የደቡብ ክልል ምክር ቤት ሶስተኛ ዓመት አራተኛ ዙር ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነዉ

ሃዋሳ የካቲት 12/2005 በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በዘንድሮ ግማሽ በጀት ዓመት በየዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት የተመዘገበባቸው መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ ። የክልሉ ምክር ቤት ሶስተኛ ዓመት አራተኛ ዙር ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነዉ ። ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የክልሉን የግማሽ በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት ካለፈዉ ዓመት ክንውን በየስራ ዘርፉ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመውሰድና በማስፋት እስትራተጂ በመጠቀም ውጤታማ ተግባራት ተከናወነዋል ። በመንግስትና በህብረተሰቡ የተሟላ ተሳትፎ የኪራይ ሰብሳቢነትን ችግሮች ለመቅረፍ በሚያሰችል መልኩ በገጠርና በከተማ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ለውጥ ማምጣት የተቻለ መሆኑን አስታዉቀዋል ። ባለፉት ስድስት ወራት በግብርና ልማት፣ በመንገድ ግንባታና በቀበሌ ተደራሽ መንገድ ስራዎች የገጠር ቀበሌዎችን ዕርስ በዕርስና ከዋና መንገድ ጋር በማገናኘት 705 ኪሎ ሜትር መንገድ ተገንብቶ መጠናቀቁን አርሶና አርብቶ አደሩ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል ። መንገዶቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች በማህበር ለተደራጁና በጉልበት ሰራ ለተሰማሩ ከ106 ሺህ በላይ ሰዎች የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመው ከ668 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ለመንገዱ ግንባታ ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ነጻ የጉልበት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል። የትምህርት ጥራት ፍትሀዊነትና ተደራሽነት በማረጋገጥ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ለማስቻል እንዲሁም በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በሚሰጡ ስልጠናዎች ጥራትና ተፈላጊነት ዙሪያ የታቀዱ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል። በህዝብ ንቅናቄ የታጀበው መከላከልን መሰረት ያደረገው የጤና ፕሮግራም አጠናክሮ በማስቀጠል ወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰቱ መከላከል መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል። በግብርናው ዘርፍ በ2004/2005 የምርት ዘመን ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር በመሸፈን ከ222 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን ከ189 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ። በመጠጥ ውሃ አቅርቦት ረገድ በክልሉ 3ሺ201 የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ጥገናና አዲስ ግንባታ በማከናወን በክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን አምና ከነበረበት በገጠር ከ55 በመቶ ወደ 74 በመቶ ፣በከተማ ከ88 በመቶ ወደ 94 በመቶ በማድረስ አበረታች ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸዉን አቶ ሽፈራው አስታውቀዋል። በስራ ዕድል ፈጠራ በቀበሌ ተደራሽ መንገድና በኮብል ስቶን መንገድ ፣ በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ፣በአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታና በተለያዩ ዕድገት ተኮር የስራ ዘርፎች በስድስት ወሩ ከ69 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል መፈጠሩን አቶ ሽፈራዉ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል። የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ በዛሬ ውሎው በርዕሰ መስተዳድሩ በቀረበው የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት እያደረገ ነዉ ።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=5640&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር