POWr Social Media Icons

Friday, November 16, 2012


በታምሩ ጽጌ
በሚያዝያ ወር 2005 ዓ.ም. የሚደረገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤትና የአካባቢ ምርጫ ከወዲሁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማወዛገብ ጀመረ፡፡ ቦርዱ ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. “የምርጫ ሰሌዳ የምክክር መድረክ” በሚል በአዳማ ከተማ በተደረገው ውይይት፣ በወቅቱ ከተሳተፉት 66 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት፣ ቦርዱ ካዘጋጀው የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ውጭ የተለያዩ ጥያቄዎችን ማንሳታቸውንና ምላሽ ማጣታቸውን ተከትሎ አለመግባባት ተፈጥሯል፡፡ 

ቦርዱ ከምርጫ ሰሌዳው በኋላ በሚወጡ የምርጫ የማስፈጸሚያ ደንቦችና መመርያዎችን ረቂቅ አዘጋጅቶ ፓርቲዎቹን ለማወያየት በጠራው የውይይት መድረክ ላይ፣ 41 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማሙበትንና መስተካከል እንዳለበት ያመኑበትን ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ በ34 ፓርቲዎች የተወከለውና ሰባት አባላት ያሉት ጊዜያዊ ኮሚቴ ጥቅምት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡ 

“በምርጫ ሰሌዳ ዙርያ ከመወያየታችን በፊት የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብና የምርጫ ውድድር ሜዳው የተስተካከለ አለመሆን፣ ቀደም ብሎ የተደረጉ ምርጫዎች በአፈጻጸም ችግሮች የተተበተቡ መሆቸውን፣ በየደረጃው ያሉ የምርጫ ቦርድ አመራርና አስፈጻሚዎች ተዓማኒነትና ተቀባይነት ላይ ቅድሚያ ሰጥተን ብንወያይ ይገባል፤” የሚል ጥያቄ ከኢሕአዴግና አጋር የፖለቲካ ድርጅቶች ውጭ ያሉት 41 የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች ጥያቄ ማንሳታቸውን ኮሚቴው አስታውሷል፡፡ 

አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ የጌዴኦ ሕዝቦች ንቅናቄ፣ የከንባታ ሕዝቦች ኮንግረንስ፣ የሲዳማ ሕዝቦች አርነት ንቅናቄን ጨምሮ 34 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከላይ ያነሷቸው ጥያቄዎች ተቀባይነት ሳያገኙ በመቅረታቸውና፣ ቦርዱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደተስማሙበት አድርጎ የጊዜ ሰሌዳ ረቂቁን በማፅደቁ፣ ተቃውሞአቸውን ፔቲሺን በመፈራረም መግለጻቸውን አስታውቀዋል፡፡ ተቃውሞአቸውን በዋናነት ለራሱ ለምርጫ ቦርድ ማቅረባቸውን፣ በግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማስገባታቸውን ኮሚቴው ገልጿል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ግን ማኅተም የለውም በማለት የተቃውሞ ደብዳቤያቸውን እንዳልተቀበላቸውም ኮሚቴው አስረድቷል፡፡  

ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከተፈለገ ከምርጫው ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንኳን በ34 ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀርቶ በአንድ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲም ቢነሱ ቦርዱ ትኩረት ሊነፍጋቸው እንደማይገባ የገለጸው ኮሚቴው፣ የዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡ 

ፓርቲዎቹ ፔቲሺን ተፈራርመው ለቦርዱ ካቀረቧቸው 18 ጥያቄዎች መካከል የምርጫ አስፈጻሚዎች የገዢው ፓርቲ አባል ወይም ደጋፊ መሆናቸውና ወገንተኛ መሆናቸው፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች የወከሏቸው ታዛቢዎች ከየምርጫ ጣቢያዎቹ መባረራቸውና መታሰራቸው፣ የመንግሥት ሀብት (ሠራተኞች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ገንዘብ…) ለገዢው ፓርቲ ምርጫ ማስፈጸሚያ መዋላቸው፣ በፌዴራልና በክልል የመንግሥት መገናኛ ብዙኅን ፍትሐዊ አጠቃቀም አለመኖሩ፣ በነፃው ፕሬስ ላይ የሚደረገው ማስፈራራትና የተለያዩ ተፅዕኖዎች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ልሳኖች እንዲዘጉ ወይም እንዳይታተሙ ማድረግ፣ ነፃና ገለልተኛ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ የምርጫ ታዛቢዎች እንዳይሳተፉና ቁጥራቸው ውስን እንዲሆን ማድረግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ 

ፓርቲዎቹ የጠቀሷቸው 18 ቅሬታዎች መፍትሔ ሳያገኙ የምርጫ ሰሌዳ የማስፈጸሚያ ደንቦችና መመሪያዎች ረቂቅ ላይ ለውይይት መጋበዛቸው የሚገርም ባይሆንም፣ በወቅቱ በውይይት ላይ ያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ ረቂቁ መፅደቁ እንዳሳዘናቸው ኮሚቴው አስረድቷል፡፡ 

የጠየቋቸው ጥያቄዎች መፍትሔ ሳያገኙ በጊዜ ሰሌዳ ላይ መነጋገርም ሆነ በምርጫው መሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ለሕገ መንግሥቱ መከበር፣ ለሕግ የበላይነት መስፈን፣ ለሰላምና ለልማት ከሚደረገው አስተዋፅኦ ይልቅ ለተቃራኒው ውጤት የሚከፈል መዋጮ መሆኑን ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ ሕዝቡንም ከቀደምት ምርጫዎች በእጅጉ ለከፋ አደጋ፣ ለእንግልት፣ ለእስራት፣ ለመፈናቀል፣ ለድብደባ፣ ለስደትና ለሞት ማጋፈጥ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ላነሱት ጥያቄ ምላሽ የማያገኙ ከሆነ ወቅታዊና ተገቢ የሆነ የጋራ ዕርምጃም እንደሚወስዱ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ 

ቀደም ባሉት ጊዜያትም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምርጫ ቦርድ የሚያቀርቡት ጥያቄ ምላሽ እንደማያገኝ እየገለጹ በድጋሚ ሌላ ጥያቄ ማቅረብ ያስፈለገበትን ምክንያት ኮሚቴው ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ፣ ችግሩ የተለመደ መሆኑን፣ 34ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ የሚያቀርቡዋቸው ጥያቄዎች ባይመለሱም፣ ደጋግሞ መጠየቅ ተገቢ መሆኑን የኮሚቴው ሰብሳቢና የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ አስራት ጣሴ ገልጸዋል፡፡ 

“ከቦርዱ ፍቱን፣ አጭርና መልካም መልስ እናገኛለን የሚል የዋህነት የለንም፤” ያሉት አቶ አስራት፣ መልስ ባይሰጣቸውም ጥያቄያቸውን ማቅረብ ግዴታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ መልስ ሲነፈጉም ከጋዜጣዊ መግለጫ እስከ ሰላማዊ ሠልፍ ወይም ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ የሚቻላቸውን ትግል ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

ቀደም ባሉት ጊዜያት ያነሷቸው ጥያቄዎች ላለመመለሳቸው ያደረጉት ጥናት ስለመኖሩና አለመኖሩ ለኮሚቴው ጥያቄ ቀርቦለት ጥናት እንደማያስፈልገው፣ ምንም ዓይነት ለውጥና የተወሰደ ዕርምጃም እንደሌለ እንደሚያውቁ የኮሚቴው አባልና የመኢአድ ተወካይ አቶ ወንድማገኘሁ ደነቀ ተናግረዋል፡፡ የ2002 የድኅረ ምርጫ ግምገማን በሚመለከት 50 የፖለቲካ ፓርቲዎች መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ተገናኝተው ባደረጉት ግምገማ ባለ 14 ገጽ መቃወሚያ ሐሳብ ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል፡፡ 

በወቅቱም ቦርዱ ዕርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ አቅርበው መልስ አለማግኘታቸውን አቶ ወንድማገኘሁ አስታውሰዋል፡፡ “በተጠየቁት ወይም በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ዕርምጃ ወስደናል፤ የመወዳደርያ ሜዳው ተስተካክሏል የሚል ምላሽ ከቦርዱ አላገኘንም፡፡ ታዲያ ለዚህ ምን ምርምር ያስፈልገዋል?” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ በማቅረብ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ከበፊቱ በከፋ ሁኔታ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ሁኔታ እየባሰበት እንደመጣ የጠቆመው ኮሚቴው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫውን በተመለከተ ፕሮግራማቸውን ለሕዝቡ ማስተላለፍ ቢኖርባቸውም፣ በፍትሐዊነት ማግኘት የሚገባቸውን የመንግሥት የመገናኛ ብዙኅን መከልከላቸውን ተናግሯል፡፡ የኢኅአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ለሚያደርገው የነገ ስብሰባ ዛሬ ከፍተኛ ሽፋን እንደሚሰጠውና ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን የኢሕአዴግን ዕድል በዓመት አንድ ጊዜ እንኳ እንደማያገኙት አውስቷል፡፡ ሕዝቡ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለውና አምባገነናዊ ሥርዓት መስፈኑንም የኮሚቴው አባላት አስረድተዋል፡፡ በገጠር አካባቢ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት እየታሰሩ፣ እየተገረፉና ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ለመሆናቸውም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለዋል ያሏቸውን ከ260 በላይ ነዋሪዎች ጠቅሰዋል፡፡ 

ምርጫ ቦርድና መንግሥት ማስተካከል አለባቸው የሚሉትም ለፖለቲካ ፓርቲዎች ትርፍ ለማስገኘት ሳይሆን በምርጫው ሕዝቡ የፈለገውን እንዲመርጥ፣ ያልፈለገውን እንዲያስወግድና በነፃነት መኖር እንዲጀምር መሆኑን ኮሚቴው አስረድቷል፡፡ ምርጫ ቦርድ ቀና አስተሳሰብ እንደሌለው ማሳያ መሆኑን የጠቆመው ኮሚቴው፣ ቦርዱ አዳማ ላይ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ የእስልምና ተከታዮች የአረፋ በዓላቸውን በሚያከብሩበት ዕለት መሆኑንና በዕለቱ ለግማሽ ቀን ብቻ ተሳትፈው ወደ በዓላቸው የሄዱትን ሰባት የፖለቲካ ፓርቲ ሙስሊም አባላትን በማስታወስ ነበር፡፡ የመጨረሻ ውጤቱን ባይሳተፉም፣ ከ34ቱ ፓርቲዎች ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው በመግለጻቸው ቁጥራቸው 41 መሆኑን ኮሚቴው አስታውሷል፡፡ 

ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ያነሱትን ቅሬታና ያቀረቡትን ሰነድ በሚመለከት ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ ወይዘሮ የሺ ፈቀደ፣ “ቦርዱንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የማያስማማ ጉዳይ በወቅቱ አልነበረም፤” ካሉ በኋላ፣ ቦርዱ የ2005 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶችና አካባቢያዊ ምርጫን በሚመለከት ባቀረበው የምርጫ ሰሌዳ ረቂቅ ላይ ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. በአዳማ መወያየታቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

ወይዘሮ የሺ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶቹ በወቅቱ ያነሷቸውን “ብንወያይባቸው ይገባል” ያሏቸውን ጥያቄዎች ማንሳታቸውንና መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ አጀንዳ ተይዞ የተደረገ ውይይትም ሆነ ምክክር ግን እንዳልነበረ ጠቁመው፣ አሁንም አለን የሚሉትን ጥያቄም ሆነ የመወያያ አጀንዳ አቅርበው ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ 

በወቅቱ የነበረው አጀንዳ የጊዜ ሰሌዳ ስለነበረ በሱ ዙርያ የነበራቸው ጥያቄ “ትንሽ ይሻሻል” የሚል እንደነበርና ቦርዱም አሻሽሎ ረቂቁ መፅደቁን ወይዘሮ የሺ አስረድተዋል፡፡ 

ቦርዱ የተቋቋመው የአገሪቱን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ሰፊ ለማድረግ መሆኑንና ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደረሱብን የሚሉዋቸውን ችግሮች ገለልተኛ ሆኖ ሲመለከትና መፍትሔ ሲሰጥ መቆየቱን የገለጹት ኃላፊዋ፣ የፖለቲካ ሙቀት ሲኖር በቦርዱ ላይ የሚናገሩት አንድ ዓይነት ነገርና የተለመደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቦርዱ ግን የምርጫ መወዳደርያ ሜዳው እንዲሰፋ እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 


http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8468-2012-11-10-12-59-50.html