ሲዳማን ጨምሮ በደቡብ ክልል ከሁለት ሚሊዮን 400 ሺህ የሚበልጥ ህዝብ ተመዝግቦ ካርድ መውሰዱ ተገለጸ

አዋሳ ጥር 08/2005 (ዋኢማ) - በደቡብ ክልል በመጪው ሚያዝያ በሚካሄደው የአከባቢ ምርጫ እስካሁን ከሁለት ሚሊዮን 400 ሺህ የሚበልጥ ህዝብ ተመዝግቦ ካርድ መውሰዱን በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ። 

ኃላፊው አቶ አብርሃም ገዴቦ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት እስከትናንት ከሁለት ሚሊዮን 400 ሺህ በላይ መራጮች ተመዝግበው ካርድ ወስደዋል፡፡ 

ካርድ ከወሰዱት መካከል አንድ ሚሊዮን 168ሺህ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

መራጮቹ ምዝገባ ያደረጉት በክልሉ 14 ዞኖች፣ 4 ልዩ ወረዳዎችና በ22 የከተማ አስተዳደር በተቋቋመው 8ሺህ 130 ምርጫ ጣቢያዎች መሆኑን ገልፀው በክልሉ ሰባት ሚሊዮን መራጮች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል፡፡ 

በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎቹ 40 ሺህ ስድስት መቶ ምርጫ አስፈፃሚዎች የምርጫውን ስራ ለማስፈፀም እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው በተመሳሳይ ቁጥርም የህዝብ ታዛብዎች ተመርጠው እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ 

የአከባቢ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አስፈፃሚዎች፣ የሙያ ማህበራት፣ ህብረተሰቡና ሌሎች የባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

የምርጫ አስፈፃሚዎች በበኩላቸው ህዝቡ ዛሬ ነገ ሳይል በመራጭነት ተመዝግቦ በህገ መንግስቱ የተረጋገጠለትን መብት መጠቀም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ 
http://www.waltainfo.com/index.php?option=com_content&view=article&id=7034:----400-----&catid=58:2011-08-29-12-55-21&Itemid=383

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር