POWr Social Media Icons

Sunday, July 1, 2012


በዛሬ ቀን በሃዋሳ ከተማ በተለምዶ ወልደ ኣማኑኤል ሃውልት ኣካባቢ ካለው ኣንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ በጊዜያዊ ካምፒነት ተከራይተው የሚገኙ የፌደራል ፖሊስ ኣባላት በኣካባቢው በመንገድ ላይ ሲጓዙ የነበሩትን  የሲዳማን ተማሪዎች በመደብደባቸው የኣካባቢው ነዋሪዎች ድርጊቱን በመቃዎወም ተቃውሞኣቸውን ድንጋይ በመወርወር ስገልጹ ማምሸታቸው ተገለጸ።

ከኣከባቢው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፤ የሲዳማ የክልል ጥያቄን ተከትለው በኣካባቢው የሰፈሩት እና በተለይ ሲዳማውን በክፉ ኣይን ስከታተሉ የነበሩት የፈደራል ፖሊስ ኣባላት ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት መንገድ ላይ የነበሩትን ተማሪዎች ደብድበው ለሆስፒታል እና ለሞት ዳርጓዋል።

ከተደበደቡ ተማሪዎቹ መካከል ከዎንሾ ወረዳ የመጣ ኣብረሃም የተባለው ተማሪ ኣንዱ ሲሆን በከፍተኛ ደረጃ ከተደበደበ በሃላ በኣንድ ፈዴራል ፖሊስ ተገድሏል የሚል ወሬ በመነፈስ ላይ ነው።


በተጨማሪም ተማሪዎቹ ለምን ይደበደባሉ በማለት የተቃዎሙ ሰዎችም ራሳቸው በፈዴራል ፖሊስ በኣሰቃቂ ሁኔታ የተደበደቡ ሲሆን ከነዚሁ ሰዎች መካከል ሁለቱ ሆስፒታል መግባታቸው እየተነገረ  ነው።


በጉዳዩ ላይ ማረጋገጫ ብሎም ዝርዝር መረጃ እንደደረደን እናቀርባለን።

ከክስተቱ ጋር በተያያዘ መረጃው ያላችሁ ሰዎች በዚህ ኢሜል መልእክቶቻችሁን ልትልኩልን ትችላላችሁ: nomonanoto@gmail.com


Sidaamu Amuwi Lanyikimeesho Wila’anoki Gede

ፖለቲካ እና ሥልጣንአርብ ግንቦት 16 ቀን 1994 ዓ.ም. የአዋሳ ከተማ ከወትሮው የተለየ ግርግር ይታይባታል። ያ አመት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተሃድሶ ፕሮግራም ቁም ስቅሉን እያየ የነበረበት ቀውጢ ጊዜ ነበር። ወቅቱ ነባር የህወሓት ታጋዮች ከቀድሞው የትግል አጋሮቻቸው ጋር በፖለቲካው መግባባት ባለመቻላቸው  ምክንያት ድርጅታቸው ለሁለት የመሰንጠቅን አደጋ ያስተናገደበት ወቅት ነበር፡፡ አዋሳም የዚህ ወላፈን ተቋዳሽ ብቻም ሳትሆን ትዕይንቱን ዘግናኝ በሆነ ታሪካዊ ክስተት ያስተናገደች ከተማ ነበረች።የአዋሳ ከተማ ከ1994 በፊት በተደነገገው የፌዴራል ሥርዓት መሰረት የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስትና የሲዳማ ዞን መስተዳደር የጋራ ዋና ከተማ ወይም ማዕከል ሆና እስከ 1994ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ዘለቀች። ይሁን እንጂ ከመንግስት ተላልፏል በተባለ ትዕዛዝ መሰረት አዋሳ የክልሉ መንግስት ርዕሰ ከተማ ብቻ እንድትሆንና ‹‹የሲዳማ ዞን መስተዳደር ወደ አለታወንዶ ከተማ እንደተዛወረ ተወስኗል›› የሚል ትዕዛዝ ተላልፏል የሚለው ዜና የሲዳማ ብሄር ተወላጆችን እጅግ አስቆጣ፡፡ ህዝቡም ህገ-መንግስቱ ይፈቅድልኛል ባለው ሰላማዊመቃወሚያ ዘዴን ተጠቅሞ ብሶቱን ለማሰማት ወደአደባባይ ለመውጣት መሰናዶውን አጠናቀቀ።

በወጣው ፕሮግራም መሰረት ሰልፉ ግንቦት 16 ቀን 1994 ዓ.ም. እንደሚካሄድና መነሻውም ከሃዋሳ ከተማ በስተደቡብ ከ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ‹‹ሎቄ›› ከተባለች ከተማ ሆኖ የሰልፍ መጨረሻም በአዋሳ እምብርት ከሚገኘው አብዮት አደባባይ እንዲሆን ታቀደ።
በታቀደው ፕሮግራም መሰረት የብሄሩ ተወላጆች ከየመንድራቸው የተውጣጡ ቁጥራቸው ከ7 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጐች በባህላቸው መሰረት የእንስሳት ተክል ዝንጣፊና እፍኝ ሳር በእጃቸው ይዘው፤ሌሎች የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማን የያዙትን ሰልፈኞች ፊት አስቀድመው ‹‹ሲዳማ ክልል የመሆን ሕገ-መንግስታዊ መብቱ ይጠበቅለት››፣ ‹‹ሃዋሳ ከተማ የሲዳማ ዞን ርዕሰ ከተማ እንዳትሆን ለምን ተፈለገ?›› የሚሉትንና ሌሎች መሰል መፈክሮችን በመያዝ ወደ ሰልፉ መዳረሻ የሚወስደውን ጎዳናተከትለው ጉዞአቸውን ቀጠሉ።
በወቅቱ ተከስቶ ስለነበረው የመንግስት የመልስ ምት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ ካወጣው ሪፖርት ትንሽ እንቀንጭብ። ‹‹ሰልፈኛው ከመነሻው ስፍራው ጀምሮ 3 ኪሎ ሜትር ያህል በሰላም ተንቀሳቅሶ ሃዋሳ መግቢያ በርአካባቢ እንደደረሰ በአካባቢ መሽጎ ይጠባበቅ የነበረው ታጣቂ የመንግስት ኃይል የፊሽካ ድምፅ እንደተሰማ በመኪናዎች ላይ የተጠመደውን ፒ.ኬ.ኤም የድግን መትረየስ አፈሙዞች ወደ ሰልፈኛው አነጣጥሮ ለ10 ደቂቃ ያህል ያወረደው የጥይት ናዳ የገደለውን ገድሎና ያቆሰለውን አቁስሎ ቀሪውን ሰልፈኛ በተነው።›› ሲል በጊዜው የነበረውን ዘግናኝ ጭፍጨፋና በጊዜው ህይወታቸውን ያጡ፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውንና በሰልፉ ምክንያት ለእስር የተዳረጉ ግለሰቦችን የስም ዝርዝር አስደግፎ አውጥቷል።
እስካሁንም በሲዳማ ተወላጆች ላይ በተወሰደው ዘግናኝ እርምጃ፣ ለጠፋው የሰው ህይወት፣ ለደረሰው የአካል ጉዳት ተጠያቂ የነበሩ የመንግስት ባለስልጣናት አንዳቸውም ለፍርድ አልቀረቡም። መንግስትም ለጥፋቱ ኃላፊነቱን ወስዶ ተገቢውን የካሳ ክፍያ ለቤተሰቦቻቸው አልሰጠም።
የኢህአዴግ ፖለቲካ አሁንም ካለፈው ስህተት ከመማር ይልቅ ‹‹ጭር ሲል አልወድም›› እንደሚባለው ሁሉ የተዳፈነውን እሳት ለመጫር እየታተረ ይገኛል። ያለፈው ቁርሾ ሳይጠግ፣ በአሁኑ ወቅት ከተማዋ ዳግም ወደለየለት ብጥብጥ ውስጥ  ልትዘልቅ በቋፍ ላይ የቆመች ትመስላለች፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የዲኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አስረኛ አመት የተሃድሶ ጉዞን በገመገመበት ወቅት ‹‹ሜትሮፖሊታን ከተማችንን እንዴት እንምራው?›› በሚል ርዕስ አንድ ሰነድ ለውይይት አቅርቦ ነበር። ይህ ባለ 13 ገፅ ጥራዝ፤ መግቢያናማጠቃለያውን ጨምሮ፣ በዋናነት የከተማችንንአመራር ቁልፍ ጥያቄ ያደረጉ ምክንያቶች፣እንዲሁም የከተማችንን አመራር ሥርዓት ለመፍጠር ልንከተላቸው የሚገቡ መርሆዎች የሚሉ ሁለት አርዕስቶችንና በውስጣቸው የተብራሩ ሌሎች ንዑሳነ-ርዕሳትን አካትቷል።
ፅሑፉ ሜትሮፖሊታን ከተማ የሆነችውን አዋሳ በድጋሚ የለውጥ ማዕቀፍ ውስጥ እንድትገባ የሚያደረጓትን ሶስት ምክንያቶች ዘርዝሯል። በሽግግሩ ብቃት ያለው አመራር መመደብ፣ የተጀመረውን የኪራይ ሰብሳቢነት አረንቋ ከምንጩ የማድረቅ ተግባርን ከግብ ማድረስና ልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ እንዲሰፍን ማድረግ የሚሉት በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው።
ኪራይ ሰብሳቢነትና መተላለቅእንደኔ እይታ ዶክመንቱን ያዘጋጁ ግለሰቦችአንድም ሀሳባቸውን በሚገባ ቋንቋ ማስተላለፍ በሙሉነህ አያሌው muleayalew@yahoo.com ተስኗቸዋል፣ አልያም ችግር ያሉትን ለመፍታት መወሰድ ይገባዋል ብለው በሚያምኑት የመፍትሄ እርምጃ በፍፁም ከችግሩ አፈታት ጋር እንዴት መሄድ
እንዳለበት አያውቁትም ብሎ መናገር ይቻላል።
ጥራዙ የከተማዋ ዋነኛ ችግር የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ስር መስደድ እንደሆነይናገራል። ይህ ችግር ምንጩ ምን እንደሆነ ለማወቅ እንደተቸገሩ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ‹‹ከተማችንን በአብዛኛው ሲፈታተናት የቆየ በመሆኑ ማደግ የምትችለውና መድረስና መሆን በሚገባት ደረጃ እንዳላደገች ለእኛ ለአመራሮች የአደባባይ ምሥጢር ሆኖ የቆየ ነው›› ይልና ትንሽ ወረድ ብሎ የአደባባይ ምስጢር ሆኖብናል፣ ልናውቀው አልቻልንም የተባሉትን ችግሮች ሳያብራራ፣ ችግሩ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ እንደሆነ ይገልፃል።
ዶክመንቱ ሁለት የተምታቱ ሀሳቦችንበተከታታይ ካስቀመጠ በኋላ የዚህ ችግር ውጤት ይሆናል ያለውን ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲህ ያስቀምጠዋል። ‹‹በውጤቱ ደግሞ የምንታገልላቸውን ማህበራዊ መሠረቶቻችንን በውድድር እንዳያምኑ በማድረግ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት የእኛም ማህበራዊ መሠረት በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም እንዲሰርፅ በማድረግ መላውን ሥርዓታችንን አደጋ ውስጥ እንጥላለን ማለት ነው። አስፍቶ በሚታይበት ጊዜ የህብረተሰብን መበስበስ (Societal decay) እንፈጥራለን ማለት ነው። በሂደትም ኋላቀርነት እየነገሰ መጥቶ መበታተንና መተላለቅን እንጋብዛለንማለት ነው›› ይላል፡፡
ከላይ በቀረበው ትንታኔ መሰረት ኪራይ ሰብሳቢነት ዋና የከተማዋ ችግር ነው በሚለው ዙሪያ አመራሩ አምኖበታል። ማህበራዊ መሰረቶች የሚለውን ቃል ለሁለት የተለያዩ ጭብጦች እኩል ትርጉም ይሰጣል። ማህበራዊ መሠረት ማለት ምን ማለት ነው? ‹‹ማህበራዊ መሠረቶቻችን በውድድር እንዳያምኑ›› የሚለው የመጀመሪያው የሀረጉ አገባብ ከአፃፃፉ ተቋማትን ለማመልከት የገባ ሲመስል፤ሁለተኛው ‹‹ማህበራዊ መሰረት በሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች›› የሚለው የከተማዋ ነዋሪዎችን ያጠይቃል።
ስለዚህ ኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ከሆነ በእዚህ ወንጀል ላይ የተሰማሩ ባለስልጣናትን ከስልጣን አባሮ ለፍርድ ማቅረብ ቀላል መፍትሄ በሆነበት ፖለቲካ ሥርዓት ‹‹መተላለቅ፣ መበታተን እንጋብዛለን›› ማለትን ምን አመጣው? የኢህአዴግ ባለስልጣናት አንድን እቅድ አውጥተው ለማስፈፀም ሲመጡ ማስፈራራት የመጀመሪያ ግባቸው ነው። የደቡብ ባለስልጣናትም ይህንኑ ቀመር እያስተጋቡ ነው። ጥራዙ ኪራይ ሰብሳቢነት የሚለውን ችግር በሽፋንነት እየተጠቀመበት እንደሆነ ካያያዙ መረዳት ይቻላል፡፡
ከአስር አመት በፊት በአዋሳ ከተማ ላይ በተካሄደው የሲዳማዎች መብት ጥያቄና በመንግስት የተወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ ከማንም ልቦና ውስጥ የሚጠፋ አይደለም። ዶክመንቱ በኪራይ ሰብሳቢ አመለካከት የተነሳ ሃዋሳ ከተሃድሶ በፊት ወደ ነበረው ሁኔታ ልትመለስ እንደምትችል ፍንጮች እየታዩ መጥተዋል ይላል።
‹‹ከተሃድሶ በፊት የነበረውና አሁንም ብቅ ጥልቅ የሚለውን የእኛን ሁኔታ በምንቃኝበት ጊዜ ይህ አባባል ለማለት ብቻ የሚባል ፅንሰ-ሃሳብ ሳይሆን በትንሹም ቢሆን ቀምሰን ያለፍነው የጥፋት መንገድ መሆኑንና ዝም ከተባለ ጎልብቶና ጊዜ ሳይሰጥ መከሰቱ የማይቀር ይሆናል ቢባል ማጋነን አይሆንም።›› በዚህ መንገድ ዶክመንቱ ቀስ እያለ ያቀደውን አላማ እያጠራ ይመጣል። ከተሃድሶ በፊት የነበረውና ‹‹ቀምሰን ያለፍነው የጥፋት መንገድ›› የተባለው የሲዳማ ህዝብ በህጋዊ መንገድ ያቀረበው ጥያቄ ነው።
የሲዳማ ህዝብ በወቅቱ አንስቶት የነበረው ጥያቄ ኪራይ ሰብሳቢነት ይወገድ የሚል ሳይሆን ‹‹የሲዳማ ህዝብ ካለው ቁጥር አንፃር የክልልነት መብት ሊሰጠው ይገባል፣ ሃዋሳ ከተማ የዞኑ ርዕሰ ከተማ ከመሆን ማንሳት ለምን አስፈለገ?›› የሚሉትን የመብት ጥያቄዎች ነው። ይህ ጥያቄ ያስነሳው ብጥብጥ አሁን ደግሞ በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ምክንያት ሊነሳስለሆነ አንድ እርምጃ መውሰድ አለበት እያሉ ነው።
ዶክመንቱ በአጭሩ ፊቱን ዳግም ወደ ሲዳማ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ይመስላል። ሲዳማዎች አዋሳን በኪራይ ሰብሳቢነት እየተጫወቱባት ስለሆነ ከዚህ በኋላ ይበቃቸዋል ለማለት የታቀደ ነው በሚል ማድረጉን ማለቴ ነው፡፡
Opening-up ለውድድር ክፍት ማድረግ (Opening-up) የሚለውን የኢኮኖሚ መርህ ቻይና ውስጥ እንዲተገበር መሰረት የጣሉት እና ቻይና ዛሬ ላለችበት የእድገት ደረጃ አብቅተዋታል የሚባሉት ታላቁ መሪዋ ዴንግ ዣንፒንግ (Deng Xiopping) ናቸው። በመንግስት የቀረበው ዶክመንት የሃዋሳን ከተማ ከሁለት ነገሮች አንፃር በምሳሌነት እንድትወሳ ይሻል። የመጀመሪያው  ከተማዋ በፍጥነት እየተለወጠች በመምጣቷ ምክንያት እንደ ግብፅ-ሸማርአልሼክ፣ እንደ ህንድ-ባንግሎር፣ እንደ ደቡብአፍሪካዋ- ደርባንና እንደ
አሜሪካዋ-ካምፕዴቪድ ከተሞች ሁሉ የኢትዮጵያዋ-አዋሳ ተብላ እንድትመዘገብ የሚሻ ሲሆን ከተማዋን በሁለተኛ ደረጃ በንፅፅር ያቆሙት ቻይና ካደገችበት “Opening-up” ሞዴል ጋር በማነፃፀር ነው። እንዲህ
ይላል ‹‹ቻይና ውስጥ ኢንቨስት ካደረጉት ባለሃብቶች መካከል ከ70% በላይ ከምዕራባዊያን አገሮችና የቀረው ደግሞ በዓይነ ቁራኛ ከሚታዩት ከጃፓን መሆኑ ሲታይ እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ህዝባቸውን ለመጥቀም ሲሉ  የሌላውን አገር በታሪክ የሚጠላሉትን አገር ጭምር ኢንቨስትመንት ለመሳብ ወደኋላ እንዳላሉ ያሳያል።›› የዚህ ንፅፅር አንዱ ችግር አዋሳ ከተማን ቻይና ከምትባል አገር ጋር ለማወዳደር ያደረገው ከንቱ ሙከራ ነው። በአንድ አገር ውስጥ የሚገኝ ከተማ እና አንድ ሉዓላዊ አገር የሚመሩበት ፖሊሲ  ለየቅል ነው። የአዋሳ ከተማ ብቻዋን (ያለፌዴራል መንግስት እውቅና እና ይሁኝታ) ከውጭ አገራት ጋር ፖሊሲ ቀርፃ መንቀሳቀስ እንደማትችል ህገ-መንግስቱ ይደነግጋል። ይህ አመክንዮ ስህተት ከሆነና መቀበል ካለብን፣ አዋሳን በፌዴራል መንግስት ሥርዓት መሠረት ለብቻዋ (ሊያውም ከደቡብ ክልልነት ነጥለን) እንደ አገር እያየናት ነው ማለት ነው። እንደእኔ አተያይ የዶክመንቱ ፀሐፊዎች፣ በዘውግ ፌደራሊዝም ውስጥ ባለ የክልል ከተማ እና ሀገር መካከል ልዩነት ምን እንደሆነ የተረዱት አይመስለኝም፡፡
ሌላው ከቻይና ተሞክሮ ብለው ያቀረቡት የጃፓንን በቻይና ኢኮኖሚ ላይ እያደረገች ያለውን ተሳትፎ ነው። ሁለቱ አገራት ከነበራቸው ታሪካዊ ጠላትነት አንፃር ‹‹ቻይና ለጃፓን ኢኮኖሚዋን ክፍት ታደርጋለች ተብሎ አይጠበቅም ነበር›› ይልና ይሄንን ማድረጓ ግን ከጉዳት ይልቅ ጥቅምን እንዳተረፈላት ለማስገንዘብ ይጥራል። ይሄ ምሳሌ ወደ አዋሳ ተሞክሮ ሲመጣ ወይም መምጣት አለበት ሲባል አንደኛ አዋሳ ታሪካዊ ጠላቶቼ የምትላቸው ህዝቦች/
ከተሞች አሉ ማለት ነው። እነዚህን ታሪካዊ ጠላቶቿ እስከዛሬ በከተማዋ ላይ ኢንቨስት እንዳያደርጉ፣ ሀብትና ንብረት እንዳያፈሩ ማዕቀብ ተጥሎባቸው የነበረ መሆኑን በተዘዋዋሪ ጥራዙ ይናዘዛል። በሯን ለሌሎች የአገሪቷ ህዝቦች ክፍት አድርጋ እንዳትቀበል የተለያዩ ግለሰቦች /በአመራር ቦታ ላይ ያሉ/ ካላቸው ግላዊ ጥላቻ አንፃር አንቀበልም የሚል አመለካከት መኖሩን ይጠቁምና በስተመጨረሻም የመፍትሄ ሃሳቡን በሚከተለው መልኩ ያቀርባል።
‹‹ከዚህ በተቃራኒ እንምራው ከተባለ ደግሞ ከተማችን መቆርቆዝ፣ ሕዝባችንም ከተጠቃሚነት አንፃር መጎዳቱና የኋላቀር አመለካከቱ ጎልብቶ ወደመናጨት መግባታችን በጭራሽ አይቀሬ ይሆናል።›› ይሄ አመለካከት እስከዛሬ ከነበረ አመራሩን መጠየቅ ቀላሉ አካሄድ ነው፡፡ከሲዳማ ህዝብ ራስን በራስ ከማስተዳደር የመብት ጥያቄ ጋር በፍፁም ሊያያዝ አይገባም፡፡ በስልጣናቸው አለአግባብ ተጠቅመዋል የተባሉትን ባለስልጣናት አስወግዶ በምትኩ ሲዳማን በደንብ የሚወክል የአዋሳ ከተማ አስተዳዳሪ መሾም ብቸኛ መፍትሄ ነው፡፡
የብሔር ፖለቲካ ተቃርኖ ኢህአዴግ በአዋሳ ከተማ አስተዳደር ላይ ሊያመጣ ያሰበውን ለውጥ በሁለት መንገድ ልናየው እንችላለን። የመጀመሪያው 20 አመት ሙሉ  ስንንገታገትበት የቆየውን የብሔር ውክልና አመራር በአፍጢሙ ደፍቶ ሌላ አይነት አስተዳደራዊ ስልትን ለመተካት ሃዋሳን እንደ ናሙና መጠቀም ሲሆን ሌላኛው አላማ ምን አልባት በአዋሳ ከተማ ላይ ያለውን የሲዳማዎች የበላይነት አንኮታኩቶ በምትኩ ከተማዋ ያላትን እምቅ የገቢ ሀብት ወደ ፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ለማስገባት የታለመ ይመስላል።
ይሄንን ለማድረግ ሲዳማዎችን ከጨዋታው ትንሽ ገለል ማድረግ ያስፈልጋል። ሲዳማዎችን ከመድረኩ ለማደብዘዝ ደግሞ የአመራሩን የአመራረጥ ውክልና በአዲስ ንድፈ ሃሳብ ቀይሮ ብሄሩን መበታተን ያስፈልጋል። ባለ13ቱ ገፅ ዶክመንትም መተግበር ያለበት ይህ ነው ይላል። ለምን አዋሳ ተመረጠች?
ከዚህ በፊት ይደረግ የነበረው ‹‹በህዝብ ብቻ ተመርጦ በሥልጣን እርከን ላይ መውጣት›› በቂ አለመሆኑን አፅንኦት የሰጠው ጥራዝ፤ አሁን ካለው የከተማዋ እድገት አኳያ የተፈለገውን ተግባር ለማስፈፀም ብቃት ያለው አመራር ፈልጎ መመደብ አስፈላጊ መሆኑን ያሰምርበታል። ‹‹ብቃት›› የሚለውን መመዘኛ ሁለት ነገሮችን በውስጡ እንደያዘ ይናገራል። የመጀመሪያው እና በዋናነት ብቃት ሲባል ‹‹የአብዮታዊ ወይም ልማት እና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና አመለካከት ብቃት›› ሲሆን፣ ሁለተኛው የብቃት መለኪያ ‹‹የአመራር ጥበብ ክህሎት ብቃትና በቦታው የሚመጥን አካዳሚያዊና የመገንዘብ ችሎታ ብቃት ማለት ነው›› ይላል። ስለዚህ ቅድሚያ የሚሰጠው ለፖለቲካው ያለው ታማኝነት ሲሆን ሁለተኛው የአካዳሚያዊ ደረጃ ከግምት ውስጥ ይገባል። ምን አልባት ሲዳማዎች ለዚህ ጥቅመኝነት አይመቹ ይሆን?
ኢህአዴግ ሁሉም ብሔሮች በተመጣጠነ መልኩ መወከል ይገባቸዋል የሚለውን የብሔር ፖለቲካ አሁን ላይ እርባና እንደሌለውና በሌላ‹‹የተሻለ›› በሚለው መልኩ መተካት እንዳለበት አምኗል። አምኗል ስል ሌሎችም ክልሎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ለማለት አይደለም/ሲዳማን ብቻ ነው የሚመለከተው/፡፡
ዶክመንቱ ውስጥ ‹‹ብሔራዊ ተዋፅኦን ለማመጣጠን ሲባል ብቃት የሌላቸው ሰዎች ተሹመው ፖሊሲው
በትክክል ሳይፈፀም ቢቀር ሕዝቡን በአጠቃላይ የሚጎዳ ነው›› የሚል ቃል ሰፍሯል። ስለዚህ የአዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የሲዳማ ብሄር ተወላጆች መያዙ አግባብ አይደለም እንደማለት ነው። ሌሎች ከሲዳማ ብሄር ውጭ ያሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ባለመወከላቸው ምክንያት ጥቅማቸው እየተከበረላቸው አይደለም ማለት ነው? ይህንን ለማመጣጠን ካቢኔው በሁለት ምክንያት እንደገና መከለስ አለበት ይላል። የመጀመሪያው ኢህአዴግ የማይንቀሳቀስባቸው ክልሎች መኖራቸው በኢህአዴግ ለሚቋቋመው ካቢኔ አለመስተካከል በቀዳሚ ምክንያት የቀረበ ሲሆን፤ ሁለተኛው ምክንያት ፖሊሲዬንበብቃት ያስፈፅሙልኛል ብሎ ሊተማመንባቸው የሚችል አቅሙ ያላቸው ሰዎች በተፈላጊው መጠን መገኘት አለመቻሉን በአስረጂነት ያቀርባል።
‘The Sidama Model’ ኢህአዴግ የሲዳማዎችን መብትና ጥቅም ሙሉ ለሙሉ ጠራርጐ ለመውሰድ የፈለገ በሚመስል መልኩ ለአዋሳ ብቻ የሚሰራ አዲስ ንድፈ ሀሳብ ማርቀቅ ጀምሯል። ከዚህስ በኋላ ምን ሊያደርግ ይችላል? የሚለውን ለመረዳት የዶክመንቱን አካሄድ በሚገባ ማየት ያስፈልጋል። ዶክመንቱ ሲጨመቅ ደግሞ ማለት የፈለገው ይህንን ነው።
1. የብሔር ተወላጅ መሆን ብቻውን ብሔርን ለመወከል መስፈርት ይሆናል የሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ መሆኑን
2. የብሔር ተዋፅኦን ለማመጣጠን ሲባል ብቃት የሌላቸው ሰዎች ተሹመው ፖሊሲው በትክክል ሳይፈፀም ቢቀር ሕዝቡ በአጠቃላይ የሚጎዳ ይሆናል
የሚለውን እነዚህ ዋና ፍሬ ሀሳቦች በቀጣይ ሌሎች መዘዞችን ይዞው ብቅ የሚሉ ይመስላል።
የመጀመሪያው የአዋሳ ከተማ አስተዳደርን በኃላፊነት የሚመሩት የሲዳማ ብሔር ተወላጅ መሆናቸው ብቻ አግባብ ስላልሆነ የሌሎች ብሔር አባላቶችም በውክልና መሳተፍ ይገባቸዋል ባይ ነው። ኢህአዴግ ይህንን ማድረግ ከቻለ የሲዳማ ፖለቲካ ልሂቃንን ሚና በእጅጉ ከማዳከሙም በላይ ሲዳማዎች የእኛ የሚሏትን የአዋሳ ይገባኛል ጥያቄ በሌሎች ሲዳማን በማይወክሉ የብሔር አባላት ተይዞ በድምፅ ብልጫ ውሳኔ ኢህአዴግ መዲናቸውን ከአዋሳ ወደ አለታወንዶ እንዲያዛውር መንገዱን ቀላል ያደርግለታል። ከዚህ በኋላ ሲዳማን በሚመለከት ወሳኝ የሚሆኑት የሌሎች ብሔር አባላቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ይሄ ደግሞ በሲዳማ ህዝብ ላይ መቀለድ ነው። እንደ እኔ እምነት ሲዳማን እና ሃዋሳን በሚመለከት የመወሰን መብት የህዝቡ እንጂ ህዝቡን እንወክላለን የሚሉ የብሔሩ ተወካዮች ብቻ አይደለም። ከእስከዛሬው ተሞክሮ ያየነው ብዙ ባለስልጣናት ለጥቅማቸው ያደሩና የህዝብን ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በቀላሉ ለፖለቲካ መጠቀሚያ መሆናቸውንም ጭምር ነው።የታሪክና የህሊና ቁስል የሚባል ፀፀት
የለባቸውም፡፡ማን በማን ይቀልዳል? ለሲዳማ ብቻ ተብሎ የረቀቀው አዲሱ ሞዴል ህዝበ ውሳኔ /Referendum/ ካልተደረገበት በስተቀር መንግስት ለማሳመን እየሄደበት ያለው አካሄድ ከትርፉ ጉዳቱ ያመዝናል።
እንደ መውጫ  ፈራ ተባ እያለ የቀረበው ዶክመንት በውስጡ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ብዙ ፅንሰ ሃሳቦችን ከመያዙ በተጨማሪ የአዋሳን ከተማ ‹‹ሜትሮፖሊታን›› በሚል ስያሜ አዲስ የአመራር ለውጥ ለማድርግ የተካሄደበት መንገድ ዳግም የ1994 ዓ.ም ቀውስ እንዳይጋብዝ ስጋት አለ። ሲዳማዎችየሚሰማቸው አካል ይፈልጋሉ። የብሔር ፖለቲካው እነርሱ ጋር ሲደርስ ለትንታኔ አስቸጋሪ የሚሆንበት ምክንያትም ግልፅ እንዲሆንላቸው ይሻሉ። ሲዳማዎች በአዋሳ ከተማ ላይ ያላቸው ቁርኝት ደማቸውና አጥንታቸው ውስጥ ዘልቆ የገባ የመሆኑን ያህል በተዳፈነው ቁርሾ ላይ ሌላ እሳት መጫር ሌላ ኪሳራ ሊያመጣ ይችላል። ክልል መሆን እንደሚችሉ ህገ-መንግስታዊ መብታቸው ቢሆንም ግልፅ ባልሆነ ምክንያት አልሆኑም። እንዲሁም በ1994 ዓ.ም. ያን የመሰለ አስከፊ አደጋ ሲደርስ ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች ዛሬመ በስልጣን ላይ በመሆናቸው ነገስ ምን አይነት መተማመኛ ሊኖር ይችላል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።
ግንቦት 23 ቀን 1994 ዓ.ም. በአዋሳ ከተማ በተካሄደው ጭፍጨፋ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ ምክትል ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዋል። የአዋሳ ከተማ ደግሞ ከ10 ዓመት በኋላ የአመራር ክለሳ ያስፈልጋታል ተብሏል። የሲዳማዎች
ጥያቄ ምላሽስ? የክልል ይገባናል ጥያቄ ዳግም ወደ ፖለቲካው መድረክ ብቅ ብሏል። አሁን ያለው አካሄድ ጥንቃቄ የሚሻና አንዱን ወገን ጠቅሞ ሌላውን ወገን ለማስከፋት የተረቀቀ ፖሊሲ መሆን የለበትም።
እነሆ ያ አስከፊ ጊዜ ካለፈ አስር አመት ሞላው። ግንቦት መጨረሻና ሰኔ መጀመሪያ በመጣ ቁጥር የሲዳማ እናቶች ነፍስ ትርገበገባለች። ይህ ወቅት የሟቾቹ ወላጆች የልጆቻቸውን ሙት  አመት የሚዘክሩበት ጊዜ ነው። ሁነቱ የትናንትና ቁርሾ የሚረሳበትና የዛሬዋን ኢትዮጵያ በአንድነት የሚገነቡበት፣ ለተተኪው ትውልድ የተሻለች አገርን ለማቆም የሚያስችል የጋራ መግባባት የሚደረስበት መሆን ይገባዋል። ዳግም የሲዳማ እናቶች ስለልጆቻቸው አንዲት ዘለላ እንባን እንዳያፈሱ መንግስት ችግሩን በህግ መንግስቱ ብቻ መፍታት ይጠበቅበታል።
ምንጭ፦ http://www.fetehe.com/