POWr Social Media Icons

Friday, December 21, 2012

አዋሳ ታህሳስ 12/2005 የሀዋሳ ከተማ ከንቲባና ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ስልጣናቸውን አለአግባብ በመጠቀም መሬት ለግለሰቦችና ድርጅቶች ሰጥተዋል በሚል የሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩ የከተማው ከንቲባና ሌሎች ስድስት ተከሳሾች በእስራትና ገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነ። የደቡብ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ባስቻለው ችሎት የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ የነበረውን ሽብቁ ማጋኔን ጨምሮ 6 ተከሳሾች ላይ ከስምንት ዓመት እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ እስራትና ከ20ሺህ እስከ 2 ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኗል። ፍርድ ቤቱ የክልሉ ጸረሙስና ኮሚሽን ይግባኝ በጠየቀባቸው ሽብቁ ማጋኔ፣ እንድርያስ ፉላሳ፣ ጸጋዬ አረጋ፣ ጉደታ ጉምቤ፣ አስራት ግቻሞና ከበደ ካያሞ ላይ የእስራትና ገንዘብ ቅጣቱን የወሰነው የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በመሻር ነው። ግለሰቦቹ ለባለኮከብ ሆቴሎችና ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶች ካልሆነ በቀር የመኖሪያ ቤት ቦታ መስጠት እንደማይቻል ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የተጻፈውን ዕገዳ በመጣስ ለግለሰቦች እንዲሁም ጋዜጠኞችን ጨምሮ በሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ላልሆኑ ስምንት ሰዎች መሬት በመስጠታቸው ቅጣቱ ተጥሎባቸዋል ብሏል። በዚሁ መሰረት የሀዋሳ ከተማ የነበረው ሽብቁ ማጋኔ ላይ የአምስት አመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራትና የአምስት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጫ ተጥሎበታል። የሃዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የመሬት ልማትና አስተዳደር የስራ ሂደት ባለቤት የነበረው እንድሪያስ ፉላሳና በማዘጋጃ ቤቱ የመሬት ልማትና አስተዳደር የስራ ሂደት ባለሙያ የነበረው ጉደታ ጉምቤ እያንዳንዳቸው በ5 ዓመት ከ6 ወር እስራትና በ15 ሺህ ብር እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል። የታቦር ክፍለ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የመሬት ልማትና አስተዳደር ስራ ሂደት አስተባባሪ በነበረው አስራት ግቻሞ ላይ የአንድ አመት ከ2 ወር እስራትና የ2 ሺህ ብር መቀጫ የከተማው ምክትል ከንቲባና የንግድና ኢንደስትሪ መምሪያ በነበረው ከበደ ካያሞ ደግሞ በአንድ ዓመት እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ወስኗል። የሃዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ የነበረው አረጋ ጸጋዬ በሌለበት በስምንት ዓመት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ የወሰነበት ሲሆን ፖሊስ ካለበት ስፍራ ፈልጎ በመያዝ ቅጣቱን ተግባራዊ እንዲያደርግና ቅጣቱ ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆን በመገናኛ ብዙሀን እንዲተላለፍ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። 
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=4163&K=1