች። ሠራተኞቹ የአካባቢው ሙቀት እና ብርድ ሳይበግራቸው የመሥራታቸው ሁኔታ በሥራ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ማለፍ እንደሚ ቻል ተምሬያለሁ ስትል ገልጻልናለች።
መንግሥት በየቦታው እያከናወናቸው ያሉ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ለሕዝቡ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያስገኙ መሆናቸውን ከጊዳቦ የመስኖ ግድብ ግንባታ መረዳት ይቻላል። እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የኮንትራት ውል ማጠናቀቅ የኅብረተሰቡን ጠቀሜታ ከማፋጠን የሀገሪቱን ዕድገት ከማሳደግ አኳያ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት። እናም ለፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያት የሆኑትን ችግሮች ወዲያውኑ በመፍታት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ለኅብረተሰቡም ሆነ ለመንግሥት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
የጊዳቦ የመስኖ ግድብ ግንባታ ከዲላ ከተማ በስተምዕራብ አቅጣጫ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ግድቡ በኦሮሚያ ቦረና ዞንና በደቡብ ደግሞ በሲዳማ ዞን ድንበር ላይ የሚገኝ ነው። ይህ ግድብ ሲጠናቀቅም የሁለቱን አጐራባች ሕዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል።
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/economy/1992-2013-02-18-07-19-10

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር