POWr Social Media Icons

Friday, October 19, 2012


ከታዛቢው
  • ሲኣን በሲዳማ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠት ያለፈ ስራ ስሰራ ኣይታይም
  • የሲዳማ ዲያስፖራ የፖለቲካ ድርጅቶች የኢንተርኔት ላይ ኣንበሶች ናቸው

ይሄ ቀጥዬ የማቀረበው ኣስተያየት የእኔ የግሌ ኣስተያየት ነው። ምናልባት በእኔ ማንነት ላይ ጥርጣሬ ቢኖር እኔ የመንግስት ደጋፊ ወይም ተቃዋሚም ኣይደለሁ፤ እንዲሁም የተቃዋሚዎች ደጋፊም ሆነ የተቃዋሚዎች ተቃዋሚም ኣይደለሁ። እኔ የሲዳም ህዝብ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መብቶች ስከበሩ ማየት የምሻ የሲዳማ ህዝብ ተቆርቋር ነኝ። እባካችሁ ከዚህ ባለፈ ሌላ ስም ኣትለጥፉብኝ ኣደራ።

ስለ እራሴ ይህንን ያህል ካልኩ ወደ ጉዳዬ ልለፍ፦ በተለይ ካለፉት ሶስት ወራት ወዲህ ሲዳማ በፖለቲካ ትኩሳት ውስጥ ናት ማለት ይቻላል። በተለይ ከክልል ጥያቄ እና ከሃዋሳ ከተማ የወደፊት እጣ ፋንታ በምወሰኑ ጉዳዮች ላይ ህዝቡ ከመንግስት ጋር ተፋጦ መክረሙ ይታወሳል። ታዲያ ይህ ፍጥጫ ከፍጥጫነት ኣልፎ ወይም ኣፍትልኮ የወጣበትም ኣጋጣም ተከስቶ ነበረ በተለይ በወረዳዎች ኣከባቢ። የሆነ ሆኖ ዛሬ ግን ፍጥጫው እየረገበ ያለ ይመስላል።

ይህንን ያነሳሁት ያለፈ ታሪክ ልተርክላችሁ ብዬ ኣይደለም፤ ያነሳሁበት ዋናው ምክንያት ስለ ሲዳማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የታዘብኩትን ጀባ ልላችሁ ብየ ነው። ምን ታዘብክ ብላችሁ ጠይቁኝ ታዲያ! ኣዎን የሲዳማ የፖለቲካ ድርጅቶችን ብዙ እየታዘብኩ ነው። ለመሆኑ የሲዳማ የፖለቲካ ፓርቲዎች እነማናቸው? ይመስለኛል ስለ ፓርቲዎቹ ማውራታችን ካልቀረ ስለ ማንነታቸው በስሱ ማንሳቱ የግድ ይመስለኛል።

እኔ ከልጅነተ ጀምሮ የማውቀው ኣንዳንዴ ስለው ተቃዋሚ ስለው ደግሞ የመንግስት ደጋፊ እየሆነ ሁለት መልክ የሚይዘው የሲዳማ ኣርነት ንቅናቄ(ሲኣን) ከቀድሞው ሲህዴድ ከኣሁኑ ደኢህዴን ቀጥሎ ዋናው የሲዳማ ፖለቲካ ድርጅት ሲሆን ሌሎች ደግሞ፤ በቅርቡ ህብረት የፈጠሩት(እነማን ህብረት እንደፈጠሩ ባይታወቅም) የሲዳማ ፓርቲዎች ቅንጅት ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ፤ የሲዳማ ኣርነት ግንባር ወዘተ የተባሉ የዲያስፖራ ተቃዋሚ ድርጅቶች ኣሉ ስባል ሰማለሁ።

ስባል እሰማለሁ ያልኩበት ምክንያት እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች በሲዳማ ምድር ቢሮ ኖሯቸው ኣባላት ኣፍርተው የተደራጁ ባለመሆናቸው ላቃቸው ኣልቻልኩም። እርግጠኛ ነኝ ኣብዛኛው እንታገልለታለን የምሉት ህዝብም በቅጡ የምያውቃቸው ኣይመስለኝም። እንደ እኔ ከሆነ ለህዝቡ ለመታገል ቆርጠው የተነሱ ኣይመስለኝም፤ የምር ለህዝቡ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ብሎም ማህበራዊ መብቶች መከበር የምታገሉ ከሆነ መታገል ያለባቸው ከህዝቡ መካከል ሆነው ነው ብዬ ኣምናለሁ።

ለነገሩ የዛሬ ሃያ ኣመት ኣከባቢ ማለትም ኢህኣዴግ ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ ዳግመኛ በሲዳማ ምድር ብቅ ያሉት ሲኣኖች በወቅቱ በርካታ ህዝብ በተከታይነት ማፍራታቸውን ኣስታውሳለሁ። የዛሬውን ኣያድርገውና ያን ጊዜ በርካታ ሲዳማዎች ኣንደኣለኝታቸው ኣድርገው ይመኩባቸው ነበር፤ ምንም እንኳን ህዝቡ የጠቀውን ያህል ምላሽ ሲኣኖች መስጠት ባይችሉም። ኣሁን ኣሁን ሲኣን ምን ያህል ኣባላት እንዳሉ መረጃው ባይኖረኝም፤ እንደምመስለኝ ከሆነ ኣገር ውስጥ ሆነው ከገዥው ፓርቲ ጋር የተኮረፉ ኣባላቱ ከእውነተኛ ኣባላቱ በቁጥር ሳይበልጡ ኣይቀሩም።

እኛ ኣገር ባህል ይመስል የፖለቲካ ፓርቲዎች የኣባላቸው ቁጥር የሚያውቁት ሳይሆን ለማወቅ ጥረት የሚያደርጉት ለምርጫ ብቻ ነው። ያነም ብሆን እነርሱ ወደ ህዝቡ ሄደው ሳይሆን በገዥው ፓርቲ የመልካምኣስተዳደር ችግር የተሰላቸው ህዝብ ነው እነርሱን ፍለጋ የሚሄደው። ይህ ስል ደግሞ እውነተኛ ከልባቸው ሲኣንን የምደግፉ ኣባላት የሉትም ማለት ኣይደለም።

የሲዳማ ህዝብ የተለያዩ በደሎች ሲደርሱበት ሽንጡን ገትሮ ከመከራከር ይልቅ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት የምቀናቸው ሲኣኖች፤ ኣንሰም በዛም በምድረ ሲዳማ ቢሮ ኖሮት፤ መሪዎቹ እነማን እንደሆኑ መንግስትም ህዝብም ኣውቆላቸው ያሉ ናቸው።

እስቲ ስለ ሌሎቹ የሲዳማ ፖለቲካ ድርጅቶች እናውራ። ከላይ ስማቸውን ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ከኣንድም ሁለት ከሁለትም ሶስት የሲዳማ የፖለቲካ ድርጅች ከውጭ ኣገራት ሆነው ይንቀሳቀሳሉ። ኣገር ውስጥ መንቀሳቀስ ምን እንዳስፈራቸው ባይታወቅም። እነዚህ ድርጅቶች የኣስራር ፊሎሶፊያቸው ምን እንደሆነ ባላውቅም ለሲዳማ ህዝብ መብት እንደምታገሉ በዌይብ ሳይቶቻቸው ላይ በለጠፏቸው መልዕክቶች ያሳወቁ ሲሆን፤ ኣላማቸውን በተመለከተ ኣንድም ጊዜ ወደምታገሉለት የሲዳማ ህዝብ ቀርበው ያስረዱበት ጊዜ የለም።

ለህዝብ የምታገል ድርጅት እንደ እኔ እምነት ከሆነ ከህዝብ ጋር መስራት ኣለበት። እርግጠኛ ነኝ የሲዳማ ህዝብ ስለ እነዚህ ለመብቱ እንታገልልሃለን የምሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ኣላማ የሚያውቅበት ሁኔታ ቢኖር ኖሮ በርካታው ህዝብ ድጋፍ ኣይነግፋቸውም። ታዲያ ምን ያደርጋል እነርሱ ከውጭ ኣገራት ሆነው ኢንቴርኔት ለማይጠቀም ህዝብ በኢንተርኔት መልዕክት ያስተላልፋሉ።

እንዴ እኔ ከሆነ የሲዳማ ህዝብ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ያስፈልገዋል። የሲዳማ ዲያስፖራውም ቢሆን እዚያ ውጭ ኣገር ሆኖ ጡሩባ ከመንፋት ወደ ሲዳማላንድ ገብቶ ቢሮ ከፍቶ፤ ከምመለከተው መንግስታዊ ኣካል እውቅና ኣግኝቶ፤ ለህዝቡ መታገል ኣለበት። የድርጅቶቹም መሪዎች ብሆኑ ማንነታቸውን ለህዝብ ኣውጥተው ማሳወቅ የጠበቅባቸዋል።

ሌላው እንደ ሲዳማ የፖለቲካ ድርጅትነቱ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት የገዥው ፓርቲ ኣካል የሆነው የቀድሞው ሲህዴድ ኣሁኑ ደኢህዴን ነው። በርግጥ ደኢህዴን በሲዳማ ውስጥ ገዥው ፓርት ከመሆኑ የተነሳ ስር ሰደዋል። እስከ ቀበሌ ድረስ መዋቅሩን ዘርግቶ ኣባላቱን በመመልመል ብዙ ደጋፊዎችን እና ኣባላትን ኣፍርቷል። ድርጅቱ የሲዳማ ድርጅትነቱን ኣረጋግጣል።ደኢህዴን የሲዳማ ስም ነው እስከ መባል ደርሷል።

ሆኖም የዞኑ ደኢህዴኖች ተቃዋሚዎችን ኣያቀርቡም፤ ተቃዋሚዎች እራሳቸውን ለህዝብ እንዲያስተዋውቁ እድል ኣይሰጡም፤ በራሳቸው ትንሽ የምቀሳቀሱ ብኖሩም የተለያየ ተለጣፊ ስሞችን እየሰጠ እንቅስቃሴታቸውን ያስተጓጉላል።በሲዳማ ህዝብ ዘንድ እኔ ብቻ ለወደድ፤ እኔ ብቻ ልስራ ይላሉ። ከተቃዋሚዎች ጋር ለመስራት እድል የሰጡበት ጊዜ የለም። በዞኑ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ በመሆኑ ኣንዳንዴ ወሳኝ የምባሉ ውሳኔዎችን ከወሰኑ በኃላ ወደ ህዝብ ያወርዳሉ። ማንኣለብኝነት ያጠቃዋል። የራሳቸውን ውሳኔ ህዝባዊ ለማስመሰል ጥረት ያደርጋሉ፤ ወዘተ የመሳሰሉትን ኣስተያየቶችን በደኢህዴን ላይ ማንሳት ይቻላል።በተለይ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በዞኑ ውስጥ በመሆን ላይ ካሉት ኣጋጣሚዎች መረዳት የምቻለው ደኢህዴን የህዝቡን የልብ ትርታ ማግኘት እንዳልቻለ ነው።

እንዳው በኣጠቃላይ ሳስበው የሲዳማ ፖለቲካ የህዝብ ፖለቲካ ሳይሆን የግለሰቦች ይመስለኛል። ምክንያቱም በተለይ ኣሁን በቅርቡ ከሲዳማ የክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ህዝባዊ ንቅናቄ በተመለከተ ከደኢህዴን በኩል ያሉት የሲዳማ ኣመራሮች ጥያቄው የግለሰቦች ነው በማለት በግለሰቦች ላይ ጣታቸውን ስቀስሩ የሲዳማ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ለጥያቄ ኣለመመለስ እንደተጠያቅ ኣድረገው የምያቀርቡት የደኢህዴን ኣመራሮችን ነው። ኣንደኛው ሌላኛውን ተጠያቂ እያደረገ ህዝቡ በመሃል እየተጎዳ ያለ ይመስለኛል። ለነገሩ ሁለቱም ኣካላት ጥያቄ የማን እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል ብዬ ኣምናለሁ።

በኣጠቃላይ የሲዳማ ፖለቲካኞች ማለትም ተቃዋሚዎችን ይሁኑ በስልጣን ላይ ያሉት ለሲዳማ ህዝብ የምበጀውን ከማድረግ ወደ ኃላ ማለት የለባቸው። ከራሳቸው ጥቅም በፊት የቆሙለትን ህዝብ ጥቅም ማስቀደም መቻል ኣለባቸው። ዛሬ ኣንዱ ሌላኛውን በመሆን ላይ ባለው ጉዳዮች ላይ የምወነጃጀሉ ከሆነ ለህዝቡ ፋይዳ የለው። ህዝቡ መልካምኣስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱለት ነው የምፈልገው፤ ህዝቡ የምያነሳቸው ጥያቄዎች በኣግባቡ እንዲመለሱለት ነው የምፈልገው፤ የሲዳማ ህዝብ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ልማት እንዲጠናክርለት ነው የምፈልገው። እነዚህ ለውጦች ለማምጣት ያሏቸውን ልዩነቶች በመተው የህዝብን ጥቅም በማስቀደም እጅለእጅ ተያይዘው መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ፈጣሪ ሲዳማን ይባርክ!
ቸር እንስንብትሰሞኑን በሃዋሳ ከተማ በተካሄደው የደቡብ ክልል የውሃ ጉባኤ የቀረበው የ2004 /ም የመምሪያው የስራ ኣፈጻጸም የተመለከተው ኣንድሪፖርት እንዳመለከተው በዞኑ ውስጥ በኣማራጭ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ኣበራታች ስራዎች ተከናውነዋል።
መምሪያው በባጀት ኣመቱ ለማከናወን ካቀዳቸው 19 አዲስ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ አምራቾች ማህበራት እንዲቋቋሙ በማድረግ ለ3- ማህበራት ፕሬስና ሞልድ ተገዝቶ ድጋፍ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ 19 ወረዳዎች በ38 አማካይ ቦታዎች የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ላይ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ከእቅዱ በላይ በመስራት 4500 የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎ አንዲሰራጩ በማድረግ በርካታ የዞኑን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ኣድርጓል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በሁሉም ወረዳዎች 100 የሚሆኑ የቤተሰብ የሶላር ተጠቃሚ ማህበራት መደራጀታቸው ሲገለጽ፤ የኃይል አማራጭ ኢነርጂ አጠቃቀም ላይ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።
እንደሪፖርቱ ከሆነ የሶላር ኢነርጂ ተከላ እና የባዮ ጋዝ ግንባታ በተለያዩ ወረዳዎች የተካሄደ ሲሆን፤ ኣራት የአማራጭ ኢነርጂ ዳሰሳ ጥናት ተከናውነዋል።


አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2005 (ዋኢማ) - ዘንድሮ የሚካሄደውን የአካባቢ ምርጫ ግልጽ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ዝግጅቶች እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የቦርዱ ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ይስማ ጅሩ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት ምርጫውን ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ  ለማድረግ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች ከወዲሁ እየተከናወኑ ነው።
በተለያየ ደረጃ የነበሩ የምርጫ ጣቢያዎችን በአዲስ መልክ በማደራጀት በኦሮሚያ፤ በትግራይ፤ በአማራና በደቡብ ክልሎች ለሚገኙ የምርጫ አስፈጻሚ አባላት  የአቅም ግንባታ ስልጠናመሰጠቱን  የገለጹት አቶ  ይስማ ለፖለቲካ ፓርቲዎችም በእጩዎች አቀራረብ ዙሪያ  ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።
የእጩ ተመራጮችና የመራጮች  ምዝገባ እንደዚሁም  ምርጫው የሚካሄድበት የጊዜ ሰሌዳ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር በመወያየት  ወደፊት እንደሚወሰን አቶ ይሰማ ገልጸዋል።
በአካባቢ ምርጫው የወረዳ፤ የቀበሌ ፤የማዘጋጃ ቤት፤ የከተማ አስተዳደርና የዞን ምክር ቤቶች አባላት እንደሚመረጡ የገለጹት አቶ ይስማ  ምርጫውን በስኬት ለማጠናቀቅ መላው ህብረተሰብ  የበኩሉን ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

ሃዋሳ ጥቅምት 09/2005 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በማዕድን ፍለጋና ልማት ላይ መሰማራታቸውን የማዕድን ሚኒስትሯ ገለጹ፡፡ ስለማዕድን ኢንዱስትሪ ግልጽነት ኢኒሼቲቭ አሰራር ለበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ግንዛቤ ለማስጨበጥ በሀዋሳ ከተማ ትናንት በተዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ስንቅነሽ እጅጉ እንደገለጹት ባለሀብቶቹ በዑጋዴን፣ በመቀሌ፣ በአባይ፣ በኦሞና በጋምቤላ በርካታ ኩባንያዎች በማዕድን ቆፋሮ ላይ ተሰማርተዋል፡፡

ማዳበሪያ፣ መስተዋት፣ ሳሙናና ሌሎችን ለማምረት በግብዓትነት የሚጠቅሙ በርካታ የማዕድን ሃብቶች እንዳሉ ያስረዱት ሚኒስትሯ በነዳጅ ዘርፍም በተለያዩ ሥፍራዎች ፍለጋው መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ 
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የምርት ዓይነቶች የማዕድን ሃብት 20 በመቶውን እንደሚይዝና ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ የወርቅ ፣ የታንተለም፣ የጌጣጌጥና የመሳሰሉት የማዕድን ጥሬ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ከ460 ሚልዮን በላይ ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱንና በዚሀ ዓመትም ይህንን በእጥፍ ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በማዕድን ፍለጋና ምርመራ ስራ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሯ የማዕድን ሃብት አለኝታ ጥናት በተለያዩ ወቅቶች በውጭና በሀገር ውስጥ የስነ ምድር ባለሙያዎች ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ እስከአሁን በተደረጉ ጥናቶች የኢንዱስትሪ፣ የኮንስትራክሽን፣ የጌጣ ጌጥ ፣ የወርቅ፣ የብረታ ብረት፣ የሃይድሮ ካርቦን ክምችትና የጂኦተርማል ማዕድናት መኖራቸው መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡ 
የማዕድን ኢንዱስትሪ ግልጽነት ኢንሼቲቭ አላማ ኩባንያዎች አምርተው ከሚያገኙት ገቢ ለመንግስት የሚከፍሉትና መንግስትም ከኩባንያዎች የሚቀበለውን ገቢ በግልፅነት ለማስተዳደርና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ መንግስት የማዕድን ሃብታችንን ለህዝብ ጥቅም ለማዋል ከባለድርሻ አካላት ጋር ስምምነት በመፍጠርና በጋራ በመስራት የማዕድን ኢንዱስትሪ ግልፅነት ኢንሼቲቭ አሰራሩን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኝነት እንዳለውም አስረድተዋል፡፡
 በዓለም አቀፍ የኢንሼቲቩ መመሪያና መስፈርት መሰረት ከመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ከማዕድን አምራች ኩባንያዎች የተውጣጣ 15 አባላት ያቀፈ ብሄራዊ ስቲሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባ ሶስት ዓመት ማስቆጠሩን ተናግረዋል፡፡ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ በማዳበርም ለማዕድን አምራች ኩባንያዎች፣ ለማዕድን ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች፣ ለፌዴራልና ለክልል ፍቃድ ሰጪና ገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቶች በአዲስ አበባና በአዳማ በቅርቡ ስልጠና መስጠቱን አስረድተዋል፡፡ 
በተፈጥሮ ሃብታችን ዙሪያ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራር ለማስፈን ብሎም ዘርፉ ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማበርከት መንግስት ትኩረት መስጠቱንም ተናግረዋል፡፡ በሀዋሳ ከተማ ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ 80 የሚጠጉ የሲቪል ማህበራትና ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
ሃዋሳ ጥቅምት 09/2005 የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለፀ፡፡ በሀዋሳ ሲካሄድ የቆየው የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ2004 አጠቃላይ የትምህርት ጉባዔ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች፣ ባለድርሻ አካላትና የትምህርት አመራሮች ማበረታቻ ሽልማትና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ መሃመድ አህመዲን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ሁሉም የህብረተሰብ ከፍልና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡ ክልሉ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የሳይንስ ዘርፍ ትምህርትን ለማጠናከር ኮምፒዩተሮች እንደሟሉና የቤተ ሙከራ ግብአቶችን በማቅረብ አበረታች ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራት ለትምህርቱ ጥራት ልዩ ትኩረት በመስጠትና በአግባቡ እንዲመራ በማድረግ በኩል ለሌሎች አርአያ እንዲሆን የሚያስችል ስራ ማከናወኑን አመልከተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ30 ሺህ በላይ የወላጅና የመምህራን ህብረት አመራሮች በትምህርት ቤቶች በመደራጀት በየጊዜው የተለያየ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ለትምህርት ቤቶች ድጋፍና ክትትል በማድረግ የትምህርት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ በማድረግ በኩል አበረታች ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ካመጡት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ቤተልሄም ታሪኩ፣ ገዛህኝ አበራ፣ ኢዩኤል ተከተልና ተማሪ ዲቦራ አበራ በሰጡት አስተያየት በትምህርት ቤቶች የተፈጠሩ አደረጃጀቶች፣ የመምህራን የዕለት ተዕለት ክትትልና አስፈላጊ የትምህርት ግብአቶች በመሟላታቸው ጥሩ ውጤት ሊያስመዘግቡ ችለዋል፡፡ መምህራኖቻቸው ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ የሚሰጧቸው ድጋፍ እንዲሁም ወላጆች ከትምህርት ቤት መልስ ብዙ ጊዜያችንን በጥናት እንድናሳልፍ የሚያደርጉት ዕገዛ ለጥሩ ውጤት አብቅቶናል ብለዋል፡፡ ከተሸላሚ መምህራን መካከልም መምህርት አልማዝ አስራት፣ መምህር ታረቀኝ ታሪኩና ወጁ ተፈራ በበኩላቸው የተሰጣቸው ሽልማት በትምህርቱ ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን በማሳካት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ራዕይ እውን ሆኖ ሁሌም እንዲታወስ ለማድረግ ከፍተኛ መነሳሳት ፈጥሮላቸዋል፡፡