ከማህበራዊ መረብ ላይ የተገኘ ጽሁፍ
 
ሲዳማ በደኢህዴን/ኢህአዴግ ዘመን
በሲህዴድ አመራር ወቅት የተከናወኑ አበረታች የልማት እንቅስቃሴዎች 
1. የሲዳማ ዞን መስተዳድርና ሲህዴድ የአመራርና የፖለቲካ ስልጣን በእጃቸው በነበረበት ወቅት በርካታ የልማት ስራዎች እንደተጀመሩ ከላይ ተገልጿል፡፡ ከተጀመሩ የልማት ስራዎች መካከል በተለይም የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ግንባታና በየወረዳውና በየቀበሌው የተስፋፋው መደበኛ ያልሆኑ የት/ ተቋማት፤ በውጭና በሃገር ውስጥ በርካታ የሲዳማ ልጆች የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ እንዲወስዱ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች፣
2. ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ የቦና ሆስፒታል ግንባታ፣
3. በሰው ጉልበት የሚሰሩ በርካታ ወረዳዎችን የሚያገናኙ መንገዶች፣
4. የሲዳማ ልማት ኮርፖሬሽን፣ የሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስ፣ በይርጋለም የሚገኘው ፉራ የልማትና ጥናት ምርምር ተቋም፣ የሐዋሳ መሐል ከተማ ጉዱማሌ የገበያ ማዕከላት መመስረትና መገንባት፣
5. የሲዳማ አስተዳደር አባላትና የልማት መስሪያ ቤት ተወካዮች በአፍሪካ፣ በኤዥያ፣ በአውሮፓና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በአካደሚክ ትምህርትና በመስክ የስራ ልምድ ጉብኝቶች ሁሉ ለሲዳማ ሕዝብ ልማትና የእድገት ጥማት ምላሽ የሰጡና ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች በዚያው ፍጥነት ቢቀጥሉ ኖሮ ዛሬ የሲዳማ ዞን የት ሊኖር እንደሚችል መገመትም አያዳግትም፡፡ 

እነዚህና በዝርዝር ያልቀረቡ የልማት ስራዎች የተሰሩት በዋናነት የሲዳማ ዞን መስተዳድር ከአየርላንድ መንግስት ባገኘው የልማት ቀጥተኛ ድጋፍ ሲሆን የመንግሥት ድጎማም እንዳለበት ይታወቃል፡፡
ሲህዴድ ከከሰመ በኋላ በሲዳማ ላይ የተፈጸሙ አሉታዊ ተፅዕኖዎች

የደኢህዴን መሰሪ አመራር የድርጅታቸው ዋናው ዓላማና ግብ የሲዳማን ህዝብ መብት መግፈፍና ማዋረድ እስከሚመስል ድረስ ህዝባችንን የበደሉ፣ ያዋረዱ፣ ወደ ኋልዮሽ እንድያድግ ያደረጉና ለዚህም አሁንም ድረስ እየተጉ ያሉ ስለሆነና ያደረሱብን በደል እንዲህ በቀላሉ ተገልጾ የማያልቅ ቢሆንም ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ አኳር አንኳሩን እንደሚከተለው ገልጸናል፡፡
1. ሲህዴድ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ ለደኢህዴን ባስረከበበት ማግስት የደኢህዴን አመራር የመጀመሪያና ፈጣን እርምጃ የነበረው የአይሪሽ መንግስት በሲዳማ መስተዳድር የሚያደርገውን የልማት ድጋፍ እንዲያቋርጥ ማድረግ ነበርና የአይሪሽን መንግስት እርዳታ በተለያየ መንገድ በማዋከብ እርዳታውን ምንም ዓይነት የመውጫ ዕቅድ /Phase out Strategy/ ለማዘጋጀት ዕድልና ጊዜ እንኳን ሳይሰጡት በፍጥነት እርዳታው እንዲቋረጥ ተደረገ፡፡ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ባሉበት ቆሙ፡፡ የልማት ድጋፍ በማስቆም ላይ ብቻ አላቆሙም፡፡ በመቀጠልም የልማት ቀናዕ የሆኑ የብሔሩ የልማት ቀያሾችና መሪ ተዋናዮች የሆኑትን በተለያዩ ሰንካላ ምክንያቶች የስም ማጥፋት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ከሃገር እንዲሰደዱ ማድረግ ነበርና እነሆ ይህንን መሰሪ ተንኮል በወራት ጊዜ ውስጥ አሳኩት፡፡ የአየርላንድ መንግስት ድጋፍ ያለ ቅድመ-ሁኔታ ሲቆም የልማት ስራዎችም ባሉበት ቆሙ፡፡ የሲዳማ ልማት አርበኞችም ከፍሎቹ ወደ ውጭ ተሰደዱ፡፡
2. ለሲዳማ ህዝብ የልማት ስራዎችን በዘላቂነት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ያግዛሉ ተብለው የተደራጁት የልማት ተቋማት በተለይም የሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስና ሲዳማ ልማት ኮርፖሬሽንን ለማፍረስ ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም፡፡ ብዙም አንገጫገጩት፡፡ ዛሬ ግን ለህዝብ ልማት ደጋፊ ሳይሆን የደኢህዴን ታማኝ ካድሬዎች እየተፈራረቁ የግል ህይወታቸውን የሚገነቡበት አንጡራ ሃብታቸው እንጂ የሕዝብ ንብረቶች አይደሉም፡፡ ጠያቂ የሌለባቸው ነፃ የግል ኑሮ መገንቢያ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች ሆነዋል፡፡ የተለያዩ ወንጀሎችን ሰርተው ነገር ግን ለስርዓቱ/ለደኢህዴን አስፈላጊ የሆኑ ግለሰቦች ጊዜያዊ ማገገሚያ፣ መደበቂያና መሸሸጊያም ጭምር ሆነዋል፡፡ 
3. የሲዳማ ልማት ማህበር በኢትዮጵያ ካሉ ግንባር ቀደም ማህበራት አንዱ ሲሆን የሕዝብ ልማት አጋርነቱን በተግባር ማሳየት የቻለው የሲዳማ ዞን መስተዳድር ሙሉ በሙሉ ከአስተዳደርና ፖለቲካ ስልጣን እስካልወጣበት ጊዜ ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ሲህዴድ ማንነቱን አሳልፎ እንደሸጠ ደኢህዴን የወሰደው አፋጣኝ እርምጃ የሲዳማ ልማት ማህበር ያለውን ገንዘብ ወደ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ እንዲያዛውር ማስገደድ ነበር፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በብድር ስም የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ወስዶ ነገደበት፡፡ ማህበሩ ግን የበይ ተመልካች እንዲሆን ተፈረደበት፡፡ በዝቅተኛ ደረጃም ቢሆን የሚያገኛቸው ገቢዎች በማህበሩ እየተደጎሙ ማህበራዊ ችግራቸውን እንዲቋቋሙ የተመደቡ ሠራተኞች መጧሪያነት የሚዘል አቅም እንዳይኖረው መንገዶች ሁሉ ተዘግተውበታል፡፡ 
ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ሕዝቡ በቁጭት ማህበሩን መልሶ ለማቋቋም በመነሳሳት ከአርሶ አደር እስከ መንግስት ሠራተኛ የአንድ ወር ደመወዝ መዋጮ ድረስ ገንዘብ የተሰበሰበ ሲሆን ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ የልማት ስራ እንዲሰራ አልተፈቀደም፡፡ ሕዝቡ ያዋጣው በርካታ ሚሊዮን ብሮች በዝግ አካውንት በባንክ ተቀምጧልም ይባላል፡፡ ነገር ግን ሕዝባዊ ልማት ለማካሄድ የደኢህዴን መልካም ፈቃድ ይጠይቃልና እነሆ እስከ ዛሬ ስለዚህ ገንዘብ እንዲወራ አይፈለግም፡፡
4. እጅግ የሚያስቆጨውና የሚያሳዝነው ጉዳይ የሲዳማ ልማት ማህበር ቴሌቶን ለማዘጋጀት የሚያስችል አገር አቀፍ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ጥናታዊ ዝግጅት አጠናቅቆ የደኢህዴን መልካም ፈቃድ በመጥፋቱ የሲዳማ ልማት ጥናት ፕሮጀክት ሌሎች የታደሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ተጠቅመው ሃገር አቀፍ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን በማዘጋጀት ለህዝባቸው በጎ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሕዝባዊ የልማት አውታሮችን አጠናክረዋል፡፡
5. ከላይ የተጠቀሱት የሲዳማ ህዝባዊ ልማት ድርጅቶች እንዳይቀጥሉ በመግታት አላበቃም፡፡ በመቀጠል ደኢህዴን/ኢህአዴግ ያነጣጠረው የሐዋሳን ከተማ አስተዳደር ከሲዳማ እጅ የመቀማት ዕቅድ ነበር፡፡ ለዚህ መሰሪ ዓላማ መሳካት የተጠቀመው ታክቲክ በሲዳማ ዞንና በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር መዋዕቅር ውስጥ ያሉትን የብሔሩን አባላት ስም ማጥፋት፣ አሉባልታ መንዛት፣ የከተማ ልማት በሚል የተዘጋጁ ማደነጋገሪያ ሰነዶችን በማቅረብ የማምታታትና ሁከት የመፍጠር ስራ በስፋት ቀጠለበት፡፡ በመጨረሻም የሐዋሳን ከተማ አስተዳደር ታስረክባለህ አታስረክብም የሚል የመጨረሻ ጥያቄ በማቅረብ አስገደደ፡፡ ይህንን የተቃወሙ የሲዳማ አስተዳደር አመራር ስልጣናቸውን እንዲለቁና እንዲታሰሩ ተደረገ፡፡ ከላይ በእነሱ ሳምባ የሚተነፍሱ የይስሙላ (ፑፔት) ከንቲባ ከብሔሩ እየመደቡ በአጠቃላይ የከተማውን አስተዳደር ስልጣን ተቆጣጠሩት፡፡
በዚህ ጉዳይ የተቆጣው ህዝብ ከሁሉም የሲዳማ ዞን ወረዳዎች በራሱ ጊዜ በመሰብሰብ ሰላማዊ ጥያቄውን ለመንግስት ለማቅረብ ተሰብስቦ ወደ ሐዋሳ ተከማቸ፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ ጥያቄ በደብዳቤ አቀረበ፡፡ ሕዝቡን ቀርቦ ብሶቱን ከማነጋገር ይልቅ ሕዝባችንን የሚጨፈጭፍ የወታደር ኃይል ማከማቸት ተያያዘ፡፡ ሕዝቡም ለሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ በፅሁፍ ተጠይቆ ምላሽ ካልተሰጠና 48 ሰዓት ከሞላው ተቀባይነት እንዳገኘ ይቆጠራል በሚለው ህግ መሠረት ሕዝቡ የሳር፣ የዘንባባ ቅጠልና የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዞ ወደ መስቀል አደባባይ ሲተም የቴክኒክና ሞያ ተቋም አካባቢ ጭካኔና ጥላቻ በተሞላበት ሁኔታ በከባድ መሣሪያ በተደራጀ የመንግስት ታጣቂዎች ግንቦት 16/1994 ዓ.ም ከቀኑ 4፡00-4፡30 ባለው ጊዜ ብቻ 42 ፍትህ ጠያቂ የብሔሩን ልጆች ዘግናኝ በሆነ መልኩ ጨፈጨፉ፡፡ ከጭፍጨፋው በፊት የጭፍጨፋው ሁኔታ ሲመቻች የተጠራው የወታደሩ/የሠራዊቱ የበላይ አመራሮች “ህዝቡ የተሰበሰበበት ድረስ ሰው በጥበብ ልከን አጣርተናል፡፡ ህዝቡ ሰላማዊ ነው፡፡ በእጁም የያዘው ቅጠልና የኢትዮጵያን ባንዲራ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄንን ህዝብ መምታት አንችልም፡፡ በሌላ ዘዴ ለማቀዝቀዝ ቢሞከር ጥሩ ነው …” ብለው ሲሉ በአቶ ኃይለማሪያም ደሣለኝ የሚመራው አስጨፍጫፊ ቡድን ግን “አይደለም ህዝቡ ህዝባችንን ሊፈጅ ነው፡፡ በቂ መረጃ አለን፡፡ ተቃዋሚው ሰልፈኛ ከተማ ከገባ ህዝባችንን ይጨፈጨፋል…ስለዚህ ይመታ፡፡ ካልተመታ አይመለስም” በማለትና በጦሩም ውስጥ የነርሱን ዓላማ አስፈጻሚ የራሳቸውን ተወላጆች በመሰግሰግ ያን እልቂት ደገሱልን፡፡ በጣም የሚያሳዝነው አውቶማትክ መሳሪያ በጠላት ላይ እንደሚተኮስ በመርጨት ልጅ ከአዋቂ ሳይለይ መረፍረፋቸው ነው፡፡ አንድና ሁለት እንኳ ቢገድሉ ሊያስፈራሩ ነው ይባላል፡፡ ታድያ ይህ የመደብ ጠላት እንጂ ሊያረጋጋ የወጣ የራስ አመራርና መንግሥት ሊሆን ከቶ ይችላል ወይ? መልሱን ጤናማ አእምሮ ላለው ሰው ሁሉ እንተው፡፡ 
በደኢህዴን/ኢህአዴግ አመራር ሰጪነት የህዝቡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የከሰመና የተደመደመ መስሎአቸው ጮቤ ረገጡ፡፡ የከተማውን መሬት በስልጣን ላይ ላሉ ጎሳዎች ያለተቀናቃኝ ተከፋፈሉ፡፡ ድሮም ቢሆን የሲዳማ መሬት እንጂ ሕዝቡን መች ይወዱና! ከ1994-1997 ዓ.ም ድረስ የሲዳማ ብሔር አባላት በሐዋሳ ከተማ ምንም ሚና እንዳይኖራቸው ተደረገ፡፡

ይቀጥላል

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር