በዞኑ ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ ተሰማሩ

አዋሳ ጥር 21/2005 በሲዳማ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ ተሰማሩ፡፡ የዞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ወልደሚካኤል ትናንት እንደገለጹት በግማሽ ዓመቱ አምስት ባለሃብቶች ፈቃድ በማውጣት ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል ስራ ጀምረዋል፡፡ ባለሃብቶቹ ከተሰማሩባቸው የስራ መስኮች መካከል አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ግብርናና ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙበት አመልክተዋል፡፡ ባለሃብቶቹ ለ88 ቋሚና 894 ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸው አንዳንድ ከተሞች ላይ ባለፈው ዓመት የተጀመሩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከ5 ሺ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡ መምሪያው በገጠር የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማጥናትና በመለየት ለባለሃብቶች ከማስተዋወቅ በተጨማሪ በግብርና፣ በማህበራዊ አገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብተቶች ከ600 ሄክታር በላይ የገጠር መሬት አዘጋጅቶ መስጠቱን የስራ ሂደቱ አስተባባሪ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ለበርካታ ባለሃብቶች የፈቃድ እድሳትና ተጨማሪ የማስፋፊያ ፈቃድ መሰጠቱን ጠቁመው ከዚህ ቀደም ቦታ ወስደው ወደ ስራ ያልገቡ ባለሃብቶችን በመከታተልና ድጋፍ በመስጠት በፍጥነት ወደ ስራ የሚገቡበትን ሂደት ለማመቻቸት ባደረገው ጥረት 288 ፕሮጀክቶች የአገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አዲስ ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ ከገቡት ባለሃብቶች መካከል አቶ ብርሃኑ አድማሱና አባተ አርጊሶ በሰጡት አስተያየት መንግስት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት እያደረገ ያለው ድጋፍና እገዛ በርካታ ባለሃብቶች በሀገር ውስጥ እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም በድህነት ላይ ለሚደረገው ትግል የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉና ለብዙዎች የስራ ዕድል እንዲፈጠር ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ በሲዳማ ዞን ባለፈው በጀት ዓመት ከ267 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 45 ባለሃብቶች በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ሲሆን በተለይ በዳሌ፣ በአለታ ወንዶ ፣ በሎካ አባያና በበንሳ ወረዳዎች የሚታየው የባለሃብቶች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=4979&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር