በሀዋሳ ከተማ የተጀመረው የተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ባለስድስት ፎቅ ህንጻ ግንባታ በመገባደድ ላይ ነው



  አዋሳ ጥር /2005 የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በደቡብ ክልል ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን የብድርና የቁጠባ አገልገሎት ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ ። ተቋሙ በክልሉ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስጀመረው የኦውቶሞቲቭ ፕሮጀክት ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑም ተገልጧል ። የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሰማ ጫሊ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ባለፈው አመት በተጀመረው የፕሮጀክት ሀዋሳ ከተማ የሚገኘው የተቋሙን ዋና መስሪያ ቤት በዞን፣ በልዩ ወረዳና በወረዳ ደረጃ ካሉት 172 ቅርንጫፎች ጋር በኮምፒተር ኔት ወርክ የማያያዝ ስራ እየተካሄደ ነው፡፡ በተጨማሪ በሀዋሳ ከተማ የተጀመረው የተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ባለስድስት ፎቅ ህንጻ ግንባታ በመገባደድ ላይ እንደሚገኝና በሚቀጥለው ወር ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አስረድተዋል፡፡ በክልሉ የ12 ቅርንጫፎች ባለሁለት ፎቅ ህንጻ ግንባታ በቅርቡ መጀመሩንና በ119 ንዑስ ቅርንጫፎች ከተጀመረው የቢሮ ግንባታ ውስጥም እስካሁን የ40ዎቹ ስራ ሲጠናቀቅ የቀሪዎቹ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ይከናወናል ብለዋል ። በየደረጃው ያሉት ሁሉም ቅርንጫፎ ቢሮዎችን በማሻሻል በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ የኮምፒተር ኔት ወርክ ዝርጋታና ተጓዳኝ የአውቶሞቲቭ ስራዎች በመፋጠን ላይ እንደሚገኝና በያዝነው በጀት አመት ማለቂያ ላይ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አላማ የተቋሙን አገልግሎት ብቃትና ጥራት ከማሳደግ በሻገር በተለይ ደንበኞችን ጨምሮ ሁሉም የክልሉ ነዋሪ በያለበት አካባቢ ተቋሙ ስለሚሰጠው የብድርና የቁጠባ አገልገሎት አስፈላጊውን መረጃና ሙያዊ ድጋፍ በቅርበት በማግኘት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል መሆኑን አቶ ሙሰማ አስታውቀዋል፡፡ ተቋሙ በዘንድሮ በጀት አመት ብቻ ለነባርና ለአዲስ ደንበኞች ከ1ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በብድር ለማሰራጨትና 9 ቢለዮን ብር ደግሞ በቁጠባ ለማሰባሰብ ማቀዱንም አስረድተዋል፡፡ የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ከተመሰረተበት ከ1989ዓም ጀምሮ እስካሁን ከ500ሺህ ለሚበልጡ ደንበኞች ወደ ሶስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ብድር መሰጠቱን፣ ከብድር ተጠቃሚዎችና ከሌሎች ከ800ሺህ ደንበኞች በአጠቃላይ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በቁጠባ መሰብሰቡም ተመልከቷል፡፡ የተቋሙ አላማ በክልሉ ገጠርና ከተማ ስራ ፈጣሪ ዜጎችን በገንዘብና በሙያ በመደገፍ የቁጠባ ባህልን በማዳበር ስራ አጥነትንና ድህነትን ለመቀነስ መንግስት የሚያደረገውን ጥረት ለማገዝ መሆኑም ተገልጿል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር