ለከተማ ኣስተዳደር ምክር ቤት ለሚካሄደው ምርጫ ሲኣን150 እጩዎችን ኣስመዘጋበ


አዲስ አበባ ፣ የካቲት 8 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሚያዝያ ወር ለሚካሄደው ምርጫ የሚወዳደሩትን እጩዎች ይፋ አደረገ።
ዛሬ ማምሻውን ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባገኘነው ጊዜያዊ መረጃ መሰረት  ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ለመወዳደር 11 ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን አስመዝግበዋል።
በዚህም መሰረት ኢህአዴግ 138 ፣ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ  87፣ የመላው ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ንቅናቄ መኢብን 85 እንዲሁም የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ኢራፓም 14 እጩዎችን አስመዝግበዋል።
የመላው ኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መኦህዴፓ 14፣ የኢትዮጵያ የፍትህና የዶሞክረሲ ኃይሎች ግንባር ኢፍዴሃግ 9 ፣ የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኢሰዴፓ 6፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ ኢዴአን 3፣ የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ ገስአፓ 2 ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኢዴፓ 1 እጩዎችን ሲያመዘግቡ በድምሩም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 393 እጩዎች ተመዝግበዋል።
አዲስ አበባ ላይ ለክፍለ ከተማ ምክር ቤት ኢህአዴግ 3ሺ 480 እጩዎቹን ሲያስመዘግብ ለወረዳ ምክር ቤትም እንዲሁ 34ሺ 794 እጩዎችን ነው ያስመዘገበው።
ኦሮሚያ ክልል ላይም ለከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምርጫ ኢህአዴግ ፥ 2 ሺህ 205 እጩዎችን ሲያስመዘግብ ፤ መኦህዴፓ 5፣ እንዲሁም ገስአፓ 1 እንዲሁም አምስት የግል ተወዳዳሪዎችም እጩዎቻቸውን አስመዝግበዋል።
ደቡብ ከልል ላይ ለከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ለሚካሄደው ምርጫ ኢህአዴግ 1ሺህ 160 ፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ሲአን 150 ፣ ኢዴፓ፣ ኢፍዲሃግና ኢራፓም በድምሩ 12 እጩዎችን  ፣ የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ዎህዴግ 1 እንዲሁም ሁለት እጩዎችም በግል ለመወዳደር ተመዝግበዋል።
በአማራ ክልል ለሚካሄደው የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምርጫ ደግሞ ኢህአዴግ 2 ሺህ 805 ፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት 20 ፣ ቅንጅትና ኢፍዲሃግ እያንዳንዳቸው ሶስት ሶስት እጩዎቻቸውን አስመዝግበዋል።
በትግራይ ክልልም እንዲሁ ኢህአዴግ 2 ሺህ 299 እጩዎቹን ለከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ያስመዘገበ ሲሆን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ ኢራፓ ሁለት እጩዎችን አስመዝግቧል።
በሃረሪ ክልል ለቀበሌ ምክር ለመወዳደር እጩዎቹን በብቸኝነት ያስመዘገበው የሃረሪ ብሄራዊ ሊግ ሲሆን ፥ ቤንሻንጉልጉሙዝ ክልል ለከተማ አስተዳደር፣ለወረዳና ለቀበሌ ለሚካሄደው ምርጫ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ቤጉህዴፓ  በብቸኝነት እጩዎቹን አስመዝግቧል።
በሶማሌና አፋር ክልሎችም የተለያዩ ፓርቲዎች ለወረዳና ለቀበሌ ምክር ቤቶች እጩዎቻቸውን አስመዝግበዋል።
ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚወዳደሩትን እጩዎች በሚመለከት ግን ፥ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለጊዜው የተጠናቀረ መረጃ እንዳልደረሰው ነው ፤ የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ረዳት ኃላፊ አቶ ይስማ ጅሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።
http://www.fanabroadcasting.com/index.php?option=com_content&view=article&id=2395:2013-02-15-15-50-32&catid=102:slide

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር