ሲዳማ ብሔረሰብ



የሲዳማ ብሔረሰብ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው። ሲዳማ የሚለው ቃል ለሕዝቡና ለመሬቱ የተሰጠ ስያሜ ሲሆን « ሲዳንቾ» የሚለው ቃል ደግሞ ለሁለቱም ፆታዎች ሲዳማነታቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ ብሔረሰቡ በዋናነት ከሚኖርበት አካባቢ ውጪ በኦሮሚያ ክልል በባሌ፣ በጉጂ፣ በምዕራብ አርሲ ዞኖች እና በክልሉ በወላይታና በጌዴኦ ዞኖች ውስጥ ይኖራል።
የብሔረሰቡ ዋና የኢኮኖሚ መሠረት እርሻና ከብት እርባታ ሲሆን፤ አነስተኛ የዕደ ጥበብ እና የንግድ እንቅስቃሴዎች በተወሰኑ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ይከናወናሉ። በብሔረሰቡ እንሰት፣ ቡና፣ በርበሬ፣ ጐመን፣ ሽንኩርት፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ አጃ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ቦሎቄ፣ አቦካዶ፣ አናናስ፣ ማንጐ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ አብሽ፣ ኮረሪማ፣ በሶብላ፣ ድንች፣ ስኳር ድንች፣ ቦይና፣ ሸንኮራ አገዳና ጫትን በዋናነት ያመርታል።
የብሔረሰቡ ቋንቋ «ሲዳምኛ» ሲሆን ከምሥራቅ ኩሻዊ ቋንቋዎች ቤተሰብ ይመደባል። ከካምባታ፣ ከጠምባሮ፣ ከኦሮሞ፣ ከሀላባ ከቀቤና እና ከጌዴኦ ቋንቋዎች ጋር ይቀራረባል። ብሔረሰቡ ከአፍ መፍቻ ቋንቋው በተጨማሪ አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና ወላይትኛን ኩታ ገጠም በሆኑ አካባቢዎች ይጠቀማል።
የሲዳማ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ባህላዊ አስተዳደርና የፍትህ ሥርዓቶች ያሉት ሲሆን፤ አጥፊዎች የሚዳኙበት «ሴራ» የተባለ ሕግ አላቸው። የባህላዊ አስተዳደሩ የበላይ አካል «ወማ» (ንጉሥ)ነው። ሥልጣኑም በዙር የሚተላለፍ በመሆኑ እያንዳንዱ ጐሣ የራሱ ወማ አለው።
በብሔረሰቡ በርካታ የጋብቻ ሥርዓቶች ያሉት ሲሆን «ሁጫቶ» በቤተሰብ ፈቃድ የተመሠረተ፣ «አዱልሻ» ማስኮብለል፣ «ዲራ» ጠለፋ፣ «ራጌ» የውርስ ጋብቻ እና «አዳዋና» ሴቆቱጋ ሴት ልጅ ዕድሜዋ ለጋብቻ ከደረሰ ልጃገረድ ወንዱ ወላጅ ቤት በመሄድ ቀጭን በትር ወደ ከብቶች በረት በመወርወር የምትፈጽመው የጋብቻ ዓይነት ነው። ከእነዚህ ጋብቻም ውጪ «ዱቃ» በሸለም ማግባትና «ቤሬዓ» ቀብቶ መስጠት የሚባሉ የጋብቻ ዓይነቶች አሉ።
በብሔረሰቡ ደንብ መሠረት ለጥሎሽ የመጣ ገንዘብ ከሌላ ገንዘብ ጋር አይቀላቀልም። ምክንያቱም በወለዱት ልጅ ልውጫ የመጣ በመሆኑ ለመሠረታዊ ጉዳዮች ልውውጥ እንዲውል ስለማይፈልግ ነው።
የሲዳማ ብሔረሰብ ከሚያከብራቸው ባህላዊ በዓላት መካከል የዘመን መለወጫ ወይም « የፊቼ» በዓል አንዱ ሲሆን «ፊቼ» ሲዳማዎች ከአሮጌ ዘመን ወደ አዲስ ዘመን የሚሸጋገሩበት የአዲስ ዓመት ብሥራት ነው። በዕለቱም ቤተ ዘመድ ተጠራርቶ ይበላል፣ ይጠጣል፣ የተጣላ ይታረቃል፣ ያጣ ይረዳዳል። ብሔረሰቡ ከፍቼ በዓል ጋር በተያያዘ የጨረቃና የከዋክብት አቀማመጥን በመመልከት የራሱ የሆነ የቀን መቁጠሪያም አለው።
የብሔረሰቡ አባላት ባህላዊ ቤታቸውን ከሳርና ከእንጨት እንዲሁም ከቀርከሃ የሚሠሩ ሲሆን «ሴሩ ማኔ» (ትልቅ ቤትአንዱ ነው። ቤቱም ሰፊና ባለ ብዙ ምሰሶ ሲሆን የአካባቢው ሕዝብ«ጭናንቾ» በሚል ተደራጅቶ የሚሠራበት ነው። አነስተኛ ቤት «ፊንጐ» ሲባል ሰቀላ ቤት ደግሞ «ዳሴ» ይባላል።
በሲዳማ ብሔረሰብ በዋናነት ባህላዊ ምግባቸው እንሰት (ቆጮነው። ቡላ ምርጥ የቆጮ ምግብ ሲሆን ቆጮን በተለያየ መልኩ ያዘጋጁታል።
በአለባበስ ረገድ ሕፃናት «ሚጤ» ወገብ ላይ የሚታሰር ጥብቆ፣ ትንሽ ቡሉኮ ሲያደርጉ፣ ሴት ሕፃናት «ቆንጦሎ» ይለብሳሉ። ሴቶች «ቆሎ» ከጥጥ የተሠራ፣ ቱባ፣ ወዳሬ ከቆዳ የተሠራ)ይለብሳል። አዛውንቶች «ሴማ» ቡሉኮ፣ ጐንፋ (ግልድምሲለብሱ «ወርቃ»፣ ብልጮ የሚባል መጋጌጫዎችን ይጠቀማሉ። በትር፣ ጦርና ጋሻም ይይዛሉ።
ብሔረሰቡ ደስታውንም ሆነ ኀዘኑን የሚገልጽባቸው ባህላዊ ዘፈኖችና ጭፈራዎች አሉት። ዘፈኖቹና የጭፈራዎቹ ዓይነት፣ በዕድሜና በፆታ የተለያዩ ናቸው።
በብሔረሰቡ ልማድ መሠረት የኀዘንና የለቅሶ ሥርዓት ሲከናወን ሟች ሽማግሌ ከሆነ አስክሬኑ ከእስከ ቀን ሳይቀበር ይቆያል። ቀብሩ ሲፈጸምም አስክሬኑ በቡሉኮ የሚገነዝ ሲሆን፤ ብሔረሰቡ ለሕፃናት ሞት ብዙም መሪር ኀዘን አይኖረውም ሲል የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፕሮፋይል ይገልጻል።
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/entertainment/1554-2013-01-30-05-48-21

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር