POWr Social Media Icons

Monday, July 16, 2012ሃዋሳ ሃምሌ 9/2004 በሀዋሳ ከተማ ከ40ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም ዛሬ ተጀመረ፡፡
የወጣቶችን የስራ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት እንዲጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የከተማው አስተዳደር ከንቲባ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የፕሮግራሙ መጀመር ምክንያት በማድረግ በሀዋሳ መስቀል አደባባይ ዛሬ በተዘጋጀው የትውውቅ ስብሰባና የቸግኝ ተከላ ስነ ስርዓት ላይ የከተማው ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት መልካሙ ጋጋዶ እንደገለጸው የከተማው ወጣቶች ባለፉት ሶስት ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተደራጀ መንገድ ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶቹ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውንና ገንዘባቸውን ለአካባቢው ልማትና ደህንነት በነፃ ያበረከቱበት በሂደትም ሌሎችን በመርዳት ከማህበረሰቡ የተለያየ እውቀት የቀስሙበት የተግባር መሳሪያ ነው ብሏል፡፡
በዘንድሮም ክረምት ከከተማው የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ከወጣት አደረጃጀቶች ጋር በመተባበር እራሳቸውንና ህብረተሰቡን ጠቅመው የከተማውን ልማት በሚያፋጥኑ የበጎ አድራጎት ተግባራት ለመሰማራት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ወጣት መልካሙ አብራርቷል ።
የከተማው አስተዳደር ህፃናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ፣ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ስምረት ግርማ በበኩላቸው የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ በከተማው ከተጀመረ ወዲህ የወጣቶች ተነሳሽነትና ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል፡፡
በ2002 የክረምት ወራት በስድስት ዓይነት የበጎ ፈቃድ አገልገሎት መስኮች 9ሺህ 463 ወጣቶች ተሳታፊ የነበሩበት ሲሆን በቀጣይ አመት የስራ መስኮቹ ወደ ስምንት የተሳታፊ ወጣቶች ቁጥር ደግሞ ከ36 ሺህ በላይ በማሳደግ በርካታ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡
በዘንድሮ ክረምት ከ40ሺህ በላይ ወጣቶች ለሁለት ወራት የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የጤና፣ የአካባቢ ፅዳትና ውበት፣ የትራፊክ ደህንነት፣ አረጋውያንና ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን መደገፍ፣ ደም ልገሳን ጨምሮ በአስር ዓይነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስኮች ይሰማራሉ ።
የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍ በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዜጎች በተለይ ወጣቶች ሁለንተናዊ አቅማቸውን ለማህበረሰብና ለአካባቢው ደህንነትና ልማት በነጻ የሚያውሉበት የተቀደሰ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት የክረምት ወራት የከተማው ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ ከማዋል ተቆጥበው ልማት የሚያጠናክሩና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ተግባራት ሲከናወን መቆየታቸውን አመልከተዋል፡፡
በዚህም በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመልከተው ዘንድሮም በተመረጡና ፋይዳ ባላቸው የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ከ40ሺህ በላይ ወጣቶች በነፃ ፍቃዳቸው ሙሉ ተሳታፊ በመሆን ካለፉት ዓመታት የተሻለ ለውጥ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
ስራውም በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በመልካም አስተዳደርና በሌሎችም መስኮች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ለሀገር ጠቃሚ ከመሆን አልፎ የአእምሮ እርካታ የሚያገኙበትና ለከተማውም ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት ነው ብለዋል፡፡
ወጣቶቹ በዚህ ስራ ያሳዩትን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ለማጠናከር የሁሉም ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎና ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፕሮግራሙ በተጀመረበት ወቅት የከተማው ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ፣የወጣት አደረጃጀት አመራሮች፣ የየክፍለ ከተማው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡