POWr Social Media Icons

Sunday, December 16, 2012በጋዜጣው ሪፖርተር

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት  በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጀመረውን ውይይት ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም. አስቀጥሎ ነበር፡፡
በተጠቀሰው ቀን ያካሄደው የውይይት ርዕስ ‹‹ወቅታዊው የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታና የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰባሰብ ሚና›› የሚል ነበር፡፡ በዚህ ውይይት ላይ የፓርቲው የፖለቲካ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙላቱ ጣሰው ለፓርቲው አባላት የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ እሳቸው በኢትዮጵያ ሁሉም ዓይነት የዜጎች መብቶች የሚከበሩበትና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የሚኖርበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት፣ ባለፉት ዓመታት በተከታታይ የተደረጉት ጥረቶች ሁሉ ውጤት አላመጣም ይላሉ፡፡

በውይይቱ ላይ እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ለምን ለውጥ እንዳላመጡ አቶ ሙላቱ ሲያብራሩ፣ ሦስት ተዋናዮችን በተወሰነ ደረጃ መመልከት አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም ማስረዳታቸውን ቀጠሉ፡፡ ሦስቱ ተዋንያን የተባሉት ገዥው ፓርቲ፣ ተቃዋሚዎችና ሕዝብ ናቸው፡፡

ገዥው ፓርቲ
ገዥውን ፓርቲ (ኢሕአዴግ) ከትናንት እስከ ዛሬ ብለው አጠር አድርገው በተነተኑበት ክፍል የራሱን አገር አስገንጥሎ ዕውቅና የሰጠ፣ የአገሪቱን የባህር በር የዘጋ፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ፣ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች አሳልፎ የሰጠና ፍትሐዊ የሀብት ክፍል የሌለበት አምባገነናዊ ሥርዓት ማስፈኑን፣ በጦርነት ወቅት የወረሳቸውን ንብረቶችና ሀብቶች በእጁ ይዞ የፓርቲ ኩባንያዎችን እያስፋፋ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹የገዥው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የአገሪቱን ሀብት በመቆጣጠር ላይ ናቸው፡፡ አገራችን ከበቂ በላይ ለም መሬትና ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች እያሏት፣ በምግብ ሰብል ራሳችንን ባለመቻላችን ሕዝባችን ለከፍተኛ ረሃብ ተዳርጓል፤›› ያሉት አቶ ሙላቱ፣ መንግሥት የሚጨነቀው ደግሞ ለገበያ ተኮር ምርቶች ነው ብለዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ አርሶ አደሩ ከተበጣጠሰ መሬት ከሚያመርታቸው የምግብ ሰብሎች ሳይቀር ለውጭ ገበያ ኤክስፖርት ስለሚደረግ ረሃቡን አብብሶታል፡፡ ‹‹የመንግሥታችን የልማት አጀንዳ የፖለቲካ አጀንዳ በመሆኑ፣ የልማት ቅደም ተከተል ስትራቴጂው ለውጤት ሳይሆን ለመንግሥት ፍላጎት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም አብዛኛው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች እየኖረ መሆኑን፣ የኑሮ ውድነቱ እነሱ ቀነሰ ይላሉ እንጂ ከዕለት ዕለት እየናረ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት ስለማይከበር ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ይረገጣሉ ያሉት አወያዩ፣ ለሁሉም ዓይነት የሕዝብ መብት ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ የአሸባሪነት ስያሜን መለጠፍ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሲቪክ ማኅበራት እንዲከስሙ መደረጉን፣ መንግሥት በሁሉም መስክ የሚሠራው ገመና እንዳይወጣበት ነፃ ሚዲያውን አፍኖ የራሱን አራጋቢዎች ያለ ኃፍረት በሙሉ ኃይላቸው እንዲሠሩ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡ ‹‹መንግሥታችን በዚህ ዘመን ገመናን ሸፋፍኖ መደበቅ እንደማይቻል ነጋሪ ወዳጅ ወይም መካሪ የለውም፡፡ ተቃዋሚዎቸ ለኢሕአዴግ መንገር የሚገባቸው ዛሬም አልመሸም የራስን ዕድሜ ለማሳጠር ከመሥራት፣ የአገሪቱን ሁሉን አቀፍ ችግሮች ብቻችሁን ልትፈቱት አትችሉምና በጋራ እንምከርበት ብለው እቅጩን ሊነግሯቸው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹በኃላፊነት ስሜት የአገራችን ህልውና ጉዳይ አሳስቦናልና በጋራ እንምከርበት ሲባሉ ደግሞ ሥልጣናችንን በአቋራጭ ሊጋሩን ነው የሚል ሥጋት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ ተቃዋሚዎች ሥልጣንን የምንፈልገው በዲሞክራሲ መንገድ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ብቻ እንጂ በሌላ በማናቸውም መንገድ መረከብ እንደማንፈልግ አረጋግጠናል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ኢሕአዴግ ከቅድመ መለስም በፊት ሆነ ዛሬ በብዙ አገራዊ ችግሮች የተዋጠ ፓርቲ በመሆኑ በሥልጣን የመቆየቱ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ያሉት አቶ ሙላቱ፣ ኢሕአዴግ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለማስተናገድና ዲሞክራሲን ለመገንባት ባህሪውም፣ አቅሙም፣ የሠራቸው ግድፈቶችም አይፈቅዱለትም ብለዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ኢሕአዴግ ዕድገቱን የጨረሰ ፓርቲ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች

የአንድነት ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሙላቱ ጣሰው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመሠረቱት የአገርን የፖለቲካ ችግር እንዲፈቱ ሳይሆን፣ በገዥው ፓርቲና በተለያዩ ወገኖች ቡድናዊ ፍላጎት ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የሚያቀርቡት ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ በብዙ አገሮች ባልታየ ሁኔታ በርካታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መመሥረታቸውን ነው፡፡ ቁጥራቸው እስከ ዘጠና ደርሶ ነበር ብለው፣ ፓርቲዎቹ የተመሠረቱትም ብሔርንና ኅብረ ብሔራዊነትን ማዕከል አድርገው ነው ይላሉ፡፡

አመሠራረታቸውን በሚገልጹበት ክፍል ፓርቲዎቹን በተለያዩ የአመሠራረት ዘይቤ ይተነትኗቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹በገዥው ፓርቲ ፍላጎት የተመሠረቱ፣ ምርጫን ለማሳወቅ በምርጫ ጊዜ ብቻ የሚመሠረቱ የምርጫ ፓርቲዎች፣ ለጥቅማ ጥቅም የሚመሠረቱ የቤተሰብ ፓርቲዎች፣ ሳንበለጥ ፓርቲዎች፣ እንደንፋሱ የሚነፍሱ፣ በአራዳ ቋንቋ ፎርጅድ ፓርቲዎች ማለትም በሌላ ስያሜና ታሪክ ላይ የሚቆሙና ተመሳሳይ ፕሮግራም ያላቸው ፓርቲዎች ብለን ማስቀመጥ እንችላለን፤” በማለት ይፈርጇቿዋል፡፡ የፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ እንደ አበቃቀላቸው የሚወሰን መሆኑንና ብዙዎቹ ለተቋቋሙበት ተልዕኮ ብቻ አገልጋይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

“ብዙዎቹ ፓርቲዎች የተመሠረቱት ዘወግን (ብሐረተኝነትን) ማዕከል አድርገው ነው፡፡
በአንድ ብሔር ውስጥ እስከ አራት የሚደርሱ የተቃዋሚ ድርጅቶች ተመሥርተዋል፡፡ የብሔሩ አባላትም በአንድ ብሔር ውስጥ በሚፈጠሩ የተለያዩ ድርጅቶች እንደገና ይበጣጠሳሉ፡፡ በዝርያ (ብሔረተኝነት) ላይ የተመሠረተ ፓርቲ ወይም የድርጅቱ አባል ስለ ብሔራዊ ጉዳይ በይፋ ለመታገል የተመሠረተበት የብሔር ድርጅት ይገድበዋል፡፡ በዚሁ የብሔር ማዕከልነት የተመሠረተን ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራሙን የሚቀበል የሌላ ዝርያ አባል ቢጠይቅም ተቀብሎ አያታግለውም፤ ዝርያው ስላልሆነ፤” በማለት ገልጸዋል፡፡

አቶ ሙላቱ እንደሚሉት፣ የኅብረ ብሔር ፍቃድ ያላቸው ፓርቲዎችም ስለ ብሔሩ ችግሮች ጉዳይ አንስቶ ቢታገልም ቅሬታ ያነሳሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር አገራዊ የሆነውን ትግል እንዲቆራረጥ አድርጓል ይላሉ፡፡ “ለመሆኑ በዘውግ (በብሔረተኝነት) ማዕከልነት የሚመሠረቱ ድርጅቶች ትግል የት ድረስ ይዘልቃል ብለን እንጠይቅ?” ብለው፣ ትግሉ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊው ጉዳይ የፈለገውን ውጤት ቢያመጣ በብሔራዊ ደረጃ ያለው ችግር ካልተፈታ የትም ሊደረስ አይችልም በማለት ያስቀምጣሉ፡፡

በዘውግ ማዕከልነት የሚመሠረቱ ፓርቲዎች ትግል ለአጠቃላይ ውጤቱ ሊረዳ ይችል እንደሆነ እንጂ የሚሉት አቶ ሙላቱ፣ ማዕከላዊ መንግሥቱ ዲሞክራሲያዊ ካልሆነ ውጤቱ የትም አያደርስም ይላሉ፡፡ “ፓርቲዎቹ በተጠና ንድፈ ሐሳብ ወይም በሚቀበሉት የፖለቲካ ፍልስፍና የሚመሠረቱ ከሆነ ግን አገራዊ ውጤት ለማግኘት ይቻላል፡፡ በንድፈ ሐሳብ ወይም ሊያዋጣ በሚቻል የፖለቲካ ፍልስፍና የሚመሠረት ፓርቲ ሁሉንም የሚያሳትፍ፣ ለሁሉም የሚሠራና አገራዊ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፤” በማለት ይሞግታሉ፡፡

አሜሪካን እንደ ምሳሌ በማንሳት አሜሪካ የፖለቲካ መረጋጋት ያላት አገር የሆነችው ለሕዝቦች ሰላምና ዕድገት ሊያመጣ በሚችል በዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ አስተሳሰብ በመመራቷ ነው ብለዋል፡፡ የፓርቲዎች የጋራ ችግር አምባገነናዊ አመራርን በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ትግል አውርዶ ዲሞክራሲያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መመሥረት ብቻ መሆኑን ገልጸው፣ በሁሉም ፓርቲዎች የጋራ ችግር ዲሞክራሲያዊ ምርጫን ለመገንባት አለመቻል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “ደግሜ ለመናገር የዲሞክራሲ ተቋምን ለመገንባት አለመቻል ብቻ ነው የሁሉም ፓርቲዎች የጋራ ችግር፤” ብለዋል፡፡

“በመሆኑም ሁለንተናዊ ችግሮች በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈቱ ከሆነ ወይም ዲሞክራሲያዊ ተቋም የማይፈታው ነገር የለም ብለን ካመንን ለምን ለየብቻ እንቆማለን?” ካሉ በኋላ፣ በሌላ በኩል በተለያዩ ፍላጎቶች ምክንያት ዲሞክራሲን የሚፈሩ ይለዩዋቸው ይሆናል እንጂ፣ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው የሚያስቡ ፓርቲዎች ግን ለመገናኘት ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ አይኖራቸውም በማለት ያስረዳሉ፡፡ “አንድ ላይ ቆመው ትግሉን ማፋጠን ሲችሉ በዚህ ባለመስማማት የሕዝቡን የመከራ ጊዜ የሚያራዝሙ ግን አንድ ቀን በሞራልና በታሪክ የሚያስጠይቃቸው ይመስለኛል፤” ብለው፣ “አገራችን ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በሕግና በባህል የተመሠረተች አገር ናት ስንል ከላይ የተገለጹት ሁሉም መሪ የሆኑ እሴቶቻችን የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ሀብቶችና መገለጫዎች ናቸው፤” በማለት አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ፓርቲዎች ለአገራዊ ትግሉ አብረው ቢቆሙ የሚጠበቅባቸውን ሕዝባዊ ኃላፊነት ለመወጣት ያስችላቸዋል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ችግርም በዲሞክራሲያዊ መንገድ ከተፈታ የእያንዳንዱ ብሔር ችግር በመርህና በነፃ ያለሞግዚት በሚቋቋም ያልተማከለ ፌዴራላዊ የራስ አስተዳደር እንደሚፈታ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ አንድ ዓይነት ፕሮግራም ያላቸው ፓርቲዎች ተበታትነው ማዶ ለማዶ እንደሚታዩ የተናገሩት አቶ ሙላቱ፣ ፓርቲዎቹ ቆመንለታል የሚሉት ሕዝብ ለምን ቢላቸው የሚመልሱትን እነሱ ያውቁታል ይላሉ፡፡ “አንድ ዓይነት የፖለቲካ ፕሮግራም ያላቸው ፓርቲዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አንድ ላይ መሥራት አለባቸው፡፡ ሕዝብም ሃይ ሊላቸው ይገባል፡፡ ባለፉት ዓመታት የተወሰኑ ፓርቲዎች ሕዝብ ወይ ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ የሚል ግፊት ስላደረባቸውና በተወሰኑ ቡድኖች ፍላጎት በተለያዩ ጊዜያት አንድ ላይ ለመሥራት ሞክረዋል፡፡ የተወሰኑትን ትልልቆቹን ኅብረት ስንመለከት አማራጭ ኃይሎች፣ ኢትፖድኅ፣ ኅብረት፣ ቅንጅትና ሌሎችም ተመሥርተው ነበር፡፡ ነገር ግን ዲሞክራሲያዊ ተቋም መገንባት ስለተሳናቸው ለመፈራረስ ጊዜ አልወሰደባቸውም፤” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የፓርቲዎችን ችግር በዘረዘሩበት ክፍል ያነሱት የጋራ አመራርና ዲሞክራሲያዊ የአሠራር መርህ አለመከተላቸውን፣ ሥራቸው አሳታፊ አለመሆኑን፣ በዕውቀት ላይ ያልተመሠረተ አመራር እንደሚያምሳቸው፣ የግለሰብ መሪዎች ወሳኝነት፣ የልዩነት ሐሳብን አለማስተናገድ፣ የብሔርና ኅብረ ብሔር የአስተሳሰብ ጽንፎችን በመወጠር ልዩነቶቻቸውን ማስፋት፣ የውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲ አለመኖር፣ መናናቅ፣ አለመተማመን፣ አለመቻቻል፣ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትን የሰጥቶ መቀበል መርህ አለመቀበል ጥቂቶቹ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ማወቅ የሚገባቸው በማለት ማንም ብቻውን አሸናፊ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ፣ ፓርቲዎች የኅብረተሰቡን ጥቅም መሠረት በማድረግ ስለሚደራጁ ሕዝባዊ ትግሉን በቅጡ ካልመሩ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለባቸው መሆኑን መዘንጋት፣ ችግሮችን በውይይት መፍታት እየተቻለ ጽንፈኛ አቋም መያዝ፣ በመለያየታቸው የሕዝቡን አመለካከትና ፍላጎት እንደሚበታትኑ አለመገንዘብ፣ ፓርቲው ለቆመለት ዓላማ ሕዝብን አለማነቃነቅና ከሌሎች ጋር ተባብሮ ካልሠራ የመክስሚያ ጊዜውን ቆሞ የሚጠብቅ መሆኑን መገንዘብ እንዳለባቸው፣ ለፓርቲዎች የለውጡን ጊዜ ለማፋጠን ብቸኛው አማራጭ መተባበር ወይም አብሮ መሥራት ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከሕዝቡ የሚጠበቅ 

“የአገራችን ሕዝብ ከጫፍ ጫፍ ከኢሕአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ነፃ መውጣት ይፈልጋል፡፡ የሥርዓቱ ተጠቃሚ ካልሆነ በስተቀር ፖለቲካዊ መብቶቹ እንዲጠበቁለትና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ያለጥርጥር ይፈልጋል፤” ያሉት አቶ ሙላቱ፣ ነገር ግን…” በማለት ሕዝቡ የተለያየ ወግና ባህል ያለው በመሆኑ፣ ደረጃው የተለያየ የሥነ ልቦና አመለካከት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ባህሎችና እሴቶች በትግሉ ላይ የተወሰነ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም፤” ብለዋል፡፡ “ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ”፣ “እግዚአብሔርን ፈሪ መንግሥትን አክባሪ” ከሚል ትውልድ በተወረሰ ባህልና ሁሉም እኛ ባልነው ይለቅ በሚሉ ልሂቃን ገዳቢነት የሚመራ ትውልድ ትግል አዝጋሚ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም በማለት ይገልጹታል፡፡

ድንፋታ፣ ስሜታዊነት፣ አጉል ድፍረትና ጀብደኝነት በተጠና ፖለቲካዊ መርህ መገራትአ አለባቸው ብለው፣ ሕዝቡ ለውጥን ከተቃዋሚዎች ወይም ከጥቂት አርበኞች መጠበቅ አይኖርበትም ይላሉ፡፡ “ለውጥ መምጣት ያለበት በለውጥ ፈላጊው ሕዝብ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሕዝብ በራሱ ትግል ነፃ መውጣት አለበት፡፡ የምንታገለው ለራሳችን መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ በጋራ መታገል የሚያስፈልገው ነፃነታችንና ክብራችንን ከሌሎች ጋርም ስለምንጋራ ነወ፡፡ በትግሉ ሒደት አንድ ነፃ አውጭ፣ ሌላው ነፃ ወጪ ሊሆን አይገባውም፡፡ የፓርቲዎች ድርሻ አባላቱን የሚያደራጁ፣ የሚያስተምሩና ትግሉ በዕውቀት ላይ እንዲመራ ማድረግ ነው፤” በማለት ገልጸዋል፡፡

ፓርቲዎች የኅብረተሰቡን ትግል ይመራሉ እንጂ ሕዝቡን የመተካት ሚና የላቸውም ያሉት አቶ ሙላቱ፣ “ዛሬም አቀርቅሮ ማልቀስም ሆነ አንጋጦ ማማረር ለውጥ አያመጣም፡፡ ነፃ የምንወጣው በነፍስ ወከፍ ትግላችን ብቻ ነው፡፡ ከእንግዲህ ነገን እየፈሩ መኖር ይብቃ፤” በማለት ገለጻቸውን ደምድመዋል፡፡

-    ከ18 መደበኛ ስብሰባዎች ስድስቱን ብቻ ተሰብስቧል
በዮሐንስ አንበርብር

በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት የሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑን የጀመረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በሳምንት ሁለት ጊዜ ማክሰኞና ሐሙስ ማካሄድ የሚገባውን መደበኛ ስብሰባዎች በአብዛኛው አላካሄደም፡፡ በምክር ቤቱ የአሠራር ሥነ ሥርዓት ደንብ መሠረት የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባዎች በሳምንት ሁለት ጊዜ መካሄድ ይገባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ ሥራውን ከጀመረበት የመስከረም ወር መጨረሻ አንስቶ እስከ ታህሳስ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ድረስ 18 መደበኛ ስብሰባዎች መካሄድ ነበረባቸው፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ያደረገው ስድስት መደበኛ ስብሰባዎችን ብቻ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በምክር ቤቱ ከሁለት ሳምንት በፊት ተገኝተው ያፀደቁት አዲስ የካቢኔ አወቃቀርና የሚኒስትሮች ሹመት የመጨረሻው ወይም ስድስተኛው መደበኛ ስብሰባው ነበር፡፡

ኅዳር 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ከተካሄደው ከዚህ መደበኛ ስብሰባ በኋላ እንኳን አራት የመደበኛ ስብሰባ ቀናት ቢኖሩትም፣ “ዛሬ ይካሄድ የነበረው መደበኛ ስብሰባ የማይካሄድ መሆኑን ከይቅርታ ጋር እንገልጻለን” የሚሉ ማስታወቂያዎችን የምክር ቤቱ አባላት መኖሪያዎች አካባቢ በሚገኙ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች፣ እንዲሁም በምክር ቤቱ ሰሌዳዎች ላይ በመለጠፍ የመደበኛ ስብሰባ ፕሮግራሞቹን መዝለል የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡

የምክር ቤቱ ዋና ሥልጣንና ተግባሮች የሚቀርቡለትን ረቂቅ አዋጆች ተወያይቶ ማፅደቅና አስፈጻሚውን ወይም ራሱ የሚያመነጫቸውን የመንግሥት አካላት መቆጣጠር ናቸው፡፡

እስካሁን ካካሄዳቸው ስድስት መደበኛ ስብሰባዎች መካከል የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የዚህን ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሥራ ዘመን መጀመርን አስመልክተው መንግሥት በዓመቱ ትኩረት ሊያደርግባቸው ይገባል በሚል ያቀረቡት ንግግር ሲሆን፣ ሁለተኛው ስብሰባ በዚሁ የፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር ላይ የተነሱ ጥያቄዎችን ተንተርሶ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመንግሥታቸውን አቋም ያብራሩበት ነው፡፡

ቀሪዎቹ ሌሎች ስብሰባዎች ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረትና ለመንገድ ግንባታ በተገኘ ብድር ዙሪያ የተደረጉ ስምምነቶች ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ በአስፈጻሚው የመንግሥት አካል አመንጭነት ከሚቀርቡለት አዋጆች ውጭ በራሱ ሕግ የማመንጨት ሥልጣን ቢኖረውም፣ ላለፉት ዓመታት ያለው ታሪክ በጣት የሚቆጠሩ ሕጎች በፓርላማው መመንጨታቸውን ነው፡፡ ለአብነት ያህልም በሦስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጨረሻ የሥራ ዘመን አካባቢ የፀደቀው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ተጠቃሽ ነው፡፡

ካለፉት ልምዶች መረዳት የሚቻለው በአስፈጻሚው አካል የሚቀርቡ አዋጆች ከሌሉ የፓርላማው መደበኛ የስብሰባ ጊዜያት ጥያቄ ውስጥ መሆናቸውን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ካለው ጠቅላይ ሚኒስትሩን በወር አንድ ጊዜ ጠርቶ የመጠየቅ ሥልጣን ሲኖረው፣ በተመሳሳይ መንገድ የተለያዩ የዘርፉ ሚኒስትሮችን በሳምንት አንድ ጊዜ በመጥራት ስለ ሥራ አፈጻጸም ክዋኔያቸውና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች መጠየቅ ይችላል፡፡

ነገር ግን ባለፉት ወራት ምክር ቤቱ አንዳቸውንም ሳያደርግ መደበኛ ስብሰባዎቹን እያስተላለፈ የግማሽ ዓመቱን የአንድ ወር ዕረፍት በየካቲት ወር ለመውሰድ አንድ ወር ከቀናት ዕድሜ ቀርቶታል፡፡

የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው ለምክር ቤቱ የቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ጥቂት መሆናቸውን፣ በዚህም ምክንያት መደበኛ ስብሰባዎች እንዳልተካሄዱ፣ ነገር ግን የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በየዘርፋቸው የሚገኙ ተጠሪ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶችን በመቆጣጠር ሥራ መጠመዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ አዋጆችን ከመመልከት በተጨማሪ የተመረጡ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶችን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶች በመደበኛ ጉባዔው የማዳመጥ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን፣ ከጥር ወር በኋላም እነዚህ መሥሪያ ቤቶች የግማሽ ዓመት ሪፖርታቸውን እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡