POWr Social Media Icons

Monday, September 24, 2012


አፍሪካ ምንም እንኳ ከሃምሳ ዓመታት በፊት ሙሉ ለሙሉ ከቅኝ ግዛት ብትላቀቅም መለያዋ ከሆነው ድህነት ነፃ መውጣት አልተቻላትም፡፡ «በአህጉሪቷ ድህነት ስር ሰዶ ሊነቀል በማይችል መልኩ ተተክሏል» የሚሉት በርካቶች ናቸው፡፡ ያደጉት አገሮችም አህጉሪቷ ከድህነት እንድትወጣ የሚያስችላትን አቅጣጫን ከማመላከት ይልቅ በየጊዜው ዕርዳታ እየሰጡ እጅ በመጠምዘዝ በፈለጉት መንገድ መምራቱን ነው የመረጡት። ያደጉት አፍሪካ አምርታ የምታገኘውን ውጤት ለዓለም ማቅረብ የማትችል እንደሆነች የበለፀጉት አገሮች ያስባሉ፡፡ አፍሪካውያን ለዘላለም ከድህነትና ከተረጂነት መላቀቅ እንደማይችሉ ይገምታሉ፡፡ እነርሱ ሊተገብሩት የሚፈልጉትን ነገር በአፍሪካ መሞከርም ምርጫቸው ነበር።
አፍሪካ መሞከሪያ ከተደረገችበት ነገር ውስጥ አንዱ የኒዮሊበራሊዝም የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም አንደኛው ነው፡፡ በ1930ዎቹ መገባደጃ መወጠኑ የሚነገርለት ይህ ርዕዮተ ዓለም የሚያጠነጥነው ኢኮኖሚውና ገበያው ሙሉ ለሙሉ ከመንግሥት ውጪ ሆኖ ይንቀሳቀስ በሚለው መስመር ላይ ነው፡፡ በእዚህ አካሄድ ላለፉት ከሦስት ያላነሱ አስርት ዓመታት አፍካውያኑም ሆኑ ያደጉት ሀገራት ተግባራዊ ሲያደርጉት ቆይተዋል፡፡
ይህንን ርዕዮተ ዓለም ተግባራዊ ያደረጉ ሀገራት በተለይም የአፍሪካ ሀገራት ዕድገት ማምጣትም ሆነ ከድህነት መላቀቅ አልቻሉም፡፡ ያደጉት ሀገራትም ቢሆኑ ቀስ በቀስ ሊወጡት በማይችሉት የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡በተቃራኒው የኒዮሊበራ ሊዝምን ርዕዮተ ዓለም ከመቀበል የታቀቡ ሀገራት ደግሞ የራሳቸውን መንገድ ቀይሰው በመንቀሳቀሳቸው ከስህተታቸው እየተማሩ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ 
የ21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ አስርት ዓመታት ኒዮሊብራሊዝምን በሚከተሉና በማይከተሉ ሀገራት መካከል ግልፅ ልዩነት የታየበት ወቅት ነበር፡፡ ያደጉት ሀገራት በሚከተሉት የኒዮሊበራሊዝም የኢኮኖሚ አቅጣጫ ቀውስ ውስጥ ሲገቡ ታየ ፡፡ ከኒዮሊበራሊዝም በተላቀቁና በራሳቸው መንገድ በሚንቀሳቀሱ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ዕድገት ተስተዋለ ፡፡ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ አዳዲስ ለውጦች ተፈጠሩ፡፡ ይህም ለአፍሪካ ኢኮኖሚ አዲስ ምዕራፍ ከፈተ፤ የለውጥ ምልክትም ታየ።
በእዚህ አጋጣሚ በኒዮሊበራሊዝም መርህ አፍሪካ ከቀሪው ዓለም ኢኮኖሚ ተገንጥላ ብትኖርም ፤ በዓለም ተወዳዳሪና ዋጋ ሊያወጡ የሚችሉ ምርቶችን አምርታ ወደ ሌሎች አህጉሮች መላክ ጀመረች፡፡ ይህም በአፍሪካ እየታዩ ላሉት ዕድገቶች መንስኤ ሆነ፡፡ በእርግጥ ያኔም ቢሆን ኒዮሊበራሊዝም ብዙኃኑን እንደተቆጣጠረ ዘልቆ ቆይቷል፡፡ሆኖም ብቸኛው አማራጭ የሚሆንበት ጊዜ ግን አበቃ፡፡
ከነመኖሯ ተዘንግታ የነበረችው፤ የመሰረተ ልማት ያልተሟላባትና ኢንቨስትመንትም ያልተስፋፋባት አህጉር በዚህ ወቅት ታወሰች፡፡ ምርቶቿን የሚፈልጉ አካላትን ትኩረት ሳበች፡፡ አህጉሪቷ ከዓለም ኢኮኖሚ በተለይም ከአዳዲሶቹ የዕድገት ማዕከላት ጋር ያላት የንግድ ትስስር እያደገ መጣ፡፡ እነዚህ በአዲስ እድገት ላይ ያሉ ሀገራት ኒዮሊበራሊዝምን በግልፅ መቃወም ሲጀምሩ ሌሎች አማራጮች ብቅ አሉ፡፡
በ21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ ዓለምን ሲያናውጥ ለሶስት አስርት ዓመታት አፍሪካን ወደ ኋላ ሲጎትታት የነበረው ኒዮሊበራሊዝም እ.አ.አ በ1990ዎቹ እስያና አፍሪካን ሲያምስ ቆየና መፈረካከስ ጀመረ። ዋነኛ አቀንቃኞቹ አሜሪካና ብሪታኒያ ታይቶ በማይታወቅ መልክ የኢኮኖሚ አዘቅት ውስጥ ገቡ፡፡
እዚህ ላይ ቀንደኛ የኒዮሊበራሊዝም ተቃዋሚ የነበሩት ታላቁ መሪያችን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት የተናገሩትን መጥቀስ ተገቢነት ይኖረዋል። «የአሁኑ የዓለማችን ቀውስ ለአፍሪካ የተለየ ዕድል እንደፈጠረላት አምናለሁ፡፡ ይህን የምለው በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ነው፡፡ መጀመሪያ የኒዮሊበራሊዝም አስተሳሰቡ ከተጠነሰሰበት መሬት ውጪ ባሉ በተለይም በድሃዎቹ የአፍሪካ ሃገራት ኢኮኖሚያቸውን ሲፈታተን መስተዋሉ ነው፡፡ በቅርብ የተከሰተው ይህኛው ቀውስ ግን እንደከእዚህ ቀደሙ ኒዮሊበራሊዝም ተቀብለው የተገበሩ ሀገራትን ብቻ ሳይሆን ራሳቸው ፈጣሪዎቹ ላይም አደጋ አምጥቷል፡፡ በአንፃሩ የኒዮሊበራሊዝምን ርዕዮተ ዓለም አንቀበልም ብለው በራሳቸው መንገድ መጓዝ የመረጡ ሀገራት በቀውሱ ቀንም ቢሆን በብልፅግና መራመዳቸው በገሃድ ታይቷል፡፡ ስለዚህ ወደ ኒዮሊበራሊዝም አድልቶ የነበረው የዓለም ኢኮኖሚ ሚዛን የሚቀየርበት ጊዜ እየተፋጠነ ነው፡፡ 
«አፍሪካም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ የራሷን ምርጫ አግኝታለች፡፡ ይህ በራሱ ነፃ ለመውጣት ጅምሮች አሉ ሊያስብል የሚችል ነው፡፡ከእዚህ በላይ አሁን አፍሪካ ወደ አዲስ የልማት ምዕራፍ የምታመራበት አዲስ ዕድል አላት፡፡ ውጤታማ ተሞክሮዎቿን የምታስፋፋበትና ፈጣን ዕድገትና ሽግግር የምታስመዘግብበትን መንገድ መምረጥ የራሷ ብቻ መሆን ጀምሯል፡፡»
«አሁን ለሦስት አስርት ዓመታት ተጭኖባት የነበረውና የቆየውን የድህነትና የጥገኝት መንፈስ ለማራገፍና ላለማራገፍ ልማትን ለማስቀጠልና ላለማስቀጠል መወሰን ትችላለች፡፡ አፍካውያን የተሳሳተውን ውሳኔ ማሳለፍ እንደሚችሉ ሁሉ በትክክለኛው ምርጫ የኒዮሊበራሊዝም ቀውሶች የፈጠሩላቸውን ዕድሎች በመጠቀም ትክክለኛውን መንገድ የመምረጥ አቅም አላቸው፡፡ ከኒዮሊበራሊ ዝምም መላቀቅ ይችላሉ፡፡
«ሁለተኛው ቀውሱ ለዓለም ችግር መንስኤ በጣም ጠቃሚ የሆኑ አካላትን እንዲለዩ አድርጓል፡፡ አሜሪካና ብሪታኒያ ከእንግዲህ የዓለምን ኢኮኖሚ ለማንቀሳቀስ እንደበፊቱ ረዥም እጆች አይኖራ ቸውም፡፡ በማደግ ላይ ያሉት ግን ከእንግዲህ የዓለምን ክፍተት ለመሙላት ብዙ ማድረግ ይችላሉ፡፡ አፍሪካና በቢሊዮን የሚቆጠር ሕዝቧም በዓለም አቀፍ የአምራችና ሸማች መረብ ውስጥ ሊካተቱ ግድ ይላል፡፡ ከእንግዲህ ቻይናም ተወዳዳሪ ያልሆነችበትና በጉልበት ላይ የተመሠረተ ምርት አሁን መድረሻ ይጠፋዋል፡፡
«ለገበያ መዳረሻነት አፍሪካን ከመምረጥ ውጪ የተሻለ ቦታ የለም፡፡ የተሻለች የሚያሰኛትም የግብርና ልማቷና ኢንቨስትመንትን የሚስፋፋባት መሆኗ ነው፡፡ ዓለም ከእንግዲህ ስለአፍሪካ ከነበረው አመለካከት ጋር ሊዘልቅ አይችልም፡፡ የኒዮሊበራ ሊዝም ቀውስ የፈጠረው የአፍሪካና የዓለም የንግድ ትስስር ትልቅ ዕድል ሆኗል፡፡ይህ ግን በራሱ ለስኬት ዋስትና አይደለም ፡፡
«አፍሪካውያን ወቅቱ በፈጠረልን ዕድል መጠቀም አንችል ይሆናል፡፡ እውነቱ ግን ለአስርት ዓመታት ያልነበረንን ልዩና በርካታ አማራጮችን ያዘለ አጋጣሚን ኒዮሊበራሊዝም በፈጠረው ቀውስ ምክንያት ማግኘት ተችሏል፡፡ አሁን ትልቁ የአፍሪካውያን ፈተና የኒዮሌበራ ሊዝም ውድቀትን ለዕድገት እንደሽግግር መጠቀሙ ነው፡፡በእዚህ ሰበብ አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር የማስተሳሰሩ ጉዳይ ነው፡፡እኛ አፍሪካውያን የራሳችንን ስህተት እየፈፀምን ከስህተቶቻችን እንማራለን፡፡ ይህ በራሱ ታሪካዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ አፍሪካ ከቀኝ ግዛት ነፃ ከወጣች ከሃምሳ ዓመታት በኋላ በወቅቱ የዓለም ቀውስ ሁለተኛ ነፃነቷን የምታገኝበት ሊሆን ይችላል፡፡» 
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አሁን የተፈጠረውን ዕድል ከመግለፅ በተጨማሪ ገና የኒዮሊበራሊዝም ጉዳት በስፋት ከመታወቁ በፊት ስለርዕዮተ ዓለሙ ክፍተትና በአፍሪካ ላይ ስላስከተለው ጉዳት በተለያዩ መድረኮች ከመግለፅና ከማስገንዘብ ወደኋላ አላለም።
«ኒዮሊበራሊዝም በአፍሪካ በ1970ዎቹ የነበሩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ያመቻል ተብሎ ነበር፡፡ነገር ግን የዓለም መንግሥታት ሊያሳስቧቸው በማይገቡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እንዲጠመዱና ለውድቀት እንዲጋለጡ ዳርጓቸዋል ፡፡ ርዕዮተ ዓለሙን ሲያቀነቅኑ የነበሩ ሀገራት ከኢኮኖሚያዊ ጣልቃ ገብነት እንዲወጡ አድርጓል፡፡ይህም በተለይ የመሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው የአፍሪካ ሀገራት እጅጉን ጎድቷል፡፡
«የመሠረተ ልማት ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ አገልግሎት ከፍተኛ የገበያ ክፍተት በሚታይባት አፍሪካ እድገቱም ሆነ ልማቱ የሚጠይቀውን ኢንቨስትመንት በማግኘት በኩል ፈቀቅ ማለት አልቻለም፡፡ለምሳሌ በመሠረተ ልማት በኩል የግሉ ዘርፍ ይሳተፋል ፤ የሚል ግምት ነበር ፡፡ ነገር ግን ይህ ለሰላሳ ዓመታት አልሆነም፡፡የውጭ ኃይሎች የአፍሪካን ምርቶችና ሸቀጦች በፈለጉበት ጊዜ ግን የመሰረተ ልማት ግንባታ ተስፋፋ፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን ቀኝ ገዢዎች የአፍሪካን ምርቶች ለማጋዝ ሲፈልጉ ለመሰረተ ልማት ብዙ ፈሰስ አደረጉ፡፡
«በኒዮሊበራሊዝም ውድቀት ወቅት የ21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ምዕራፍ ደግሞ ህንድና ቻይናን የመሳሰሉ ሀገራት በተለየ መልኩ ምርቶችን ለመሸመት ለመሰረተ ልማት ገንዘብ ማፍሰስ ጀመሩ፡፡ በማደግ ላይ ያሉ አዲስ ሀገራት ብቅ ባሉበት በእዚህ ዘመን የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት እየተስፋፋ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ መሰረተ ልማት የተስፋፋው ኒዮሊበራሊዝም ተግባራዊ በተደረገበት ዘመን ሳይሆን የአፍሪካ ሀብት በተፈለገበት ወቅት ነው፡፡ 
«አሁን ዋነኛው ተቃውሞ የኒዮሊበራሊዝም መርህ በብዙ መልኩ ክፍተት ላለባት አፍሪካ መንግሥታቱ የገበያ ክፍተት በሚታይባቸው የልማት ሥራዎች አወንታዊና አግባብ የሆነ ድርሻቸውን እንዲወጡ አለመፍቀዱ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ አያልማ አይደለም፡፡ መንግሥት በትልልቅ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ይሳተፍ፤ መሰረተ ልማቶችን ይገንባ፤ የግሉ ዘርፍም አቅሙ በሚፈቅዳቸው ገበያዎች ላይ በመሰማራት ክፍተቱን ይሙላ፡፡ ያለበለዚያ በተለይ በአፍሪካ ካሉት ውስንነቶች አንፃር ኢኮኖሚው ከመንግሥት ይልቅ ሙሉ ለሙሉ በግለሰቦች ቁጥጥር ስር ይዋል፤ ማለት የሚፈጥረው አደጋ ከባድ ነው፡፡
«አፍሪካውያኑ የኒዮሊበራሊዝም ፖሊሲን እንዲቀርፁ የሚያስገድዷቸውን አካላት ተቃውመው የራሳቸውን መንገድ በመፈለግ ያዋጣናል የሚሉትን ፖሊሲ መቅረፅ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ በራሷ መንገድ በመጓዝ የራሷን ፖሊሲ ቀርፃ በመንቀሳቀሷ የኒዮሊበራሊዝምን ርዕዮተ ዓለም ከሚከተሉ ሀገራት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ አፍሪካውያን ከኒዮ ሊበራሊዝም እስር ቤት ውጡ፡፡አሁን የመጣው ቀውስ በራሳችሁ መንገድ ተጉዛችሁ ውጤት እንድታመጡ ከመርዳቱም በተጨማሪ ከሌሎች ሀገሮች መንግሥታት የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት እንድትላቀቁ የሚስችል ይሆናልና ዕድሉን ተጠቀሙበት፡፡»
New
አዲስ አበባ መስከረም12/2005 ቅድስተ ማርያም ኮሌጅ በዲግሪ ፣በዲፕሎማ እና በሰርተክፌት መርሀ ግብር ያስተማራቸውን 3 ሺ 325 ተከታታይ የርቀት ትምህርት ተማሪዎቹን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ እና በሀዋሳ ከተሞች አስመረቀ። ምሩቃኑ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በቢዝነስ 1 ሺህ 498፣ በመምህራን ትምህርት ፕሮግራም 76፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ፕሮግራም በደረጃ 4 መርሀ ግብር 1ሺህ 430 በደረጃ አራት ደግሞ 319 ተማሪዎች ናቸው ። ኮሌጅ ለአስራ ሶስተኛ ጊዜ በተከታታይ ርቀት ትምህርት ያስተማራቸውን ተማሪዎች ባስመረቀበት ፕሮግራሙ ላይ የኮሌጁ ፕሬዝዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ወንደሰን ታምራት ባደረጉት ንግግር ምሩቃኑ የተማሩትን ትምህርት ወደ ተግባር በመለወጥ ለሀገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፆኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ። በክብር እንግድነት የተገኙት ታዋቂው የግብርና ሳይንስ ተመራማሪ ዶክተር ስሜ ደበላ ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂዎቹ ስራ ጠባቂ ሳይሆን ስራ ፈጣሪ በመሆን ራሳቸውንም ሌሎችንም ዜጎች መጥቀም እንደሚገባቸው ተናግረዋል ። በተለይ በቴክኔክና ሙያ ዘርፍ ተመራቂዎች በግብርና ዘርፍ ላይ ቴክኖሎጂዎችን በሰፋት በመጠቀም ኋላ ቀር የግብርና አሰራሮችን ለማስወገድ በሚደረገው ስራ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ።