POWr Social Media Icons

Saturday, December 1, 2012


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለፓርላማ ያቀረቡትን ሹመት ፓርላማው አፅድቆታል፡፡ ተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችም ተሹመዋል፡፡
እያንዳንዱ ሹመት በፓርቲ ውስጥ ተሳትፎን ያረጋገጠ፣ አመኔታ ያሳደረ፣ የሕዝብ ጥቅምና ክብርን ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ መሆኑን አደራ በማለት ልዩ ትኩረት ሰጥታችሁ አረጋግጡ፣ ወስኑ፣ ፈጽሙ፣ ከማለት በስተቀር ለምን ሾማችሁ አንልም፡፡ ተሿሚዎች ኃላፊነታቸውን በሚፈለገው ብቃት፣ ሥነ ምግባርና ፍጥነት ሲወጡ ለማየት እንጓጓለን እንጂ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በአጠቃላይ ለመንግሥት፣ መንግሥታዊ ሥልጣን ለያዘው ኢሕአዴግ አንድ ዓብይና ጠቃሚ እንዲሁም አስቸኳይ የሆነ የምናቀርበው ጥያቄ ግን አለን፡፡

ጥያቄያችንም ስለመሾም ስታስቡ ስለሚሻሩም ታስባላችሁ ወይ? የሚል ነው፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥ ከተፈለገም ክፍት ቦታ ላይ መሾም ብቻ አይደለም ቁም ነገሩ፡፡ የተያዘ የሥልጣን ወንበር ካለና ወንበሩ ላይ የተቀመጠው ሹምም ብቁ ካልሆነ፣ ከሥልጣኑ በማንሳት የተሻለ መሾም አስፈላጊ መሆኑን አምናችሁ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ናችሁ ወይ? የሚል ነው፡፡

መሾም አለባቸው ከሚለው ጎን ለጎን መሻር አለባቸው የሚባሉ እንዳሉም መታመን አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የኃላፊነትና የሥልጣን ወንበሮች ላይ ተቀምጠው ሥራቸውን በሕግ፣ በግልጽነት፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ መወጣት ያልቻሉ አሉ፡፡ በአቅም ማነስ፣  በሥነ ምግባር ጉድለትና በፖለቲካዊ አመለካከት ምክንያት፡፡

መንግሥትም ሆነ ኢሕአዴግ ይህንን ሁኔታ በድፍረትና በቆራጥነት አይተው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት የማይወጡትን ከኃላፊነት ማንሳት አለባቸው እንላለን፡፡

ብቁዎችን ሾሜያለሁ ከማለት ጎን ለጎን ብቃት የሌላቸውን ሽሬያለሁ ወይም እሽራለሁ መባል አለበት፡፡ ስለሚኒስትሮችና ኮሚሽነሮች ብቻ አይደለም እያነሳን ያለነው፡፡ በተለያዩ የሥልጣን እርከኖች ያሉትን በሙሉ በመፈተሽና በመገምገም ብቃትና ሥነ ምግባር የሌላቸውን መሻር ወይም ማባረር ያስፈልጋል እያልን ነው፡፡ ያውም በአፅንኦት!!!

በፌዴራል ደረጃ ብቻ ስላለው ሥልጣን አይደለም እየተነጋገርን ያለነው፡፡ በክልሎችም እንደዚሁ ብቁዎችን እንሾማለን ሲባል ብቃት የሌላቸውን እንሽራለን በሚል መታጀብ አለበት፡፡ ክፍት ቦታ ሲኖርና ሲገኝ እንሾማለን መባል ብቻ የለበትም፡፡

እከሌ ወይም እከሊት ብቃት ስላለው ወይም ስላላት የተሻለ ኃላፊነት እንስጥ ሲባል፣ እከሌና እከሊት ግን ሕዝቡን እያገለገሉ ስላልሆኑ እንሻራቸውና በምትካቸው የተሻለ ይሾም የሚለው መኖር አለበት፡፡

መፈራራት ካልሆነ በስተቀር ኢሕአዴግ አቅምና ብቃት የሌላቸው፣ በጉቦና በሙስና የተዘፈቁ ሹሞች እንዳሉት አያውቅም አንልም፡፡ ያውቃል፡፡ መንግሥትም አያውቅም አንልም፡፡ ያውቃል፡፡ ያውቃል ብቻ ሳይሆን የግል ሌቦች ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥት ሌቦችም አሉ ብሎ በይፋ መናገሩ ይታወሳል፡፡

ስለዚህ ጥያቄያችን የመንግሥት ሌቦች ይነሱ፣ የመንግሥት ሌቦች ይሻሩ፣ የመንግሥት ሌቦች ለፍርድ ይቅረቡ፣ የመንግሥት ሌቦች ተጠያቂ ይሁኑ ነው፡፡ ሕዝብም እያየ፣ እያስተዋለ፣ እየታዘበና እያዘነ ነው፡፡ ሕዝብን ለማገልገል ቃለ መሀላ ፈጽመው መንግሥት ከሾማቸው በኋላ ሕዝብንና አገርን ትተው ለግል ሀብትና ንብረት የሚሯሯጡ ሹሞች እንዳሉ ሕዝብ እያየ ነው፡፡

አገርንና ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ግለሰብንና ባለገንዘብን የሚያገለግሉ ሹሞች እንዳሉ ሕዝብ በዓይኑ እያየ በጆሮው እየሰማ ነው፡፡ አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁሌም፡፡ ሌላውን ሕግ አክብር፣ ሥነ ሥርዓት ይኑርህ፣ በአገርና በሕዝብ አትቀልድ እያሉ እየወነጀሉና መግለጫ እየሰጡ፣ እነሱ ራሳቸው ግን ሕግ ሳያከብሩ፣ ሥነ ሥርዓት ሳይኖራቸው፣ በአገርና በሕዝብ ሲቀልዱና ሲያስቀልዱ ይታያሉ፡፡

‹‹ሹሞች›› ተብለው ተቀምጠው ‹‹ተላላኪዎች›› መባልን የመረጡም አሉ፡፡ ተላላኪዎች ደግሞ ከሹመት ይሻሩ፣ ይባረሩ ነው እያልን ያለነው፡፡ በተግባር እነዚህን ሰዎች ለመሻር ቀላል እንዳልሆነ ይገባናል፡፡ ለኢሕአዴግም ለመንግሥትም ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹የመንግሥት ሌቦች›› የያዙት የሥልጣን ስፋት በካሬ ሜትር ሲለካ ‹‹የሕዝብ አገልጋዮች›› ከያዙት ይዞታ በላይ ሊሰፋ ይችላል፡፡ ከላይ ከላይ በቀላሉ ቢታወቅም ውስጥ ለውስጥ ያላቸው ኔትዎርክ ግን ሰፊና የተወሳሰበ ነው፡፡ የተበላ ቢቃወማቸውም የበላ ይደግፋቸዋል፡፡

በመሆኑም ትግሉ ቀላል ነው ማለት አይደለም፡፡ ትግሉ ቀላል ባይሆንም ግን ግዴታ ነው፡፡ በፍላጎትና በእምነት ደረጃ ሕዝብና መንግሥት ዕድገት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ ይመኛሉ ይፈልጋሉ፡፡ በተግባር ግን እንቅፋት አለ፡፡ እንቅፋቶቹም በሕዝብ የሚቀልዱና በአገር የሚነግዱ፣ ብቃት የሌላቸው፣ ሥነ ምግባር የጎደላቸው፣ የአገርና የሕዝብ ፍቅርና ወገናዊነት የሌላቸው ሹሞችና ኔትዎርኮቻቸው ናቸው፡፡

ፍላጎትን ዳር ለማድረስ፣ ዕቅዶችን በብቃት ለማሳካት ከተፈለገ ምርጫው አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ፀረ ሕዝብ ሹሞችን፣ ሙሰኛ ባለሥልጣናትን፣ ተላላኪዎችንና አስመሳዮችን ከሥልጣን ማንሳት፣ ተጠያቂ ማድረግ፣ ለፍርድ ማቅረብ የግድ ነው፡፡

የብቁዎችን ሹመት እንደግፋለን፡፡ የደካሞችን፣ የሙሰኞችንና የመንግሥት ሌቦችን ሽረት ደግሞ እንጠብቃለን፡፡
 http://www.ethiopianreporter.com/editorial/294-editorial/8693-2012-12-01-08-49-39.html


-    ካቢኔው በሕገ መንግሥቱ መሠረት አንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ይኖረዋል
-    የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ ያላቸው ሁለት ባለሥልጣናት ተሹመዋል
-    አዲሱ አደረጃጀት ከሌሎች ሕጐች ጋር ተቃርኖ አለው እየተባለ ነው

በዮሐንስ አንበርብር
የሥራ አስፈጻሚውን ከፍተኛ ሥልጣን በማግኘት አገሪቱን መምራት ከጀመሩ ሁለት ወራት ከቀናት ያስቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመቅረብ ካቢኔያቸውን በአዲስ መልክ እንዳደራጁ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት የሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችንና የሌሎች ሚኒስትሮችን ሹመት አፀድቀዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ የካቢኔ አደረጃጀትም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የሚኒስትሮች ምክር ቤት (ካቢኔ) በሕገ መንግሥቱና በመመሥረቻ አዋጁ የተጣለበትን ኃላፊነቶች በብቃት ለመወጣትና የአስፈጻሚነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ ለማድረግ፣ እንደ አዲስ በሦስት ዘርፎች መዋቀሩ አስፈላጊ መሆኑን ለፓርላማው አስታውቀዋል፡፡

በዚህም መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲፕሎማሲ፣ የደኅንነት፣ የመከላከያ እንዲሁም ከፍተኛና ግዙፍ (ሜጋ) ፕሮጀክቶችን በቀጥታ እንዲከታተሉ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ አስፈጻሚው የሚከታተላቸውን ተግባራት በብቃት ለመምራት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሦስት ዘርፎች እንዲዋቀር መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ማኅበራዊ ጉዳዮችን፣ መልካም አስተዳደርና ረፎርምን፣ ፋይናንስና ኢኮኖሚን የሚመለከቱ ሦስት የሥራ ዘርፎች በአዲሱ የካቢኔ መዋቅር የተፈጠሩ ሲሆን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የማኅበራዊ ዘርፉን የሚመሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ቢሮን በሚኒስትር ማዕረግ ሲመሩ የነበሩት አቶ ሙክታር ከድር በአዲሱ የካቢኔ መዋቅር መሠረት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደርና ሪፎርም ዘርፍን እንዲያስተባብሩና እንዲከታተሉ ተሹመዋል፡፡ በሽብር ተግባር ከተከሰሱት ባለቤታቸው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ አባልነታቸው የተወገዱት አቶ ጁነዲን ሳዶ የሚመሩትን የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴርን በሚኒስትርነት እንዲመሩም ተሹመዋል፡፡

በቅርቡ የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትርነታቸው በተጨማሪ፣ የካቢኔውን የፋይናንስና ኢኮኖሚ ዘርፍ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ እንዲከታተሉና እንዲያስተባብሩ ተሹመዋል፡፡

ያልተጠበቁ ሹመቶች
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሕልፈት ተከትሎ የሥራ አስፈጻሚውን ሥልጣን ማን ይይዛል በሚል በርካታ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ በኢሕአዴግ መተካካት ፖሊሲ መሠረት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን እንደሚይዙ በመንግሥት በኩል ቢገለጽም፣ ተግባራዊነቱ በመዘግየቱ ለጥርጣሬዎችና ለተለያዩ መላምቶች ክፍት እንደነበር ይታወሳል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሾሙ በኋላ ቀደም ሲል ይመሩት የነበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ላለፉት ሁለት ወራት በተጠባባቂ ሚኒስትሩ መመራቱ ለተመሳሳይ መላምቶች ሰለባ ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው እንዲሠሩ መደረጉ፣ በቀጣይነት የሙሉ ሚኒስትርነት ሹመት ይሰጣቸዋል የሚለውን ግምት አጠናክሯል፡፡ በተለይም አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ የረጅም ዓመታት ልምድ ማካበታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥልጣንን በርካቶችን ከእሳቸው ውጭ ማንም አይወስድም የሚል ግምት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡

ይሁን እንጂ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩን ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖንም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በማሾም በርካቶችን አስገርመዋል፡፡

ዶ/ር ቴዎድሮስ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ አድናቆት የተቸራቸው ናቸው፡፡ በጤናው ዘርፍ ከሚፈለገው የውጭ ግንኙነት አንፃርም በቂ የሆነ ተደማጨነትን አግኝተዋል፡፡ የወባ በሽታን ለማጥፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረገውን ርብርብ የሚመሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ መሆናቸው የዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና የፀጥታ አስቸጋሪነት፣ እንዲሁም በዚህ ዘርፍ ምንም ዓይነት ልምድ የሌላቸው ከመሆኑ አንፃር ሲገመገም፣ አሁን የተሾሙበት የሥራ ኃላፊነት አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል የሚሉ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበለጠ ሁኔታ ተጠናክሯል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሥልጣናቸው ላይ እንዲቆዩ መደረጉ ዶ/ር ቴዎድሮስ በጤናው ዘርፍ የውጭ ግንኙነት መስክ ካተረፉት ተደማጭነት ጋር ተዳምሮ ትልቅ ጉልበት ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡

የአቶ ሙክታር ከድር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ለመልካም አስተዳደርና ሪፎርም፣ እንዲሁም አቶ ጁነዲንን ተክተው ለሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትርነት ተሹመዋል፡፡ በወቅቱ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ አቶ ጁነዲን በተነሱበት ምክንያት ላይ ማብራሪያ የጠየቁ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ምላሽ ሳይሰጡ ዘለውታል፡፡ 

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው፣ ኦሕዴድ አቶ ጁነዲንን ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው በማውረድ ተራ አባል እንዲሆኑ በማድረጉና ከባለቤታቸው ጋር በተያያዘ ለመገናኛ ብዙኅን በሰጡት አስተያየትም በመተቸታቸው፣ ይህንኑ ያገናዘበ ዕርምጃም በኢሕአዴግና በመንግሥት በኩል ሊወሰድ እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ የዶ/ር ቴዎድሮስን መዛወር ተከትሎ በጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት የተሾሙ ሲሆን፣ ላለፈው አንድ ዓመት ያህል በንግድ ሚኒስትርነት ሲሠሩ የነበሩት አቶ ከበደ ጫኔ በዚሁ ሥልጣን ላይ እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡

አቶ ከበደ ጫኔ በሚኒስትርነት እየሠሩ የነበረ ቢሆንም፣ የሚኒስትርነታቸውን ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያላፀደቀው በመሆኑ ይህንኑ ለማሟላት ብቻ ሹመታቸው ወደ ፓርላማው ሊቀርብ ችሏል፡፡

የሕግ ጉዳይ
በአዲሱ የካቢኔ አወቃቀር መሠረት ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንዲኖሩ መደረጉ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጋጫል የሚሉ የተቃውሞ አስተያየቶች እየተሰሙ ነው፡፡ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ግን ሕገ መንግሥቱ ስለ ብዛት አያወሳም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ያሾማል ነው የሚለው በማለት አስተያየቱን ውድቅ አድርገውታል፡፡ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ግን አሁንም የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው ይላሉ፡፡ ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌሎቹን ተሿሚዎች ያቀረቡት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ነው በሚል ነው፡፡

‹‹..ይህ ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከዚህ ቀደም ለምክር ቤቱ አቅርቤ ካፀደኩት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት በተጨማሪ ሁለት የኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ መሾም አስፈልጓል፤›› በማለት ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለፓርላማው ያስረዱት፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም ሹመቱ ከተለያዩ የአገሪቱ ሕጐች ጋር ተቃርኖ እንዳለው ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም የብሔራዊ ባንክና የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተቋማትን ማቋቋሚያ አዋጅ ይጠቅሳሉ፡፡

ነሐሴ 5 ቀን 2000 ዓ.ም. የተሻሻለው የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ክፍል ሁለት አንቀጽ 3(4) የብሔራዊ ባንክ ተጠሪነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል በማለት ያስረዳል፡፡ በመሆኑም በአዲሱ የካቢኔ መወቅር መሠረት የፋይናንስና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን እንዲከታተሉ ዶ/ር ደብረፅዮን በመሾማቸው፣ ከተጠቀሰው አንቀጽ ጋር የሚቃረንና ብሔራዊ ባንክም ከተቋቋመበት አዋጅ ውጭ ለዶ/ር ደብረፅዮን ሪፖርት እንዲያደርግ ያስገደድዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር ኮሚሽንም በመቋቋሚያ አዋጁ መሠረት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሆንም፣ በአሁኑ መዋቅር መሠረት ግን ለአቶ ሙክታር ከድር ሪፖርት እንዲያደርግ ይገደዳል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከፍተኛና ግዙፍ (ሜጋ) ፕሮጀክቶችን ራሳቸው ለመከታተል በአዲሱ መዋቅር ኃላፊነት የወሰዱ ቢሆንም፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከፋይናንስና ከኢኮኖሚ ጉዳዮች ጋር በቀጥታ የሚገናኙ በመሆኑ ፕሮጀክቶቹን ነጥሎ መከታተል አዳጋች እንደሚሆን ያስረዳሉ፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም የአሁኑን ሹመትና ምደባ በሌላ መንገድ የሚመለከቱ ወገኖች አሉ፡፡ እነሱ እንደሚሉት፣ የኢሕአዴግ አራቱ አባል ድርጅቶች በአዲሱ አመራር ሥልጣኖችን ተከፋፍለዋል፡፡ ደኢሕዴን የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ሲይዝ፣ የተቀሩት ማለትም ሕወሓት፣ ኦሕዴድና ብአዴን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ተከፋፍለዋል ይላሉ፡፡ በዚህ መደባ መሠረት ደግሞ ሕወሓት የፋይናንስና የኢኮኖሚ ዘርፍን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን፣ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስቴርን በመያዙ ከሌሎቹ በተሻለ ሁኔታ ሥልጣን ማግኘቱን ይተቻሉ፡፡ 
 http://ethiopianreporter.com/news/293-news/8738-2012-12-01-11-22-47.html
Written by  መታሰቢያ ካሳዬ

ኃላፊነቴን ከህዝቡ ጋር በአግባቡ እወጣለሁ - ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም
ሹመቱ ኢህአዴግ ያለበትን የፖለቲካ ሽኩቻ ለማስታገስ ያደረገው ነው
የተሰጠው ሹመት በብቃት ላይ የተመሰረተ አይደለም
ሹመቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚ/ር አሻራ አለበት (ተቃዋሚዎች)
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ያፀደቀውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት፣ የንግድ ሚኒስትርነት፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነትና ሌሎች ሹመቶችን አስመልክቶ ሹመቱ በአግባቡና በሥርዓት ያልተሰጠና ህጋዊ ሥርዓት የሚጐድለው ነው ሲሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡ ሹመቱ ህገመንግስቱን የሚጋፋና ከህግና ሥርዓት ውጪ የተሰጠ ነው ሲሉም ተችተውታል፡፡
በአንድ ድምፀ ተአቅቦና በሙሉ ድምጽ ድጋፍ በፀደቀው ሹመት መሠረት ሁለት ተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሮችም ተሹመዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተከናወነው ሥነሥርዓት ሹመታቸው የፀደቀላቸው አቶ ሙክታር ከድር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር እና ሪፎርም ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በምክትል ጠቅላይ ሚ/ር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ አቶ ታደለ ጫኔ የንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር እና ዶ/ር ከስተብርሃን አድማሱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡
ብቸኛው የመድረክ ተወካይና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ በሹመቱ ወቅት ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል፡፡ አቶ ግርማ ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉበትን ምክንያት ሲናገሩም፤ ሹመቱ ከመሰጠቱ በፊት ስለተሿሚዎቹ ለምክር ቤቱ አባላት መረጃ እንዳልደረሳቸው አመልክተው፤ ሹመቱ የተሰጠበት አሠራር ቀደም ሲል ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ በቆዩበት ህግ መሠረት በመሆኑና መዋቅሩ አስቀድሞ መጽደቅ ቢገባውም ባለመጽደቁ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ፓርቲያቸው ምክር ቤቱ የሰጠው ሹመት ትክክል ነው ብሎ እንደማያምን የገለፁት አቶ ግርማ፤ በተለይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ የተሰጠው ሹመት ህግና አሠራርን የተከተለና አግባብ የሆነ ነው ብሎ መቀበል እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ ሹመቱ ኢህአዴግ የለበትን የፖለቲካ ሽኩቻ ለማስታገስ ያቀረበው መፍትሄ ነው ያሉት አቶ ግርማ፤ ህጋዊ አሠራርን ያልተከተለና በብቃት ላይ ያልተመሰረተ ሹመት ነው ሲሉ ገልፀውታል፡፡
የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ ፓርቲው እንደ ፓርቲ አቋም ለመያዝና መግለጫ ለማውጣት ገና አለመገናኘቱን ጠቁመው እንደግለሰብ ግን ሹመቱ ህጋዊ አሠራርን የተከተለ ነው ብሎ ማመን እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ ይህ ሹመት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አሻራ ያለበትና ከዚህ ቀደም ይወራ የነበረውን ጉዳይ በይፋ ያረጋገጠ ሹመት ሆኖ እንደሚሰማቸውም ተናግረዋል፡፡
ሹመቱ የተሰጠበት አግባብ ህገመንግስታዊ ሥርዓቱን የተጋፋ ነው ያሉት አቶ ሙሼ፤ ይህንን ለማድረግ ከፈለጉም በቅድሚያ ህገመንግስቱን ማረም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ ቀደም ሲል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በሚሰሩት ደረጃ ለመሥራት አቅም የለንም የሚለውን ሃሳብ የሚያጠናክርና በራሳቸው አቅም ማስቀጠል አለመቻላቸውን አመላካች ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
“በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር በርካታ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን በመሾም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስልጣኖች ቀንሰው ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡
በሹመቱ ላይ ያለው ሁኔታ ግን ቀደም ሲል ሲወራ የቆየውን ጉዳይ ተግባራዊ ማድረግ ነው፤ ምንም አዲስ ነገር የለውም” ሲሉ ተናግረዋል - አቶ ሙሼ፡፡ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተሾሙት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ሹመቱን አስመልክቶ በስልክ በሰጡን አስተያየት፤ የተጣለባቸው ሃላፊነት እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቁመው፤ ህዝብ እምነት አሳድሮ እስከመረጠኝ ድረስ ሃላፊነቴን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡ ለአመታት የሰሩበትን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መ/ቤትን አስመልክተው ሲናገሩም፤ ቀደም ሲል በተዘጋጁ መስመሮች በመጓዝ ህዝቡን በሚያሳትፍ መልኩ ሥራዎችን መሥራት ከተተኪው ሚኒስትር የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ዶ/ር ቴዎድሮስ ጠቁመዋል፡፡ 
http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=5293:%E1%89%B0%E1%89%83%E1%8B%8B%E1%88%9A-%E1%8D%93%E1%88%AD%E1%89%B2%E1%8B%8E%E1%89%BD-%E1%88%B9%E1%88%98%E1%89%B1-%E1%88%85%E1%8C%88%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%88%B5%E1%89%B1%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%8C%8B%E1%8D%8B-%E1%8A%90%E1%8B%8D-%E1%8A%A0%E1%88%89&Itemid=20

ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ለምክር ቤቱ አቅርበው ያፀደቁትን አዲስ የካቢኔ አደረጃጀት እንዴት ያዩታል?
ከዚህ በፊት ሰምቼ ነበር፤ ሶስት ቦታ እንክፈለው የሚለውን፡፡ በዛን ጊዜ ግን ስምምነት ላይ አልተደረሰም፡፡ በአንድ ነገር ላይ ግን ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ አዲስ የሚመጣው ጠ/ሚኒስትር ማንም ይሁን ማን ከዚህ በፊት የነበረው ጠ/ሚ የነበረውን ሃይል ክምችት ይዞ መቀጠል እንደማይችል ተነጋግረው ጨርሰዋል፡፡ ማን ጠ/ሚ ይሆናል የሚለው አይደለም ወሳኙ፤ ህወሓት አካባቢ ማን እየተሾመ ነው የሚል ነው ወሳኙ፡፡ አሁንም ቢሆን ምንም ወዲያና ወዲህ የለኝም፡፡
በእኔ ግምት ሕወሓት አሁንም ቢሆን ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ ተቀምጧል - ጠ/ሚ ለመሆን፡፡ በሁለት መንገድ ነው እየሄዱ ያሉት፡፡ በውጭ ጉዳይም ትክክለኛ የስልጣን ቅብብል ነው የሚባለው ጉዳይ አሁን ጥያቄ ውስጥ የገባ መሰለኝ፡፡
ህወሓት ከያዘው ቁልፍ የሚኒስቴር መ/ቤቶች ስልጣን አኳያ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ ሊሆን የሚችለውን ለመገመት ስንሞክር አመራሩ እንደ ዱላ ቅብብል ነው የሚባለው ጥያቄ ውስጥ የገባ ይመስለኛል፡፡ ወሳኝ ወሳኝ ቦታዎችን ወስደዋል፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሄዷል፤ እዛው ተመልሶ ቦታው ገብቷል፡፡ ወሳኝ የሚባለው የፋይናንስና ኢኮኖሚው ሄዷል፤ ተመልሶ ቦታው ገብቷል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የጠ/ሚኒስትርነት ስልጣኑ (ቢሮ) የተጠናከረ ነውና ለሶስት መክፈል አለብን የሚል ሃሳብ ተነስቶ ነበር፡፡
በጊዜው ያ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የጠ/ሚ ቦታ ከህወሓት እጅ ከወጣ የህወሓት የበላይነት ያከትማል የሚል ስጋት ነበራቸው፡፡ አሁን እንግዲህ አንድ ጠ/ሚኒስትርና ሦስት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች አሉን ማለት ነው፡፡ እያንዳንዳቸው ደግሞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በክላስተር ተከፋፍለው አስተባባሪነት ተሾሞባቸዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ መተያየት ያለበት ማንኛውም ለየትኛው ክላስተር (ዘርፍ) በአስተባባሪነት እንደተመደበ ነው? ሽግሽግ ሲመጣ ሹመት ሲመጣ ህወሓት ተጠናክሮ እንደመጣ እንመለከታለን፡፡ ፋይናንስና ኢኮኖሚውን ዶ/ር ደብረጽዮን ያዘ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩን ዶ/ር ቴዎድሮስ ያዘ፤ በሶስተኛ ደረጃ መከላከያው የት ቦታ እንዳለ እናውቃለን፡፡ ይህንን ሁሉ የያዘ ፓርቲ የስልጣን ፍፁም የበላይነቱን ያዘ፣ ተቆጣጠረ ማለት ነው፡፡ ሕወሓት አካባቢ ማን ነው የበላይነት የያዘ የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡
ህወሓት ሁለት አመራሮቹን አጭቷል፤ ዶ/ር ደብረጽዮንና ዶ/ር ቴዎድሮስን፡፡ ከሶስት ዓመት በኋላ ስለጠ/ሚኒስትሩ ማንነት ስገምት ግምቴ ወደ ዶ/ር ደብረጽዮን ያደላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ህወሓት ተደከመ፣ ሞተ የሚባለው ወሬ የተጋነነ ይመስለኛል፡፡
ታላቁ መሪያችን የፃፈውን እንተገብራለን ብለው የአሁኑን ጠ/ሚኒስትር በመሾም የመጀመሪያውን ፎርሙላ ካሳዩን በኋላ፣ በይደር ያስቀመጡት ሁለተኛው ፎርሙላ መሆኑ ነው የአሁኑ ለሶስት መካፈል - እኛ እስከምንዘጋጅ ነው ነገሩ፡፡ በዚህ ክፍፍል ለማን ምን እንደደረሰው አሁን ግልጽ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ከተቀመጠ በኋላ ሌሎች ሁለት ምክትሎች ከጐኑ ማሰለፍ የሚገርም ነው፡፡ አንዳንዶቹ ሰውዬው ልምድ ስለሚያንሳቸው ነው ይላሉ፡፡ መቼ እድል ተሰጠው፡፡ እስከ አሁንስ በመለስ ምስል አይደል እንዴ ያለነው፡፡
አቶ ሃይለማርያም መከላከያው፣ ደህንነቱ፣ ዲፕሎማሲው በጠ/ሚኒስትሩ ስር እንደሆነ ተናግረዋል?
ይህማ እንዳልሆነ ሊሾሙ አራት ቀን ሲቀራቸው 37 ከፍተኛ መኮንኖች መሾማቸውን ሰምተናል፡፡ እነዚህን ከፍተኛ መኮንኖች ማሾም የነበረበት ማን ነው? ከዚህ አንፃር የህወሓት የበላይነት ተመልሷል ለሚሉት ቀድሞስ መች ጥያቄ ውስጥ ገባና እንላቸዋለን፡፡ አቶ ሃይለማርያም የካቢኔውን አደረጃጀት ሲያስረዱ፤ ከሌሎች በፓርላሜንታዊ ዲሞክራሲያዊ ሲስተም ከሚተዳደሩ ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት እያደገ ከሚገኙት አገሮች የካቢኔ አወቃቀር የተወሰደ ልምድ እና የተካሄደ ጥናት እንዳለ ገልፀዋል …
ይህ የተለመደ የኢህአዴግ ፊሊጥ (MODUS Operandi) ነው፡፡ ከግሪክ አመጣነው ከግብጽ ወሰድነው ይላሉ፡፡ ሌጂቲሜሲ ለመመስረት የሚደረግ ነው፡፡ 
http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=5294:%E1%8A%A0%E1%8B%88%E1%89%83%E1%89%80%E1%88%A9-%E1%8B%A8%E1%88%85%E1%8B%88%E1%88%90%E1%89%B5%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%88%A5%E1%88%8D%E1%8C%A3%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%89%A0%E1%88%8B%E1%8B%AD%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%8B%AB%E1%88%B5%E1%8C%A0%E1%89%A5%E1%89%85-%E1%8A%90%E1%8B%8D&Itemid=20

ሃዋሳ ህዳር 22/2005 ህገ መንግሰቱ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የተጀመረውን የፀረ ድህነት ዘመቻና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ራዕይ ከዳር ለማድረስ ህብረተሰቡ በጋራ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት አስገነዘቡ ። ለሰባተኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዩኒቨርሲቲው ግቢ ከትናንት ጀምሮ በተለያየ ዝግጅት በድምቀት እየተከበረ ነው ። ፕሬዚዳንቱ ዶክተር ዮሰፍ ማሞ በአሉን አስመልክቶ የተዘጋጀውን የፓናል ውይይት ሲከፍቱ እንደተናገሩት ህገ መንግስቱ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ድህነትን ለማስወገድና በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተቀየሱ የልማት ራዕዮችን ለማሳካት ሁሉም በጋራ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል። የክልሉ ህዝብና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በህገ መንግሰቱ የተጎናፀፈውን ራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነት በመጠቀም ባለፉት ሃያ አንድ አመታት በርካታ የልማት ድሎችን ሊያስመዘግብ መቻሉን አስታዉቀዋል ። በሀገሪቱ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ልማት በማስመዝገብ ድህነት ለማስወገድ ለተያዘው እቅድ መሳካት ሁሉም በየተሰማራበት ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል። በአሉ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ሲያነሱት የነበረው የነፃነትና የእኩልነት መብት ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ዕለት በመሆኑ በአሉ ለዘላለም ሲዘከር ይኖራል ብለዋል ። የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፌ ጉባኤ አቶ መሃመድ ረሽድ በበኩላቸዉ በሀገሪቱ ሁሉም አከባቢ እየተካሄዱ ያሉትን የልማት ጅምሮች በማፋጠን ዋንኛ ጠላት የሆነውን ድህነት ድል ለመንሳት የሁሉም አካላት የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል። የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀር ላይ የመሰረቱትን አንድነታቸውን በማጠናከር ባለፉት አመታት በድህነት ላይ በጋራ በከፈቱት ዘመቻ በርካታ አኩሪ ድሎችን ማስመዝገብ መቻላቸውን ተናግረዋል። በሀገሪቱ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች የመሰረተ ልማት ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶች ህገ-መንግስቱ ያስገኛቸው ትሩፋቶች በመሆናቸው እነዚህ ድሎች ሳይቋረጡ ለማስቀጠል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ አመራር፣ ተማሪዎችና የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡ በትናንትናው የፓናል ውይይት የተለያዩ የልማት ስኬቶችና በህገ መንግሰቱ ዙሪያ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን በዓሉ ዛሬም ቀጥሎ የደቡብ፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የትግራይና የታዳጊ ክልል የብሄር ብሄረሰቦች አልባሳትና ባህላዊ ትዕይንትና ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ከወጣው መርሀ ግብር ለማወቅ ተችሏል።