POWr Social Media Icons

Saturday, August 11, 2012


አዋሳ ነሐሴ 05/2004 በደቡብ ክልል በተያዘው የበጀት ዓመት ቁጠባን መሰረት ያደረገ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር ገንዘብ ለተጠቃሚዎች ማመቻቸቱን የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አሰታወቀ፡፡
በክልሉ በሚገኙ የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች የተጀመረው የቁጠባ ኤክስቴንሽ አገልግሎት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል፡፡
የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሀላፊ አቶ ሰሎሞን ገለቱ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት ብድሩ የተመቻቸው ሀዋሳን ጨምሮ በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ተደራጅተውና በግል ስራ ፈጥረው ለሚንቀሳቀሱ ከ200 ሺ በላይ ተጠቃሚዎች ነው፡፡
ለስራቸው ማጠናከሪያና ማንቀሳቀሻ የሚሰራጨው ይሄው የብድር ገንዘብ ለእያንዳንዳቸው ከ5 ሺ እስከ 100 ሺ ብር የሚሰጥ መሆኑን አመልከተው ሰርተውበት ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ተመላሽ እንዲያደርጉ የክትትልና የሙያ ድጋፍ እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተመሳሰይ ሲሰጥ የቆየው የብድር ገንዘብ በአብዛኛው ተመላሽ መደረጉን ያመለከቱት ኃላፊው ህብረተሰቡ የወሰደውን የብድር ገንዘብ በአግባቡ በመጠቀም በወቅቱ የመመለሱ ባህሉ እየዳበረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ከ896 ሺ በላይ አዲስና ነባር ደንበኞች ላይ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በቁጠባ ለማሰባሰብ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ባለፈው የበጀት ዓመት በክልሉ በሚገኙ ቀበሌዎች ባለሙያዎች በመመደብ የተጀመረው የገንዘብ ቁጠባ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በዚህ ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሰሎሞን አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ ከ3 ሺ በላይ የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች መጀመሩን አመልከተው እስካሁንም ከ120 ሺ በላይ የቁጠባ ሳጥኖች ለተጠቃሚው መሰራጨታቸውን አስረድተዋል፡፡
በእያንዳንዱ ቀበሌ የተመደቡት የቁጠባ ኤክስቴንሽ ባለሙያዎች ህብረተሰቡ በየተሰማራበት የስራ መስክ ከሚያገኘው ገቢ እንዲቆጥብና የቁጠባ ባህልን እንዲያዳብር ሙያዊና ቴክኒካዊ ድጋፍ በመስጠት አገልግሎቱን ለሁሉም ለማዳረስ አየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ህብረተሰቡም ገንዘቡን የሚቆጥበው በንፍሰ ወከፍ የቁጠባ ሳጥንና ሁለት ቁልፍ ተሰጥቶት ከተቆለፈ በኋላ አንድ መፍቻ በቆጣቢውና ሌላ አንድ መፍቻ ደግሞ በኤክስቴንሽን ባለሙያው እጅ እንደሚሆን ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡
በየወሩ መጨረሻ ሳጥኑን በጋራ ከፍተው ሂሳቡን በመቁጠር በደረሰኝ ተረካክበው በዕለቱ ባንክ ተጠቀማጭ እንደሚደረግና ወለድ ያለው የቁጠባ ሂሳብ ደብተርም እንደሚኖራቸው አመልከተዋል፡፡
የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ከተመሰረተበት ከ1989 ጀምሮ በስሩ ባሉት ዋናና ንዑስ ቅርረንጫፎች አማካኝነት እስካሁን 471 ሺ ለሚሆኑ ደንበኞች ወደ ሶስት ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ በብድር መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
የብድር ተጠቃሚዎችንና ሌሎችን ጨምሮ ከ799 ሺ በላይ ደንበኞች እስካሁን ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በቁጠባ መሰብሰቡም ተመልክቷል፡፡
የተቋሙ ዓላማ በክልሉ ገጠርና ከተማ ስራ ፈጣሪ ዜጎችን በገንዘብና በሙያ በማገዝ የቁጠባ ባህልን በማዳበር ስራ አጥነትንና ድህነትን ለመቀነስ መንግስት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ መሆኑም ታውቋል፡፡

http://www.ena.gov.et/story.aspx?ID=1608
ፎቶ ኣዲስ ኣድማስ

ፍላጐት እውቀትና ሙያ፣ ጉልበትና በራስ መተማመን እንጂ፣ ቤሳ ቤስቲን አልነበራትም፡፡ አንድ የቤትና የቢሮ ቁሳቁስ ማምረቻ ድርጅት ሄዳ ጣውላ በዱቤ እንዲሸጡላት ጠየቀች፡፡ የድርጅቱ ባለቤት ወጣቷ ሴት በድፍረትና በልበ ሙሉነት ባቀረበችላቸው ጥያቄ ቢገረሙም፣ “ከየት አምጥተሽ ልትከፍይኝ ነው? አይሆንም” አላሉም፡፡ “እሺ ውሰጂ” አሏት፡፡ ድርጅቱ የሽመና መሳሪያ አምርቶ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ራሷ የመሸመኛውን፣ የማድሪያውን፣ የምርት መጠቅለያውን ዲዛይን ሠርታና እንጨት ገጣጥማ እያሳየች አሠራች፡፡ ክር መሸጫ ሄዳ በዱቤ፣ የ80 ብር ክር ወስዳ፣ በሽመና መሳሪያው ክሩን ወደ ጨርቅነት ለወጠችው፡፡ ከዚያም ጨርቁን ቆራርጣ መንገድ ዳር አሰፋች፡፡ በገና 1995 በዓል ዕለት ሰባት የሰፈር ሕፃናት ሰብስባ ያሰፋቻቸውን ልብሶች አልብሳ ለቀቀቻቸው - ሳትታዘዝ፡፡

የአራቱ ልብሶች ዋጋ ወዲያው ሲከፈላት ሦስቱ በዱቤ ተሸጡ፡፡ መቶ ብር በማይሞላ የክር ዱቤ ሥራ ጀምራ ዛሬ ከግማሽ ሚሊዮን (500,000) ብር በላይ፣ እንዲሁም የተለያዩ ማምረቻ መሳሪያዎች ስለተገዙ በደንብ ሂሳብ ከተሠራ ከተጠቀሰው በላይ (ኧረ በግምት ሚሊዮን ሳይደርስ ይቀራል ብላችሁ ነው?) ካፒታል እንዳላት ተናግራለች - ወጣት ዙፋን ኢብራሂም፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ምርቶቿን በምሥራቅ አፍሪካ እያስተዋወቀች መሆኑን ተናግራለች፡፡ በናይሮቢ - ኬንያ አስሊ 10th street እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ምርት ማሳያና መሸጫ ሱቅ መክፈቷን ገልፃለች፡፡

ዙፋን፣ በታንዛኒያም ተመሳሳይ ሱቅ ለመክፈት ሐሳብ እንዳላት ገልፃለች፡፡ ዙፋን፣ ወላጆቼ እኔን ከሙዚቃ ለመለየት ኢትዮ ስዊድሽ ሕፃናትና ወጣቶች ማረሚያና ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ቢያስገቡኝም፣ ዛሬ፣ ኢትዮ ስዊድሽ መተዳደሪያ ሆኖኛል ትላለች፡፡ ምን ይሆን ምሥጢሩ?እንዴት መሰላችሁ፤ ዙፋን በልጅነቷ ሙዚቃ ነፍሷ ነበር፡፡ ቤትም፣ ት/ቤትም መዝፈንና መደነስ ነበር ሥራዋ፡፡ ታዲያ ወላጆቿ በተለይ አባቷ ይህን ሁኔታዋን አልወደዱላትም፡፡ የእሳቸው ፍላጐት በትምህርት ጐበዝ እንድትሆን ነበር፡፡ እሷ ግን አብዛኛውን ጊዜዋን ለጥናት ሳይሆን ለሙዚቃና ለዘፈን ነበር የምታውለው፡፡

አቶ ኢብራሂም የመንግሥት ሠራተኛ ስለሆኑ ልጃቸውም በትምህርቷ በርትታ በአንዱ መ/ቤት ተቀጥራ እንድትሠራ ምኞታቸው ቢሆንም ነገረ ሥራዋ አላምርህ አላቸው፡፡ ነግ ተነገ ወዲያ፣ ሙዚቀኛና ዘፋኝ ሆና በየመድረኩ ስትውረገረግና ስታቀነቅን “አታውቃትም ይቺን፤ የእገሌ ልጅ ናትኮ” እየተባለ ስማቸው በ”ክፉ” ሲነሳ ታያቸው፡፡

ከዚያ ድርጊቷ እንዴት እንደሚለዩዋት ሲያስቡ ኢትዮ - ስዊድሽ ታወሳቸው፡፡ እዚያ ገብታ ከሙዚቃና ዘፈን ተላቃ፣ ፀባይዋ ታርሞና ተሻሽሎ፣ በትምህርቷ ጐብዛ ስትመረቅ፣ ታያቸውና ሐሳቡን ለእናቷ አጫወቱ፡፡ እናት “ለምን በዝንባሌዋ አትቀጥልም” ማለት ስለማይችሉ በአባት ሐሳብ ተስማሙ፡፡ በዚያ መሠረት እናት በ1993 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ኢትዮ ስዊድሽ ሕፃናትና ወጣቶች ማረሚያና ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ወስደው አስገቧት፡፡

ዙፋንን ያገኘናት ባለፈው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የሴቶች፣ የወጣቶችና ሕፃናት 7ኛው ዓመታዊ የሴክተር ጉባኤ ላይ ነው፡፡ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መንግስቱ አበበ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

========================================================

እንዴት በግልሽ መሥራት ጀመርሽ? ሥልጠና እንደጨረስሽ ነው ሥራ የጀመርሽው?

አይደለም፡፡ ሥልጠና እንደጨረስኩ ውጤቴ ጥሩ ስለነበር እዚያው በረዳትነት መምህርነት ማሠልጠን ጀመርኩ - በ105 ብር ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ በ250 ብር ለአንድ ግለሰብ ተቀጥሬ በሥራ አስኪያጅነትና በአስተማሪነት ሴቶችን አሠልጥኛለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው በግል መሥራት የጀመርኩት፡፡

በሽመና የሠራሽውን ጨርቅ አሰፍተሽ ሕፃናቱን አልብሰሽ ለቀቅሻቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ምን ሆነ?

የሠራሁት፣ የሲዳማ ባህላዊ የሕፃናት ልብሶች፣ አራቱ በካሽ፣ ሦስቱ በዱቤ ተሸጡና መነሻ ካፒታል ሆኑኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ክፍለ ከተማው መጥቶ አየኝ፤ አበረታታኝ፡፡

ያቺኑ እያገላበጥኩ ስሠራ ቆይቼ ኦሞ ማይክሮፋይናንስ - ሲዳማ፣ በአንድ ዓመት የሚከፈል አራት ሺህ (4,000) ብር ብድር የሰጠኝን፣ በስድስት ወር ከፍዬ ጨረስኩ፡፡ ከዚያ በኋላ 7ሺህ፣ 15ሺህ፣ 20ሺህ፣ 80ሺህ ብር እየተበደርኩ መሥራት ቀጠልኩ፡፡

በእንዲህ ዓይነት እየሠራሁ ከአምስት ዓመት በኋላ በ2000 ዓ.ም የሚሌኒየሙ የልማት አርበኛ በመባል ከሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸለምኩ፡፡ በክልል ደረጃ ደግሞ አንድ ሴትና ዘጠኝ ወንዶች ለአሸናፊዎች አሸናፊ ተወዳድረን እያንዳንዳችን ዲያስፖራ ላይ 200 ካ.ሜ ቦታ፣ የወርቅ ሜዳሊያና ዋንጫ፣ 800 ካ.ሜ የመሥሪያ ቦታ ክፍለ ከተማውና ማዘጋጀ ቤቱ ሰጥተውኝ ችግሬን ቀረፉት፡፡ በተሰጠኝ ቦታ ላይ 85 ቆርቆሮ የለበሰ ማምረቻ ሠርቼ በርካታ ሴቶችን እያሰለጠንኩበት ነው፡፡

አሁን ካፒታልሽ ምን ያህል ደርሷል?

ከሁለት ዓመት በፊት መንግሥት ከጥቃቅን ወደ መካከለኛ ደረጃ አስመርቆኛል፡ ከ500ሺህ ብር በላይና ከዚያም በላይ ይኖረኛል፡፡

ምክንያቱም፣ የማምረቻ መሳሪያዎች አሉ፡ከዚህም በላይ በኬንያና ታንዛኒያ እየዞርኩ ምርቶቻችንን እያስተዋወቅሁ ነው፡ በናይሮቢ ከተማ አስሊ 10th street በሚባል ቦታ ሱቅ ከፍቻለሁ፡፡

ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በአገር አቀፍ የባህል ቀን እየጋበዘን አራት ጊዜ በዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ተካፍያለሁ፡፡ በቅርቡ መስከረም ላይ ቡርኪና ፋሶ ላይ በሚደረገው ኤግዚቢሽን ላይ እንድገኝ ስለተጋበዝኩ ያገሬን ባህላዊ ልብሶች ይዤ በመቅረብ አስተዋውቃለሁ፡፡

አገር ውስጥ ኤግዚቢሽን አዘጋጅተሽ ታውቂያለሽ?

ብዙ ጊዜ የምሳተፈው መንግሥታዊ መ/ቤቶችና ድርጅቶች በሚያዘጋጁት ኤግዚቢሽኖች ነው፡፡ ከተሰጡኝ 55 ሰርቲፊኬቶች መካከል በአዲስ አበባና ሀዋሳ የኢንተርፕሪነር ኮርስ ከወሰድኩባቸው አራት ሰርቲፊኬቶች በስተቀር ቀሪዎቹ ኤግዚቢሽን በመሳተፍ ያገኘኋቸው ናቸው፡፡

ከዚህ ውጭ በባህል አልባሳት፣ በምግብ፣ በመጠጥ…ዘርፍ የተሰማራን ሴቶች የደቡብ ክልል ኢምፖርት ኤክስፖርት የሴቶች ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ከሁለት ዓመት በፊት ስናቋቁም ኤግዚቢሽን አዘጋጅተናል፡፡

ዙፋን ማናት? የት ተወለደች? የት ተማረች?

እኔ የተወለድኩት ወሎ ሲሆን 29 ዓመቴ ነው፡፡ አባቴ አፋር፣ እናቴ ወለዬ ናት፡፡ አባቴ የመንግሥት ሠራተኛ ስለሆነ ይዞን ወደ ደቡብ መጣ፡፡ ያደኩት ሃዋሳ ነው፤ የማውቀውም ደቡብን ነው፡፡

እኔ የተማርኩት ሃዋሳ ኢትዮጵያ ትቅደም ት/ቤት ሲሆን በ1997 ዓ.ም 10ኛ ክፍል አጠናቅቄአለሁ፡፡ የአባቴን ፍላጐት ለማሟላት አንድ ዓመት ሕግ ተምሬአለሁ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮ ስዊድሽ ሲያስገቡኝ ዓላማቸው ሙያ እንድማር አልነበረም፡፡ እኔን ከሙዚቃ አላቀው በትምህርት እንድበረታ ነበር፡፡

እያደኩ ስሄድና ሪስክ መውሰድ ስጀምር፣ ጉዳት ይገጥማታል በማለት በጣም ይሰጉ ነበር፡፡ ምክንያቱም በተማርኩት የቀርከሃ ሙያ ለመሥራት ሸምበቆና ቀርከሃ ፍለጋ ሀገረ ሰላም፣ ቦሬ፣ ቡሌ እየሄድኩ ሦስትና አራት ሰዓት ጫካ ለጫካ እየተጓዝኩና እያደርኩ ጭምር ቀርከሃዎቹን አዲስ አበባ በመውሰድ ኡራኤል አካባቢ ላሉ ደንበኞቼ ሳስረክብ በጣም ይሰጉ ነበር፡፡

በዚህ የቀርከሃ ሙያ ዩኒዶ ከክልሉ ጥቃቅን ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ጋር በመሆን ባለሙያዎችን ከሕንድ አስመጥቶ የቀርከሃ ምርቶች እንዳይነቅዙ (ባንቡ ትሪትመንት) እና ዕድሜ እንዲኖራቸው አስተምሮናል፡፡ አሁን እንዲያውም በቦሪክ አሲድና በቦራክስ እያደረግን ጐጆ ቤቶችን ጭምር እንሠራለን፡፡

ኢትዮ - ስዊድሽ ፕሮጀክት በዋነኛነት ያሠለጠነሽ ምንድነው?

በዋነኛነት ያሠለጠነኝ ሽመና ነው፤ ባለውለታዬም ነው፡፡ ሥልጠናውን ስጀምር ሙያውን ወድጄ ቀጠልኩበት፡፡ በመጀመሪያ በወር 75 ብር የኪስ ገንዘብ እየተከፈለኝ ለ3 ወር የባህርይ ለውጥ፤ ሥነ ተዋልዶ፣ ስለ አደገኛ እፆች፣… ተማርኩ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ለ6 ወር በሽመና፣ በቀርከሃ፣ በሸክላ፣ በቆዳ፣…ሥራ ሙያ ሠለጠንኩ፡፡

አባቴ ከሙዚቃ ያገለለኝ መስሎት ተጨማሪ እውቀት ነው የሰጠኝ፡፡ ሙያውን የወደድኩት እዚያ ሙዚቃዬን ስላገኘሁ ነው፡፡ ኢትዮ ስዊድሽ ታሪካችንን ጠይቆን “ምንድነው የምትፈልጉት?” ሲለን እኔ “መዝፈን ነው የምፈልገው” ነበር ያልኩት፡፡

በዚያ መሠረት ግማሽ ቀን ሙዚቃ ግማሽ ቀን ሙያ ተማርኩ፡፡

ቤተሰቦችሽ ከሙዚቃ እንድትርቂ ፈልገው ኢትዮ -ስውዲሽ አስገቡሽ፡፡ አንቺ እዚያ ሙዚቃ ተማርሽ፡፡ ታዲያ መጨረሻው ምን ሆነ?

እነሱ ለሙዚቃ ያላቸው ጥላቻ በጣም ከባድ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ለሙዚቃ ካለኝ ፍቅር የተነሳ ካልዘፈንኩ የምሞት ይመስለኝ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን እነሱ ተይ ሳይሉኝ ራሴ እያቀዘቀዝኩ መጣሁ፡፡ አባቴን ያሸነፍኩት በየዓመቱ በሚከበረው የሲዳማ ዘመን መለወጫ የፍቼ በዓል ላይ ስዘፍን አይቶኝ ነው፡፡

እናቴ፤ ጓደኞቹ በዘዴ እኔ ወደምዘፍንበት ባህል አዳራሽ ይዘውት እንዲገቡ አደረገች፡፡

እዚያ ካየኝ በኋላ “ትምህርቷን እየተማረች ትንሽ ትንሽ ትዝፈን” አለ፡፡

እያደግሁ ስመጣ የተማርኩት የሽመና ሥራ ለብዙ ሴቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ስለተገነዘብኩ፣ ወደ ሽመናው አዘነበልኩ፡፡

አሁን ሙዚቃ የምጫወተው ለሆቢ (ለጊዜ ማሳለፊያ) ብቻ ነው፡፡ አሁን የስዋህሊኛና የቡርጂ ዘፈን ክሊፕ እያሠራሁ ነው፡፡ ዘፈኖቹ በሀዋሳ ኤፍ ኤም ራዲዮም እየተደመጡ ነው፡

የስዋህሊውን የሠራሁት ናይሮቢ ሲሆን ክሊፑ ገና ነው፡፡ አሁን ክሊፑ እየተሠራ ያለው የቡርጂው ነው፡፡

የስኬትሽ ምስጢር ምንድነው?

ጠንክሮ መሥራትና የመንግሥት ድጋፍ ነው፡፡ እኔ ጋ ደከመኝ የለም፡፡ ሌት ተቀን ነው የምሠራው፡፡ ቅዳሜና እሁድ፣ የበዓል ቀን፣ ዕረፍት፣ መዝናናት አላውቅም፡፡ ትዕዛዝ ሲመጣ አንቀበልም ማለት የለም፡፡ የተቀበልኩትን ሥራ ዲዛይን ስሠራና ለነገ ሥራ ስዘጋጅ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ድረስ እቆያለሁ፡፡

የመንግሥት አካላት ደግሞ ጥረቴን እያዩ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉልኛል፡፡ ኤግዚቢሽን ሲኖር ራሳቸው የቦታ ኪራይ ከፍለው ነው እንድሳተፍ የሚያደርጉኝ፡፡ እኔን እዚህ ያደረሰኝ የሁሉም ርብርብ ነው፡፡ እኔ ክፍለ ከተማው፣ ቀበሌው፣ ከተማ አስተዳደሩ፣ ማዘጋጃ ቤቱ የተለያዩ ሴክተር መ/ቤቶች … በአጠቃላይ ሁሉም ጓደኞቼ ናቸው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ የሁሉም በር ለእኔ ክፍት ነው፡፡ ድጋፍ ስንጠይቅ በሚቻለው መንገድ ሁሉ ይረዱናል፡፡ ከዚህም በላይ ትራንስፖርት ይፈቅዱልናል፤ ምርቶቻችንን እንደ ራሳቸው ዕቃ ያስተዋውቁልናል፡፡

የ7ኛውን ጉባኤ የአንገት ሻርፕ ማነው የሠራው?

እኔ ነኝ ጨረታውን አሸንፌ በአንድ ሳምንት ለ400 ሰዎች ሻርፖችና 31 ሙሉ ልብስ የሠራሁት፡፡

እኛ የምንሠራው የ56ቱንም ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ አልባሳት ሲሆን አሁን የሠራነው ደማቅ የሆኑትን የ26ቱን ነው፡፡

ሌላም ጊዜ ዝግጅት ሲኖር የባህል አልባሳት የምንሠራው እኔና ፀሐይ ባህል አልባሳት የሚል ድርጅት ያላት ሴት ነን፡፡ የክልሉን አምባሳደር የኪነት ቡድን አልባሳት በአብዛኛው እኔ የሠራሁት ነው፡፡

ቤተሰብ መሥርተሻል?

ቤተሰቦቼ ሠራተኞቼ ናቸው፡፡ እወዳቸዋለሁ፣ እነሱም ይወዱኛል፡፡ የሦስት ዓመት ተኩል ወንድ ልጅ አለኝ፡፡

ስንት ሠራተኞች አሉሽ?

18 ቋሚና 19 ጊዜያዊ፣ በአጠቃላይ 37 ሠራተኞች አሉ፡፡

የወደፊት ዕቅድሽ ምንድነው?

ተጨማሪ መሳሪያዎች ገዝቼ በፋብሪካ ደረጃ ባህላዊ አልባሳትን ማምረትና ኤክስፖርት እያደረኩ የአገሬን ባህላዊ አልባሳት በውጭ አገራት ማስተዋወቅ፣ ተጨማሪ ሴቶችን በሙያው በማሠልጠን የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ አለኝ፡፡

 http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_content&view=article&id=2703:2012-08-11-11-35-57&catid=69:2011-01-30-11-13-29&Itemid=496

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 4፣ 2004 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከሶስት አመት በኋላ በምግብ ዋስትና ራሷን እንደምትችል የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት የዛሬ ሶስት አመት፤ ከ400 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የግብርና ምርት በዓመት የማምረት አቅም ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል።

ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ይህን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲነግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

እቅዱ በይፋ በተጀመረበት በ2003 ዓመተ ምህረት ከዋና ዋና ሰብሎች የተገኘው 203 ሚሊዮን ኩንታል የግብርና ምርት በልማት እቅዱ ከተቀመጠው የዘጠኝ በመቶ እድገት አሳይቷል።

በተመሳሳይ በ2004 ዓመተ ምህረት 218 ሚለዮን ኩንታል የምርት መጠን ለማግኘት ታስቦ እቅዱን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት መቻሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።    

ለእቅዶቹ መሳካት ደግሞ በዋነኝነት አርሶ አደሩን በልማት ሰራዊት በማደራጀት ንቅናቄ መፈጠሩ በምክንያትነት ተቀምጧል።

በቀጣይነት ይህን የተደራጀውን አርሶ አደር አቅም መገንባት ከተቻለም እቅዱን ለማሳካት አያዳግትም ባይ ናቸው።

በኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን ሄክታር የሚደርሰው መሬት በመስኖ ሊለማ ይችላል።

ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር ያህሉ በአነስተኛ መስኖ የሚለማ ሲሆን ፥ ቀሪው ደግሞ በመካከለኛና በከፍተኛ መስኖ ሊለማ የሚችል ነው።

አሁን እየታየ የሚገኘው የምግብ እህል የዋጋ ንረትም እንደሚረጋጋ ጠቁመው ፥ በመንግስት በኩል ይህን የዋጋ ማሻቀብ ለመቀልበስ ዋና ዋና የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ እንዳይላኩ ከመከልከል ጨምሮ ብዙ የፖለሲ እርምጃዎች እንደተወሰዱ መናገራቸውን ታደሰ ብዙአለም ዘግቧል።
 http://www.fanabc.com/Story.aspx?ID=25312&K=