POWr Social Media Icons

Wednesday, November 21, 2012


የእቅድ ክንውን ሪፖርት በቀረበበት ወቀት የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደሰታ ዶጊሶ አንደተናገሩት በሩብ አመቱ የእናቶችንና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
ከከተማዋ ፈጣን እድገት ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤናና የማህበራዊ ችግሮች በመፈታት ነዋሪውን ጤናማ፣ አምራችና የበለፀገ ለማድረግ የጤና ልማት ሰራዊት ግንባታ ተግባራዊ መሆን መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
የህብረተሰብ ጤና ልማት ሰራዊትን ከመገንባት አንፃርም ከ63 ሺህ 993 ሞዴል ቤተሰቦች ማፍራቱን ተናግረዋል፡፡
በሪፖርቱ እንደቀረበው የሳንባ ነቀርሳ በሽታን መከላከያ ክትባት ለ2 ሺህ 678 ህፃናት ለመስጠት ታቅዶ 2 ሺህ 971 የተከናወነ ሲሆን ባለፈው ሩብ አመት አብዛኛዎቹ አፈፃፀሞች ከእቅዱ 9ዐ በመቶ እና ከዚያ በላይ ተግባራዊ መሆናቸው በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡
ከመንጋጋ ቆልፍ በሽታ የተጠበቀ ህፃናት እንዲወለዱ ከማድረግ አንፃርም በሩብ አመቱ 2 ሺህ 678 ህፃናት አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ ከእቅድ በላይ መከናወኑንም ተጠቁሟል፡፡
በመቀጠልም በበጀት ዓመቱ የጤና ሴክተር ትኩረት የሚያደርገው የጤና ተቋማት በማስፋፋትና በግብዓት በሟሟላት የጤና አገልግሎቶች ጥረት ማሻሻል የእናቶችና የህፃናት ሞትን በመቀነስና ዋና ዋና ተላላፊ በሽታዎችና መከላከልና መቆጣጠር ላይ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት 124 እናቶች የወሊድ አገልግሎት ለመስጠት እቅድ ተይዞ ለ49 እናቶች ብቻ አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን በቀጣይም በተሻለ ሁኔታ ለመስራት ጥረት እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
በምክክር መድረኩም የሀዋሣ ክፍለ ከተሞች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የጤና ባለሙያዎች እና ሌሎች አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡http://www.smm.gov.et/_Text/11HidTextN105.html
ጽህፈት ቤቱ 7ኛውን የአለም ህፃናት ቀን ከትምህርት ቤቶች ጋር አክብbል፡፡
የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ አብርሃ አታሮ እንዳሉት ትምህርት ቤቶች ሰብአዊ መብትን በተመለከተ ህፃናት ተኮትኩተው የሚያድጉበት በመሆኑ የኮሚሽኑን አላማ ለማሳካት ትልቅ ፋይዳ አላቸው፡፡
መጪው ትውልድ ሰብአዊ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር የሚያስችለውን ስንቅ ከትምህርት ቤቶች ይቀስማል ብለዋል ፡፡
በሀገራችን ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም ህፃናት ቀን “ሁሉም ህፃናት ሰብአዊ መብቶችን በማከበር፣ በማስከበርና ሌሎችንም በማስገንዘብ ትምህርት ቤቶች ትልቅ ሚና አላቸው” የሚል መርህ አላው፡፡
በበአሉ አለም አቀፍ የህፃናት መብቶች ኮንቬንሽንን፣ የአፍሪካ ህፃናት ሰብአዊ መብትንና የኢትዮጵያ መንግስት ለሠብአዊ መብቶች የሠጠውን ትኩረት የሚዳስስ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡
የበአሉ ተሳታፊ ህፃናቶች የተለያዩ ጭውውቶችንና ሥነ ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች በሥነ ምግባር የታነፀ የሞራል እሴት ያለው፣ የነቃና ህግ አስከባሪ ዜጋ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት  ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት እንዲደግፉ ጥሪ ቀርቧል ፡፡ ባለደረባችን ደስታ ወ/ሰንበት እንደዘገበው፡፡http://www.smm.gov.et/_Text/11HidTextN305.html
ሰላም! ሰላም! ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ላላችሁ በሙሉ። አንድ ወዳጄ ይኼንን የአቅጣጫ ሰላምታ እንደማይወደው አጫውቻችሁ አውቃለሁ? ለምንድን ነው ስለው ‹‹የሰው ልጅ እንደ ንፋስ በአቅጣጫ ላይ ተመሥርቶ ሰላምታ ሲለዋወጥ እበሽቃለሁ፤›› አይለኝ መሰላችሁ? የዘንድሮን ሰው የሚያበሽቀውን ነገር ብዛት ቆጥረን መጨረስ አቃተን! ግን ግን ንፋስን ለምንከተል የዘመኑ ሰዎች ይህ ሰላምታ ካልተሰጠ ለማን ይሰጥ? ለራስ ብቻ የሚሮጥበት ዘመን መሆኑን ካየን ዘንዳ ከዚህ ሌላ ምን ይባላል? አንዳችን ያለ ሌላችን መኖር እንደማንችል እያወቅነው ‘እኔ’ን ብቻ ላማከለ ነፍስ መሮጣችን ይገርመኛል። የሚገርማችሁ ደግሞ አባባልን እንኳ መርጠን አለመጠቀማችን ነው። ለምሳሌ ‹‹ዘመኑ የውድድር ነው›› የሚለውን አባባል ለተቀደሰ ይሁን ለረከሰ ተግባር እንደምንጠቀምበት ሳንለይ ለሁለቱም እንዳሻን እንገለገልበታለን። አሁንማ ሙሰኛውም በሰሞነኛ ተቆጣጣሪዎች ሲያላግጥ ‘ዘመኑ የውድድር ነው’ ማለት ጀምሯል አሉ። ‹‹ውድድሩ ጤናማ ዕድገት ለማስመዝገብ ነው? ወይስ እንደተለመደው ጠልፎ ለመጣል ነው?›› ይሉኝ ነበር ባሻዬ ይኼን ጉድ ቢሰሙ፡፡

ሌባ ቀጪ አጥቶ ለሕዝብ አገልግሎት በሚውል ገንዘብ ደልቦ ሲንጎማለል ይውላል። ተጠቂው ሰፊው ሕዝብ አቧራ ለብሶ ለዕለት ጉርሱ ይማስናል። ፍትሕ የናፈቃት ዓለም። በየጥጋጥጉ ዲስኩር ብቻ ተለጥፎ ይነበባል! ይነበነባል! የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አሁንማ የሰለቸኝ መፈክር ማንበብ ነው፤›› አለኝ፡፡ ‹‹ለምን?›› ብለው፣ ‹‹በመፈክር ውስጥ የተሸጎጡ በርካታ ውሸቶች አሉ፤›› ሲለኝ የገዛ ሳቄ ጆሮዬን አደነቆረው፡፡

ባለፈው ሰሞን አንድ የመንደራችን ጎበዝ ተማሪ ‹‹እኔ ከእንግዲህ ወዲያ ትምህርት የሚባል በቃኝ አቅለሸለሸኝ፤›› ብሎ አቆመው ተብሎ ሲወጣ ሲገባ የሠፈሩ መጠቋቆሚያ መሆኑን ሰማሁ። አንድ ቀን ከባሻዬ ልጅ ጋር ሆነን ልጁ ከሩቅ ሲመጣ አየነውና ጨዋታ ጀመርን። ‹‹ይኼ ልጅ በቃ ትምህርቱን ተወው?›› አልኩት የባሻዬን ልጅ። ሽምግልና የተላከው እሱ ስለሆነ ሚስጥሩን ማወቁ አይቀርም በሚል። በነገራችን ላይ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ይኼን ለመሰለው ነገር የሠፈሩ ቀንደኛ ተመራጭ መካሪና አግባቢ ነው። አሳክቶ መናገሩን ይችልበታል። አሳክቶ መናገሩን እየቻሉበት ስንቱን ከገደል አፋፍ መመለስ የሚችሉ እያሉ በዝምታቸው ምክንያት ስንት ትውልድ ጠፋ ይሆን? ‹‹አይ አንቺ አገር! ይብላኝልሽ ወልደሽ የወላድ መካን እንደሆንሽ ሁሉ ልጆችሽ እያሳመሙሽ ስትኖሪ። ስንቱ በላዩ ላይ በሩን ዘግቶ ተኝቷል መሰለህ አንበርብር? የጋን መብራቱን አትቁጠረው፤›› ይሉኝ ነበር ባሻዬ። ባሻዬ ኢትዮጵያ በምሁር ልጆችዋና በተፈጥሮ ሀብት ክምችቷ ምንም አልተጠቀመችም ከማለት ቦዝነው አያውቁም። እውነታቸውን አይደል ታዲያ? አውቃለሁ ባይ እንጂ እስቲ እንሰማማ የሚል የለም። ቆርጦ ቀጥል ተሰብስቦ ዕውቀት አሳፋሪ መስሏል። በአስተሳሰብ ድህነት ስንጠወልግ ግድ የሚለው መጥፋት ነበረበት? ኧረ ወዴት ነው እየተጨካከንን የምንጓዘው? አንድ የማውቀው ሰው፣ ‹‹አንበርብር ነዳጅ ላይ ተቀምጠን የምንራበው እኮ አገሪቱ ላቧን ጠብ አድረጋ ያስተማረችው ስለተኛ ነው፤›› ያለኝን አልረሳውም፡፡

እናም የባሻዬ ልጅ እንዲህ አለኝ። ‹‹የትምህርት ቤት ዲስኩር ሰልችቶኛል። ተግባር ላይ የማይውል ቢቀር ምን ይጎዳል? ህሊናዬን እየኮሰኮሰኝ ለአገር ዕድገት የማይጠቅም ትምህርት ከምማር ድንጋይ መፍለጥ ይሻለኛል ብሎ አመፀ፤›› ሲለኝ ገረመኝ። ጎበዝ! እንዲህ ያሉ ጠያቂ ታዳጊዎችን እንዴት እያስተናገድናቸው ይሆን? ነገሮችን አብራርተን በማስረዳት ወይስ ‘ለራስህ ስትል ተማር’ እያልን? የባሻዬ ልጅ እንደሚያጫውተኝ ከሆነ ይኼን መሰል ጥያቄ የሚያነሱ ንቃተ ህሊናቸው ከፍ ያለ ተማሪዎች በአግባቡ ከተያዙ ዛሬ አለ የሚሉትን ችግር ነገ አድገው መቀየራቸው እንደማይቀር ነው። ለውጥን በአንድ ጀንበር ካላደረግን ብለው ሲያደናብሩን ስንቶች ወደ ኋላ ጎተቱን መሰላችሁ? ትውልድ ቀርፆ በትውልድ ውስጥ የነገዋን እናት አገር ሰፋ አድርጎ ተመልካቹ ጠፋ። ‹‹ለነገሩ ማንቸስተርና አርሰናል የዘመኑ መላዕክት ሆነው ሌላ መመልከት ይቻል ኖሯል?›› ያለኝ ደላላ ጓደኛዬን አልረሳውም፡፡ ‹‹የዛሬን አያድርገውና በፊት የአርሰናል ደጋፊዎች ሲሸነፉ እሪ ብለው ያለቅሱ ነበር። ያውም በባላንጣቸው ማንቸስተር። ዛሬ ሲለምዱት እንኳን ለቅሶውን ቁጭቱንም ተውት፤›› ብሎኛል አንድ የማንቸስተር ደጋፊ ወዳጄ። ‹‹ሥራ እንዴት ነው?›› ብዬ ስጠይቀው ከልቡ አልሰማኝም መሰል፣ ‹‹ማንቼ ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ ነው፤›› አለኝ፡፡ ወይ አገሬ!

አንዳንዴ የእኛን ነገር ሳስበው እንዴት አድርጌ መሰላችሁ? በአንድ ክንፍ ብቻ እንደሚበር አውሮፕላን ነው። በአጋጣሚም ይሁን በታሪክ በአንድ ክንፍ የበረረ አውሮፕላን ሰምታችኋል!? አዎ! ታዲያ ይኼ አጋጣሚና ታሪክ ለእኛም ደረሰን። እንዴት? ብትሉኝ ነገሮችን ሚዛናዊ አድርገን ከመጓዝ ፅንፈኛ ሆነንና ለሚመቸን ነገር ብቻ ማድላት ሥራችን ስለሆነ ነው። ምሳሌ ልስጥ መሰል? አዎ! ለምሳሌ የቁስ እንጂ የሐሳብ አልሆን ብለናል። ለሚታየው ነገር እንጂ ለማይታየው ዋጋ መስጠት እየተውን እንደመጣን እስኪ በእኔ ይሁንባችሁና ታዘቡ። ማንጠግቦሽ አንድ ማለዳ በሬዲዮ የሚተላለፈውን ማስታወቂያ እየሰማች አንበርብር ‹‹ትሰማለህ ጉዳችንን?›› አለችኝ። ‹‹ምን?›› ስላት  ‹‹አዲስ የፊልም ማሳያ ነው መሰል መጣ ተብሎ በአፍሪካ ብቸኛዋ አስመጪና ቀዳሚ አገር ሲባል? መዝናናቱስ ይሁን። ግን በሥልጣኔ ቀደምት ነን ባልንበት አፋችን ለመፍዘዝ መቅደማችንን ማወጃችን አያበሳጭም?›› ስትለኝ ነው ይኼ ስላችሁ የነበረው በአንድ ክንፍ የመብረር ነገር ወደ አዕምሮዬ የመጣው። ለባሻዬ ልጅ ማንጠግቦሽ ያለችውን እነግረዋለሁ፣ ‹‹አንዳንዴ እኮ ሚዲያዎቻችን የሚሠሩትን የሚያውቁ አይመስለኝም። ጐን ለጐን የሚባለውንና የማይባለውን ቢለዩ ጥሩ ይመስለኛል። አይደለም እንዴ?›› አለኝ፡፡ በማከልም፣ ‹‹የእያንዳንዳችን ትንሽ የሚባል ድርጊት ሕፃናትን በተዘዋዋሪ መተንኮሱ አይቀርም። መልዕክት ስናስተላልፍ ሕፃናትን እናስብ፤›› ብሎ ዝም አለ። ይኼ የአንደኝነት አባዜ የት እንደሚየደርሰን እንጃ፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት የፈራሁት ነገር ቢኖር በመፈክር ብቻ አንደኛ ሆነን ይኼንንም ለዓለም እንዳናስተዋውቅና እንዳንዋረድ ነው፡፡

እስኪ ትንሽ ስለ ሥራ ደግሞ እናውራ። የቢዝነስ ሰው ሆኖ መክሰርን የማይፈራ ያለ አይመስለኝም። ቢሆንም ቢሆንም ከአደጋው ጋር እየተጋፈጡ ካልሠሩ ደግሞ የት ይደረሳል? ይኼን ሰሞን ስንቱ ግዥና ሽያጭ እየተፋረሰ በወጣሁበት አዙሮ ቤቴ አስገባኝ መሰላችሁ? ውዷን ማንጠግቦሽን እላችኋለሁ አንዳንዴ አልፋረስ ብሎ የፀናው የእኔና የማንጠግቦሽ ፍቅር ብቻ ይመስለኛል። ‹‹ማንጠግቦሽ?›› ስላት ‹‹እህ? ደግሞ ምን ሆንክ?›› ትለኛለች። ማንጠግቦሽ ዘንድ ‘አርቴፊሺያል’ ፈገግታ የሚባል ነገር ቦታ የለውም። ‹‹እንዲያው የእኔና ያንቺ ነገር አይገርምሽም ግን?›› ስላት፣ ‹‹ኤድያ አንተ ደግሞ ነገር መደጋገም ትወዳለህ፤›› ስትለኝ፣ ‹‹ይኼ የምን ነገር ነው አንቺ የፍቅር ወግ ነው እንጂ፤›› ስላት፣ ‹‹ኡኡቴ!›› ብላ ለዛ ባለው የኃፍረት ሳቅ ፍርስ ትላለች። ልቤ በስስት አብሯት ይፈርሳል። በተረፈ ውል የሚይዘው፣ ሊሻሻጥ የሚደራደረው፣ አከራይና ተከራዩ፣ ሰውና ቃሉ እየተፋረሰ አስቸግሯል። አንዳንዴ አገሪቷ በመልሶ መገንባት ውስጥ ያለች ‹‹ጥንታዊ ከተማ›› ትመስለኛለች። መፋረስ ሲበዛ እኮ ሰላም መደብዘዙ አይቀርም። ሰላም ከሌለ ምን አገር አለ? እንዴ ለእያንዳንዳችን ወጥተን ለመግባታችን ዋስትናው በስምምነትና በመቻቻል ላይ የተመሠረተ ሰላም ነው። ‘ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ’ ያለው ማን ነበር? ትራንስፎርሜሽኑም እኮ በመፋረስ አይሳካም። ‹‹ትራንስፎርሜሽኑን ለማሳካት የሚቻለው በዕቅድ ላይ የተመሠረተ ተግባር ሲከናወን ነው፤›› እያለ ሬዲዮኑ ሲናገር የሰሙት ባሻዬ፣ ‹‹መጀመርያ ራስህ መፈክር ከመደርደር ተላቀቅ፤›› ሲሉ ሳቄን መቆጣጠር አቃተኝ፡፡ 

እናማ ‹‹ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው›› እንደሚባለው ሆኖ እንዲህ በሳምንት አንዴ ብቻ ያገናኘናል። ሠርቶ የሚያርፈውን ወይም አውርቶ የሚያርፈውን ግን ዕለተ እሑድ ትቁጠረው። በየቢሮው ተወዝፎ የሚውለውን፣ ሥራ ሳይሠራ የሚውለውን፣ ፌስቡክ ላይ ተጥዶ እንቅልፍ የሚይዘውን፣ ከገባበት እስከወጣበት ሰዓት ድረስ ስልክ ላይ የሚለጠፈውን፣ ወዘተ ስትታዘቡ አገሪቱ ህዳሴ ላይ ሳይሆን ፅሞና ላይ ያለች ይመስላችኋል፡፡ ትልቅ ግድብ የምትሠራ አይደለም የጭቃ ቤት የምትለስን አትመስልም፡፡ አገር መንደሩ ተደበላልቆ ደህናው ከብልሹው አልለይ ብሎ ስንታይ ያስፈራል፡፡ ቆይ ግን መንግሥት የሆነ ማጣሪያ ነገር ቢያዘጋጅ ጥሩ አይመስላችሁም? ኦኦ ረስቼው። ለካ እዚህ አገር ሥራ አላሠራ ያለው ይኼ አጣሪ ኮሚቴ የሚባል የተተበተበ ቢሮክራሲ ወላጅ አባት ነው። ትርፉ ድካም ነው። ግን እስከ መቼ አይጥ በበላው ዳዋ እየተመታ እንደምንዘልቅ አይገባኝም። ፍርደ ገምድልነት ስንቱን ትኩስ ነፍስ አቀዘቀዘው መሰላችሁ? ይኼንን መቼም እንደ እኔ ደላላ ሆናችሁ ዞር ዞር ስትሉ ነው የምታውቁት። በትኩስ ኃይሉ ለአገሩ፣ ለወገኑና ለራሱ የሚተጋውን ከአጥፊ ጋር አብሮ እየተወቃ ከሩጫው ጋብ ብሎ እናየዋለን። እኔ ደላላው አንበርብር በምዞርበት ቦታ ሁሉ የምታዘበው ላቡን ጠብ የሚያደርገው ሳይሆን የማያላግጠው ሲበለፅግ ነው፡፡ ኧረ በሕግ!

በነገራችን ላይ ሰሞኑን ጥሩ አቋም ላይ ያለ ዩሮ ትራከር አሻሽጬ ነበር። ታዲያ ጠቀም ያለ ረብጣ ቆጥሬያለሁ። ‹‹አንዳንዴ በጀቱ ከሰማይ ሲለቀቅ እኮ ከምድር ለመሰብሰብ ቀላል ነው ልጅ አንበርብር፤›› አሉኝ ባሻዬ አንዲት ኪሎ ሥጋ ገዝቼ ብወስድላቸው። ፈጣሪ እንደገና እንዲጎበኘኝ ምርቃታቸውን አዥጎደጎዱት። ለምን እንደሆነ አላውቅም ምርቃትና አድናቆት ረዘም ላለ ጊዜ ሲቆይ እፈራለሁ። ስንቱ በአድናቆትና በምርቃት ሲኩራራ እንዳይሆን ሲሆን ስላየሁ ነዋ። ስንቱን መሰላችሁ ይኼ ሥራዬና ዕድሜዬ የሚያሳየኝ። የባሻዬን ልጅ ሥጋቴን ብነግረው፣ ‹‹አዎ ልክ ነህ። ገዢው ፓርቲንም አሁን ያልከውን ነገር እሰጋለታለሁ፤›› አለኝ። ‹‹እንዴት?›› አልኩት ወሬውን እዚያ ላይ የማድረሱ ፍጥነት አስገርሞኝ። ‹‹አየህ ገዢው ፓርቲ በአሁኑ ሰዓት ሕዝብ ከእኔ ጋር ነው፤ ሕዝብ ያምነኛል፤ ይወደኛል ብሎ በእርግጠኝነት አምኗል። በዚህ ያልተረጋገጠ አድናቆት ታውሮ ማስተካከል ያለበትን ነገር እየረሳው ያለ ይመስላል። ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የዲሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብት ፈተናዎች፣ ድህነት፣ የፍትሕ እጦት፣ ወዘተ ሕዝቡን የፊጥኝ ይዘውት የሕዝብ ድጋፍ አለኝ እያሉ መደስኮር ዋጋ ያስከፍላል፤›› አለኝ፡፡ ያለው ሁሉ ልክ ስለነበር አንገቴን እያወዛወዝኩ አዳመጥኩት፡፡ ‹‹አንበርብር›› ብሎ ስሜን ጠራው። ‹‹አቤት?›› አልኩት እንደገና፣ ‹‹ይኼ ዘመን በፍቅር እንጂ በኃይል የትም አይደረስበትም፤›› ሲለኝ መልዕክቱ በደንብ ገባኝ፡፡ የገባችሁ ይግባችሁ፣ ያልገባችሁ ልቦና ይስጣችሁ ከማለት ሌላ ምን ይባላል?

እንደተለመደው ወደ ግሮሰሪያችን ‘ዋን’ ‘ዋን’ ልንል ተጓዝን። እኔም እሱም ጥማችንን የሚቆርጠውን አዝዘን ጨዋታችንን አሜሪካ ላክነው። ‹‹ለመሆኑ ኦባማ በማሸነፋቸው ምን ተሰማህ?›› አልኩት። ‹‹‘እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው’ ሲባል አልሰማህም? ማንም ቢመረጥ ከብሔሪዊ ጥቅማችን ጋር የሚሄድ ፖሊሲ ካለው ይመቸኛል፤›› አለኝ። በዝምታ ትንሽ በየራሳችን ዓለም ሰጠምን። እንዲህ በፍጥነትና በቅልጥፍና ግልጽ የሆነ ምርጫ ለማድረግ ስንት ዓመት ይፈጅብን ይሆን? እያልን ራሳችንን አስጨነቅነው። ‹‹ለመሆኑ አንበርብር ኦባማ ካሸነፉ በኋላ የተናገሩትን ሰምተሃል?›› አለኝ። ‹‹በምን አባቴ የቋንቋ ችሎታ እሰማለሁ ብለህ ነው? አዳሜ የተሰባበረ እንግሊዝኛ ላያችን ላይ እየለቀቀብን የምንችለው እንኳ ይጠፋብን ጀመር፤›› ስለው ከት ብሎ ሳቀ። ሳቁን ሲያባራ፣ ‹‹ምን አሉ መሰለህ? ‘ዛሬ ዋናው ነገር ኦባማን ወይንም ሚት ሮምኒን መምረጣችሁ ሳይሆን በድምፃችሁ ልዩነት መፍጠራችሁ ነው’ ያሉት ንግግር ውስጤ ቀረ፤›› ካለኝ በኋላ ትንሽ አሰብ አድርጎ፣ ‹‹ሥልጣን የሕዝብነቱ ተረጋግጦ በድምፃችን ልዩነት ለማምጣት የዲሞክራሲ ጉዞ ምንጊዜም ወሳኝ ነው፤›› ሲለኝ ተቀበልኩት። ልዩነት በድምፅ ብቻ ይፈጠር ዘንድ ለአገሬ ተመኘሁ። በመፈክር ሳይሆን በተግባር የሚረጋገጥ ዲሞክራሲ ማን ይጠላል? ከመፈክር ይልቅ ዲሞክራሲ ናፈቀኝ፡፡ መልካም ሰንበት! 
http://www.ethiopianreporter.com/component/content/article/304-delalaw/8443-2012-11-10-09-07-38.html

በዮሐንስ አንበርብር
ሰሞኑን ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች 18 አገሮችን በሥሩ ለሚገኘው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል አድርጐ መርጧል፡፡
ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ሆና መመረጧ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አስደንቋል፤ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን አባል መሆን በአገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያላገናዘበ ሲሉ ተችተውታል፡፡ በሌላ በኩል የውጭ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አጋጣሚውን የወደዱት ቢመስልም የሰብዓዊ መብት ወቀሳቸው ግን ቀጥሏል፡፡

የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ምርጫ 47 መቀመጫዎች ላሉት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤቱ 18 አባል አገሮችን በተተኪ አባልነት ለቀጣይ ሦስት ዓመታት እንዲያገለግሉ መምረጡን ይፋ አድርጓል፡፡ የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የ193 አባል አገሮችን ድምፅ የያዘ ሲሆን፣ በሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ውስጥ አባል ለመሆን ከ96 በላይ የሚሆኑ አባል አገሮችን ይሁንታ ማግኘት ይጠይቃል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ምርጫ ከኢትዮጵያ ጋር ሌሎች ስድስት የአፍሪካ አገሮችም ተመርጠዋል፡፡ እነዚህ የአፍሪካ አገሮች ያገኙት ድምፅ የተሻለ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ከ193 የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ድምፅ የ178 አገሮችን ይሁንታ በማግኘት ምክር ቤቱን በአባልነት ተቀላቅላለች፡፡

ለሰብዓዊ መብቶች  መከበር የፀና እምነት መኖርና ለተግባራዊነታቸው መንቀሳቀስ፣ የተሻለ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝና ለዚህ የሚሠሩ ጠንካራ ተቋማት መኖር የምክር ቤቱ አባል ሆኖ ለመመረጥ ከሚያበቁ ዋነኛ መስፈርቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ምክር ቤቱ ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር በመላው የዓለም አገሮች ውስጥ የሚሠራ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገሮች እንዲሰፍን የመተባበር፣ የማጐልበትና የመከታተል መሠረታዊ ኃላፊነቶቹ ሲሆኑ፣ በተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚፈጽሙ አገሮች ላይ እስከ ማዕቀብ መጣል የደረሰ ዕርምጃ ሊወሰድ ይችላል፡፡

የምክር ቤቱ አባል አገሮችም ለዚህ ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነት አስተዋጽኦ ከማበርከት ጐን ለጐን በአባልነት ዘመናቸው ልዩ ተሞክሮን በመውሰድ በአገራቸው ያለውን የመብት አከባበር ማጠናከር እንዲችሉ ዕድልን ይፈጥራል፡፡ ይሁን እንጂ አንድ አባል አገር በአባልነት ዘመኑ ወቅት በአገሩ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ማስተካከልና ማሻሻል ከተሳነው ካውንስሉ የመተባበር አስተዋጽኦውን ወደ ጐን በመተው፣ በአባል አገሩ የካውንስል ወንበር ላይ በመወያየት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ከአባልነት የማስወገድ ሥልጣን አለው፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ አንዳንድ ግለሰቦች የኢትዮጵያ በአባልነት መመረጥ በእጅጉ አስገርሟቸዋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብቶቻቸው መጣሱ በየጊዜው ይነገራል፡፡ ይህ ጥሰት ለማንም የተደበቀ እንዳልሆነም በግልጽ የሚናገሩ አሉ፡፡ በሥራ ቦታዎች፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የጤና ተቋማትን ጨምሮ የዜጐች መብቶች ይረገጣሉ የዕለት ተዕለት የኑሯችን አካልን ነው የሚሉት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች የኢትዮጵያን የተመድ ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባልነት የሰሙት በመደነቅ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ራሱ ተመድን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮች ይህንኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተገንዝበው ወቀሳቸውን በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ ሲዘነዝሩ እስከዛሬ ቆይተው፣ በአሁኑ ወቅት ምን ታይቷቸው እንደሆነ ለማወቅ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸውም ይናገራሉ፡፡ እነዚሁ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወቀሳቸውን በተለያዩ ጊዜያት ሲሰነዝሩ በተለያዩ መገናኛ ብዙኅን ቢሰሙም በኢትዮጵያ የተለወጠ ነገር የለም ብለው፣ ሰሞኑን የኢትዮጵያን መመረጥ አስመልክቶ የሰሙትን በተለየ ሁኔታ ባያዩትም በምን መስፈርት እንደተመረጠች መጠየቃቸው ግን አልቀረም፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግን ኢትዮጵያ የተመረጠችበትን መስፈርቶች እንዲሁም አግባብነቱን ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ያለማንም ተፅዕኖ የራሷን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ እንዲሁም የእንባ ጠባቂ ተቋምን በመመሥረት የዜጐቿን ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር የምትሠራ አገር መሆኗን፣ እንዲሁም ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መመሥረትና መጠናከር ያደረገችው አስተዋጽኦና እገዛ ለመረጧ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የአገሪቱ በምክር ቤቱ የአባልነት ወንበር ማግኘትም የተለያዩ የውጭ ሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩትን ወቀሳ ያጋለጠና መሠረት የሌለው መሆኑን የጠቆመ ነው ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ የኢትዮጵያን የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል መሆን መልካም ጐኖች ይኖሩት ይሆናል የሚል እምነት ቢኖራቸውም፣ መመረጧ ብቻውን ግን በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሊቀረፍ አይችልም በማለት ያስረዳሉ፡፡ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የአገሪቱን መመረጥ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ላይም አይስማሙም፡፡ ‹‹ሲጀመር በማንኛውም መስፈርት ብትመረጥ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጉድለቶች እንዳልነበሩ ሊያደርግ አይችልም፤›› ሲሉ ሊቀመንበሩ አቶ ሙሼ ያስረዳሉ፡፡

ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ባደረገችው አስተዋጽኦ ልትመረጥ ትችላለች ብሎ ለመቀበል ይቅርና ለማሰብ እንደሚከብድ የሚናገሩት አቶ ሙሼ፣ ከዚህ ይልቅ በዲፕሎማሲ የፈጠረችው ጫና ለመገለጫነቱ ሚዛን ይደፋል ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላት ሚና እየገዘፈ መጥቷል፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በአፍሪካም ሆነ በራሷ ጉዳዮች ላይ ተሰሚነትን አግኝታለች፡፡ ይህም የምክር ቤቱ አባል ለመሆን ረድቷታል፤›› የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል መሆን ተገቢ አይደለም የሚል እምነት እንደሌላቸው የሚገልጹት ሊቀመንበሩ፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በዚህ ከመኩራራትና ለሚሰነዘርባቸው ወቀሳ ጋሻ ከሚያደርጉት በቅንነት ቢጠቀሙበት ለሕዝብ ይጠቅማል ብለዋል፡፡

‹‹የዓለም አገሮች ለኢትዮጵያ ዕድል ሰጥተዋል፡፡ በመሆኑም በአባልነት ቆይታዋ ወስጥ ሯሳን ከሌሎች ተሞክሮዎች አርማ ማውጣት ብልህነት ነው፡፡ ይህንን ተቀብሎ መተግበርና ኃላፊነትን መውሰድ ካልተቻለ ግን ከካውንስሉ አባልነት በውርደት መሰናበትን ሊያመጣ ይችላል፤›› የሚል ምክር አዘል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሥልጣን መያዙን ተከትሎ የፀደቀው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በርካታ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የያዘ፣ እንዲሁም በዚሁ ዙርያ ተመድ ያፀደቃቸውን ስምምነቶች የካተተ ከመሆኑም ባሻገር ባለው አጠቃላይ ይዘት ከሞላ ጐደል ደረጃውን የጠበቀ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ከፀደቀ በኋላ የመጀመርያው የኢትዮጵያ ርእሰ ብሔር በመሆን የተመረጡት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም በዚሁ ጉዳይ ላይ ይስማማሉ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ከሕገ መንግሥቱ መፅደቅ በኋላም የአገሪቱ ሕግ አውጪ አካል ያወጣቸውን የሕዝቦች መብትን የተመለከቱ ማስፈጸሚያ አዋጆችን ፕሬዚዳንት በነበሩባቸው ወቅቶች በፊርማቸው አፅድቀዋል፡፡

‹‹በሕገ መንግሥቱ የተካተቱ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሰብዓዊ መብቶችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥታችን ሚዛኑን የጠበቀ ነው፡፡ ነገር ግን አገሪቱ በተመድ ምክር ቤት ውስጥ የተመረጠችው በዚህ ከሆነ አስገራሚ ነው፤›› በማለት በአሁኑ ወቅት የአንድነት ለፍትሕና ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ይገልጻሉ፡፡

ድንጋጌዎቹ በወረቀት ላይ የሰፈሩ ከመሆን ያለፈ ትርጓሜ ለመስጠት አስቸጋሪ እንደሆነ በአገሪቱ በየዕለቱ የሚስተዋሉት የመብት ጥሰቶች ምስክር ናቸው ብለዋል፡፡ በርካታ አገሮች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ዙሪያ ወቀሳቸውን እየሰነዘሩ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ አገሪቱን የምክር ቤቱ አባል አድርጐ መምረጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ እንዳይጋለጡና እንዳይመረመሩ ከለላ ለመስጠት መተባበር የመጨረሻው ውጤት እንዳይሆን ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

መቀመጫቸውን በተለያዩ የውጭ አገሮች ያደረጉ በሰብዓዊ መብቶች መከበር ዙርያ የሚሰሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ወቀሳዎችን በመሰንዘር ከመንግሥት ጋር ንትርክ ውስጥ እስከ መግባት ደረጃ የደረሰው ሒዩማን ራይትስ ዎች የተባለውን ድርጅት ጨምሮ የኢትዮጵያ በተመድ ሰብዓዊ መብት ካውንስል ውስጥ አባል መሆን የተለየ አጋጣሚን ይፈጥራል የሚል ግምት የያዙ ይመስላሉ፡፡

ሒዩማን ራይትስ ዎችና ስድስት የሚሆኑ ሌሎች ተመሳሳይ ተግባር ላይ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኢትዮጵያ አባል ለመሆን እያደረገች የነበረውን ፉክክር ቀደም ብለው የተገነዘቡ ሲሆን፣ ተመድና አባል አገሮቹ ኢትዮጵያን እንዳይመርጡ መወትወት ውስጥ ከመግባት በመቆጠብ ለየት ያለ ባህሪ አሳይተዋል፡፡ በተጨማሪም ተመድ ኢትዮጵያን ከመምረጡ በፊት ድርጅቶቹ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጋራ በመሆን ደብዳቤ ልከዋል፡፡

በደብዳቤያቸውም ኢትዮጵያ የተመድ ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባል ለመሆን እየተወዳደረች እንደመሆኗ መጠን አሁን ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዟ ላይ ማስተካከያ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡

የመናገር፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብቶች ላይ በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና በዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት ማሻሻያ እንዲደረግ በደብዳቤያቸው አቶ ኃይለ ማርያምን አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለተመድ ሰብዓዊ መብት ካውንስል ዕጩ ሆኖ ስትቀርብ አልያም ከተመረጠች በኋላ ጫናን ለመፍጠር በሚመስል ሁኔታ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ወቀሳቸውን መሰንዘር ቀጥለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ ውስጥ አባል ለመሆን በዕጩነት እየተወዳደረች ባለችበት ሳምንት ውስጥ ኮሚሽን ኦን ኢንተርናሽናል ረሊጂየስ ፍሪደም የተባለ በእምነት ነፃነት ላይ የሚሠራ የአሜሪካ መንግሥት ተቋም ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን የእስልምና ሃይማኖት ነፃነትን በማፈን ወቅሷል፡፡

የዚህ ኮሚሽን አባላት በቀጥታ በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የሚመረጡ ሲሆን፣ በመግለጫቸውም መንግሥት በሃይማኖቱ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባትና በማፈን እንዲሁም እስካሁን 29 የሚሆኑ ጣልቃ ገብነቱን የተቃወሙ አማኞችን ማሰሩን ገልጾ ከድርጊቱ እንዲታቀብ ጠይቀዋል፡፡  

በኮሚሽኑም ሆነ በተለያዩ ወገኖች በዚሁ ጉዳይ ለሚቀርቡ ወቀሳዎች መንግሥት ምላሹን ሲሰጥ፣ በእምነት ጉዳይ ላይ ጨርሶ ጣልቃ እንዳልገባ የታሰሩት ግለሰቦች ከእምነት ጋር በተገናኘ ሳይሆንሕ እምነትን ሽፋን በማድረግ አገሪቱን የማወክና እስላማዊ መንግሥት የማቋቋም ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሆናቸው ነው ሲል ገልጿል፡፡

ባለፈው ሳምንት ውስጥም የጀርመኑ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሄኒሪክ ቦል ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ረገጣ ቀጥሏል፣ ሰብዓዊ መብትንና የዲሞክራሲ ሥርዓት በአገሪቱ እንዲሰፍን እየተወጣሁ ያለሁትን ሚናም ገድቦብኛል የሚል ወቀሳ በማቅረብ በአገሪቱ ያከናውናቸው የነበሩ ሥራዎችን አቋርጦ መውጣቱን አሳውቋል፡፡

አሁንም ባለፈው ሳምንት ውስጥ በተመሳሳይ ነገር ግን ባልተለመደ ሁኔታ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) ኢትዮጵያ የሠራተኞችን የመደራጀት መብት በማፈን መብታቸውን እየረገጠች ነው ሲል ኮንኗል፡፡

በተለይ የመምህራን ማኅበርን ለመመሥረትና ሕጋዊ ምዝገባና ፈቃድ እንዲኖረው በመምህራን በተደጋጋሚ የተደረገውን ጥረት መንግሥት የመከልከልና ዕውቅና የመንፈግ ተግባሩን ቀጥሎበታል ያለው ድርጅቱ፣ በመሆኑም ከድርጊቱ በመታቀብ የመደራጀትና መብታቸውን የማስከበር ጥረታቸውን እንዲደግፉ ጠይቋል፡፡

መንግሥት ግን ይህንን ተግባር እንዳልፈጸመ በመግለጽ ወቀሳውን አጣጥሏል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ መላ መምህራንን የሚወክል ማኅበር መኖሩን በመጠቆም ወቀሳው በመረጃ ላይ ያልተመሠረተ ነው ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ከዓመት በፊት በአዲስ አበባ የሚገኙ መምህራን የደመወዝ ጭማሪ ሊደረግልን ይገባል በማለት ተቃውሟቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ከዚህ አልፎም በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች የሥራ ማቆም አድማ እስከማድረግ መድረሳቸው ይታወቃል፡፡ በወቅቱ ካነሷቸው ተቃውሞዎች መካከል የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አይወክለንም፣ መንግሥት የመምህራንን የመብት ጥያቄ ለማፈን ያቋቋመው ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ሰሞኑን የተመረጡት አገሮች በአባልነት ሥራቸውን የሚጀምሩት እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 2013 ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ባላት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉድለት እንዲሁም ከተመረጠች በኋላ እየቀረበባት ባለው ወቀሳ ውስጥ የሦስት ዓመታት የአባልነት ዘመኗን እንዴት ታገባድድ ይሆን? የሚል ጥያቄን ጭሯል፡፡

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግን፣ ‹‹ይህ የመንግሥት ሥጋት አይደለም፡፡ የካውንስሉ አባል ባይኮንም በአገሪቱ ሰብዓዊ መብቶችን ሥር ለማስያዝ የተጀመሩ ጥረቶች ይቀጥላሉ፤›› በማለት ለዚህም የመንግሥት ቁርጠኝነት እንዳለ ገልጸዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/politics/295-politics/8576-2012-11-21-06-36-09.html