POWr Social Media Icons

Tuesday, December 18, 2012


የዓለም የጤና ድርጅት የስኳር ህመም ቆሽት የተሰኘዉ የዉስጥ አካል ኢንሱሊን የተባለዉን ተፈላጊ ቅመም በበቂ ማምረት ሲሳነዉ ወይም፤ ቆሽት ያመረተዉን ኢንሱሊን ሰዉነት በአግባቡ መጠቀም ሲያቅተዉ ሊከሰት እንደሚችል ያመለክታል።
 እንዲህ ያለዉ እክል ሰዉነትን ሲያጋጥም ደግሞ ደም ዉስጥ በርከት ያለ የስኳር ፈሳሽ/ግሉኮስ/ ይከማቻል። ይህ የመጀመሪያዉ ዓይነት የስኳር ህመም ሲሆን፤ ሁለተኛዉ ዓይነት ደግሞ፤ በተመሳሳይ ሰዉነት ተገቢ ያልሆነ የኢንሱሊን አጠቃቀም ሲኖረዉ የሚከሰት ሆኖ፤ መጠን ያጣ ክብደት ሲኖርና በአግባቡ የሰዉነት እንቅንቃሴ ባለመደረጉ እንደሚከሰት መረጃዉ ያብራራል። የኢትዮጵያ የስኳር ህመም ማኅበር ፕሬዝደንትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ሃኪም ቤት በተለይ የስኳር ህመምን የሚከታተሉት ባለሙያ ዲክተር አህመድ ረጃ ይህ የጤና እክል የእድሜ ዘመን ህመም መሆኑን ያመለክታሉ። የስኳር በሽታ ታማሚዎች ቁጥር ከመቼዉም ጊዜ በላይ እየጨመረ እንደሚገኝ ጥናቶች እያመለከቱ ነዉ። እንዲያም ሆኖ ጥናቱ እንደሚለዉ የህመሙ ተጠቂ ከሆኑ ግማሽ ያህሉ ገና ተገቢዉን ምርመራ አላደረጉም።
የሰዉነት ክብደትን መቆጣጠር
ከአንድ ዓመት በፊት 366 ሚሊዮን የነበረዉ በዓለማችን የስኳር በሽታ ታማሚዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 371 ሚሊዮን መድረሱን በቅርቡ የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ። ዓለም ዓቀፍ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን እንደሚለዉም ከሆነም በጎርጎሮሳዊዉ 2030ዓ,ም ቁጥሩ ወደ552 ሚሊዮን ማሻቀቡ አይቀርም። ቻይና ዉስጥ ብቻ 92,3 ሚሊዮን ህዝብ ለዚህ የጤና ችግር ሲጋለጥ የጤና አገልግሎቱ ባልተስፋፋበት በአፍሪቃም እንዲሁ ቁጥሩ ሊበረክት እንደሚችል ይገመታል።
ሸዋዬ ለገሠ
ሂሩት መለሰ
ታህሳስ ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ድርጅቶቹ ባወጡት መግለጫ በጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በአዳማ ኤክስኪዩቲቭ ሄቴል በዚህ አመት በሚደረገው የአካባቢ እንዲሁም የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ ምርጫ የግዜ ሰሌዳን አስመልክቶ  የውይይት መድረክ መጥራቱን ጠቅሰዋል።
ድርጅቶቹ በመግለጫቸው ” ምርጫ ለማካሄድ ነባራዊ ሁኔታው የማይፈቅድ ስለሆነ በፖለቲካ ምህዳሩና በህዝብ ወሳኝነት ሁሪያ መወያየት አለብን ብለን ፒቲሺን ተፈራርመን ለቦርዱ ያስገባን 33 ፓርቲዎች ጉዳይ ወደ ጎን ተትቶ ቀልድ በሚመስል መልክ በጾታ ጉዳይ ልናወያያችሁ እንፈልጋለን ማለት የህዝብን የምርጫ ባለቤትነት የሚጋፋ ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል።” ካሉ በሁዋላ፣ ቦርዱ ጾታን በተመለከተ እና አሁን ላለንበት ሁኔታ ቀላል የሆነ ጉዳይ ጠቅሶ በጠራው የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት  መድረክ የማንሳተፍ መሆናችንን ፔቲሺን የፈረምን 33 የፖለቲካ ፓርቲዎች እናሳውቃለን።” ብለዋል።
33ቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ምርቻ ቦርድ በገለልለተኛ ወገኖች እንዲቋቋም፣ ነጻና ፍትሀዊ የመገናኛ ብዙሀን እንዲኖሩ፣ የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ሁሉንም ድርጅቶች በእኩል እንዲያገለግሉ፣ መከላከያ፣ ፖሊስና የደህንነት ተቋማት በነነጻነት እንዲዋቀሩ፣ በተቃዋሚዎች ላይ የሚደርሰው ማዋከብ እንዲቆም የሚሉና ሌሎችንም በርካታ ጥያቄዎች መጠየቃቸው ይታወሳል።

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 9 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የሃዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ህጻናት በነጻ የሚሰጠውን "ፕላምፕኔት" የተሰኘ ምግብ ለገበያ ባቀረቡ 25 የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ ነው።
ምግቡን መንግስት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከፍተኛ ወጪ እያደረገበት ለታለመላቸው ህጻናት እንዲደርስ የሚያደርግ ሲሆን ፥ የሚቀርበውም በጤና ተቋማት በኩል በነጻ እና በባለሙያ ትዕዛዝና ክትትል ብቻም ይሰጣል።
ይሁን እንጂ በሃዋሳ ከተማ ይህ ህይወት አድን ምግብ ከታለመለት ዓላማ ውጪ እየዋለ መሆኑን ፥ በመምሪያው የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብዓቶች ስርዓት ቁጥጥር ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ዘመን ለገሰ ተናግረዋል።
በተለያዩ መንገዶች ከየጤና ተቋማቱ እየወጣ ለንግድ እየቀረበ በመሆኑ ፥ ዛሬን ጨምሮ ሰሞኑን መምሪያው ይህን ምግብ ለገበያ በሚያቀርቡ የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ተገዷል።
አቶ ዘመን እንዳሉት ወደ እርምጃ የተገባው በተለያዩ መንገዶች በተደጋጋሚ ፥ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ቢሰጥም ለውጥ ሊመጣ ባለመቻሉ ነው።
አስቀድሞ እርምጃ ተወስዶባቸው ዳግም ወደ ህገ ወጥ ስራው ላለመግባት ፥ መተማመኛ ፈርመው የንግድ ተቋሞቻቸው የተከፈቱላቸው እንዳሉም ነው ያስረዱት።
በዚህ ህገ ወጥ ስራ ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ ሁለት የህክምና ባለሙያዎችም አሉ ነው ያሉት አተ ዘመን።
ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንጻር የጤና መምሪያው በከተማዋ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮን ጨምሮ ፥ ዘጠኝ ያህል ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የህብረተሰብ ጤና ተቆጣጣሪ ግብረ ሃይል ማቋቋሙን በዛብህ ማሞ ዘግቧል።

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2005(ዋኢማ) - በመጪው ሚያዝያ 6 እና 13 ለሚካሄደው የአካባቢና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ የምርጫ ቁሳቁሶችን ከዛሬ ጀምር ማሰራጨት እንደሚጀምር የምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ ወይዘሮ የሺ ፍቃዱ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ለምርጫው የሚያስፈልጉ የምርጫ ቁሳቁሶችን ቦርዱ በማዘጋጀት በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት ቀናት ለሁሉም ክልሎች ለማሰራጨት ዝግጅቱን አጠናቋል።
ቦርዱ ካሁን በፊት የመራጮች መመዝገቢያና የምርጫ ካርዶችን በአማርኛ ብቻ ያሳትም እንደነበረ ጠቁመው፤ በዘንድሮው ምርጫ ግን ከአማርኛው በተጨማሪ  በኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛና ሶማሊኛ ቋንቋዎች ማዘጋጀቱን ገልፀዋል።
የዘንድሮው ምርጫ ፍትሀዊነቱ የተረጋገጠ ለማድረግም ለባለድርሻና ለአስፈፃሚ አካላት ስልጠና መሰጠቱን ተናግረው፤ በቅርቡም ከ100 በላይ ለሚሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጥ ወይዘሮ የሺ ገልፀዋል።
ምርጫውን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ለማድረግም በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በተለያዩ ቋንቋዎች ትምህርት በመሰጠት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የምርጫ ክልል የምርጫ አስፈፃሚዎችን የመመልመሉ ስራም መጠናቀቁን ጠቁመው፤ በዚህም 2ሺ የሚሆኑ አስፈፃሚዎች በቋንቋቸው ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል ብለዋል።
የምርጫ አስፈፃሚዎች ገለልተኛ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ወይዘሮ የሺ የስራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት እንዲኖራቸው በተለይም የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎ ከባለፈው ምርጫ የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ ወይዘሮ የሺ ገለፃ የመራጮችና የእጩዎች ምዝገባ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከታህሳስ 22 ጀምሮ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ሚያዝያ 6 እና 13 ለሚካሄደው ምርጫም እስከ አሁን 26 የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክቶቻቸውን መምረጣቸውን ወይዘሮ የሺ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።


በአስፋው ብርሃኑ ልዩ ዘጋቢ ከሐዋሣ
ሐዋሣ ከተማ በ1952 ዓ.ም. ስትቆረቆር የነዋሪዎቿ ቁጥር ከ2,500 አይበልጥም ነበር፡፡ ኀዳር 2003 ዓ.ም. የአምሳኛ ዓመት ልደቷን ስታከብር የሕዝቧ ቁጥር ከሦስት መቶ ሺሕ በላይ የደረሰ ቢሆንም ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት የተከሰተው ባለፉት አሥር ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በአገራችን በፍጥነት እያደጉ ከመጡት ከተሞች ግንባር ቀደም የሆነችው ሐዋሣ ዛሬ አራት መቶ ሺሕ ለሚገመት ሕዝቧ መጠለያ እያጠራት ከመሆኑም በላይ “ለመኖሪያ የተመቸች” መባሏን ተከትሎ እንዲሁም የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች መጐልበት በርካታ ዜጐች እንዲፈልሱ አስችሏል፡፡ መሰል ሁኔታ የመኖሪያ ቤት እጥረትንና የአንድ ክፍል ወርሃዊ ኪራይ ንረትን አስከትሏል፡፡ የከተማዋ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ የአገራዊ ፖሊሲ አካል የሆነውን የጋራ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገ ቢሆንም እጥረቱና የኪራይ ንረቱ ዛሬም ለሐዋሣ ነዋሪዎች የኑሮ ውድነቱ አካል ሆኗል፡፡ 

የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና የመጠለያ እጥረት 
ሐዋሣ የክልሉ መንግሥትና የሲዳማ ዞን አስተዳደር መቀመጫ መሆንዋ፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ፕሮጀክቶች መስፋፋት፣ የንግድና የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች መበራከት የግልና የመንግሥት የትምህርት ተቋማት መንሰራፋትና ሌሎች ተያያዥ ነገሮች ለሐዋሣ ለፈጣኑ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ለቢዝነስ፣ ለትምህርትና ለሥራ ጉዳይ ወደ ሐዋሣ የመጣ ዜጋ ቡና ቤት አይኖርምና ቋሚ መጠለያ ይፈልጋል፡፡ ያለው አማራጭ ከተገኘ የቀበሌ (ዕድለኛ ከሆነ) እና የግለሰብ መኖሪያ ቤት ተከራይቶ መኖር ነው፡፡ ይሁንና በአጭር ጊዜ ውስጥ የአንድ ክፍል ኪራይ ዋጋ አቅም የሌላቸውን በየወሩ ቤት እንዲቀያይሩ እያስገደዳቸው ይገኛል፡፡

ወርሃዊ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ያልተቋረጠ ጭማሪ 
በሐዋሣ ከተማ በቋሚነት የሚኖሩ ቤት የሌላቸው ዜጐች የግለሰብ ቤት ኪራይ ጭማሪ መማረር ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡ ያም ብቻ አይደለም ከጥቂት ዓመታት በፊት ማለትም ከ2001 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ፈላጊ አጥተው የነበሩት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ማግኘት ቅንጦት፣ የኪራይ ዋጋ አበሳ የአጭር ጊዜ ትዝታ ሆኗል፡፡ ይህንንም የኪራይ ዋጋ ንረት ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረው ጋር እያነጻጸሩ መመልከት ይቻላል፡፡ በ1994 ዓ.ም. አንድ 3ሜx4ሜ ስፋት ያለው ክፍል አማካይ ኪራይ ከአርባ ብር የማይበልጥ ሲሆን ዛሬ ተመሳሳይ ቤት ትንሽ ቀለም እንደመቀባት ተደርጐ 450.00 ብር ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ቤቱን ለሥራ ቅርብ በሆኑ አካባቢዎች (የትራንስፖርት ወጪ የሚቀንስ) ማግኘት እንደ ከዚህ ቀደሙ ነፃ መሆን (ዘመድ ጓደኛ ወዳጅ ወይም ፍቅረኛ ማስጠጋት) ዘበት ነው፡፡ በአጭሩ የግለሰብ ቤት መከራየት ማኅበራዊ ግንኙነት ካልኖረ ወይም ካልተቀነሰ በየሁለት ወሩ ቤት መቀያየር ግድ ይላል፡፡ 

ታዲያ የመንግሥት ሠራተኞችና የተሻለ ገቢ ያላቸው ፊታቸውን ወደጋራ መኖሪያ ቤት ማዞራቸው አልቀረምና እዚያም ሌላ የዋጋ ንረት ተከሰተ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት 2ዐዐ2 ዓ.ም. ስቱዲዮ ባለአንድና ባለሁለት መኝታ ቤት ወርሃዊ አማካይ ኪራይ ለእያንዳንዳቸው 3ዐዐ.ዐዐ፣ 600.00፣ 800.00 ብር የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ተመሳሳይ ቤቶች 750.00፣ 1,350.00፣ 2,200.00 ብር መከራየት ግድ ሆኗል፡፡ ያም ግድ ቢሆን እንደልብ አይገኝም ወይም የሦስትና የስድስት ወር ክፍያ በአንዴ ውለዱ የሚባል አስገዳጅ ሕግ አለው፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከላይ በተገለጸው የዋጋ ልዩነት መሠረት እንደየደረጃቸው ከ150 እስከ 275 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል ማለት ነው፡፡ በወር 1,500.00 ብር ደሞዝ የሚያገኝ  የመንግሥት ሠራተኛ ስቱዲዮ ተከራይቶ ለመኖር ሌላ ገቢ ማግኘት፣ ከግማሽ በላይ ደሞዙን ለቤት ኪራይ ማዋልና መሠረታዊ ፍላጐቱን ዝቅ ማድረግ አሊያም በግለሰብ ቤት አጐብድዶ መኖር ዙሪያው ገደል ዓይነት አስከፊ አማራጮች ተደቅነውበታል፡፡ አንዳንድ የተማረሩ የመኖሪያ ቤት ዋጋ ጭማሪ በዚህም ባቆመልን ሲሉ ሌሎቹ “ዕድሜ ስለተነገሩት የሐዋሣ ማስታወቂያዎች አከራዮች በኪራይ ጭማሪ ከተማዋን በአጭር ጊዜ እስኪያስለቅቁን እንኖራለን” እያሉ በምፀት ቁጭታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በእርግጥ የመጠለያ እጥረትና የኪራይ ንረት አነሳን እንጂ በገንዘብ የማይገለጹ የአከራይ ተከራይ ድራማዎች በየሽንት ቤቱ የሚፃፉ የማስታወቂያ ብዛት የሰዓት እላፊና የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ገደብ የሃይማኖት ቅድመ ሁኔታዎችና ሌሎች ሁኔታዎች ሐዋሳን “ለመኖሪያ ምቹ” የተባለላትን ማስታወቂያ የሚያስቀይሩ ሆነዋል፡፡

ተስፋ የተጣለበት ግን ብዙ ያልተጓዘ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ 
በሐዋሣ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ከተጀመረ ከ1999 እስከ ዛሬ ድረስ ከ2000 የማይበልጡ ቅድሚያ ክፍያ ለፈፀሙና በአንዴ ለገዙት ነዋሪዎች ቁልፍ ተሰጥቷል፡፡ በሐዋሣ ከተማ አስተዳደር በአሁን ወቅት ያልተጠናቀቁና በሂደት የሚገኙት 1890 ሕንፃዎች በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መኖራቸውን የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚህ በፊት 14,000.00 ብር የነበረው የባለሁለት መኝታ ቤት ቅድመ ክፍያ ዛሬ 29,000.00 ብር መሆኑን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡ በጣም አስገራሚው ነገር የጋራ መኖሪያ ቤት ወርሃዊ ኪራይ ብቻ ሳይሆን የቅድመ ክፍያ መጠን በእጥፍ መጨመር፤ ጨምሮም ቢሆን ማግኘት በአድሎና ብልሹ አሠራር ከተፈለገው አላማ ውጪ መኖሪያ ቤት ላላቸው እየተሰጠ መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ ይህን ሀቅ እስከዛሬ ለነዋሪ ከተሰጡት ምን ያህሉ እየኖሩበት ስንቱ አከራይቶ እንዳለ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የሆነው ሆኖ በሐዋሣ ቅድመ ክፍያ ለባለሁለት መኝታ ቤት መኖሪያ በ2001 ዓ.ም. 14,000.00 ብር የነበረው ዛሬ 29,000.00 ብር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡ የባለ አንድ መኝታ ቤትና ስቱዲዮም ዋጋ ቢሆን እንደዚሁ ነው፡፡ 

ስለዚህ እጥረቱ እንዳለ ሆኖ የአሁኑን ቅድሚያ ክፍያ ሰጥቶ ቁልፉን የሚያገኘው የትኛው የመንግሥት ሠራተኛ ነው? ለመከራየት እንኳን ካለው የኑሮ ውድነት ጋር የማይሞከር በሆነበት የጋራ መኖሪያ ቤት ያን ያህል ገንዘብ መክፈል የማይታሰብ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞች ይገልጻሉ፡፡ በሐዋሣ ከተማ ግንባታቸው ተስተጓጎሎ በተቀመጠላቸው ጊዜ መጠናቀቅ ያልቻሉ በተለይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማና ኤስኦኤስ አካባቢ በድምሩ 1980 ሕንፃዎች የሚገኙ ሲሆን ተመዝግበው የሚጠባበቁ ነዋሪዎች “የተስፋ መኖሪያዎች” በማለት አስተዳደሩ ለመኖሪያ ቤት እጥረት ተገቢውን ትኩረት እንዳልሰጠ ይናገራሉ፡፡  የአስተዳደሩ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በደንቡ መሠረት 80 ከመቶ አጠናቀናል፣ ያን ያህል ዘገየ የሚባል አይደለም በማለት ያስተባብላል፡፡ ይሁን እንጂ የተወሰነ መዘግየት በተለያዩ ምክንያቶች መኖሩን ጽሕፈት ቤቱ አልሸሸገም፡፡ የመኖሪያ ቤት ኖሯቸው ኮንደሚኒየም የወሰዱ አሉ ስለመባሉና እጣው ሲጣል ተገቢውን ማጣራት ሳይደረግ ነገር ግን ባለፉት ወራት 87 ቤቶች ላይ ከማዘጋጃ ቤት ጋር በተደረገው ጥናት መለየቱን የጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውዴ ለማ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ የገለጹ ሲሆን እነዚያ ቤቶች ተነጥቀው ለተጠባባቂዎች እንደሚሰጡም አስታውቀዋል፡፡

ከከተማው እንደ ደሴት ተነጥለው የቆዩት የዳቶ ሰፋሪዎች መኖሪያ ቤት ዕጣ ፈንታ 
በቱላ ክፍለ ከተማ ስር ባለውና ዳቶ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ “ከገበሬዎች ጅምር ቤት” ገዝተው መጠለያ የሰሩ ነዋሪዎች ጥር 2003 ዓ.ም. ሕገወጥ ሰፋሪዎች ተብለው ቤታቸውን ማፍረስ ተጀምሮ መቋረጡ የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህ ነዋሪዎች ከአስር ዓመት በላይ ግለሰብ ቤት ተከራይተው የቆዩ ቤት መሥሪያ መሬት ማግኘት ያልቻሉና ሌሎች ችግሮች ያለባቸው ዜጐች መደበኛ ኑሮ ቀጥለው ከመከተማቸው በላይ የመሠረተ ልማትና ማኅበራዊ ተቋማት ተስፋፍቶላቸው ነገር ግን ሕጋዊ የከተማ መኖሪያ ቤት ባለቤትነት ካርታ ያላገኙ ናቸው፡፡ ሆኖም 2003 ዓ.ም መጨረሻ አስተዳደሩ አስፈላጊውን መረጃ ሰብስቦ በሊዝ ወደ ከተማዋ እንደሚቀላቅላቸው እየተነገረ ነው፡፡ በመሠረቱ ወደ አርባ ሺሕ የሚጠጉ አባወራዎች እዚያ ዳቶ አካባቢ “ጅምር ቤት” ገዝተው ኑሮን ባይጀምሩ በሐዋሣ የመኖሪያ ቤት እጥረትና የኪራይ ዋጋ ንረት በጣም ከፍተኛ ምናልባትም ሐዋሣ ለኑሮ የሚመርጧት ሳይሆን የሚሸሿት ከተማ በሆነች ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን አዝማሚያው ወደዚያው ነው፡፡ አንድ መፍትሔ ካልተፈጠረ በስተቀር፡፡ 

የሐዋሣ ከተማ የመኖሪያ ቤት ቦታ እጥረትና ቀጣይ የስፋት ወሰን
በስምንት ክፍለ ከተሞች በ1996 ዓ.ም. የተዋቀረው የሐዋሣ ከተማ አስተዳደር በስተሰሜን ጥቁር ውኃ፣ በስተምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ሐዋሣ ሐይቅ፣ በስተምሥራቅ ወንዶገነት፣ ማልጋና ሸበዲኖ ወረዳዎች፣ በስተደቡብ ሐዋሣ ዙሪያ ወረዳ የሚያዋስኗት ሲሆን በመሀል አካባቢዎች ለመኖሪያም ሆነ ለንግድ እንቅስቃሴ የሚውል የግንባታ ቦታዎች እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የቀበሌ ቤቶችንና የቆዩ የግለሰብ መንደሮችን በማንሳት ለኢንቨስትመንት የሚሆኑ ቦታዎችን ለማዘጋጀት መታቀዱን ምንጮች ይናገራሉ፡፡ 

ለመልሶ ማልማት ከታሰቡት መካከል የከተማዋ ቀደምት መንደሮች ማለትም ሐረር፣ ውቅሮ፣ ኮረምና አዲስ አበባ ሰፈሮችን እንደሚያጠቃልል ለአስተዳደሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ ዝርዝር አፈጻጸሙና የካሳ ወይም የምትክ ቦታ አሰጣጥ መመሪያ እንዳልተዘጋጀ እኚህ ምንጭ ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል በተጠቀሱት ድንበሮች አካባቢ ከተማው የመስፋት ዕድሉ ቢኖረውም በዋናነት ዕድገቷ ወደቱላ ክፍለ ከተማና አጐራባች ወረዳዎች (ወንዶ ገነት ማልጋና ሸበዲኖ) አቅጣጫ መቀጠሉ ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ለቱላ ክፍለ ከተማ በገጠር ቀበሌዎች ሰፊ ቦታዎች ያሉ በመሆኑ አስተዳደሩ ቀጣይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፊቱን ወደዚያው አካባቢዎች ማዞሩ ግድ ይለዋል፡፡ እስከዛሬ በቱላ ክፍለ ከተማ ምንም አይነት የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ አልተጀመረም፤ ሆኖም አንዳንድ ግለቦች ልክ እንደ ዳቶ ሰፈር “ጅምር ቤት” እየገዙ መጠለያ ሰርተው እየገቡ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ በሐዋሣ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤት ከሕዝቡ ቁጥር ዕድገት አንፃር እየተጓዘ ያለው በስተጀርባ መሆኑን ነባራዊ ሁኔታዎች ያመለክታሉ፡፡ ሆኖም በቅርቡ በአዲስ አበባ የታሰበው የ40/60 የመኖሪያ ቤት ፖሊሲ በሐዋሣም ተግባራዊ መደረጉ የሚቀጥል እንደሆነ የጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ጠቁመዋል፡፡ ያም ሆኖ በከተማዋ መጠለያ ያጡ ነዋሪዎች ችግር ፈቺ መፍትሔ ስለመኖሩ ይጠራጠራሉ፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤት ተስፋም እንደዚሁ የታሰበውን ርቀት ስለመጓዙ የሚያመላክት እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ 

http://www.ethiopianreporter.com/component/content/article/300-social/8872-2012-12-15-08-55-12.html