ሲዳማ ኔት ኮሌጅ የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ፌስቲቫል በመሳተፍ ላይ ነው

ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ፌስቲቫል ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚጀመር አዘጋጁ አስታወቀ።
የፌስቲቫሉ አዘጋጅ የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኀበር ትናንት በሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ አራተኛው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ፌስቲቫል ቅዳሜ የካቲት 16 ቀን 2005.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በድምቀት ይጀመራል።
ይሄው መታሰቢያነቱ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተሰጠው የ2005.ም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ከኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች አምስት እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ አሥራ አምስት በድምሩ ሃያ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ማኀበሩ ገልጿል።
በስፖርት ፈስቲቫሉ ማኀበሩ በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች ውድድር እንዲደረግ ዝግጅት ቢያደርግም ተሳታፊ ተቋማቱ በስምንቱ ብቻ ለመሳተፍ በመመዝገባቸው በእነዚሁ ስፖርቶች ውድድሩ እንደሚካሄድ የማኀበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ግርማዬ አስታውቀዋል።
ለአሥራ ሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ የስፖርት ፌስተቫል ለመሳተፍ ከክልሎች ለሚመጡ ስፖርተኞች በሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሾላ ካምፓስ ማረፊያ መዘጋጀቱንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
በስፖርት ፌስቲቫሉ ላይ ሃያዎቹን ተቋማት የወከሉ ሦስት ሺ የሚጠጉ ስፖርተኞች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ አብነት አስረድተዋል።
ለፌስቲቫሉ ስኬት ፌዴራል ስፖርት ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህ ተግባራቸውም በኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ተወካይ በፌስቲቫሉ ውድድር የሚካሄድባቸው የማዘውተሪያ ስፍራዎች በሙሉ ዝግጁ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
አሥራ ሦስት ተቋማት የሚሳተፉበትን የእግር ኳስ ውድድር ለማስተናገድ አዲስ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ አበበ ቢቂላና ጃንሜዳ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ኃላፊው አስታውቀው፤ የቮሊቦል ውድድር በትንሿ ስታዲየምና በአራት ከሎ ጅምናዚየም የሚካሄድ ሲሆን ሁሉም የቅርጫት ኳስ ውድድሮች በትንሿ ስታዲየም እንደሚደረጉም ገልጸዋል።
የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮች በሙሉ በጃንሜዳ ጅምናዝየም የሚካሄዱ ሲሆን፤ ቼዝ በአራት ኪሎ፣ አትሌቲክስ በአዲስ አበባ ስታዲየም፣ ሜዳ ቴኒስ በአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ፣ ባድሜንተን ደግሞ በአራት ኪሎ ውድድር እንደሚካሄድባቸው ተወካዩ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ለውድድሮቹ ፌዴሬሽኖች ዳኞችን እንዲመድቡ ከማድረግ አንስቶ ፌስቲቫሉ በጥሩ መልኩ እንዲጠናቀቅና በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት እንዲከናወን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም አስታውቀዋል።
በስፖርት ፌስቲቫሉ ላይ ከሚሳተፉት ሃያ ተቋማት መካከል ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በስምንቱም ስፖርቶች ለመወዳደር ሲመዘገብ አዲስ ኮሌጅ በስድስት፣ ሐያት ጤና ሳይንስ ኮሌጅና የደቡቡ ተወካይ ሲዳማ ኔት ኮሌጅ በአራት አራት የስፖርት ዓይነቶች እንደሚሳተፉ ታወቋል።
የአራተኛው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ፌስቲቫልን የማዘጋጀት ኃላፊነት ወስዶ የነበረውና ለውድድሩ አንድ ወር ሲቀር ራሱን ያገለለውን ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የማኀበሩ ፕሬዚዳንት እንደተናገሩት፤ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በውድድሩ እንደማይሳተፍ ቢያስታውቅም ተቋሙ በማኀበሩ አባልነት ይቀጥል አይቀጥል በሚለው ጉዳይ ላይ ጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል።
ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ውድድሩን ባለማዘጋጀቱም ሆነ በፌስቲቫሉ ተካፋይ አለመሆኑ የፈጠረው ምንም ተጽዕኖ እንደሌለ የገለጹት አቶ አብነት፤ የስፖርት ፌስቲቫሉ ዓላማ ተቋማቱ እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ ተማሪዎችም ባህሎቻቸውን እንዲለዋወጡ ማስቻል መሆኑን አብራርተዋል።
በፌስቲቫሉ 13 ተቋማት በእግር ኳስ ለመወዳደር ሲመዘገቡ በአትሌቲክስ ወንድ አስር፣ ሴት 13፣ በቅርጫት ኳስ አምስት፣ በጠረጴዛ ቴኒስ ወንድ 12፣ ሴት ዘጠኝ፣ በቼዝ አምስት፣ በሜዳ ቴኒስና ባድሜንተን አራት አራት ተቋማት ለመወዳደር መመዝገባቸው ከአዘጋጆቹ ለማወቅ ተችሏል።
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ፌስቲቫል በሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አስተናጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የተሳታፊ ተቋማት ቁጥር ከ30 በላይ የነበረ ሲሆን፤ በሃዋሳ በተካሄደው በሁለተኛው 18፣ አምና በአዳማ ለሦስተኛ ጊዜ በተካሄደው ውድድር 16 ተቋማት ተካፋይ እንደነበሩ ይታወሳል።
የስፖርት ፌስቲቫሉ «አንድም ሰው በኤችአይኤድስ እንዳይያዝ፣ አድልዎና መገለል እንዳይደርስበትና በኤድስ ምክንያት እንዳይሞት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኀበረሰብ አባላት ኃላፊነታችንን እንወጣ » በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ማኀበሩ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ታውቋል።
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/sport/2069-2013-02-21-06-04-03

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር