በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቡና ግብይት ጥያቄ አስነስቷል


በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቡና ግብይት ጥያቄ አስነስቷል


•    ኤክስፖርተሮች የገዙትን ቡና በጥራት ደረጃው ማግኘት አልቻሉም
•    ንግድ ሚኒስቴር ችግሩን ደርሼበታለሁ ብሏል

 የአገሪቱን የግብይት ሥርዓት ዘመናዊ ለማድረግ ከአምስት ዓመት በፊት ሥራ የጀመረውና ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፈው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት (ኢሲኤክስ) የተዝረከረከና ሕገወጥ አሠራር እየተንሰራፋበት መሆኑን ተገልጋዮች ገለጹ፡፡
መንግሥት በገበያ ማዕከሉ የሚስተዋለውን አሳሳቢ ችግር ደርሼበታለሁ፤ በሕገወጥ ሥራ ተሰማርተው በተገኙ ሠራተኞች ላይም ዕርምጃ እየወሰድኩ ነው ይላል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ በቡና ኤክስፖርት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የገበያ ማዕከሉ በሚያስተዳድራቸው የቡና መጋዘኖች ውስጥ የቡና ቅሸባ ተንሰራፍቷል፡፡ ይህም ከውጭ አገር ደንበኞች ጋር እያጋጫቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የገበያ ማዕከሉ ከአገር ወስጥ አቅራቢዎች ቡናን በመረከብ የቡናውን ናሙና በመውሰድ የቀረበው ምርት የኤክስፖርት ደረጃን ማሟላት አለማሟሟላቱን ካረጋገጠ በኋላ፣ ላኪዎች እንዲጫረቱበት ያደርጋል በማለት የግብይት ሥርዓቱን የሚናገሩት እነዚሁ ቅሬታ አቅራቢዎች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዚህ የግብይት ሥርዓት ውስጥ አሳሳቢ ችግሮች እየተስተዋሉ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በግብይት ሥርዓቱ መሠረት የኤክስፖርት ደረጃን አሟልቷል የተባለ ቡና ጨረታን ካሸነፉ በኋላ ምርቱን ወደ ውጭ ለመላክ ያሸነፉበትንና የከፈሉበትን ማስረጃ በመያዝ ወደ ገበያ ማዕከሉ መጋዘኖች በሚሄዱበት ወቅት፣ የቡና ምርቱን በደረጃው እንደማያገኙ ከዚህ በተጨማሪም የከፈሉበት የቡና ምርት ከመጠኑ አንሶ እንደሚያገኙት ተናግረዋል፡፡

ይህም ከውጭ ገዥዎች ጋር እያጋጫቸው እንደሆነና ኮንትራታቸውንም እስከመሰረዝ እያደረሳቸው መሆኑን በምሬት ያስረዳሉ፡፡ ይህ ችግር ያልገጠማቸው ሌሎች ላኪዎችም ከውጭ ገዥዎቻቸው ጋር ተመሳሳይ ግጭት ውስጥ ላለመግባት የከፈሉበትን ደረጃውን የጠበቀ የቡና ምርት ከመላካቸው በፊት ናሙና በመውሰድና በድጋሚ የቡናውን ደረጃ ለማረጋገጥ አላስፈላጊ ሥራ ውስጥ መግባታቸውን፣ ይህም ቡናው መላክ ከነበረበት ጊዜ እንዲዘገይ እያደረገው ነው ብለዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የምርት ገበያው ዋና ስትራቴጂክ ኦፊሰር የሆኑት አቶ አብነት በቀለ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ የቡና ደረጃዎች የሚወጡበት አሠራር እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ የመጠን መለኪያ ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በግብይት ባህሪው የደረጃና የመጠን ልዩነት ሊከሰት የሚችል በመሆኑ ይህ ችግር ቢከሰትም የሚፈታበት አሠራር መዘርጋቱን አብራርተዋል፡፡ የገበያ ማዕከሉ ሥራ በጀመረበት ወቅት የተጠቀሰው ችግር በተደጋጋሚ ተከስቶ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን በከፍተኛ ደረጃ ተቀርፏል ብለዋል፡፡ ምርት ገበያውን በበላይነት የሚቆጣጠረው 11 አባላትን የያዘ ቦርድ ሲሆን፣ የንግድ ሚኒስቴር ከቦርድ አባላቱ አንዱ ከመሆኑም ባሻገር የአገሪቱን የግብይት ሥርዓት የመምራት ኃላፊነት አለበት፡፡ በምርት ገበያው ያለውን ችግር አስመልክቶ ከንግድ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ግን ችግሩ መኖር ያረጋገጠ ከመሆኑም ባሻገር፣ ችግሩ በቡና ምርት ኤክስፖርት ላይ ተፅዕኖ እንዳደረሰ ይገልጻል፡፡

የንግድ ሚኒስቴርን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የያዘ ሰነድ የዝግጅት ክፍላችን ደርሶታል፡፡ ይኸው ሰነድ የተጠቀሰው ችግር መኖሩን ከማረጋገጡም በላይ እስካሁንም ሊቀርፍ እንዳልቻለ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ናሙና በመውሰድ የሚካሄደው የቡና ምርት የጥራት ምደባ አሰጣጥ፣ እንዲሁም በምርት ግብይትና ርክክብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሮች መኖራቸውን መረጃው ያስረዳል፡፡

‹‹ግብይት የተፈጸመበት የቡና ምርት ርክክብ ከተፈጸመ በኋላ በጥራትም ሆነ በመጠን ልዩነቶች በመኖራቸው በብዙ ተገልጋዮች (ላኪዎች) ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን ማስነሳቱና ችግሩ አሁንም ያልተቀረፈ ነው፤›› በማለት ያስረዳል፡፡ በዚህና ሌሎች ተጨማሪ ችግሮች ሳቢያ በስድስት ወራት ውስጥ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ የነበረውን የቡና መጠን መላክ እንዳልተቻለ፣ ይህም ከቡና ምርት መገኘት የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል ሲል መረጃው ያትታል፡፡

ከተጠቀሰው ዋነኛ ችግር በተጨማሪ የዓለም የቡና ገበያ መቀዛቀዝ እንዲሁም ላኪዎች ኤልሲ በወቅቱ መክፈት ባለመቻላቸው ዕቅዱን ለማስፈጸም አለመቻሉን በተጨማሪነት ይገልጻል፡፡ በዋነኛው የምርት ገበያው ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ ለመስጠት እየሞከረ እንደሆነና በተወሰኑ ሕገወጥ ሠራተኞች ላይም ዕርምጃ መውሰዱን መረጃው ያስረዳል፡፡

በግማሽ ዓመት ውስጥ 113,376 ቶን ቡና በመላክ 464.5 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በተጠቀሱት ችግሮች ሳቢያ መላክ የተቻለው የቡና ምርት 91, 941 ቶን መሆኑን፣ የተገኘው 361.15 ሚሊዮን ዶላር ገቢም የዕቅዱን 77.7 በመቶ ብቻ መሆኑን መረጃው ያስረዳል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/item/723-%E1%89%A0%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%88%9D%E1%88%AD%E1%89%B5-%E1%8C%88%E1%89%A0%E1%8B%AB-%E1%8B%A8%E1%89%A1%E1%8A%93-%E1%8C%8D%E1%89%A5%E1%8B%AD%E1%89%B5-%E1%8C%A5%E1%8B%AB%E1%89%84-%E1%8A%A0%E1%88%B5%E1%8A%90%E1%88%B5%E1%89%B7%E1%88%8D

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር