POWr Social Media Icons

Wednesday, October 31, 2012አዲስ አበባ፣ጥቅምት 21 ፣2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የስኳር ምርትን ባለፈው ዓመት ወደ ውጭ መላክ ይጀመራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም የስኳር ፕሮጀክቶቹ በታሰበላቸው ፍጥነት እየሄዱ እንዳልሆነ ተገለጸ። 
የስኳር ኮርፖሬሽን እንደሚለው ለፕሮጀክቶቹ መጓተት ዋነኛው ምክንያት የአቅም ውስንነት ነው። 
ቀደምሲልየማስፋፊያስራእየተሳራባቸውየነበሩየስኳርፋብሪካዎችንና ነባርየስኳርፋብሪካዎችንበመጠቀምካለፈውዓመትጀምሮየስኳርምርትለውጭገበያለማቅረብታቅዶየነበረሲሆን፥እንደታቀደውግንማድረግአተቻለም።
የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ልዩ አማካሪ አቶ አስፋው ዲንጋሞ እንዳሉት ፥ የኮንትራክተሮችም ሆነ የአማካሪዎች አቅም ውስንነት ፣ የገንዘብ እጥረት ፣ በበቂ የሰው ኃይል አለመደራጀት ፣ ለፕሮጀክቶቹ መጓተት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው።

ከፕሮጀክቶቹ ግዝፈትና ውስብስብነት ጋር በተያያዘም ፥ የስኳር ኮርፖሬሽንም ቢሆን የፕሮጀክት አመራርና አስተዳደር ድክመት እንደነበረበትና፥ በአሁን ወቅት ግን ችግሮቹ በመለየታቸው በያዝነው ዓመት ፕሮጀክቶቹን በአዲስ መልክ ለማፋጠንና ለማጠናቀቅ ርብርብ በመደረግ ላይ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቶቹን በአዲስ መልክ ለመምራት እንዲያስችለውም ፥ ባለፉት ሶስስት ወራት ቁልፍ ችግሬ ነበር ላለው የአቅም ውስንነት ትኩረት ሰጥቶ ሰርቷል ፥ እየሰራም ነው። የሰው ኃይሉን አቅም ለማጎልበትም በውጭ ሃገራት ጭምር በመላክ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እያደረገ ነው።

የከሰም ስኳር ፋብሪካ በጣም ከዘገዩት ውስጥ አንዱ ሲሆን ፥ የፋብሪካ ግንባታውንም በዚህ ዓመት በአብዛኛው በማጠናቀቅ በቀጣዩ ዓመት ወደ ማምረት ስራ እንዲገባ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ፥ የወልቃይት፣የበለስና ስድስት ፋብሪካዎች የሚገነቡበት የደቡብ ኦሞ ኩራዝ ፕሮጀክቶችም ላይ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩባቸው ይገኛሉ።

በነዚህ ፕሮጀክቶች ከጥናትና ዲዛይን ስራ ጀምሮ የመስኖ መሰረተ ልማት ፣ የመንገድና የቤቶች ግንባታ ፣ የመሬት ዝግጅትና የአገዳ ተከላ እንዲሁም የፋብሪካ ተከላ ስራ በተለያየ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

አቶ አስፋው እንዳሉት ፋብሪካዎቹ በዚህ ዓመትና በቀጣዩ ዓመት ግንባታቸውን በማፋጠን 2007 ላይ የማምረት ስራ እንዲጀምሩ ከፍተኛ ርብርብ በመደረግ ላይ ነው ፥ ባለፈው ዓመት ለተጠቃሚዎች ከተሰራጨው ከ4 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል ውስጥ 2 ሚሊየን ኩንታል የሚጠጋው ከውጭ የገባ ሲሆን እስከ ዓመቱ ማብቂያ ድረስ ይህ መጠን እየቀነሰ ሄዶ እንደውም በቀጣዩ ዓመት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ይጀመራል ፥ ባልደረባችን በዛብህ ማሞ እንደዘገበው።
http://www.fanabc.com/Story.aspx?ID=26640&K=

በታደሰ ገብረ ማርያም
በመላ አገሪቱ የሚገኙና በአጠቃላይ የ15 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ የነበሩ 15 ምርጥ የመንግሥት ሆስፒታሎችን ከፍተኛና ጥራት ባለው የሕክምና ቴክኖሎጂ በማደራጀት፣ የልቀት ማዕከል እንዲሆኑ የማድረግ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ መሆኑ ታወቀ፡፡ እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ አዲስ አበባ ከተማ ለሚገኝ አንድ ምርጥ ሆስፒታል ኤምአርአይ የተባለ ዘመናዊ የሕክምና መሣርያ የቀረበለት መሆኑን፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሜዲካል ሰርቪስ ዳይሬክቶሬት ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

ምንጮች በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የትኛውንም የአካል ክፍል ጥራት ባለው ምስል የሚያሳየው የተራቀቀ ቴክኖሎጂ የቀረበውም ለቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ አጠቃላይ ሆስፒታል ነው፡፡ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ሌሎችም ምርጥ ሆስፒታሎች አቅም በፈቀደ መጠን በየተራ የዚሁ የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ባለቤት የሚሆኑበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተጠቁሟል፡፡

በመላ አገሪቱ ከሚገኙ 119 የመንግሥት ሆስፒታሎች መካከል፣ 15ቱ ብቻ ምርጥ ተብለው ሊለዩ የቻሉት የተለያዩ ደረጃዎች ያሉትና የተገልጋዩን እርካታ ማዕከል ያደረገ መስፈርት በማውጣት መሆኑን ምንጮች ጠቅሰው፣ የመጀመርያው መስፈርት የሆስፒታሎቹን አገልግሎትና የአፈጻጸም ሁኔታን የሚመለከት መሆኑንና በመስፈርቱ 30 ሆስፒታሎች መመረጣቸውን አስረድተዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው መስፈርት ተግባራዊ የሆነው የሰላሳዎቹን ሆስፒታሎች የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን በአካል ተገኝቶ በማየትና በመገምገም ሲሆን፣ በዚህ ዓይነቱም አካሄድ 15 ሆስፒታሎች የሚፈለገውን ደረጃና መስፈርት አሟልተው በመገኘታቸው፣ ‹‹ምርጥ ሆስፒታሎች›› ተብለው መመረጣቸውን ከምንጮች ማብራሪያ ለመዳት ተችሏል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ትብብር ለጥራት›› በሚል ፕሮጀክት አማካይነት መስፈርቱን በሚገባ ካሟሉት 15 ምርጥ ሆስፒታሎች መካከል አንዱ የአዲስ አበባው የቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲሆን፣ ከኦሮሚያ ክልል ደግሞ የቢሾፍቱ፣ የአዳማ፣ የሻሸመኔ፣ የነቀምቴና የቢሲዲሞ ሆስፒታሎች ናቸው፡፡

በትግራይ ክልል የቅድስት ማርያም አክሱምና የለምለም ካርል፣ በደቡብ ክልል የቀርጫ፣ የጅንካና የቡታጅራ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል የደብረ ብርሃንና ደብረ ታቦር፣ ከድሬዳዋ አስተዳደር ካውንስል የድል ጮራ ሆስፒታሎች ምርጥ መባላቸውን ተናግረዋል፡፡

እያንዳንዳቸው ምርጥ ሆስፒታሎች በአካባቢያቸው ከሚገኙ ከ15 እስከ 20 ከሚሆኑ ሌሎች ሆስፒታሎች ጋር በጥምረት ተሳስረዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከቅዱስ ጳውሎስ ሪፈራል አጠቃላይ ሆስፒታል ጋር የተሳሰሩት ሌሎች ሆስፒታሎች የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጥምረት (ክላስተር) እንደሚባሉ ነው ምንጮች ያመለከቱት፡፡

በዚህ መንገድ የተሳሰሩት ሆስፒታሎች በየሁለት ወሩ እየተገናኙ ልምድና ተሞክሮ ይለዋወጣሉ፡፡ በጠንካራና ደካማ ጎኖቻቸው ላይ በመወያየት ለድክመቶቻቸው መፍትሔ የሚሆን አቅጣጫ ይቀይሳሉ፡፡ የበሽተኞች ቅብብሎሽም (ሪፈራል) ያለምንም ችግር ያካሂዳሉ ተብሏል፡፡ ይህ ዓይነቱ የሕክምና አካሄድ ለአገሪቱ እንግዳ ቢሆንም፣ ባደጉ አገሮች ዘንድ በሰፊው እየተሠራበት መሆኑን ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡

ከምርጥ ሆስፒታሎች ጋር ትስስር የፈጠሩት ሌሎች ሆስፒታሎች በበጀትና በባለሙያ እጥረት የተነሳ ሁለገብ አገልግሎት ለመስጠት የአቅም ማነስ ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ትስስር ግን ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ይቀርፈዋል የሚል እምነት ማሳደሩንም አክለዋል፡፡

የመንግሥት ድጋፍ ሲታከልበት ውጤቱ የበለጠ አመርቂ ሊሆን እንደሚችል ምንጮች ገልጸው፣ ከዚህ ቀደም የፅኑ ሕሙማን ማቆያ (አይሲ) የነበረው በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ አጠቃላይ ሆስፒታል ብቻ እንደነበር፣ አሁን ግን የቅዱስ ጳውሎስ፣ የቢሾፍቱና የደብረ ብርሃን ሆስፒታሎች በቅርቡ ይህ ዓይነቱ ማቆያ እንዲኖራቸው የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ምርጥ ሆስፒታሎቹ በይፋ የታወቁት ወይም የተመረቁት ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ሲሆን፣ በዚህም ሥነ ሥርዓት ላይ እያንዳንዳቸው የአንድ ሚሊዮን ብር ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ሽልማቱንም የሰጠውና ለሥራቸውም ማንቀሳቀሻ የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርገው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነው፡፡    
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8297-2012-10-31-07-07-52.html

በዳዊት ታዬ
የንግድ ኅብረተሰቡ የሚጠበቅበትን አገራዊ አስተዋጽኦ እንዲወጣ ለማድረግ መንግሥት፣ ኢሕአዴግራና የንግዱን ኅብረተሰብ ያጣመረ የንግድ ልማት ሠራዊት መፍጠር የግድ ነው ሲሉ የንግድ ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ይህንን የገለጹት ትናንት በተካሄደው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡ በሦስቱ ጥምረት ይመሠረታል የተባለው የንግድ የልማት ሠራዊት አገሪቱ ለጀመረችውና ተግባራዊ በማድረግ ላይ ላለችው ዕቅድ መሳካት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል በማለት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የንግድ የልማት ሠራዊት መፍጠርን በተመለከተ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፣ በሌሎች ዘርፎች እየተፈጠሩ እንዳሉት የልማት ሠራዊቶች ዓይነት አደረጃጀት እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ ልማታዊ አስተሳሰብ እንዲኖር ሚኒስቴሩ የንግድ አሠራር ለውጥ እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ከበደ፣ የንግድ ኅብረተሰቡን ከሚመለከቱ ሁለት ፓኬጆች ጐን ለጐን የንግድ ልማት ሠራዊት ለመፍጠር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

‹‹በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኅን እንደምትሰሙት በሦስት አካላት የሚመሠረት ነው፤›› ያሉት የልማት ሠራዊት ጥምረት የሚፈጠረው ‹‹ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ ከመንግሥትና ከሚመለከተው የኅብረተሰብ ክፍል ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹በዚህ ጥምረት መንግሥትን የሚወክለው ንግድ ሚኒስቴር ነው፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር አንፃር ሊፈጠር የታሰበው የንግድ ልማት ሠራዊት መንግሥት፣ ኢሕአዴግንና የንግድ ምክር ቤቶችን በጋራ እንዲሠሩ ዕድል ይፈጥራል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ይህም በመግባባትና በመመካከር የሚፈለገውን ወጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዘመን ማጠቃለያ የንግዱ ዘርፍ 10.47 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማስገኘት የሚጠበቅበት መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፣ በሌላ በኩል ግን በንግድ ዘርፉ ላይ ትልቅ ፈተና ተደቅኗል ብለዋል፡፡

ይህም በንግድ ዘርፉ የሚታየው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ድርጊት ፈጣን ልማትና መልካም አስተዳደር በማስፈን ጉዞ ላይ ችግር ፈጥሯል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹በተለይ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ ዋነኛ ትኩረት የሚሰጠው የጋራ ጉዳያችን ነው፤›› በማለት፣ ይህንን የጋራ ጉዳይ በጋራ መሥራትና ለሚፈለገው ግብ የንግዱ ኅብረተሰብ አስተጽዋኦ ማድረግ እንዲችል ከተፈለገ፣ ሦስቱ የልማት ኃይሎች የሚፈጥሩት ጥምረት ቁልፍ ተግባር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ይዘጋጃሉ የተባሉት ሁለቱ ፓኬጆች የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን፣ አንዱ የንግድ አሠራርና ውድድር ማጠናከርያ ፓኬጅ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የንግዱ ኅብረተሰብ ፓኬጅ የሚል መጠርያ ያለው መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የተለያዩ የንግድ ምክር ቤች ኃላፊዎች ይፈጠራል ስለተባለው የንግድ ልማት ሠራዊት አደረጃጀት በወሬ ደረጃ ከመስማታቸው ውጭ ዝርዝር መረጃ የሌላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ውይይት የሚደረግበት መሆኑን መገንዘብ መቻላቸውን ተናግረው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8306-2012-10-31-07-16-26.html