POWr Social Media Icons

Sunday, June 24, 2012


የሲዳማ ምሁራን የማወያያ ጽሁፉን በተመለከተ በተለያዩ ማህበራዊ መረቦች ላይ ያቀረቡት ትችት እንደምያመለክተው፡ በደኢህዴን ስራ ኣስፋጻሚ ኮሚቴ የተዘጋጀው የማወያያ ጽሁፍ የሃዋሳ ከተማ በጥቂት ኣመታት ውስጥ ያሳየችው እድገት በሲዳማ ኣስተዳደር ብቃት መሆኑን የክድ፤ የሲዳማን ህዝብ እንግዳ ተቀባይነትን ከግምት ውስጥ ያላስገባና በጭፍን የሲዳማን ህዝብ የሚያጥላላ ነው ብለዋል::

በማወያያ ጽሁፉ ላይ የቀረበውን ሙሉ ትችት እንደምከተለው ኣቅርበናል::


ሲዳማ ከዘመነ አፄ ምኒልክ እስከ ደኢህዴን/ኢህአዴግ


የአፄ ምኒልክ ተዋጊ ኃይል የሲዳማን ህዝብ በአስከፊ ጭቆናና ብዝበዛ ስር ለማስተዳደር ባካሄደው ወረራ በወቅቱ ይጠቀምበት የነበረውን የጦር መሳሪያ ከህዝቡ ስነ-ልቦናዊ ዝግጅት አንጻር የማይጣጣም በመሆኑ የሲዳማን ህዝብ በግፍ እየጨፈጨፈ እስከ ደቡባዊ አገር ድረስ መዝለቁ አልቀረም፡፡


በወቅቱ ያደረሰው ብዝበዛና ጭቆና የህዝባችንን ሰብዓዊ ክብር ያዋረደና ነፃነቱን ያሳጣ በመሆኑ የሲዳማ ህዝብ በቡድንና በተናጥል ባልተደራጀ ሁኔታም ቢሆን ከምኒልክ ወረራ ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለስላሴ ውድቀት ድረስ ለማንነቱና ለሰብዓዊ ክብሩ ያደረጋቸው የነፃነት ተጋድሎዎች ለታሪክ የሚዘከሩ ናቸው፡፡


በተለያየ መንገድ ፈርጀ ብዙ የሆኑ የፀረ ነፍጠኛ ወይንም መልከኛ ትግል እስከ ደርግ መንግስት ቀጥሎ የመልከኛ ስርዓት ተወገደ፡፡ እንደማንኛውም ነፃነት ፈላጊና ገባሪ ብሔሮች ሁሉ የሲዳማ ሕዝብ የተቀማውን የመሬት ባለቤትነት መብት አገኘ፡፡ ቀጣይ የማንነትና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎች ባይመለሱለትም የሲዳማ ሕዝብ ከ70 ዓመታት በፊት ከአባቶቹ እጅ የተነጠቀውን መሬት መልሶ በማግኘት ለአጭር ጊዜም ቢሆን እፎይታ ያገኘ መስሎ ቢታይም ሰው በላው የወቅቱ መንግሥት ግን በርካታ ህዝባዊ ጥያቄዎችን በአግባቡ ከማስተናገድ ይልቅ በዘዴና በጉልበት በማፈን ህዝቡን ረግጦ፣ አፍኖና ጨቁኖ ለመግዛት የሚያስችል ስልጣኑን በማደላደልና ወጣቶችን በነጻ እርምጃ መጨፍጨፍ ጀመረ፡፡


በአርሶ አደሩ ላይም የባሰ የጭቆና ቀንበር ጫነበት፡፡ ልቡ ያበጠበት፣ ጆሮው የደነደነበት፣ ከራሱ ድምፅና ስሜት በቀር የሕዝብን ስሜት የማይሰማ አምባገነን ገዳይ መንግስት ሆነ፡፡ ደርግ፡፡


የትግል ሸክም ከላያቸው ያልወረደ የብሔሩ ተወላጆች በህቡዕ ይንቀሳቀሱ ከነበሩበት በመውጣት የትጥቅ ትግል አማራጭ የሌለው እየሆነ የመጣው በጥር ወር 1970 ዓ.ም ነበር፡፡
በዚህ የተነሳ ሰፊው የሲዳማ ወጣቶች እና ጎልማሶች ለነፃነት ትግል ዝግጅት ወደ ሶማሊያ ከ30-50 ቀናት የሚፈጅ አደገኛ የእግር ጉዞ በማድረግ የሲዳማ አርነት ንቅናቄን (ሲአንን) መሠረቱ፡፡
የረሃብና የውሃ ጥማት እልቂት ሳይበግራቸው እጅግ አደገኛ የበረሃ ጉዞ በማድረግ ዘመናዊ የጎሬላ ውጊያ ለረጅም ጊዜ ስልጠና በመውሰድና ዓለም አቀፍ የነጻነት ታጋይነት ዕውቅናን ከማግኘት በላይ ሁለት የታወቁ የውትድርና ማሰልጠኛዎችን በማቋቋም በርካታ ዙር ስልጠና በማካሄድ ብቃትና ንቃት ያላቸውን ታጋዮች ያዘጋጀ ከመሆኑም በላይ  የራሱ የሆነ የሬዲዮ ጣቢያ በማቋቋም ለመጀመሪያ ጊዜ የሲዳሚኛ ቋንቋ ትምህርት በላቲን ፊደል የመማሪያ መፅሀፍ በማዘጋጀት በሬዲዮ ስርጭት ላይ የዋለው ከሞቃዲሾ በመሆኑ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡
በወቅቱ አምባገነኑ የደርግ ስርዓት የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያገደ፣ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችን ለማስተናገድና አማራጭ ሃሳብ ለመስማት ትዕግስት የሌለውና ጆሮው የተደፈነ፣ ኃይልንና አፈናን እንደ ዋነኛ የፖለቲካ መሳሪያ አድርጎ የሚጠቀም በመሆኑ የትጥቅ ትግል ማድረግ የወቅቱ ትክክለኛና አማራጭ የሌለው የፖለቲካ መስመር ሆኖ ነበር ማለት ይቻላል፡፡


ዳሩ ግን ይህን አለም በሙሉ ያወቀውን የሲዳማ ህዝብ ትጥቅ ትግልን የደኢህዴን ካድሬዎች በቅርቡ በብርሸለቆና በሌሎች ማስለጠኛ ካምፖች በሚሰጡ ስልጠናዎች ላይ ‹‹ትግሉ ብሔርን መሰረት ያደረገ ሳይሆን የግል ጥቅምን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ሲዳማ በብሔር ደረጃ ያደረገው የፖለቲካ ትግል የለም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ኢህአፓን፣ መኢሶንን ወዘተ በመቀላቀል ከተደረገ ሙከራ በቀር የተደራጀ ትግል አላደረገም…›› በማለት ለማጣጣል ያደረጉት ጥረት አስቂኝ ነው፡፡ የደኢህዴን አፈ ጮሌ ካድሬዎች ይህን ያደረጉት የሲዳማን ትግል ሳያዉቁ ቀርቶ ሳይሆን በደቡብ ክልል ውስጥ የታቀፉት ብሔረሰቦች እንደ ሲዳማ ተደራጅተው ከደርግ መንግስት ጋር ያደረጉት የነጻነት የትጥቅ ትግል ባለመኖሩ ሲዳማ ብቻ ተለይቶ ለምን ከታጋዮች ጎራ ይቆጠራል ከሚል  ቅናትና ቁጭት የተነሳ ነው፡፡


በወቅቱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ዘመናዊ አውቶማቲክ መሳሪያዎች በመጠቀም ለደርግ ውድቀት ሲአን ያደረገው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀ ነበር፡፡ በመጨረሻም የደርግ ወታደር የሲአንን ኃይል መቋቋም ሲያቅተው እሾህን በእሾህ በሚል ወይንም እራሱን በእራሱ ጠልፎ መጣል በሚል መሴሪ ዘዴ በመጠቀም የገዛ ልጆቹን በሆድና በሌሎች መናኛ ጥቅማ ጥቅሞች በመደለል እርስ በራሱ እንዲተላለቅ አደረገ፡፡
ዛሬም ቢሆን እኛን በእኛው የማባላትና የማጫረስ፣ በሚበላና በሚጠጣ በመደለል እርስ በእርሳችን እንድንጋጭ ማድረጉ በስፋት የቀጠለ ሳጥናኤላዊ ድርጊት ነው፡፡ ባንዳ በመላው ሀገራችን መቼም ጠፍቶ አያውቅምና፡፡
ሲዳማ በደኢህዴን/ኢህአዴግ ዘመን


የደርግ ስርዓት በህዝብና በነፃነት ታጋይ ኃይሎች ከስልጣን ከተባረረ በኋላ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ለሰላም ወዳድና ነፃነት ታጋዮች ጥሪ ተደርጎ የሽግግር መንግስት አባል ከሆኑት የፖለቲካ ኃይሎች አንዱ ሲአን ሲሆን ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያም ሆነ በሲዳማ ውስጥ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተሞክሮ ነበረ፡፡


ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ የኢህአደግ መንግስት ˝ድመት መንኩሳ ዓመሏን አትረሳ ˝እንዲሉ ሲህዴድ/የሲዳማ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ በሚል ስያሜ ሌላ ተቀናቃኝ ድርጅት አቋቁሞ ሁለት ወንድማማቾች ጎራ ለይተው ወደ ግጭት እንዲገቡና ለዳግም እልቂት እና ደም መፋሰስ ሴራ ጠነሰሰብን፡፡


በዚህ የተነሳ በሁለቱም የሲዳማ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል በተፈጠረው ሹክቻ በሐዋሳ፣ በአሮሬሳና አርቤጎና አካባቢ የትጥቅ ትግል የታከለበት ግጭት ተከስቷል፡፡ ጠላቶቻችን ጎራ ለይተን እንድንተላለቅ ያውጠነጠኑብንን ተንኮል በመረዳት የሲዳማ ዓርነት ንቅናቄ ያገኘው ግንዛቤ የሲዳማ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የሚል ካባ ደርበው በማቅረብ መሰሪ ዕቅዶቻቸውን እንዲያስፈፅሙ ከተፈጠረውና የራሱ የሆነ የመተንፈሻ ሳንባና ዘላቂ የፖለቲካ ዓላማ ከሌለው ጋር ወደማያቋርጥ ንትርክና ጭቅጭቅ ውስጥ በመግባት ህዝባችን ዳግም ተጎጂ እንዳይሆን አርቆ በማሰብ የሲዳማ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ሲህዴድ/ የተፈጠረው አሻንጉሊት ድርጅት የህዝባችንን እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ካልተደፈረና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን አንጻራዊ በሆነ መልኩም ቢሆን በማስወገድ ህዝባችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር እስከተቻለ ድረስ በቀጥታና ቀጥተኛ ያልሆነ ድጋፍ በመስጠት ሚና ላይ ብቻ ማተኮር እንደሚያስፈልግ በመረዳት ከፖለቲካ ሽኩቻና ግጭት ገታ የማድረግ ፖለቲካዊ ታክቲክ መጠቀም ግድ ሆኖበት ነበር፡፡


በዚህ የተነሳ ሲአን በአነስተኛ ደረጃም ቢሆን ውስጥ ውስጡን ህዝቡን በማንቃትና የይስሙላ ምርጫ ተብዬው ወቅት ሲደርስ ህልውና እንዳለው በማሳየት በተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ብቅ እያለ ራሱን ከማስታወቅ የዘለለ የፖለቲካ ስራ ለመስራት የሚያስችል የፖለቲካ ምህዳር አላገኘም፡፡ ይሁን እንጂ ለሲህዴድ ከበቂ በላይ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ በመገኘት የህዝባችን የፖለቲካና የልማት ችግሮች እንዲወገዱለት ሳይታክት እንዲሰራ ተፅዕኖ ማሳደር በመቻሉ እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ በሲህዴድ አመራር ሰጪነት  በሲዳማ ዞን አስተዳደር ውስጥ በመንግስት መደበኛ በጀትና በአይሪሽ ልማት ፕሮግራም አማካኝነት በጤና፣ በትምህርት፣ መሰረተልማቶችና ሌሎች የልማት ስራዎች የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ህዝባችን በራሱ ምሁራን እየተመራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት አረንቋ ውስጥ መውጣት እንደሚችል ማሳያ የሆኑ ተስፋ ሰጭ የልማት ስራዎች ተጀምረው ነበር፡፡
የሲዳማ ልማት ማህበር፣ የሲዳማ አነስተኛ ብድር ተቋም፣ የሲዳማ ልማት ኮርፖሬሽን እና ፉራ የልማትና ጥናት ምርምር  ተቋም ጨምሮ አብዛኛውን የልማት ተቋማት  የተመሰረቱትና የህዝባችን የልማት ጥማትና ፍላጎት ለማነቃቃት፣ ብሎም  በማነሳሳት ገንቢ ሚና መጫወት የተቻለው በሲህዴድና በሲዳማ ዞን አስተዳደር የቅርብ ክትትልና አመራር ሰጭነት መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡


በርካታ የብሔሩ ወጣቶች በተከታታይ ወደ አውሮፓና አሜሪካ በመላክ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት የተከታተሉትና የልማት ደጀን ለመሆን የቻሉትም የሲዳማ ዞን አስተዳደር ሙሉ በሙሉ የአስተዳደር ስልጣን በእጁ በነበረበት ጊዜ ነበረ ለማለት ይቻላል፡፡


ይሁን እንጂ ሲህዴድን በተለያየ መንገድ በማባበልና በማግባባት ለህዝቡ ያለበትን ኃላፊነትና የፖለቲካ ስልጣን ደኢህዴን ለሚሰኘውና በአብዛኛው ፀረ-ሲዳማ አቋም ባላቸው መሰሪ ፖለቲከኛ ግለሰቦች ለሚመራው ድርጅት እራሱን ገፀ-በረከት አድርጎ እንዲያቀርብ በማድረግ የሲዳማን ህዝብ የማንነትና የፖለቲካ ጥያቄ ወደሚያፍኑት መሰሪዎች አሳልፎ ተሰጠ፡፡


ኤሳው ለምግብ ብኩርናውን አሳልፎ ለታናሹ እንደሰጠ ሁሉ ሲህዴድ የሲዳማን ማንነትና ህልውና አሳልፎ የሰጠ በመሆኑ እስከዛሬ ድረስ በሕዝባችን ላይ የደረሱት ጥቃቶች፣ ሕዝባዊ ጭፍጨፋዎች፣ የልማት ወደ ኋላ መቅረት ምክንያት በመሆናቸው በታሪክ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡


በሲህዴድ አመራር ወቅት የተከናወኑ አበረታች የልማት እንቅስቃሴዎች 
1. የሲዳማ ዞን መስተዳድርና ሲህዴድ የአመራርና የፖለቲካ ስልጣን በእጃቸው በነበረበት ወቅት በርካታ የልማት ስራዎች እንደተጀመሩ ከላይ ተገልጿል፡፡ ከተጀመሩ የልማት ስራዎች መካከል በተለይም የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ግንባታና በየወረዳውና በየቀበሌው የተስፋፋው መደበኛ ያልሆኑ የት/ ተቋማት፤ በውጭና በሃገር ውስጥ በርካታ የሲዳማ ልጆች የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ እንዲወስዱ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች፣
2. ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ የቦና ሆስፒታል ግንባታ፣
3. በሰው ጉልበት የሚሰሩ በርካታ ወረዳዎችን የሚያገናኙ መንገዶች፣
4. የሲዳማ ልማት ኮርፖሬሽን፣ የሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስ፣ በይርጋለም የሚገኘው ፉራ የልማትና ጥናት ምርምር ተቋም፣ የሐዋሳ መሐል ከተማ ጉዱማሌ የገበያ ማዕከላት መመስረትና መገንባት፣
5. የሲዳማ አስተዳደር አባላትና የልማት መስሪያ ቤት ተወካዮች በአፍሪካ፣ በኤዥያ፣ በአውሮፓና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በአካደሚክ ትምህርትና  በመስክ የስራ ልምድ ጉብኝቶች ሁሉ ለሲዳማ ሕዝብ ልማትና የእድገት ጥማት ምላሽ የሰጡና ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች በዚያው ፍጥነት ቢቀጥሉ ኖሮ ዛሬ የሲዳማ ዞን የት ሊኖር እንደሚችል መገመትም አያዳግትም፡፡ 


እነዚህና በዝርዝር ያልቀረቡ የልማት ስራዎች የተሰሩት በዋናነት የሲዳማ ዞን መስተዳድር ከአየርላንድ መንግስት ባገኘው የልማት ቀጥተኛ ድጋፍ ሲሆን የመንግሥት ድጎማም እንዳለበት ይታወቃል፡፡
ሲህዴድ ከከሰመ በኋላ በሲዳማ ላይ የተፈጸሙ አሉታዊ ተፅዕኖዎች


የደኢህዴን መሰሪ አመራር የድርጅታቸው ዋናው ዓላማና ግብ የሲዳማን ህዝብ መብት መግፈፍና ማዋረድ እስከሚመስል ድረስ ህዝባችንን የበደሉ፣ ያዋረዱ፣ ወደ ኋልዮሽ እንድያድግ ያደረጉና ለዚህም አሁንም ድረስ እየተጉ ያሉ ስለሆነና ያደረሱብን በደል እንዲህ በቀላሉ ተገልጾ የማያልቅ ቢሆንም ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ አኳር አንኳሩን እንደሚከተለው ገልጸናል፡፡
1. ሲህዴድ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ ለደኢህዴን ባስረከበበት ማግስት የደኢህዴን አመራር የመጀመሪያና ፈጣን እርምጃ የነበረው የአይሪሽ መንግስት በሲዳማ መስተዳድር የሚያደርገውን የልማት ድጋፍ እንዲያቋርጥ ማድረግ ነበርና የአይሪሽን መንግስት እርዳታ በተለያየ መንገድ በማዋከብ እርዳታውን ምንም ዓይነት የመውጫ ዕቅድ /Phase out Strategy/ ለማዘጋጀት ዕድልና ጊዜ እንኳን ሳይሰጡት በፍጥነት እርዳታው እንዲቋረጥ ተደረገ፡፡ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ባሉበት ቆሙ፡፡ የልማት ድጋፍ በማስቆም ላይ ብቻ አላቆሙም፡፡ በመቀጠልም የልማት ቀናዕ የሆኑ የብሔሩ የልማት ቀያሾችና መሪ ተዋናዮች የሆኑትን በተለያዩ ሰንካላ ምክንያቶች የስም ማጥፋት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ከሃገር እንዲሰደዱ ማድረግ ነበርና እነሆ ይህንን መሰሪ ተንኮል በወራት ጊዜ ውስጥ አሳኩት፡፡ የአየርላንድ መንግስት ድጋፍ ያለ ቅድመ-ሁኔታ ሲቆም የልማት ስራዎችም ባሉበት ቆሙ፡፡ የሲዳማ ልማት አርበኞችም ከፍሎቹ ወደ ውጭ ተሰደዱ፡፡
2. ለሲዳማ ህዝብ የልማት ስራዎችን በዘላቂነት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ያግዛሉ ተብለው የተደራጁት የልማት ተቋማት በተለይም የሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስና ሲዳማ ልማት ኮርፖሬሽንን ለማፍረስ ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም፡፡ ብዙም አንገጫገጩት፡፡ ዛሬ ግን ለህዝብ ልማት ደጋፊ ሳይሆን የደኢህዴን ታማኝ ካድሬዎች እየተፈራረቁ የግል ህይወታቸውን የሚገነቡበት አንጡራ ሃብታቸው እንጂ የሕዝብ ንብረቶች አይደሉም፡፡ ጠያቂ የሌለባቸው ነፃ የግል ኑሮ መገንቢያ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች ሆነዋል፡፡ የተለያዩ ወንጀሎችን ሰርተው ነገር ግን ለስርዓቱ/ለደኢህዴን አስፈላጊ የሆኑ ግለሰቦች ጊዜያዊ ማገገሚያ፣ መደበቂያና መሸሸጊያም ጭምር ሆነዋል፡፡ 
3. የሲዳማ ልማት ማህበር በኢትዮጵያ ካሉ ግንባር ቀደም ማህበራት አንዱ ሲሆን የሕዝብ ልማት አጋርነቱን በተግባር ማሳየት የቻለው የሲዳማ ዞን መስተዳድር ሙሉ በሙሉ ከአስተዳደርና ፖለቲካ ስልጣን እስካልወጣበት ጊዜ ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ሲህዴድ ማንነቱን አሳልፎ እንደሸጠ ደኢህዴን የወሰደው አፋጣኝ እርምጃ የሲዳማ ልማት ማህበር ያለውን ገንዘብ ወደ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ እንዲያዛውር ማስገደድ ነበር፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በብድር ስም የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ወስዶ ነገደበት፡፡ ማህበሩ ግን የበይ ተመልካች እንዲሆን ተፈረደበት፡፡ በዝቅተኛ ደረጃም ቢሆን የሚያገኛቸው ገቢዎች በማህበሩ እየተደጎሙ ማህበራዊ ችግራቸውን  እንዲቋቋሙ የተመደቡ ሠራተኞች መጧሪያነት የሚዘል አቅም እንዳይኖረው መንገዶች ሁሉ ተዘግተውበታል፡፡ 
ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ሕዝቡ በቁጭት ማህበሩን መልሶ ለማቋቋም በመነሳሳት ከአርሶ አደር እስከ መንግስት ሠራተኛ የአንድ ወር ደመወዝ መዋጮ ድረስ ገንዘብ የተሰበሰበ ሲሆን ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ የልማት ስራ እንዲሰራ አልተፈቀደም፡፡ ሕዝቡ ያዋጣው በርካታ ሚሊዮን ብሮች በዝግ አካውንት በባንክ ተቀምጧልም ይባላል፡፡ ነገር ግን ሕዝባዊ ልማት ለማካሄድ የደኢህዴን መልካም ፈቃድ ይጠይቃልና እነሆ እስከ ዛሬ ስለዚህ ገንዘብ እንዲወራ አይፈለግም፡፡
4. እጅግ የሚያስቆጨውና የሚያሳዝነው ጉዳይ የሲዳማ ልማት ማህበር ቴሌቶን ለማዘጋጀት የሚያስችል አገር አቀፍ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ጥናታዊ ዝግጅት አጠናቅቆ የደኢህዴን መልካም ፈቃድ በመጥፋቱ የሲዳማ ልማት ጥናት ፕሮጀክት ሌሎች የታደሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ተጠቅመው ሃገር አቀፍ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን በማዘጋጀት ለህዝባቸው በጎ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሕዝባዊ የልማት አውታሮችን አጠናክረዋል፡፡
5. ከላይ የተጠቀሱት የሲዳማ ህዝባዊ ልማት ድርጅቶች እንዳይቀጥሉ በመግታት አላበቃም፡፡ በመቀጠል ደኢህዴን/ኢህአዴግ ያነጣጠረው የሐዋሳን ከተማ አስተዳደር ከሲዳማ እጅ የመቀማት ዕቅድ ነበር፡፡ ለዚህ መሰሪ ዓላማ መሳካት የተጠቀመው ታክቲክ በሲዳማ ዞንና በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር መዋዕቅር ውስጥ ያሉትን የብሔሩን አባላት ስም ማጥፋት፣ አሉባልታ መንዛት፣ የከተማ ልማት በሚል የተዘጋጁ ማደነጋገሪያ ሰነዶችን በማቅረብ የማምታታትና ሁከት የመፍጠር ስራ በስፋት ቀጠለበት፡፡ በመጨረሻም የሐዋሳን ከተማ አስተዳደር ታስረክባለህ አታስረክብም የሚል የመጨረሻ ጥያቄ በማቅረብ አስገደደ፡፡ ይህንን የተቃወሙ የሲዳማ አስተዳደር አመራር ስልጣናቸውን እንዲለቁና እንዲታሰሩ ተደረገ፡፡ ከላይ በእነሱ ሳምባ የሚተነፍሱ የይስሙላ (ፑፔት) ከንቲባ ከብሔሩ እየመደቡ በአጠቃላይ የከተማውን አስተዳደር ስልጣን ተቆጣጠሩት፡፡
በዚህ ጉዳይ የተቆጣው ህዝብ ከሁሉም የሲዳማ ዞን ወረዳዎች በራሱ ጊዜ በመሰብሰብ ሰላማዊ ጥያቄውን ለመንግስት ለማቅረብ ተሰብስቦ ወደ ሐዋሳ ተከማቸ፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ ጥያቄ በደብዳቤ አቀረበ፡፡ ሕዝቡን ቀርቦ ብሶቱን ከማነጋገር ይልቅ ሕዝባችንን የሚጨፈጭፍ የወታደር ኃይል ማከማቸት ተያያዘ፡፡ ሕዝቡም ለሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ በፅሁፍ ተጠይቆ ምላሽ ካልተሰጠና 48 ሰዓት ከሞላው ተቀባይነት እንዳገኘ ይቆጠራል በሚለው ህግ መሠረት ሕዝቡ የሳር፣ የዘንባባ ቅጠልና የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዞ ወደ መስቀል አደባባይ ሲተም የቴክኒክና ሞያ ተቋም አካባቢ ጭካኔና ጥላቻ በተሞላበት ሁኔታ በከባድ መሣሪያ በተደራጀ የመንግስት ታጣቂዎች ግንቦት 16/1994 ዓ.ም ከቀኑ 4፡00-4፡30 ባለው ጊዜ ብቻ 42 ፍትህ ጠያቂ የብሔሩን ልጆች ዘግናኝ በሆነ መልኩ ጨፈጨፉ፡፡ ከጭፍጨፋው በፊት የጭፍጨፋው ሁኔታ ሲመቻች የተጠራው የወታደሩ/የሠራዊቱ የበላይ አመራሮች “ህዝቡ የተሰበሰበበት ድረስ ሰው በጥበብ ልከን አጣርተናል፡፡ ህዝቡ ሰላማዊ ነው፡፡ በእጁም የያዘው ቅጠልና የኢትዮጵያን ባንዲራ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄንን ህዝብ መምታት አንችልም፡፡ በሌላ ዘዴ ለማቀዝቀዝ ቢሞከር ጥሩ ነው …” ብለው ሲሉ በአቶ ኃይለማሪያም ደሣለኝ የሚመራው አስጨፍጫፊ ቡድን ግን “አይደለም ህዝቡ ህዝባችንን ሊፈጅ ነው፡፡ በቂ መረጃ አለን፡፡ ተቃዋሚው ሰልፈኛ ከተማ ከገባ ህዝባችንን ይጨፈጨፋል…ስለዚህ ይመታ፡፡ ካልተመታ አይመለስም” በማለትና በጦሩም ውስጥ የነርሱን ዓላማ አስፈጻሚ የራሳቸውን ተወላጆች በመሰግሰግ ያን እልቂት ደገሱልን፡፡ በጣም የሚያሳዝነው አውቶማትክ መሳሪያ በጠላት ላይ እንደሚተኮስ በመርጨት ልጅ ከአዋቂ ሳይለይ መረፍረፋቸው ነው፡፡ አንድና ሁለት እንኳ ቢገድሉ ሊያስፈራሩ ነው ይባላል፡፡ ታድያ ይህ የመደብ ጠላት እንጂ ሊያረጋጋ የወጣ የራስ አመራርና መንግሥት ሊሆን ከቶ ይችላል ወይ? መልሱን ጤናማ አእምሮ ላለው ሰው ሁሉ እንተው፡፡ 
በደኢህዴን/ኢህአዴግ አመራር ሰጪነት የህዝቡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የከሰመና የተደመደመ መስሎአቸው ጮቤ ረገጡ፡፡ የከተማውን መሬት በስልጣን ላይ ላሉ ጎሳዎች ያለተቀናቃኝ ተከፋፈሉ፡፡ ድሮም ቢሆን የሲዳማ መሬት እንጂ ሕዝቡን መች ይወዱና! ከ1994-1997 ዓ.ም ድረስ የሲዳማ ብሔር አባላት በሐዋሳ ከተማ ምንም ሚና እንዳይኖራቸው ተደረገ፡፡
ከ1994 ዓ.ም-1998 ዓ.ም ደኢህዴን ምን ሰራ?
1. ከሲዳማ አስተዳደር እጅ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደርን ለመንጠቅ ይቀርቡ ከነበሩ ምክንያቶች  መካከል- የአስተዳደር ብልሹነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ አድሎአዊ አሰራርና ወዘተ ነበሩ፡፡ ግን ከላይ በተጠቀሱት ዓመታት ደኢህዴን/ኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛውን ስልጣን የተቆጣጠሩ ግለሰቦች ምን ሰሩ? ማንን ጠቀሙ? ማንንስ ጎዱ? የሚያላዝኑለትን ፍትሐዊነትን አሰፈኑ ወይ? መልሱ ምንም የልማት ተግባር አላከናወኑም ነው፡፡ እንዲያውም በከተማው ዋና ዋና መንገዶች ዳርና ዳር በሙሉ ለባለስልጣናት ብሔር አባላት በጥቃቅን ንግድ ስም የጉልት ገበያ አድርገውት አለፉ እንጂ፡፡ እነዚህን የከተማውን ውበት ያበላሸውን አሰራር መስመር ለማስያዝ ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት መሆኑ ሊረሳ አይችልም፡፡
2. የአንድ አስፋልት ሥራ ተጀምሮ 3 ኣመት ለሚሆን ጊዜ ከ20 እና 30 በላይ መተግበር ተስኗቸው ቆይተው በኋላም የከተማው አመራር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ወደ ሲዳማ አመራር ከተቀየረ በኋላ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተጀመረው አስፋልት አልቆ በቀጣይነትም ዛሬ ውቧ ከተማችን ብለው የአዞ እምባ የሚያነቡለት ስም እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ እነርሱማ የክልል የተለያዩ የመንግሥት መ/ቤት ጽ/ቤት ቢሮዎች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ቢሠሩ ለከተማው ውበትና እድገት የበኩላቸውን እንደሚጫወቱ ስለገባቸውና ይህም እንዲሆን ዓላማቸው ስላይደለ ሁሉንም ቢሮዎች ማለት በሚቻል መልኩ አንድ ግቢ ውስጥ አደራሾችና ጉረኖዎችን በመሥራት አጎሯቸው፡፡ ዛሬ አደገ ተብሎ የሚነገርለት የባህር ዳር ከተማ አንዱና ዋናው የውበቱ ምንጭ የክልሉ መንግሥት ቢሮዎች ናቸው፡፡ ባለቤት ያለው ከተማ አይደል፡፡
የደኢህዴን በደል በሞላበት ከ1994-1997 ባለው አስተዳደር ላይ የሲዳማ ህዝብ የወሰደው እርምጃ
1. የሲዳማ ህዝብ ህገ መንግስታዊ መብት የተከለከለ መሆኑ
የሲዳማ ህዝብ በደኢህዴን አመራር ተብየዎች ከላይ በዝርዝር የቀረቡና በሲህዴድ መክሰም የተጀመሩ የልማት ስራዎች ጨርሰው እንዲቆሙ በማድረጋቸው መልካም አስተዳደር በመጥፋቱ በሀዋሳ ከተማ የሲዳማ ህዝብ የበይ ተመልካች ከመሆኑ በላይ በተለያየ መንገድ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና እንዲበዛበት በክልሉ ባለሥልጣናት የሚደረግበት ግፍ በጥናት ከተረጋገጠ በኋላ የሲዳማ ህዝብ እርምጃ ለመውሰድ ወሰነ፡፡ በመሆኑም የሲዳማ ህዝብ በኢትዮጵያ ህገ መንግሰት አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ እንደተደነገገው ˝ በክልሎች ውስጥ የተካተቱ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈለጉበት ጊዜ የራሳቸውን መንግስት ወይም ክልል ማቋቋም ይችላሉ˝ የሚለውን መነሻ በማድረግ እራሱን በራሱ ለማስተዳደር የሚያስችለውን የክልል ጥያቄ በ1998 ዓ/ም አቅርቦ በሲዳማ ዞን ምክር ቤትና በክልሉ ምክር ቤት ፀድቋል፡፡ ይሁን እንጂ እስከ ዛሬ ድረስ ህገ መንግስትን በጣሰ መልኩ ምላሽ ሳይሰጥ ታፍኖ ቆይቷል፡፡ ይህ የሚያመለከተው መንግስት በራሱ ጊዜ የሚመራበትን ከህጎች ሁሉ በላይ የሆነውን ህገ መንግስት መጣሱን ነው፡፡ በሌላ በኩል ለህዝብ ህጌ መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ደንታ ቢስ መሆኑን ነው፡፡  


ደኢህዴን በአሁን ጊዜ ምን እየሠራ ነው?


1. በ1998 ዓ/ም የተላለፈውን የክልል ጥያቄ ተከትሎ በተፈጠረው መልካም ሁኔታ የተነሳ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ለሲዳማ የተመለሰ ቢመስልም እጃቸው ረጅም የሆኑ የደኢህዴን አመራሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከተማዋን ሲዳማ እንዳያስተዳር ጫና ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡ በአሁን ጊዜ እንኳ የደኢህዴን አመራር የሆነው አቶ አለማየሁ የማይደውልበትና በስልክ ትእዛዝ የማይሰጥበት ጉዳይ የከተማው አመራሮች የሚበሉትን የምግብ ዓይነት ለመወሰን ብቻ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ተጠሪነቱ ለክልሉ መንግሥት መሆኑ ለዚህ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸው ቆይቷል፡፡ የክልሉ “ፕረዝደንትም” ለይስሙላ ይቀመጥ እንጅ “ከእኔ በቀር ሰው የለንም…” ለሚለው አባባሉ እንዲመቸው ሊወጡ ያሉ የሲዳማ ልጆችና አመራሮችን ማስወገድ ዋና ሥራው አድርጎ ስለቆየ ብቻውን ያለ በመሆኑና መሰሪዎቹም አጋራቸው ያደረጉትም ይሄንን ባህሪያቸውን ወዶላቸው ስለሆነ የኋላ ኋላ ብቻውን መሆኑን ስላወቁ አዋረዱት፡፡ የማስፈጸም አቅምም አጣ፡፡ ይህን ካመቻቹ በኋላ ነው እንዳሻቸው ማሽከርከር የተያያዙት፡፡ ማን ተው ሊላቸው፡፡ ታድያ ዛሬ ደኢህዴኖችና ተላላኪዎቻቸው (እነ ሳሙኤል ሼባ) “ፕረዝደንቱን” ቢሰድቡ፣ ህዝቡን ቢሰድቡ ምን ይደንቃል፡፡   
2. የሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስ ከኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር እንዲቀላቀል ያልተደረገ ሙከራ የለም፡፡ ምክንያታቸው ውጤታማ አይደለም የሚል ሲሆን እውነታው ግን ተቃራኒ ነው፡፡ የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ካበደረው ውስጥ ሲዳማ ያስመለሰው 83 ሲሆን ወላይታ 20፣ አርባምንጭ 17፣ ሆሳዕና 20 ነው፡፡ ሆኖም ግን የተኮነነው ሲዳማ ዞን ነው፡፡
3. ሙስናን በመዋጋት ሰበብ የሲዳማን የአመራር አካላት ብቻ በመሰብሰብና እሥር ቤት በማጎር ከተማውን ሲያምሱና ህዝቡ ላይ ሁከት ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡ የእገሌ ብሄረሰብ መንደር/ቀበሌ ወዘተ እስኪባል ድረስ መሬት የቸረቸሩና አሁንም ወገኖቻቸውን ብቻ በመለየት ሲጠቃቀሙ ያሉ ኪራይ ሰብሳቢዎች ግን ምንም አልተጠየቁም፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን በወከባው ወቅት ሆን ብለው በደቡብ ኤፍ ኤም ራድዮ ህዝባችንን አፍ አውጥተው እየሰደቡና እያሰደቡ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡     


የ2004 የደኢህዴን /ኢህአዴግ ድብቅ አጀንዳ ካባ
ሜትሮፖሊታን ከተማችንን እንዴት እንምራው?
1. ደኢህዴን /ኢህአደግ ለካድሬዎቹ ሰሞኑን ለውይይት አቅርቦት የነበረው አደናጋሪ ሰነድ ሲፈተሸ:-
˝የሜትሮፖሊታን ከተማችን የአመራር ጥያቄ ቁልፍና ዋና ዓለማ በሽግግሩ ወቅት ብቃት ያለው ምደባ ተካሂዶ በከተማው የተጀመረው የኪራይ ስብሳቢነት አረንቋን ከምንጩ ለማድረቅ˝ እንደሆነ ያብራራል ፡፡ ይህን አረፍተ ነገር በዝርዝር በመፈተሸ የጋራ ግንዛቤ ለመጨበጥ እንሞክር፡፡
ሜትሮፖሊታን ማለት ምንድነው ነው?.ሜትሮፖሊታን ማለት ምንም ማለት አይደለም፡፡ ከተሞች ካሏቸው የህዝብ ቁጥር አንፃር እና በአንድ እስኮዌር ኪሎ ማይል የሚይዙት የህዝብ ብዛት መሠረት የሚሠጣቸው ስያሜ አንዱ ነው፡፡ እስከአሁን ባለው ሁኔታ በዓለም ላይ እስከ 6 ደረጃ የደረሰ አሰያየም አላቸው፡፡
ሀ. የህዝብ ብዛት 2500≤50,000
ለ. የህዝብ ብዛት ≥50,000
ሐ. ሜትሮፖሊታን ከ≥50,000 ሆኖ በአካባቢ ሌሎች ድንበርተኛ ከተሞች ኖሮት በማዕከላዊነት ለማስተዳደር እንዲያስችል የሚዋቀር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ50,000 በላይ የህዝብ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያ ከተሞች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ታዲያ ለምንድነው በሀዋሳ ላይ ልዩ ትኩረት ተስጥቶ ሜትሮፖሊታን ከተማችን የሚባለው? ለምን ሌሎች ከተሞች እንደዚህ አልተባሉም?
በሌላ አንጻር፡- 
ሜትሮፖሊታን የሚባለው ከተማ በመንግስት ደረጃ ሌሎች ከተሞች ከሚሠሩት የተለየና መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚፈለግ ተግባር ሲኖር ነው፡፡ ታዲያ የሀዋሳ ከተማ ከባህር ዳር፣ ከአዳማ፣ ከመቀሌ፣ ከሀረር ከተሞች እጅግ ልዩ የሆነ ተግባር የሚያሥተናግደው ምንድነው? ከማንኛውም እድገት  ላይ ካሉ ከኢትዮጵያ ከተሞች የተለየ ሥራ የላትም፡፡ ስለዚህ ከሌሎች ከተሞች ልዩ ተደርጋ የምትታይበትና ደኢህዴን ደርሶ ተቆርቋር የሚሆንበት በቂ ምክንያት የለም፡፡ "ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ይሏታል" ነው ነገሩ፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው ሜትሮፖሊታን መሰኘት ያስፈለገበት ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋትና ለማድረቅ በሁሉም ብሔር የተዋቀረ ተዋጊ ሀይል ለማደራጀት እንደሆነ ይናገራል፡፡ 
2. ለመሆኑ ደኢህዴን የምር ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋትና የማድረቅ ፍላጎት አለው ወይስ በሙስና ስም አንድን ብሔር ተወላጆችን ለይቶ ማጥፋት? ኪራይ ሰብሳቢዎችስ ማዕከል የት ነው? እስከ አሁን በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ የተወሰዱ ተጨባጭ እርምጃዎች ምንድናቸው?
ምናልባትም የሀዋሳ ከተማ ባለስልጣናትን የሲዳማ ብሔር ተወላጆችን ለይቶ ማሰሩ ይሆን? እንዲህ ማለታችን ያጠፋ አይጠየቅ ማለት ሳይሆን ለምን ኪራይ ሰብሳቢነት እንዋጋ እያሉ ዲስኩር ከሚነፉልን ከሲዳማ ጠላቶች ከሆኑት ከደቡብ ተወላጅ ከፍተኛ ባለስልጣነት አልጀመረም፡፡ ሳይገባን ቀርቶ አይደለም የህዝብን ደም የመጠጠ ባለስልጣን ሆኖ ሀዋሳ ከተማን ከሲዳማ እጅ ፈልቅቆ ለማውጣት ሲዳማን የሚያፈንቅልላቸቸው ከሆነ ከሙስና የፀዳ የስርአቱ አርበኛ ተደርጎ መቆጠሩ አይደንቅም፡፡ በአጠቃላይ ለደኢህዴን ሙስናን መዋጋት ማለት በወረዳ ህዝብን የበዘበዘ የህዝብ ጩሄት ሲበዛ በዞን ላይ መሾም፤ የዞኑን በክልል፤ የክልሉን ወደ ፈዴራል አዛውሮ መሾም መሆኑ ከማንም ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አይደለም፡፡ በዚህ አይነት ከደቡብ ዞኖች ወደ ክልልና  ወደ ፈዴራል ተሸጋሽገው  ለስልጣን ሽልማት የበቁት ባለስልጣናትና ለሹመት ሽልማት ያበቃቸውን ስራ ለግንዘቤ እንዲረዳ ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
2.1 የደኢህዴን መጨረሻ ስልጣን ደረጃ ላይ የተቀመጡ በአሁኑ ጊዜ በፌዴራል የተሾሙ ባለስልጣናት በልዩ ትዕዛዝ ከሊዝ ደንብና መመሪያ ውጪ ለራሳቸው 425 ካ/ሜ በተጨማሪ ማስፋፊያ ሳይጠይቁ 250 ካ/ሜ ጨምረው በህገ ወጥ መንገድ የያዙት መሬት ከሙስና የጸዳ ይባል ይሆን?  
2.2 እኚው ባለስልጣን ለጓደኞቹና ለብሔሩ ተወላጆች በተመሳሳይ ትዕዛዝና መንገድ ለኢንቨስትመንት የተሸነሸነውን መሬት ወደ መኖሪያ ቦታነት አስቀይረው ለእያንዳንዳቸው 500 ካ/ሜ ያሰጡበትና የመሬት አገልግሎት አጠቃቀም እንዲዛባ ማድረጉ ምን ያስጠይቃል ጃል? ያሸልማል እንጂ፡፡
2.3 ለደቡብ ፖሊስ ባንድ መሣሪያ ግዥ ምክንያት 5000,000 ብር የተመዘበረና በተጨባጭ ተደርሶበት ክስ ተጀምሮ ሳለ በልዩ ትዕዛዝ የታፈነ፤ ይባስ ብሎ ይህን ምዝበራ የፈፀመውን ኮሚሽነር መልሶ በመሾም ይህን አድራጎት የታገሉ የፖሊስ አባላት ብላቴ ተወስደው በእኚ ባለስልጣን በበቀል እንዲባረሩ መደረጉ ሽልማት ቢያሰጥ ለምን ይገርማል፡፡
2.4 ይህ ኮሚሽነር በዳቶ ኦዳሄ ቀበሌ አርሶ አደሮችን በማፈናቀል 1000 ካ/ሜ የግሉ በማድረግ ሽጦ በህገ ወጥ የበለፀገበት ሙስና ወይስ ድቁና ተደርጎ ታሰበላቸው?
2.5 በሀዋሳ ከተማ የተሰራ አስፋልት ስራ ሳይጠናቀቅ በልዩ ትዕዛዝ ክፍያ እንዲፈፀም ተደርጎ ቦዮቹ ሳይከደኑ በመቅረታቸው በተደጋጋሚ በሰውና በንብረት ላይ የሚደረስው አደጋ ያደረሱ የክልሉ ቁንጮ ባለስልጣናት እንደ ወንጀል አይቆጠር ይሆን፡፡  
2.6  የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ባለስልጣን የነበሩትና የፈዴራል መንግስት ቁንጮ ባለስልጠን የሆኑት ከሀዋሳ ከተማ በጉልበታቸው በህገ ወጥ መንገድ በአስፋልት መንገድ ላይ የወሰዱትን መሬት 1.5 ሚሊዮን ብር ሽጠው ያካበቱት ገንዘብ ወንጀል ሳይሆን ወደ ፈዴራል ሲዛወሩ ለሽኝት የተሰጣቸው ገጸበረከት ይሆንን? 
2.7 አንዳንድ የደኢህዴን ቁንጮ ባለስልጣናት የህዝብን ሀብት በዝብዘው በቤተሰቦቻቸውና በጥገኛ ባለሀብት ስም ያፈሩት ሀብት በፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲደረስባቸው ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሀዋሳ ከተማን ከብሔሩ ለማስነጠቅ መስማማታቸው ደኢህዴን ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ያቋቋመው ለምን ኣላማ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጢር እንዲሆን አድረጎታል፡፡   እንዲህ ነው ኪራይ ሰብሳቢነትን/ሙስናን መዋጋት!!! 
2.8 የክልሉ ቤቶች ልማት እንተርፕራይዝ ከሚያጠናቅቃቸው መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 25% ወይም 104 ቤቶች ለሲዳማ ዞን ያለቅድመ ሁኔታ ከተሰጣቸው ቤቶች ውስጥ 49 ቤቶችን በሚስጢር በሲዳማ ስም የተከፋፈሉና በአሁኑ ወቅት ሚስጢሩ ታውቆ በመተረማመስ ያለው ጉዳይ የእነ ማን ተግባር ነው? እነዚህንና ሌሎች መሰል ደባዎች ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ ያለበት አካል ማነው? 
2.9 ማንነታቸው በውል በማይታወቁ ሰዎች በ26 በማህበራት እንደተደራጁ በማስመሰል በተናጠልም በዘመድ አዝማዶቻቸው ስም በሀዋሳ ከተማ ባልተለመደ መልኩ የወላይታ ሰፈር፣ የካንባታ ሰፈር ወዘተ እየተባለ በህገ ወጥ መንገድ የተመዘበረ መሬት ምን ቆርጦት ወንጀል ይሆናል፡፡ በእነዚህ ማህበራት ስም 644 የቤት መስሪያ መሬት ወስደው ተቀራምተዋል፡፡ እንደ ዜጋ ማንም ኢትዮጵያዊ በግልም ሆነ በማህበር ተደራጅቶ የከተማ ቦታ መጠየቅና ማግኘት የዜግነት መብት አለው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ማህበራት ፋይል እንጂ የሰዎቹ ማንነት በግንባር ተፈልጎ አለመገኘታቸው ጉዳዩ ሙሰኛ ባለስልጣናት ረጅም እጅ ያለበት መሆኑን ልዩ የሚያደርገው ነው፡፡ ይህ ማለት በወቅቱ በግርግሩ የሚፈልጉትን ወገን ለመጥቀም ሲባልና የማህበሩ አባላት በግንባር መገኘት ሳያስፈልግ በአንድ ግለሰብ እና በባለስልጣናት አማካይነት ተቀነባብሮ የተዘረፈ መሬት ነው፡፡ ታዲያ ይህን የምዝበራ ወንጀል የፈፀሙትን ባለስልጣናት ማን ይጠይቃቸው? አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ ነውና፡፡
በማህበር ስም ከተቀራመተው ከከተማ መሬት ውጭ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቅርብ ዘመዶቻቸውን ከያሉበት ዞን በመጥራት እንደ እሳት አደጋ መከላከያ ስራ በዘመቻ መሬት በመከፋፈል የዚህ ብሔር ቀበሌ፣ የዚያ ብሔር መንደር እየተባለ ዛሬ በጥቂት ባለስልጣናት ብሔረሰቦች ስም የተሰየመው መንደሮች የተመሰረቱት በሲዳማ አስተዳደር ወቅት አይደለም፡፡ ታዲያ ሲዳማ ሲያስተዳድር እኮ በተቻለ መጠን የሁሉንም የደቡብ ብሔር አባላትን ብቻ ሳይሆን ማንንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በከተማው አስተናግዷል፡፡ የሲዳማ ብሔር አባላት ትንኝ የምታህል ጉድፍ በትልቁ ተጋንኖና ተባዝቶ ˝ ከቁንጫ ሌጦ እንደማውጣት˝ ያክል ተደርጎ ህዝቡ እንዲታወክ ይደረጋል፡፡ የእነሱ ምሰሶ የሚያክል ጥፋት በዓይናቸው ውስጥ ተደንቅሮ አይቆረቁራቸውም፡፡ እውነታውን ህዝብ የሚሰማበት መንገድ የለም፡፡ የደቡብ መገናኛ ብዙሀንም ቢሆን እውነቱን ፈልፍሎ ለህዝብ ከማቅረብ ይልቅ የባለስልጣናትን የውሽት ፕሮፖጋንዳ ከማናፈስ የዘለለ ስራ የለውምና፡፡ የደቡብ መገናኛ ብዙሀን የሚበረታው የሲዳማን ህዝብ ለመሳደብ በሚዘጋጅ ፕሮግራሞች ላይ ምላሳቸውን ማርዘም እንጂ ለእውነትና ለፍትህ በመቆም ሀቁን ቆፍሮ ለማውጣት የሙያ ስነምግባር የላቸውም፡፡ 


በዚህ አጋጣሚ ለእውነት የቆሙ ወገኖች ወይም የፍትህ አካላት ደኢህዴን አስተዳደሩን ከሲዳማ በመቀማት ባጭር ጊዜ በማደራጀት መሬት እንዲቀራመቱ የተደረጉ ማህበራት ስም የተጠቀሰ ስለሆነ የያንዳንዱ ማህበር አባላት ከተጠቀሰው ቁጥር አንፃር ሰዎቹን (አባላቱን) በግንባር ተቆጥሮ ማረጋገጥ ይቻል ይሆን? ከሌሉስ መሬት እንዴትና ለማን ተከፋፈለ? ይህ ወንጀል እንዲሰራ አመራር የሰጡ ባለስልጣናት እነማን ናቸው? ያስፈፀሙትስ?


ሠንጠረዥ 1. የሀዋሳን መረት ለመቀራመት ሽፋን የሆኑ አባላቱ በውል የማይታወቁ ማህበራት ዝርዝር
ተ.ቁ የማህበሩ ስም   የአባላት ብዛት
ተ.ቁ
የማህበሩ ስም
የአባላት ብዛት
1
ተስፋ የቤቶች ልማት
23
14
ጮራ ቤት ስራ ማህበር
25
2
ሰላም ባንኮች የቤቶች ልማት
21
15
ድርሻችን ቤት ስራ ማህበር
24
3
ጽዮን የቤቶች ልማት
24
16
ኤደን ቤት ስራ ማህበር
26
4
ስምጥ ሸለቆ ቤቶች ልማት
24
17
ወይራ ቤት ስራ ማህበር
23
5
ገጠር መንገደ አምባ
24
18
መብት ቤት ስራ ማህበር
22
6
ግርን ላንድ ቤቶች ልማት
32
19
ጥረት ቤት ስራ ማህበር
26
7
መብራት ኃይል ኅ/ሥራ
24
20
ዳሞት ቤት ስራ ማህበር
23
8
ቤታችን በቶች ልማት ኅ/ስራ
32
21
ምርምር አምባ ቤት ስራ/ማ
24
9
ንጋት ቤቶች ልማት ኅ/ስራ
24
22
እንደየአቅም ቤት ስራ/ማ
30
10
ብርሃን ቤት ስራ ማህበር
35
23
ግንቦት ሃያ ቤት ስ/ ማህበር
32
11
ጆሊ ቤት ስራ ማህበር
22
24
ዋልታ ቤት ስራ ማህበር
24
12
እውቀት ፋና ቤትስ/ማህበር
25
25
ፋና ቤት ስራ ማህበር
23
13
ትግል የቤት ልማት ማህበር
32


እጅግ የሚገርመው ነገር ቢኖር ከላይ ከተጠቀሱት ማህበራት ውስጥ አንድም የሲዳማ ብሔር እንዳይገባበት መንገዶች ሁሉ ዝግ መደረጉ ነው፡፡ ይህ በአጋጣሚ የሆነ ሳይሆን ሆን ተብሎ የተደረገ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ናቸው ወይ ስለ ህዝቦች አንድነትና እኩልነት የሚደሰኩሩት? ስለ መልካም አስተዳደር ተቆርቋሪ መስለው የፍትህና የልማት አርበኛ ሊሆኑ የሚቃጣቸው? ጅብ በማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል አሉ፡፡  


ሌላው የሀዋሳ ከተማ መሬት በደኢህዴን ካድሬዎች ተቀራምተው ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ አውሮጳ እና ሌሎች አገሮች መሄጃ የትራንስፖርት ገንዘብ እንዲያገኙ ሆን ተብሎ በተደራጀ መልኩ በአንድ ሌሊት በመቶዎች የሚቆጠር የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰርቶ ተስጥቶ ወዲያው በሚያሻሽጡ ደላሎች እየተቸበቸበ የብሔር አባላቶቻቸውን ብቻ ተጠቃሚ ያደረጉ እነማን ናቸው? ለምን የእነሱ ጉዳይ በደኢህዴን ባለስልጣናትና ካድሬዎች አጀንዳ ሆኖ ሲቀርብ አይሰማም? የሲዳማ ጉዳይ ሲሆን ግን ለምን ይንጫጫል? 
  
3. ከተማችንን ሀዋሳን ተፈላጊ ከሚያደርጓት በርካታ ምክንያቶች  መካከል ሊጠቀስ የሚገባ ነገር ግን ያልተጠቀሰ ቀዳሚ ጉዳይ የሲዳማ ህዝብ በከተማም ሆነ በገጠር እንግዳ ተቀባይ፣ ሰላማዊ ህዝብ፣ ማንኛውም የሰው ልጆችን የሚቀበል፣ ያለአድሎ አዋህዶና ተዋህዶ የሚያኖር፣ ወደ ውጭ የሚገፋ ሳይሆን የባህሉ የወጉ፣ የማህረጉ አባልና ባለመብት አድርጎ የሚቀበል መሆኑ፣ ከሰዎች ልጆች ጋር በቀላሉ የሚግባባና ቶሎ የሚዋሃድ መሆኑ፣ ደኢህዴን የተሰኘው በስውር ህዝባችንን በሁሉም የሚያጠቁ መሰሪ አመራሮችን ጭምር በትዕግስት ተቀብሎ የሚኖር ሆደ ሰፊ በመሆኑ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሀዋሳን ለመኖሪያና ለንግድ ማዕከልነት ይፈልጓታል፡፡ ዳሩ ግን ምን ያደርጋል ደኢህዴን የሚባል ድርጅት በጭራቅ አመራር የሚመራ ወቅት እየጠበቀ ያነታርከዋል (ያውከዋል) እንጂ፡፡ 


ደኢህዴን ህዝባችንን በሆነ ባልሆነው ሲያውክ፣ ሰላም ሲነሳና መብቱን ሲገፍ ዝም ማለታችን፣ በሙስና ሰበብ እውነታው እንኳ በወጉ ሳይጣራ ሲዳማ የሆነ ብቻ ተመርጦ ሲታሰር ዝም ማለታችን ፍርሃት ሆነብን? በህዝብ ራድዮ ሳይቀር ጠቅላላ ህዝብ ሲሰደብ ዝም ማለታችን አላዋቂነት ነው? ዝምታ በራሱ አይናገርም እንዴ? ቢያንስ ቢያንስ ነገር ያለመፈለጋችንን፣ ሰላም ናፋቂ መሆናችንን፣ ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር በሰላምና በመተሳሰብ ለመኖር ዋጋ ለመክፈል መወሰናችንን አይናገርም? የመቻቻል ባህላዊ መንፈሳችንን አይገልጽም? አዋቂ ለመባል እንደናንተ መሳደብና መናናቅ፣ ብሎም መዳፈር ሆነ? እኛ እንኳ ይህ አሁንም ይቅርብን፡፡ እናንተ ይመቻችሁ፡፡
ዋናው ጉዳይ ይሄ ቀምበር በህዝባችን ክንድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያበቃለታል፡፡ ደኢህዴንም ስሙ ይቀየራል፡፡ ለነገሩ እኛ ምን አገባን ሲዳማን ሳይጨምሩ ደኢህዴን ብለው ቢቀጥሉስ ምን አገባን፡፡ ቀድሞስ ቢሆን መች ወደን በአቅጣጫ ስም ተጠራንና፡፡
   
4. "በውድድር የሚያምንና ራሱን ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የፀዳ አመራር በባትሪ ፈልገን መመደብ፣መደገፍና መከታተል የወቅቱ ቁልፍ ጥያቄና አስፈላጊ ጉዳይ ነው" ይላል፡፡
ማንን ከማን ጋር ለማወዳደር ተፈልጎና ታስቦ ይሆን? የሲዳማን ብሔር ምሁራንን ከ1993 ዓ/ም ጀምሮ አስከ 1998 ዓ/ም ባለው ጊዜ ብቻ ድብቅ አጀንዳቸዉን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያመቻቸው የሀሰት ወሬና ፕሮፖጋንዳ በመንዛትና በማሳደድ አገር ለቀው እንዲበታተኑ አድርገው ሲያበቁ የቀሩትን በየእስር ቤት አጎሯቸው፡፡ ሌሎችን ያልሆነ ስም እየሰጡ ከልማት መስመር እንዲርቁ በማድረግ በየመንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ሄደው እንዲሰደዱ አደረጉ፡፡ ከዚህ በላይ ደኢህዴን ከሲዳማ የሰበሰባቸው አብዛኛዎቹ ሳይጠሩአቸው አቤት ሳይልኩአቸው ወዴት የሚሉ የህዝባችንን ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎት ያለበትን ደረጃ መገንዘብ የተሳናቸው ለጊዜያዊ ሆድና ምቾት ህሊናቸውን የሸጡትን ነው፡፡ በመጀመሪያ ለራሳቸው ህሊና ነጻነት የሌላቸው፣ ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ የሲዳማ ህዝብ ስም ያለበትን ካባ ደርበው የተኮለኮሉ አሻንጉሊቶች  መላውን የሲዳማን ህዝብ አንጡራ ሀብት ሲያዘረፉና ለልማቱ ሳይቆረቆሩ ተኝተው ከርመው  ዛሬ ደግሞ ብቃት የላችሁም ደካማ ናችሁ ችሎታ የላችሁም የተባሉ ናቸው፡፡
ከላይ በተጠቀሰው  ሁኔታ  የሲዳማ ህዝብ ሲተረማመስ የደኢህዴን ቁልፍ የአመራር ቦታ የተቆጣጠሩ የድል ማግስት አርበኞች የእራሳቸውን ብሔረሰብ አባላት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር በገፍ አስተምረው እራሳቸው ከራሳቸው ጋር የሚወዳደሩትን አዘጋጅተዋል፡፡ እውነተኛ ውድድር በለለበት “ብቃት” መለኪያ ባይኖረውም፡፡ በክልል ደረጃ ያላቸውን የማይደፈር ስልጣን በመጠቀም የሀዋሳን ከተማ መሬት በልዩ ትዕዛዝ እየተቀራመቱ የብሔራቸውን አባላት በኢኮኖሚ አጠናክረዋል፡፡ ታዲያ ዛሬ በተለያየ መንገድ በእቅድ የራሳቸውን  የተማረ ሀይል  አዘጋጅተው ሲያበቁ ለህዝብና ለፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን ለሆድ ጉዳይ ከተሰበሰቡት ጋር ማወዳደር ማለት አስቀድሞ ለተበላ እቁብ የማደናገሪያ አጃቢ መጠየቅ ነው ብለን እናምናለን፡፡


ሌላው ደግሞ "በባትሪ ፈልገን" የሚል አረፍተ ነገር ተሰንቅረው አገኘነው፡፡ እናንተ የክልሉ ወሳኝ ቦታ የተቆጣጠራችሁ አመራር አንድ ነገር እንጠይቃችሁ ማንን ለማጭበርበር ነው በሌሊት እንደ ሌባ በባትሪ የሚትፈልጉት? የተማረ ሰው ፍለጋ? ወይስ የራሳችሁን የግል ጉዳይ አስፈጻሚ? ሞኛችሁን ብሉ የሲደማን ህዝብ እርስ በርሱ እያዋጋችሁና እያናቆራችሁ ስትፈልጉም የመከላከያ ሀይል እያዘዛችሁ እያስጨፈጨፋችሁ ካልሆነም እያስፈራራችሁ እንኳንስ ለሀዋሳ ከተማ ለሀገሪቱ ሙሉ የሚበቃ የተማረ የሰው ሀይል እስትራቴጅ ነድፋችሁ ስታወድሙን እንደከረማችሁ የማይነቃ መስሎአችሁ ይሁን? 


የሚያሳዝነው ነገር ቢኖር የሲዳማ ህዝብ አለም ያወቀው የነጻነት ተጋድሎና ልምድ ያለው እንኳንስ የእናንተን ያገጠጠ ተንኮልና የፖሊቲካ ሽወዳ በተግባር እያየ ቀርቶ ገና ምን ሊመጣ እንደሚችል ሳይነገር ምን እንደታሰበ ሊረዳ የሚችልን ህዝብ ማንነታቸውን በመሸጥ የሚላላኩላችሁን ጥቂት ካድሬዎች አይን ማየታችሁ ነው፡፡


የደኢህዴን ጭፍን ግልቢያ የሀገሪቱን ህገ መንግስት በመናድ ላይ መሆናችሁን  ልብ ማለት አለመቻላችሁ  የፖለቲካ ብቃታችሁን ያስገምታል፡፡ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ እራሱን የማስተዳደር ያለቅድመ ሁኔታ የተረጋገጠለት መብት ነው፡፡ ደኢህዴኖች ማድረግ የሚቻላችሁ ከሆነ በመጀመሪያ የኢትዮጵያን ህገ መንግስት ከፈዴራላዊነት ወደ አሀዳዊነት አስለወጡ፡፡ እያንዳንዱ ብሔር እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ይነሳ፡፡ ከዚያ በኋላ የቋመጣችሁ አመራሮች ሀዋሳን ትቀራመታላችሁ፡፡


ለነገሩማ ደኢህዴን የሲዳማን ህዝብ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት ወደ ኋላ እንዲቀር ያልፈነቀለው ድንጋይ ባይኖርም በግል ጥረታቸውም ሆነ ግመልን በመርፌ ቀዳዳ እንደ ማሾለክ በሆነው ጠባብ እድል ሁሉ በመጠቀም በእልህና በቁጭት በመማር እንኳንስ ለሀዋሳ ከተማ በሀገር ደረጃም ብቁ ተወዳዳሪ ወጣቶች በብቃትና በጥራት እራሳቸውን ያዘጋጁ ወጣት ምሁራን በገፍ ደርሰውልናልና ምቀኞች ምስጋና ይጡ፡፡ ስለሆነም  የሲዳማን ህዝብ ስልጣን በመቀማት ለመቀራመት ያለማችሁት እንደማይሳካ አውቃችሁ የዘረጋችሁትን ረጅም እጅ እንድትሰበሰቡ እንመክራችኋለን፡፡ ሲዳማንና ሌሎች ከሲዳማ ጋር በሰላም በፍቅር የኖሩ ህዝቦችን አታወኩ፡፡
በጽሁፍ ውስጥ ሌላው የተገለጸው "ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት ካልተቻለ የህብረተሰብ መበስበስ/Societal decay/እንፈጥራለን " ይላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ እውነታ ላይ መስማማት ያስፈልጋል፡፡ በማንኛውም ፖሊቲካ ስርአት ውስጥ መጀመሪያ የሚበሰብሰው ህብረተስብ ሳይሆን የፖለቲካ ስርአቱ ነው፡፡ የፖሊቲካ ስርአቱ በሰበሰ የሚባለው ከህዝብ የተረከበውን የፖለቲካ ስልጣን የስርአት መሪዎችና አባላቱ የግል መጠቀሚያ በማድረግ ህብረተሰቡን ማገልገል ሲያቅታቸው ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የበሰበሰው ህዝብ ሳይሆን አመራሩ መሆኑን ለግንዘቤ እንዲረዳ በገጽ 5 ላይ ተጨባጭ ማስረጃ በማቅረብ አብራርተናል ፡፡ ህዝባችንንማ በኤፍ ኤም ራድዮ እስከሚበቃችሁ ድረስ ሰድባችሁታል፡፡ አሁን ግን ይብቃችሁ አትስደቡት፡፡ ህዝቡ አልበሰበሰም፡፡ አይበሰብስምም፡፡ የድንቅ ባህል ባለቤት ነው፡፡ ሰማችሁ ወይ (‹አፊኒ›) ሳይል/ሳይመክር ተቻኩሎ ስህተት ውስጥ አይገባም፡፡ ክራይ ሰብሳቢነት የህዝባችን ችግር አይደለም፡፡ የእናንተው እንጂ፡፡
በሰነዳችሁ ገጽ አራት ላይ ˝አብዮታዊና እድገት ገቺ /Opening up/አመለካት አስፈላጊነት˝ ያወሳል፡፡ ለዚህ አርአያ ነው በማለት የቻይናን ተሞክሮ ያቀርባል፡፡ በእርግጥ የቻይና ኢኮኖሚ እድገት ለታዳጊ አገሮች አርአያነት ያለው ነው፡፡ ይህንን ተሞክሮ ሀዋሳ ከተማ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ተመኝታችኋል፡፡ ምኞት አይከለከልም ነገር ግን ለቻይና እድገት ሁለት ወሳኝና መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ደኢህዴን በተግባር ኮፒ ለማድረግ ለምን አልደፈረም?
ቻይናን  ለእድገት ያበቁት ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን እንጠቁማችሁ፡- 
1. በኪራይ ሰብሳቢነት/ሙስና/ ላይ የማያዳግም እርምጃ ትወስዳለች፡፡ በተጨባጭ በቅርብ ጊዜ የወሰደችውን እርምጃ እንመለከት፡-
በእናት ሀገርና በህዝብ ፍቅር በታነጹ መሪዎች ቁርጠኝነት የፖሊስ ኮሚሽነሩን ጨምሮ የከተማዋ ከንቲባና ሰባት ከፍተኛ መኮንኖችን በኪራይ ሰብሳቢነት በስቅላት ቀጥታለች
በአሁኑ ሰዓት ከአንድ መቶ በላይ የመንግስት ባለስልጣናት ተይዘው በምርመራ ላይ ይገኛሉ፡፡
በርግጥ በአቋራጭ መበልፀግና ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት የልማት ስሜት ገዳይና አውዳሚ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እኛ እያልን ያለነው ከአመለካከት በላይ ተራምዳችሁ በተጨባጭ ኪራይ የሰበሰቡ፣ የህዝብን ሀብት የተቀራመቱ፣ የህዝባችን ፖለቲካ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትና እድገት ማነቆ በሆኑት ላይ  ትክክለኛ እርምጃ በመውሰድ ተአማኒነታችሁን አሳዩን ነው፡፡ 


የደኢህዴን አመራር ግን በማስ ሚዲያና በወረቀት ላይ ከመደንፋት ባለፈ ከፍተኛ የንቅናቀው አመራር አባላት የአደባባይ ሚስጥር የሆነው ኪራይ ሰብሳቢነት/ሙስና / ተግባር በፈፀሙት የፈደራልና ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ለምን እንደቻይና የእርምት እርምጃ አልወሰዳችሁም? ይህን ተሞክሮ ኮፒ ማድረግ ያስፈራል አይደለ? አዎን ያስፈራል፡፡ 
2. በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር በትምህርት ወይም በስራ ጉዳይ የወጡ ዜጎችዋና እንዲሁ እስከታችኛው አርሶ አድር ድረስ ማንኛውም ለሀገር የሚጠቅም ሀሳብ መሬት ላይ አይወድቅባትም፡፡ ቻይና፡፡ ሀሳቦች ሁሉ ወደ አንድ ማዕከል ተሰባስቦ በከፍተኛ ባለሙያዎች እየተገመገሙ ደረጃ በደረጃ ወደ ተግባር ይገባል፡፡ ደኢህዴን ግን የተማረ ይሁን ያልተማረ ተጽፎ ከሚቀርብላቸው ሰነድ ውጪ የህዝብን የልማት  ሀሳብ አይሰማም፡፡ የተማሩ ሰዎቸ ልማት ተሳትፎ የሚያደርጉበት አሠራር የላቸውም፡፡ ስትፈልጉ የአንዱን ብሔር ነጥላችሁ በማጥቃት ባለሙያዎች ከሙያቸው ጋር እንዲሰደዱ ታደርጋላችሁ፡፡ ስለዚህ ከቻይና ተሞክሮ የሚወሰድ ከሆነ ስሙን ብቻ ሳይሆን ተግባሩን መዋስ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው እናንተ እንደጠቀሳችሁ ቻይና 70% የውጭ ባለሀብቶችን አስገብታለች፡፡ ሀዋሳም በሲዳማ ህዝብ አስተዳደር ስር ሆኖ ከ90% በላይ የብሔሩ አባላት ያልሆኑ ዜጎች ኢንቨስት ያደረጉባትና ከህዝባችንና ከአመራሩ ጋር በፍቅርና በሰላም የሚኖሩባት ከተማ ናት፡፡ ታዲያ እናንተ ከዚህ የተሻለ ምን ልታደርጉ አቀዳችሁ? ወይስ ከ90% ውስጥ ከላይ እንደዘረዘርነው ማህበሮቻችሁ 70% የእናንተ ጎሳ አባላት ብቻ እንዲሆኑ ፈለጋችሁ? የሲዳማን ህዝብ ከከተማውና ከአካባቢው በማባረር የራሳችሁን መዋቅር ለመተካት? የሲዳማ ብሔር የሀገሬ ጅብ ይብላኝ የሚል እምነት የሌለው መሆኑን እስከ ዛሬ አለመረዳታችሁ ይገርማል ፡፡ የሲዳማ ህዝብ በታሪኩ ከራሱ ልጅ ይልቅ ሌላውን የሚያስቀድም ዛሬ ደኢህዴን የሚያስተምረው ሳይሆን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣና የተዋሃደ ባህል እንደሆነ መረዳት የማትፈልጉ ስለሆነ እንጂ በከተማም ሆነ በገጠር ይህ ሁኔታ እውነት ነው፡፡ በመሰሪ ደኢህዴን ጥቂት አመራር ምክንያት በርካታ የሚያስመርሩ ደባዎች ቢፈፀሙበትም የነበረውን  የሰው ልጅ የማክበር፣ የመቀበል ተስማምቶና ተዋህዶ የመኖር ባህላችን እንደማይቀዘቅዝ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፡፡ ይህንን የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች አባላትም ይመሰክሩልናል፡፡ ምንም እንኳ በከፍተኛ አመራሮች አእምሮ የሞላው ክፋትና ጥፋት ቢሆንም፡፡


በገጽ ስድስት ላይ የተቀመጠው እንዲህ የሚል ነው፡፡ ˝የተፈለገውን ተግባር ለመፈፀም የሚያስችል ብቃት ያለው አመራር አፈላልጎ መመደብ˝ ላይ የተቀመጡ ሶስት መስፈርቶች ሲፈተሹ፡፡


1ኛ. የብቃት ዋና መለኪያ ˝አብዮታዊ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አመለካከት˝ ነው ይላሉ፡፡ እነዚህ ጽንፀ ሀሳቦች ምንነትና ለኢኮኖሚ ልማት ያላቸው ፋይዳ ምን እንደሆነ ምንም ክርክር ሳያስፈልገው መስፈርቱ ምንም የትምህርት ብቃትና ዝግጅት ከግንዛቤ የማያስገባ፣ የሚለካበት ምንም መስፈርት የሌለው ግለሰቦች ለአመራሩ ካላቸው ቅርበትና አገልጋይነት ወይም ተላላኪነት አንጻር ብቻ የሚቆናጠጡበት መስፈርት ነው፡፡ ለብቃቱም ማረጋገጫ ሰነድ የሌለውና የማይቀርብለት በመሆኑ ይህች መስፈርት ለኪራይ ሰብሳቢ ደኢህዴን  አመራር ወገኖቸ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የተበላ እቁብ ነው ፡፡ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ የተከፈተ በር አይደለም፡፡ ምክንያቱም የአብዮታዊነት መለኪያ ቁና ይሁን ስልቻ የሚያወቁት እነርሱ ብቻ ናቸው፡፡ ልማታዊነት  የሚታወቀው በቁሳዊና ስነ ልቦናዊ የራሳቸው መለኪያና የአገላለጸ ሁኔታዎች አሉአቸው፡፡ ይህኛው ልማት በየትኛው መስፈርት እንደሚለካ የሚያውቁት ያው እነሱ ናቸው፡፡ ዴመክራሲ ደግሞ የህዝብ አስተዳደር ነው፡፡ ሌላው መሠረታዊ መርህ የህዝብና የግለሰቦች  ህገ መንግስታዊ ዋስትና መረጋገጥ ነው፡፡ ለእነርሱ ግን ዴሞክራሲ ህዝብን በመጨቆን፣ በመርገጥ፣ የህዝብን ሀሳብ በጉልበት በማፈንና በመግዛት የግል ህይወትን ማበልጸግና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ህገ-መንግስትን መናድ ነው፡፡ 


2ኛ. ሌላው መስፈርት ˝የአሰራር ጥበብና ክህሎት ብቃት˝ ነው፡፡ የሚገርመው ይህም ጥበብና ክህሎት ብቃት ማዕረግ የሚሰጠው ከደኢህዴን አመራር ነው ፡፡ እስከአሁን በታየው ተጨባጭ ሁኔታ ደኢህዴን ለአመራርነት የሚያመጡአቸው  ሰዎች ምንነትና ማንነት ስታይ አዎ ለደኢህዴን ፖለቲከኞች የአመራር ጥበብና ክህሎት ማለት የሲዳማን ህዝብ ከፖለቲካውና ኢኮኖሚ ጨወታ ውጭ ለማድረግ በክልል ደረጃ የሚወጠኑ መሰሪ እቅዶችን ምንም ሳያንገራግርና ለምን ሳይል ተግባራዊ ለማድረግ ተላላኪ መሆን ነው፡፡ ግደል ሲባል ይገድላል ቀማ ሲባል ይቀማል፡፡ ዋሽ ሲባል ይዋሻል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ ለእናንተ የአመራር ጥበብና ብቃት ማለት ፈረንጆች /Wagging dog/ የሚሉት ወይም ለሆዳቸው ብለው ጭራ እንደሚቆሉ ውሾች ያሉ ናቸው፡፡ይህች መስፈርትም ምንም የትምህርት ማስረጃና ልምድ የማይጠየቅበትና ለአመራሩ ውሳኔ ክፍት የሆነ ሁለተኛው የማጥመጃ ልዩ እድል ናት፡፡


3ኛ. ˝ለቦታው የሚመጥን አካዳሚና የመገንዘብ ችሎታ ብቃት ነው˝ ይላል ከላይ ለማየት እንደተሞከረው፡፡ በዚህ መስፈርት መሠረት ሲዳማን እንወክለዋለን ተብየዎቹ ማመለከቻ ሊያስገቡ ይችሉ ይሆናል፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል በመጀመሪያዎቹ ሁለቱ መስፈርቶች መሠረት 75% የተበላ እቁብ ላይ ለ25 % ውድድር ቀርቦ በዝረራ ተሸንፎ ይወጣታል እንጂ፡፡  


ሌላው በገጽ ሰባት ላይ የተገለጸው ˝ከቀበሌ ጀምሮ የህዝብ ደሞክራሲያዊ ተሳትፎና አስተዋጽኦ አስፈላጊነት ከሌሎች ልዩ የሚያደረገው መሆኑ˝ ተጠቅሷል፡፡ እዚህ ላይ ማለት የሚቻለው ጥቂት ተጨባጭ ነገር ብቻ ነው፡፡ አስከአሁን ባሳለፍናቸው ረጅም የአገዛዝ ዘመናችሁ የብሔሩን ታፔላ ለጥፈው ከተሰገሰጉት ሆድ አደር ካድሬዎቻችሁ ጋር በሚስጥር ስታቦኩ ከርማችሁ በህዝብ ላይ በጡንቻና በፍጥጫ በግዳጅ ለመጫን ከመንቀሳቀስ ውጭ መቼ ነው ከህዝብ ጋር ልብ ለልብ ተውያይታችሁ የጋራ ውሳኔ ላይ ሲደረስ የታየው? ጨርሶ የለም ፡፡ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ዴሞክራሲ የህዝብ አስተዳደርና ልዕልና መግለጫ ሆኖ ሳለ እናንተ ግን ህዝባዊ ተሳትፎ ልታረጋግጡ ቀርቶ የህዝብን ብሶትና ስሞታ እንኳ ለመስማት ያልታደላችሁ ናቸሁ፡፡ ያለፈው ታሪካችሁ የሚያረጋግጠው ይህንን እውነት ነው፡፡ ምናልባት እናንተ ህዝብ የምትሉት ህዝብ የሚጠላቸውንና እንትፍ ብሎ የተፋቸው ሆድ አደር የካድሬ መንጋ ከሆነ ያድርግላችሁ፡፡ እነሱም ቢሆኑ አብዛኞቹ የእናንተ ብልሹ አሠራርን እያወገዙ  የማምለጫ መንገድ በየስርቻው እያለሙ መሆኑን እያየን ነው፡፡ እስኪ እንጠይቃችሁ ለመሆኑ ካድሬ እራሳቸው በእኩል ይታያሉ ወይ? የሀዋሳ መሬት እንኳ በየወረዳው እና በከተማው ጮማ ስልጣንና ወፍራም የባለስልጣን ወገኖች ብቻ በሚስጢር ተጠራርተው ሲከፋፈሉ ብዙሃኑ ካድሬ የበይ ተመልካች ሆነው አልተዘነጉም? ለቅስቀሳ የሚንከራተቱላችሁ ዝቅተኛ ካድሬ፣ ጥቅም  ስትከፋፈሉ ግን የላይኛውን መዋቅር የተቆጣጠራችሁ ብቻ  ናችሁ፡፡ በእንዲህ አይነት የምትታወቁ ስትሆኑ  በማንኛውም ፖለቲካ ጉዳይ እንኳን ሰፊውን ህዝብ ልታሳተፉ ቀርቶ ካድሬዎቻችሁንም አታሳትፉም፡፡ ስለዚህ ተሳትፎ የሚትሉት የወረቀት ላይ ፕሮፖጋንዳ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡


˝የብሔሩ ተጠቃሚነት የሚወሰነው በተመዘገበው የመልካም አስተዳደር ተግባር እንጂ በተመደበው ጥቂት የሰው ኃይል አይደለም˝ ይላል ሰነዳችሁ፡፡ ይህ አባባል የፖለቲካ ብቃትና ንቃት ለሌላቸው እንደ ሆድ አደር ካድሬዎቻችሁ ወርቁን ወደ ጎን ትተን ሰሙን ብቻ ከተመለከትነው እንዲያው ዝም ተብሎ የየዋህና ገራ ገር ካድሬዎችን ያቀፈ  ሃሳብ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ወርቁ ሀሳብ ሰነዱ እንደዋዛ ደኢህዴን በስውር ሲቀምር ወደ ነበረው የሲዳማን ብሔር የማንነትና እራስን በራስ የማስተዳደር የዘመናት ተጋድሎን ወደ ከርሰ መቃብር የሚያደርስ ውስጠ ወይራ ሃሳብ ነው፡፡


በመጀመሪያ ደረጃ ደኢህዴን ያልተረዳው ወይም መረዳት የማይፈልገው ሀቅ ቢኖር የሲዳማ ህዝብ ያለፉትም ሆነ የአሁኑ ትውልድ የፖለቲካ ጥያቄ እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ብሔሩ በሰፈረበት ጅኦግራፍዊ ክልል ፖለቲካውና ኢኮኖሚውን  ያለ ተጽእኖ በራሱ መምራት መቻል ነው፡፡ ይህ ሰነድ የሚለው ግን ህዝቡ ተስፋ ማድረግ ያለበት በሚመዘገብ የመልካም አስተዳደር እንጂ የፖለቲካ ቁልፍ ጥያቄ መሠረት የሆነውን ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን እርሳው ደኢህዴን ከየትም ፈልጎ ይመድባልና ሰነዱን ሳትጠራጠር እመንና ተቀበል ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለብልጣብልጥነታችሁ እናደንቃለን ፡፡ አንድ ተረት እንንገራችሁ˝ ከጦጣ ላይ ሸምቶ የሚያተርፍ ዝንጀሮ የለም˝፡፡ ተነቃቃን? ጉዳዩ የሲዳማ ህዝብ የዘመናት ትግል ማጠንጠኛ ነው፡፡ ብዙዎች የሞቱለት፡፡ ተግባባን?


ገጽ ዘጠኝ ላይ ˝ የአመራር ምደባ መስፈርቶችና መርሆች አማካይነት ብቃታቸው እስከተመደቡ አመራሮች ካንድ ብሔር ቢሆን ምንም የሚጎድለው  አብዮታዊነት የለም˝ ይላል፡፡ ልብ በሉ፣ ዋና ግባችሁ ጋ ደርሰናልና በትዕግስት ስሙን፡፡ አመራሩ ካንድ ብሔር ቢሆን እንኳ ምንም ጉድለት የለበትም ይሉናል፡፡ ስለዚህ የሀዋሳን ከተማ ከሲዳማ አስተዳደር በመቀማት ከዚህ በፊት በጥንቃቄ ያዘጋጁትን የራሳቸው የብሔር አባላት ያለ ተቀናቃኝ መመደብ የሚያስችል ቀመር መሆኑ ነው ፡፡ ይህ አሰራር በሁለት ዋና ምክንያቶች ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡
1ኛ. የምደባውን 60-70% ዋጋ የያዘው የሚታይ ማስረጃ የሌለውና በአመራሩ በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆኑና ለማንም ባለስልጣን ህሊና ብቻ የተሠጠ መብት መሆኑ፡፤
2ኛ. አንዱን ብሔር ከእውቀትና ልምድ እንዲርቅ እየተደረገ ለሌሎች ደልዳላ ሜዳ እየተመቻቸላቸው የቆየ በመሆኑ የውድድር እድሉ ለሁሉም እኩል ባለመሆኑ ጨርሶ ተቀባይነት የሌለው አሠራር ነው፡፡


አገራቸውን ትተው የተሰደዱበት፣ በዱር በገደል የተንከራተቱበት፣ ትናንትና በሀዋሳ ከተማ ሣርና ቅጠል እንዲሁም ባንዲራ ይዘው የወጡት የሲዳማ ንጹሀን ዜጎች የተጨፈጨፉበት የራስ መብት ለማስከበር 
መሆኑን የዘነጋ መርህ ነው፡፡


˝ብሔራዊ ተዋጽኦን ለማመጣጠን ሲባል ብቻ ብቃት የሌላቸው ሰዎች ተሹመው ፖሊስውን በትክክል ካልተፈጸመ ህዝብ ይጎዳል˝ ፡፡ እውነት ነው፡፡ በክልል ይሆን በፈዴራል ደረጃ በትምህርት ዝግጅት ከፖለቲካ ብቃትና ንቃት ከህዝባዊ ወገተኝነት አንጻር ከሲዳማ ህዝብ የተሻሉ ሰዎች መቼ እንዲቀርቡ ታደርጋላችሁ? እናንተ ምንም በሉ ምን፣ ፈዴራል ሆነ በክልል ደረጃ በማንኛውም መስፈርት የሲዳማን ህዝብ የማይወክሉ፣ ስሜቱን የማያዳምጡ ፣ለህዝቡ የማይቆረቆሩ፣ የህዝቡ ልማት የሚያስጠላቸው፣ ቢቻላቸው የተጀመሩ ልማቶችም እንኳ ከማዘጋት ወደ ኋላ የማይሉ፣ ህዝብ የማያውቃቸው፤ እነሱም ህዝብን የማያዉቁ መሆኑ በይፋ ቢነገር ይከፋችሁ ይሆን? እስቲ እናንተስ አትታዘቡአቸውም? ምኑን ካላችሁ እናንተ ህዝባችሁን አስተባብራችሁ መንገድ፣ የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች ለመገንባት የሚያስችል የልማት ገንዘብ መዋጮ በዞን፣ በክልል፣ በፈዴራል ደረጃ በማስተባበር ህዝባችሁን ስትታደጉ የእኛዎቹ ጉዶች ግን ምንም አይነት መንፈሳዊ ቅናት የማያድርባቸው መሆኑን እያወቃችሁ ለምን አልመከራችሁም፡፡ ታዲያ ይህ ያከባብራል? ወደ አንድነትና ፍቅር ያመራል? የእኛን ጉዶች እያጃጀላችሁ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣልን ተግባራዊ እያደረጋችሁ እስከ መቼ ትኖሩ? ለነገሩ እውነት መናገር ስላለብን ጻፍን እንጂ እናንተ የምትመርጡልን ለእናንተ የሚመቸውንና በእናተ ሳምባ የሚተነፍሰውን መሆኑን እናውቃለን፡፡


በዚህ አይነት አድሎአዊ አሠራር እስከወዲያኛውም ቢሆን የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ሊመጣ አይችልም፡፡ አንዱን እያቆረቆዙና ሌላውን በተለያየ መንገድ እያሳደጉ እንዴት ይሆናል?


የዚህ ሰነድ አዘጋጅ የደቡብ ፖለቲካ ቁማርተኞች ሰነዳችሁ የሚያጠነጥነው  በሁለት መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ የአዘጋጆቹና የሲዳማ ህዝብ  ፍላጎቶች ተቃራኒ ግቦች እንዳለአቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡
1ኛ. የፖለቲካ ደላሎች የሀዋሳን ከተማ በመረከብና ከታቸ  የራሳቸው ክሊክዚም አደራጅተው እስከሚበቃቸው ጊዜ ድረስ በስልጣን መክበር፣ በስልጣን መበልፀግ፣ ራስንና ከተቻለም የራስን ብሔር ከላይ የስልጣን ሽፋን እየተደገረገላቸው የእኔ የሚሉትን ወገን የመገንባት ግብ ያለው ሲሆን 
2ኛ. በተቃራኒው ደግሞ የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ እራስን በራስ የማስተዳደርና የማንነት ጥያቄ የሚቀብር  መሆኑ ነው፡፡ ሆዳሞቹ ለጥቅማቸው፣ የሲዳማ ህዝብ ደግሞ ለማንነቱ ከምን ጊዜም በላይ ነቅቶ ያለበት፡፡ ለሆድ የሚታገልና ለማንነት የሚታገል የትግል ታክቲክም ይለያልና እነዚህ ሁለት ተቃራኒ ሀሳቦች  የማይታረቁ ስለሆነ አያያዙ  የፖለቲካ ብስለትን የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ 


የፖለቲካ ደላሎች የግል ፍላጎታቸውን ያለተቀናቃኝ ለማሟላት እንዲቻላቸው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት የሚቻለው የእኔ የሚላቸው በብዛት በማስገባትና የሚቀናቀኑትን የሲዳማ ብሔር አባላትን  ከፖለቲካ አመራር ማግለል ብቻ አማራጭ የሌለው ስለሆነ ሞተን እንገኛለን ይሉናል፡፡ ሰበቡ ደግሞ የቴክኒክ ብቃት እና የፖለቲካ ተነሳሽነት ሆኖ ቀርቧል፡፡


እውነቱን እንናገር ከተባለ የሀዋሳ ከተማ በኢትዮጵያ ደረጃ ሶስት ጊዜ የአንደኝነት ደረጃ አግኝታ ተሸላሚ የሆነች በብሔሩ አመራር አይደለምን? እየመረራችሁም ቢሆን ሀቅ ነውና አዎን በሉ፡፡ የእናንተ አሉታዊ ተጽዕኖና ጫና ባይኖር የበለጠ መሥራት እንደሚቻል እሙን ነው፡፡ ታዲያ ይህንን እውነት በመካድ በጊዜ የለንም መንፈስ /Sense of argency/ መርህ ቶሎ የሲዳማ ብሔር ከከተማ አስተዳደር እናስወግድ ይሉናል፡፡ በደኢህዴን ምሽግ ውስጥ ተደብቀው የሚወጉን ጠላቶቻችን፡፡


ገጽ 12 የአፈጻጸም መርሆች ላይ
ሀ. ˝ የሲዳማ ብሔር ከተማው በዞኑ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የሚወከልበት ሥርዓት በአዋጅ ተመልሷል˝ ይላል፡፡
ይህ አባባል የተንሸዋረረና በአማርኛ ቋንቋ አጻጻፍ ጥበብ ተጠቅመው ሊያስተላልፉ የሞከሩትን ውስጠ ወይራ ዓላማቸውን ያሳብቃል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሀዋሳ ከተማ በሲዳማ ዞን ውስጥ  የተገኘ  ሳይሆን፡-
1. የሲዳማ ህዝብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዕከል መሆኑንና
2. የሲዳማ ዞን ዋና ከተማም  መሆኑን መጥቀስ እራሳቸውን ስለምያማቸው ነው መጥቀስ ያልፈለጉት፡፡ ከዚህ አንጻር በማንኛውም መስፈርት በሀዋሳ ከተማ ላይ የፖለቲካ አመራሩ ሥልጣን ምንም ሊሸራረፍ የማይገባ የሲዳማ ህዝብ መሆኑ እየመረራችሁ ቢሆንም ለመዋጥ ትገደዳላችሁ፡፡ ሌላው ከዚህ ጋር የሚነሳ ጉዳይ የትኛው አዋጅ ነው የሲዳማን የውክልና ሥርኣት የሚወስነው፡፡ ማን ያወጣለት? ማንና መቼ የተነጋገረበት? ብቻ ለሆዳቸው የተሰበሰቡትን ካድሬዎች ስብሰባችሁ አጨብጭባችሁ ከሆነ ይህ ጉዳይ የልጆች ጨወታና የራሳችሁ ጉዳይ እንጂ አዋጅ ሊሆን አይችልም፡፡ ሲዳማን አያገባውም አልተነጋገረበትም አያውቀውም፡፡


ለኢህአዴግ ወይም ለክቡር ጠ/ሚንስትሩ የቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች


ወደማጠቃለያ ከመሄዳችን በፊት አንዳንድ ጉዳዮችን ከጠ/ሚንስትሩ ጋር ማንሳት ተገቢ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ይሄን ስንል አንዳንድ ሰዎች የትግል መንገድ ያልገባን አድርጎ ሊያዩን ይችላሉ፡፡ እስከአሁንስ በደኢህዴን ላይ የተነሱ ጉዳዮች እርሳቸውን ወይም ድርጅታቸውን አይወክልም ወይ? እና መሠል ጥያቄዎች ሊያነሱ ይችላሉ፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን የሲዳማ ሰው ከባህሉ አንጻር ከተላላኪ ወይም ከሌላ ሰው ብቻ በሰማው ተነስቶ ወደ እርምጃ አይሄድም፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰው የአባቱን ገዳይ እንኳ ዘሎ ልበቀል/ልግደልህ ብሎ አይነሳም፡፡ ይልቅ ቁጭ ብሎ “ሰማችሁ ወይ ይህ ሰው ይሄንን በደል አደረሰብኝ… ወይም ይህ ነገር እርሱ ያለው ወይም ያደረገው መሆኑ ይጠየቅልኝ…” ብሎ ይመክራል፡፡ ከምክክር በኋላም የሚሆን ሁሉ ይሆናል፡፡ በአሁን ጊዜ ችግር ውስጥ የገባነውም የኛዎቹ መሪዎች ተብዬዎች ይሄንን ድንቅ ባህላችንን ወደ ጎን በመተው ሳያማክሩንና ሳይመክሩ እየሸጡን ስለቆዩ ነው፡፡ ስለዚህ እርሳቸውንማ ልንጠይቃቸውና ልንሰማቸው ግድ ይለናል፡፡ ለነገሩ ባትጠይቋቸውስ ሌላ ምን ልትሉ ወይስ ምን ልታመጡ? የሚልም አይጠፋም፡፡ አማራጭ የላችሁም፤ ያበጠና የደነደነ ጡንቻ ያላቸውና ሚሌነሮች የሆኑ ግለሰቦችና ተቃዋሚ መሪዎች ምን አመጡ ልንባል እንችላለን፡፡ መልሳችን በዚሁ ሰነድ በሰፊው የተመለሰና እዚህ ላይ በአጭር ቃል የሚመለስ ባይሆንም እንዲህ ነው -  እኛስ እንኳ እንደህዝብ ተነስተናል፡፡ አንድ የአልጄዚራ ቴሌቪዥን ፕሮግራም እናስታውሳችሁ ‹people and power› የሚል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ የሚተላለፉ ቁምነገሮች መልስ የሚመልሱ ቢሆንም ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ የፕሮግራሙ መለያ የሆነው ካርቱን በጥሩ ሁኔታ ያስረዳል፡፡ ካርቶኑ ጉንዳን የሚያካክሉ ከሲታ የሆኑ ብዙ ሰዎች (ህዝብ) ትልቅና ሃያል ባለ ሃይል (ባለ ፓዎር) ጎትተው ሲጥሉ ያሳያል፡፡ ታዲያ ከ1997 ዓ/ም ምርጫ ተከትሎ አ/አበባ የተነሳው የህዝብ አመጽ የከሸፈው በመንግሥት ብርታት ብቻ ይመስላችኋል? ጡንቻቸው አይሎ? አይደለም፡፡ በርግጥ ጡንቻው የሚናቅ አይደለም፡፡ ይህ ጡንቻ ከህዝብ ክንድ ግን አይበልጥም፡፡ የሆነው ነገር እንዲህ ነው - በተለያዩ ክልሎች ያለው ህዝብ ሰላም ፈላጊና አንጻራዊ በሆነ መልኩም ቢሆን ጥያቄዎቹ የተመለሱ ሲመስለው እንቅስቃሴውን በሰፊው ደግፎ ባለመቀላቀሉ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ነበር፡፡ ሀዋሳን ጨምሮ አንዳንድ መልሶች ተመለሱ፡፡ ስለዚህም ቀዝቀዝ ተባለ፡፡ ግልጽ ይመስለናል፡፡ በርግጥ ይህን ስንል አንዱ ህዝብ በአንድ አከባቢ ሲበደል ሌላችን በመጠኑ ስለተመቸን ብቻ ዝም ማለት አለብን ከሚል ጠባብ ብሂልም አይደለም፡፡ መች ይህ ሆነና፣ መችስ የራሳችንን ቀንበር አወረድንና፡፡ ይሄንን ያነሳነው ለማስፈራራትም አይደለም፡፡ እውነታው ይህ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ወደ ዋናው ቁምነገር እንመለስ፡፡


ክቡር ጠ/ሚንስቴር፡ -
1. ለመሆኑ የደቡብ/የደኢህዴን የፖለቲካ ደላሎች ለዛሬው ጥያቄና ውሳኔ እንዲመቻቸው የከተማውን አመራር በራሱ አቅዶ እንዳይሠራ ሲያዋክቡና ህዝባችንን በደቡብ ኤፍ ኤም ራድዮ ሲሰድቡና ሲያሰድቡ አልሰሙም? እኳንስ የራሶት መዋቅር ለረዥም ጊዜ የሠራውን በየቀኑ በየሥርቻው የሚፈጸመውን ይከታተላሉ፣ ያውቃሉ ተብሎኮ ይታመናል፡፡
2. በርግጥ እነዚሁ ደላሎች በአሁን ጊዜ የጻፉትን ወረቀትና ወደከተማው አመራርና ሠራኛ ያወረዱትን አጀንዳ አያወቁም? ለነገሩ ይሄንን ጥያቄ ስንጠይቆት ራሶትም ሳይታዘቡን አይቀሩም፡፡ “እነዚህ ሰዎች እኔን አያውቅም ይሆናል ብለውም ያምናሉ ማለት ነው?…” ብለውም ሳይሉ አይቀሩም፡፡ ለነገሩ የባህል ጉዳይ ሆኖ ነው እንጂ እኛም የምናምነው ነገር አለ፡፡ ¤ረ ለመሆኑ እነርሱ ያንን መጣጥፋቸውን አዘጋጅተው እርስዎ ጋ መጥተው ይሄንን ለመተግበር አስበናል ሲሉ ትንሽ ካንገራገሩ በኋላ እሽታዎትን እንደገለጹና አቶ ኃይለማሪያም ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲያስፈጽም ሃላፊነትና ተጠያቂነት እንደሰጡ ይነገራል፤ እውነት ነው ወይ? በእርግጥ ኢህአዴግ ይሄንን አያውቅም? ማለት እውነተኛው ኢህአዴግ? በርግጥ አይደለም ለማለት አይሞክሩም ብለን እናምናለን፡፡ አያዋጣማ፡፡ ማለት ማንንም አያሳምንማ፡፡ በርግጥ የማሳመን ችሎታ እንዳሎት ይታመናልና እስኪ ከራስዎ አንደበት እንስማው፡፡  
3. ¤ረ መልሱ ምንም ይሁን ለመሆኑ ይህ ቢሳካላቸው ኖሮ ማንን ሊያስደስቱ ፈለጉ? የማንን ጥያቄ ለመመለስ ፈለጉ? የኃይለማሪያምን? የሬድዋንን? የአለማየሁን? የመኩሪያ ሃይሌን? ወይስ የእነርሱን ወገኖች? የእነርሱ የሀዋሳ ጥያቄ ባይመለስ ምን ያመጣሉ? ወልቂጤን፣ ወራቤን፣ ሶዶንና ሌሎቹንም ከተሞች ማን ነካባቸው? በእውነት እኛን ግራ የገባን አንዱና ዋናው ነገር ማንን ለማስደሰት ነው ይሄንን አጀንዳ ሲያነሱ ዝም ያሉት? እውን የእነርሱም ፍላጎት ብርቱና የማይናቅ ከሆነቦት ፍላጎቱ ባይከበር በእርግጠኝነት ከህጋዊነት አንጻርም ይሁን ከሎጂክ የየትኛችን ፍላጎት ባይስተናገድ ነው ኢህአዴግን የሚጎዳው? የትኛችንን ቢያጡ ይሻሎታል (በዚህ ጉዳይ ማለታችን ነው)? እነኃይለማሪያምን ወይስ ሲዳማን? በእርግጠኝነት ይህ የወላይታ ጥያቄ አይደለም፡፡ የወላይታ ህዝብ በእኛ ላይ ችግር ኖሮበት አያውቅም እነኃይለማሪያም ከሚፈጥሩብን ወከባ በቀር፡፡ በሰላም አብረን እየኖርን ነው፡፡
4. እሺ ሌላው ቢቀር ያኔ ሀዋሳ መጥተው የገቡልን ቃል ከወዴት ነው? ወይስ ዘነጉት እንበል? አይመስለንም፡፡ ክቡር ጠ/ሚንስቴር እኛ እኮ ያኔም ቢሆን ከርሶም ሆነ ከድርጅቶ ለመግባባት የሞከርነው ጥያቄያችን ተመልሶ አይደለም፡፡ ሳናዝንና ሳንከፋ ቀርቶ አይደለም፡፡ ሰላም ወዳድ በመሆናችን አንጻራዊ በሆነ መልኩም ቢሆን ፍላጎቶቻችን ከተከበሩ ይሁና ብለን ነው፡፡ ለእኛ የገቡትን ቃል ከዘነጉ አ/አበባ ለጋዘጠኞች በነጮች ቋንቋ የሰጡትን መግለጫ አያስታውሱም? ማለት ጋዜጠኞች “አ/አበባ ምርጫ ቢደረግ እናልፋለን/እናሸንፋለን ብለው ያምናሉ…?” ብለው ሲጠይቁዎት “ኢህአዴግ እንደማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ይሳሳታል፡፡ ኢህአዴግ ከሌላው የሚለየው ግን ስህተቱን ቆም ብሎ ያያል፡፡ ራሱን ይገመግማል፡፡ ካለፈው ስህተቱም ይታረማል፡፡ ዛሬም መሳሳታችንን አውቀናል፡፡ ህዝባችንን መበደላችንን አውቀናል፡፡ ህዝቡም ካርዱን ተጠቅሞ ይሄንን ነግሮናል፡፡ ተቀጥተናል፡፡ ስለዚህም ስህተታችንን አውቀን መድረክ ፈጥረን ከህዝባችን ጋር ተነጋግረናል፡፡ ተግባብተናል፡፡ ታርመናል፡፡ ስለዚህም አ/አበባን ጨምሮ እናሸንፋለን ብለን እናምናለን …” ብለው ነበር፡፡ ይህ መልስ ለአ/አበባ ህዝብ ብቻ አይመስለንም፡፡ ለእኛም ህዝብ ነው፡፡ ታዲያ ይሄን ዘነጉት?
ሀ. ስለዚህ መልሱ ምንም ይሁን ምን ህዝባችንን ቃላት ከሚገልጸው በላይ በድለውታልና ሽማግሌውን፣ ወጣቱን፣ ተማሪውንና ጎልማሳውን ያነጋግሩ፡፡ “የመንግሥት ሽማግሌዎችን” ሳይሆን የሚወክሉንን ሽማግሌዎች፡፡ ህዝባችንን በግልጽ ይቅርታ ይጠይቁ፡፡ ህዝባችን ከምን ጊዜውም በላይ ማዘኑን ይገንዘቡ፡፡ ከዚህ በኋላ ህዝባችን በጥርጣሬ ዓይን እንደሚያያችሁ ይወቁ፡፡
ለ. በዚህ ሰነድ የቀረቡ ጥያቄዎቻችን ይመለሱ፡፡
ሐ. ሌሎች መሠረታዊነት ያላቸው ዋና ዋና ጥያቄዎቻችን በዚህ ሰነድ መጨረሻ ላይ በቀረበው መሠረት በአግባቡ ይመለሱ፡፡ ከዚህ ቀደም ለኢህአዴግ ጊዜው ጥሩ አይደለም በሚል ተሳስበን ተላልፈናል፡፡ አሁን ተራው የእኛ ነው፡፡ ጥያቄው ካልተመለሰ ለሲዳማ ጊዜው ጥሩ አይደለም፡፡ ጥያቄው ካልተመለሰና አይቻልም ከተባለ (ለነገሩ ጥያቄ ሳይሆን ውሳኔ ነው፡፡ ውሳኔው ካልተከበረ) ለመኖር ሌላ አማራጭ መፈለግ ግድ እንደሚል በቅንነት ይረዱልን፡፡


ለኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች የቀረቡ አስተያየቶችና ጥሪ


ውድ የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች የሲዳማ ህዝብ ታሪክ ያለው፣ ለማንነቱና መብቱ ተቆርቋሪና ለዘመናት ሊዘከርና ሊወደስ የሚገባው የአርነት ትግሎችን ያደረገ፣ በአሁን ጊዜ እየተመካንበትና ጠቅሰን እየታገልንበት ያለውን ህገ-መንግሥት እውን እንዲሆን የሞተለትና የበኩሉን ያበረከተ፣ ድንቅ የሆነ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን እንደራሱ በማየት አብሮ በፍቅርና በመተሳበብ የኖረ ታላቅ ህዝብ ነው፡፡ የደርግ መንግሥት ወድቆ ይህ ሥርዓት ተመሥርቶ ራሳችንን በራሳችን እንድናስተዳድር በር የከፈተልን ህገ-መንግሥት ተቀርጾ አንጻራዊ እፎይታ አግኝተን ጥቂት አመታትን ባስቆጠርን ማግሥት በ1993 ሲህዴድ ከሲዳማ ህዝብ ፍላጎት ውጭ ከደኢህዴን ጋር ተጋባ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በደል፣ ሁከት፣ ሰላም ማጣት፣ የረብሻ ቀጠና መሆንና ስጋት የሁል ጊዜ ዕጣ ፋንታው ሆኖ ቆየ፡፡ ይህ ያንገሸገሸውም ህዝብ፡ -
1. ግንቦት 16 ቀን 1994 ዓ/ም የሃዋሳ ከተማ የባለቤትነት መብት ይረጋገጥልን የሚል ጥያቄ በማንገብ በሰላማዊ መንገድ ያካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከባድ መሣሪያ በታጠቀ ኃይል ተጨፍጭፎ ዝም ብሎ ተመለሰ፡፡
2. ሐምሌ 1998ዓ/ም የሚደርስበት ኢሰብአዊ የመብት ረገጣና የአስተዳደር በደል የመረረው የሲዳማ ህዝብ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ላይ በመመስረት ክልል የመሆን ጥያቄ አቀረበ፡፡ አሁንም ህገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ ጥያቄው ታፈነ፡፡ 
3. ለዛሬው ክህደታቸው ይረዳቸው ዘንድ የከተማውን አመራር እንዳይንቀሳቀስና እንዳይሠራ ሽባ አድርገውት ቆይተው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሲዳማን ስም እየጠሩ ምንም ሳያፍሩ በደቡብ ኤፍ ኤም ራድዮ ሲሰድቡ ቆዩ፡፡ አሁን ግን ይባስ ብለው የሲዳማን ህዝብ ከሀዋሳ ከተማ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሻራውን የሚያስወግድ ሰነድ አቅርበው ህዝባችንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ትግስቱ ካለወትሮው እንዲያልቅና በቁጣና በቁጭት እንዲነሳ አስገድዶታል፡፡ ዝርዝር በደልና ሴራቸውን ከዚህ ሰነድ መመልከት ይቻላል፡፡ 
¤ረ ለመሆኑ ትዕግስት ያስንቃል? ያሰድባል? መቻቻልና ጊዜ ይመልሰው ብሎ ዝም ማለት ያስደፍራል እንዴ? ለመሆኑ የሲዳማ ህዝብ ከሀረር፣ ከአፋር፣ ከሱማሌ፣ ከጋምቤላና ከቤንሻንጉል ወገን ብሄሮችና ብሄረሰቦች በምን ተለይቶና አንሶ ተናቀ? እነዚህ ወገኖች ክልል መሆን ችለዋል አይደለም እንዴ? እኛስ ክልል ብንከለከል ከተማችንን እንኳ እንዳናስተዳድር ለምን ተፈለገ? አትችሉም አቅም የላችሁም ተባልን፡፡ ይህ እውነት ነው ብላችሁ እናተስ ታምናላችሁ? አቅም የላችሁም ብለው በደፈናው ህዝቡን የሚሳደቡ ወገኖች የቱን አቅም ሊነግሩን ይሆን፣ እናንተስ አታውቋቸውም? ለመከበር ሲዳማ እንደናተ ድንበር ላይ መሆን አለበት? ምናልባትም ችግር ከተፈጠረ የግድ ጠመንጃ ለመያዝ በሚያመች ቦታ መሆን አለበት ማለት ነው ለመከበር?


እናንተስ ዝምታችሁ ከምኑ ላይ ነው? አባልና አጋር መሆን ለአባላቱ ጭምር መሆን የለበትም? አንድ አባልና አጋር ድርጅት አባላቱ/ጓዱ ሲበደል ለምን ማለት የለበትም? እኔ እስካልተነካሁ ይሁን ብሎ ዝም ማለት አይመስልም? ድንበር ያሉትን የጠቀስነው ላነሳናቸው ጥያቄዎች ጥሩ መገለጫ ስለሚሆኑ ነው እንጅ ቅሬታማ በኦህዴድ፣ በብአዴንና በሕወሀትም ላይ አለብን፡፡ እናንተን የመጠየቃችን ሚስጢር አንድም ከባህላችን አንጻር አንድ ሰው ከሌላው ጋር ሲጣላ ወደለየለትና መራራ ጥል ውስጥ ከመግባቱ በፊት “ሰማችሁ ወይ (‹አፊኒ›) ተበደልኩ እከሌ በደል አደረሰብኝ…” ብሎ በአገር ሽማግሌና በዘመድ አዝማድ ያስመክራል፡፡ ይመክራል፡፡ ከዚያ በኋላ ለሚሆን ነገር ተጠያቂ አይሆንም አይወቀስም፡፡ ይህን ስንል ታዲያ የእኛ በደል እንኳንስ ለናንተ ለአባላቱ ለዓለምም ግልጽ ነው፡፡ ድንኳን ጥለን ባናለቅስም በየቤታችን አልቅሰናል፡፡ አዝነናል፡፡ ተንቀናል፡፡ የውርደታችንን ደረጃ የሚገልጸው ነህምያ 2 ላይ ያለው ቃል ነው፡፡ ቅጥራችን ፈርሷል፡፡ እነሰንባላጥና ጦብያ ምንም አያመጡም ቅጥራቸውን አይሠሩም አያስከብሩም፣ በኛም ላይ ሊያምጹ አይችሉም ብለው ተሳልቀውብናል፡፡ እኛ ግን አማኝ ነን እንዲህ እንላን - “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፣ እኛም ባሪያዎቹ ተነስተን እንሠራለን፣ እናንተ ግን በሀዋሳ እድል ፈንታና መብት መታሠቢያም የላችሁም…”፡፡ ይህን ያልነው ለመሰሪ የደኢህዴን አመራሮች ነው፡፡ ስለዚህ ነግ በእኔ ነውና ፍረዱልን፡፡ ከጎናችን ቁሙ፡፡ የምንጠይቀውም ፍትህ፡ -
1. የክልል ጥያቄያችን/ውሳኔያችን መልስ ያግኝ፡፡ 
2. የበደሉን እነሰንባላጥና ጦብያ ከሥልጣን ወርደው በህግ ይጠየቁልን፡፡ ሙሰኞችም ናቸውና፡፡ ከዛሬ ጀምረው እኛን አይወክሉንም፡፡ ኢ-ደሞክራስያዊ ስለሆኑ የእናንተን ህዝብም እንዳይወክሉ እንድታደርጉ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
3. ደኢህዴንና አመራሩ በህዝባችን ላይ ሲፈጽም የቆየው በደል፣ ወከባና ሴራ ወደር የለሌውና ከመሪ ድርጅት ሳይሆን ከጠላት የሚጠበቅ ተግባር ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ ስለዚህ የህዝብ ጠላት መሪ መሆን ስለማይችል ደኢህዴን ከዛሬ ቀን ጀምሮ ሲዳማን አይወክልም፡፡ ስለዚህ ይሄንን አቋማችንን እንድትደግፉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
4. ይህ ግን ባይሆን አሁን ሀዘናችን ከጥግ ስለደረሰ፣ ውርደታችን ስለከፋ፣ እንባችን ስለበዛ፣ መብት ስላጣን ትግላችን ቀጣይ ይሆናልና ህዝባችን አለአግባብ እንዳይመታ፣ እንዳይገደልና እንዳይዋከብ የአብዮታዊ ጓድነታችሁን ሚና እንድትጫወቱ ህዝባዊ የወገናዊነት ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡ 


ማጠቃለያ


ሜትሮፖሊታን ከተማችንን እንዴት እናልማው በሚል ርዕስ የቀረበው ሰነድ ባነሳሳው ሁኔታ  ላይ ላዩን ፀጥ ያለ መስሎ እየተዳፈነ ወቅቱን ይጠብቅ የነበረ የህዝባችን የማንነት መብት ረገጣና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን ለማንሳት ምንም ቅስቀሳና አደራጅ ሳያስፈፈልገው ከዳር እስከ ዳር ሁሉንም ህዝብ አንቀሳቅሶታል፡፡ ይህም የሆነው ገና ከጅምሩ ነው፡፡ ሰላማዊና ህዝባዊ ትግሉ ገና አልተቀጣጠለም፡፡ ይህ ጽሁፍም አፄ ምኒልክ እስከ ኢህአዴግ በሚል ርዕስ የሲዳማን ህዝብ የማንነት ጥያቄዎችን ያስተናገደበት አካሄድና ያጋጠሙ  ችግሮችን ዳስሷል፡፡ በዚህ መሠረት ከተጫረው የፖለቲካ እሳት አንጻር ያለውና የሚኖረው የትግል አቅጣጫ ጠቋሚ ማጠቃለያዎች እንደሚከተለው ተቀምጧል፡፡
1. የሲዳማ ህዝብ ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ ለሰብአዊ መብቱና ለማንነቱ ሲል መራራ መስዋእቶችን ይከፍል እንደነበረና የትግሉ ውጤትና ፍሬ ለማየት እንዳይታደል አሉታዊ ሚና የሚጫወቱት በየዘመኑ ከወገኑ በሚፈጠሩ ሆድ አምላካቸው የሆኑ የዛሬን ሆድ መሙላት እንጂ ነገን አሻግረው ማየት የተሳናቸው የአእምሮ ድሆች አማካይነት ጠላቶቻችን ባገኙት ቀዳዳ እርስ በርሳችን እንዲንጋጭ በማድረግ ዋና የትግል ዓላማ እንዲዘነጋና እንዲስተጓጎል  በማድረግ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን እንዳለፉት ዘመናት ሁሉ የአእምሮና የአስተሳሰብ ድሆች የሆኑ ፖለቲከኞች የህዝባችን የማንነትና ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ለማዳፈን የሚሯሯጡ ተላላኪዎች በግልጽ እያየናቸው ነው፡፡
2. ደኢህዴን በደቡብ ላይ በተለይም በሲዳማ ህዝብ የአገዛዝ በትረ ስልጣኑን ከተቆጣጠረበት ከ1993 ጀምሮ የሲዳማ ህዝብ የልማት ፍላጎትና ጥማት እንዳይሟላና ከልማት ወደ ኋላ እንዲቀር ሆን ተብሎ በተጠና መንገድና ሴራ ወደ ኋላ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ የልማት ራእይ ያላቸው የብሔሩ ልጆች በዘመቻ እየታዱኑ እዲሰደዱና እንዲበታተኑ ተደርጓል፡፡ በራሳቸው ጥረት የተማሩ ወጣቶች በአግባቡ ስራና ሰራተኛ በሚያገናኝ መልኩ ተሠማርተው ለህዝባቸው የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲችሉ የሚያስችል መልካም አስተዳደር የለም፡፡ በሲዳማ ውስጥ እንኳንስ አዳዲስ ተምረው የሚመጡ ተማሪዎችን የሚያስተነግድ የልማት ስራዎች መፍጠር  ቀርቶ በፊት የተጀመሩትም ቢሆን  ባሉበት ቆመዋል፡፡ ለምሳሌ የፉራ ኮሌጅ ወደኋላ እንዲመለስና እንዲጠፋ ያደረገው ይሄው አስተዳደር መዋቅር ነው፡፡ በገጠር ሲኬድ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ የሚኖረው አርሶ አደር ተመርቆ የመጣን ልጁን ሥራ እስከሚያገኝ ድረስ የሚሸከምበት ጫንቃ የለምውም፡፡ 
3. ይህ የቀረበው ሰነድ ሲፈተሸ ደግሞ ደኢህዴን የሲዳማን ህዝብ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ረግጦ እንዲገዛ መንገዱን አልጋ በአልጋ  ያደረጉለት ሆዳም ካድሬዎቹን በመሳደብ ይጀምራል፡፡ ሙሰኞች ናችሁ፡፡ ብቃት የላችሁም፡፡ ተላላኪዎች ናችሁ፡፡ የእናንተ የተላላኪነት ኮንትራት ጊዜ አልቆአል፡፡ አሁን እናንተ ወግዱ ይላል፡፡ ከአሁን በኋላ የተዘጋጁና በደቡብ ቁልፍ አመራር ብቻ እየተፈተሹ ለእኛ የሚመቹ ብቻ በኛው መስፈርት ይመደባሉ ይላል፡፡ በመቀጠል ˝ጥቂት ኪራይ ሰብሳቢዎችና መረባቸው ያካበቱትን ሀብት በመቀራመት ላምባ እንደተጨመረበት ኩራዝ ለጊዜው ቦግ ቢልም ወዲያው ይጠፋል˝ ይላል ሰነዳቸው፡፡ እዚህ ላይ ማንን እንደሚሳደቡ ግልጽ ባይሆንም ትክክለኛ ኪራይ ሰብሳቢነት /ሙስና የሚመለከት ከሆነ የሙስናን ክብረ ወሰን የሰበሩ የክልሉ ቁልፍ ደኢህዴን አባላት ናቸው፡፡ በቂ መረጃ የቀረበ ስለሆነ መመለከት ይቻላል፡፡ በሙስና ሰበብ ሠርቶና ነግዶ ብቅ የሚልን የብሄሩ ተወላጆች ሳይለዩ ለመምታትና ለማቆርቆዝ ሆን ብለው ሲሠሩ እንደቆዩ ይታወቃል፡፡ አሁንም ቢሆን የተለያዩ ታፔላዎችን እየለጠፉባቸው እንዳሉና ሁኔታዎች ሲመቻቹላቸው ለማሳደድና ለማቆርቆዝ ዝግጁ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ከላይ “…ላምባ እንደተጨመረበት ኩራዝ ለጊዜው ቦግ ቢልም ወዲያው ይጠፋሉ” ብለው የተነበዩት ነገ ምን ሊሠሩ እንዳቀዱ ከወድሁ ሸፋፍነው እየነገሩን ነው የማይገባን መስሏቸው፡፡ ይሄንን ስንል የእኛ ሌቦች መነካት የለባቸውም ከሚል መነሻ እንዳይደለ ይታወቅልን፡፡ ጉዳዩ ሙስናን ካልሆነ የሚሳደቡት ህዝብን ነው ማለት ነው፡፡ 


እስከ ዛሬ ድረስ ደኢህዴን ሦስት ጊዜ የሲዳማን ህዝብ ተፈታትኗል፡፡
1ኛ.ግንቦት 16 ቀን 1994 ዓ/ም የሃዋሳ ከተማ የባለቤትነት መብት ይረጋገጥልን የሚል ጥያቄ በማንገብ በሰላማዊ መንገድ ያካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከባድ መሣሪያ በታጠቀ ኃይል ተጨፍጭፎ ዝም ብሎ ተመለሰ፡፡ የደቡብ ባለስልጣናት በአሸናፊነት የሲዳማ ህዝብ በተሸናፊነት ፍትህ ርትዕ አጥቶ ተመለሰ፡፡ በፖሊቲካ ቋንቋ ግን የሲዳማ ህዝብ አሸናፊ ነው፡፡ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ህገ-መንግስቱን መሠርት አድርጎ ተንቀሳቀሰ፡፡ ህገ-መንግስቱን በራሳቸው ጊዜ ያፈረሱ አምባገነኖች ግን በአውላላ ሜዳ ላይ ንጹሀን ዜጎችን በጨፍጨፍ  ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ረገጣ አካሄዱ፡፡
የሲዳማ ህዝብ ሰብአዊና ደሞክራሲያዊ መብቱ መረገጡ፣ የአምባገነኖች ኢ-ህጋዊነት በአለም ተመዘገበ፡፡ ይህም በፖለቲካ ቋንቋ አሸናፊው የሲዳማ ህዝብ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ፍትህ በጊዜው ተፈልጎ መገኘቱ አይቀረ ነውና፡፡ ሁሉም ጊዜ አለው ይል የለም የእግዝአብሄር ቃል፡፡


2ኛ. ሐምሌ 1998ዓ/ም ሰብአዊ መብት ረገጣና የአስተዳደር በደል የመረረው የሲዳማ ህዝብ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ላይ በመመስረት ክልል የመሆን ጥያቄ አቀረበ፡፡ አሁንም ህገ መንግስታዊ አካሄድ ተከትሎ ለቀረበው ጥያቄ መንግስት ግን ህገ መንግስታዊ ባለሆነ መንገድ ጥያቄውን አፈነው፡፡ ይህም ለአምባገነኖች ድል ይመስላቸዋል፡፡ ለሲዳማ ህዝብ ግን ከፍተኛ ድል ነው፡፡ ጥያቄው ህገ መንግስታዊ መሆኑና ህገመንግስታዊ ባልሆነ መንገድ መገደቡ በዓለም ተመዝግቧልና፡፡


3ኛ. ከላይ ያቀረብናቸውን የህዝብ ጥያቄ በማፈናቸው በአሸናፊነት የተወጡ የመሰላቸው የደቡብ ሙሰኞች ከላይ በርዕሱ ላይ የተጠቀሰውንና የሲዳማን ህዝብ ከሀዋሳ ከተማ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሻራውን የሚያስወግድ ሰነድ በማቅረብ እየተፈታተኑትና ይህ ጉዳይ ለሲዳማ ሆነ ለክልሉ ክራይ ሰብሳቢዎች ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰ ጉዳይ ነው፡፡ የሲዳማ ህዝብ ይህንን የሙሰኞች ሰነድ በመቀልበስ መብቱን ማረጋገጥ ወይም እንደተባለው የሀዋሳን ጉዳይ ለታሪክ ትቶ ወደ ገጠር መመለስ፡፡ 


በዚህ መሠረት ህዝቡ የመጨረሻ ጫፍ ላይ ደረሶ በአንድ ሀሳብ በአንድ ዓላማ ሁሉን ነገር ለሀዋሳ ጉዳይ ያለበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡ የዩኒቨርሲት ተማሪዎች፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ አስተማሪዎችና ተማሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶ አደሮች የሀዋሳ ጉዳይ ጫፍ ለማድረስ እጅና ጓንት ሆነዋል፡፡ በዚሁ ሁኔታ ላይ የተቀናጀ የትግል አካሄድ ስልት መከተል አስፈልጓልና በጥንቃቄ ብንከተል ጥሩ ነው እንላለን፡፡
ጥያቄዎቻችን፣ አቋሞቻችን፣ አቅጣጫዎቻችን፣ ግቦቻችንና የትግል ስልቶቻችን ሲጠቃለል


ትግላችን የተበታተነና ወጥነት የለሌው ሆኖ ዓላማው እንዳይዛባ፣ ስሜታዊነትና ጠባብነት ተስፋፍቶ የትግል ራዕያችን ፈር እንዳይለቅ፣ ሰላማዊና ሰላማዊ ትግል ብቻ መርሃችን እንዲሆን ከዚህ ቀጥሎ ባለው አቋምና አካሄድ ጸንተን ይህን ዓላማ ብቻ ከግብ ለማድረስ እንድንተጋ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡


ጥያቄዎቻችን፣ አቋሞቻችን፣ አቅጣጫዎቻችንና ግቦቻችን


1. በ1998 ዓ/ም ህጋዊ ስነ ስርአት ተከትሎ የቀረበው ህገ-መንግስትን መሠረት ያደረገው ክልል የመሆን ጥያቄ የሲዳማ ህዝብ ቁልፍ ጥያቄ ስለሆነና ይህ ውሳኔ አሁን መልስ የሚገባው ታሪካዊ ጊዜ ላይ ስለደረስን ይሄንን ጉዳይ ኢህአዴግ ከግምት ውስጥ በማስገባትና የህዝብን ውሳኔና የመብት ጥያቄ ህጋዊነት በለሌው መልኩ ሁሌም ለመጫን መሞከር የመልካም አስተዳደር መርሆ ካለመሆኑም በላይ በህዝብና በመንግሥት መካል መተማመንን የሚያጠፋና ሰላም እንዲጠፋ የሚያደርግ ስለሆነ የህዝባችንን ውሳኔ እንዲያከብር እንጠይቃለን፡፡
2. በዚህ ሰነድ ውስጥ በከፊልም ቢሆን ለማቅረብ እንደሞከርነው ደኢህዴንና አመራሩ በህዝባችን ላይ ሲፈጽም የቆየው በደል፣ ወከባና ሴራ ወደር የለሌው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከዚህ በኋላ ከደኢህዴን ጋር መቀጠል የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ደኢህዴንና አመራሩ እኛን ከዛሬ ጀምሮ እንደማይወክለን መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ደኢህዴን የምናቀርበው ማመልከቻም ሆነ የምንጠብቀው ምላሽ እንደለሌን ይታወቅልን፡፡
3. የደኢህዴን አመራር የፈጸመብን በደል ፍትህን ፍለጋ የሚያስኳትን ነው፡፡ ስለዚህ እነ አቶ ሃይለማሪያምና ግብረአበሮቻቸው ለፍርድ ይቅረቡልን፡፡ አሁን ባላቸው የስልጣን ወንበር ላይ ሆነው የሚወክሉት ሠፊውን የኢትዪጵያን ህዝብ ቢሆንም እርሳቸው ግን ክልል በነበሩ ጊዜ እንደሚተጉለት ሁሉ አሁንም እየሠሩ ያሉት ለብሔራቸው ብቻ ነው፡፡
4. ደኢህዴን እስማይወክለን ድረስ መሠረታዊነት ያላቸው ጥያቄዎቻችን መልስ እስከሚያገኙ ድረስ በአሁን ጊዜ በከተማችን በተለያዩ የአመራር ቦታዎች ተሰግስገው ያሉና እያደሙን ያሉ የደኢህደን አመራሮች (የእነኃይለማሪያም ተወካዮች) በአስቸኳይ ይነሱልን፡፡
5. ቀድሞውንም ቢሆን ሲህዴድ ከደኢህዴን ጋር ያደረገው ጋብቻ ያለአቻ ጋብቻ ስለሆነና ተስማምቶ ማደር/መኖር ያልተቻለ ከመሆኑም በላይ በህልውናችን ላይ የመጣ ስለሆነ ሲህዴድ እንደገና እራሱን ችሎ እንዲደራጅ እንጠይቃለን፡፡ 


መከተል የሚገባን የትግል ስልቶቻችን


1. ደኢህዴን እንደሚያደናግረን ሳይሆን የሲዳማ ህዝብ በሁሉም መስፈርት መብታችን ተረግጧል፡፡ ነጻነት አጥተናል፡፡ ሁሌም የስጋትና የትርምስ ቀጠና ሆነናል፡፡ እኛ ሳንገፋቸው ገፍተውናል፡፡ ሳንጠላቸው በውሸት ፕሮፓጋንዳ ጠልተውናል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ የምናደርገው ትግል ከምን ጊዜውም በላይ በእግዚአብሄር ተቀባይነት ያለውና በእግዚአብሄር ጊዜ የሆነ ስለሆነ እውነተኛ ፍርድ የሚሰጥና በደላችንን ሊበቀልልን በሚችል አምላክ ፊት መገኘትን ሁላችንም የትግላችን መርህ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ (ነህምያ 2 እና ት. ህዝ. 37፡ 1-14 መመሪያችን ይሁን)፡፡
2. ከሁሉም በላይ አጽንኦት ሰጥተን ልንከተለው የሚገባው ጉዳይ ትግላችን እጅግ ሰላማዊ (none violent) በሆነ መንገድ ብቻ መካሄድ ያለበት የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ በ21ኛው ክ/ዘመን ተቀባይነት የለለው ሰላማዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ እንዳይበክለን በብርታት ልንጠባበቅ ይገባል (በጉልበት ማሰብ የደኢህዴኖች ባህሪ እንጂ የእኛ ሊሆን አይችልም፡፡ አይገባም)፡፡ አብውን የሚኖሩ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች የወትሮውን ፍቅራችንንና መተሳሰባችንን እንደውም ከወትሮው በበለጠ ሊቸሩ ይገባል፡፡ አክብሮት፣ ፍቅርና ፍትህ እነርሱም ይናፍቃቸዋልና፡፡
3. ሠላማዊ በሆነ መንገድ ስንታገል ግን አምባገነን ከሆኑና አንዳንዴም ወገን ከሚመስሉ ለሆዳቸው ካደሩ ወገኖች ብርቱ ውግዘት፣ ጫናና ወከባ ሊመጣብን ይችላል፡፡ ይህ ግን ከዓላማችን ፈቀቅ እንድንል ሊያደርገን አይገባም፡፡ ዛሬ ኢህአዴግ ስልጣን ሊይዝ የቻለው ከዚህ ቀደም ጭቆናው ባንገሸገሻቸው ታጋዮች (በህይወት ባሉትና በሰማዕታት) ዋጋ መክፈል በኋላ መሆኑ ትምህርት ሊሆነን ይገባል፡፡ የእኛዎቹ ታጋዮችና ሰማዕታትም ለዚህ አንጻራዊ ድል ካበቁን ባለውለታዎቻችን ዋናዎቹ ናቸው፡፡ መቼም ዛሬ ህገ-መንግሥታዊ መብታችን ስለተረገጠ ብቻ ተነስተን ህገ-መንግሥቱ የሰጠንን እፎይታ ልንክድ አንችልምና፡፡ ዛሬ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ጥያቄዎቻችንን ወደራሱ ወደበዳዩ የማድረጋችንና የመቻቻላችን ሚስጢር ምክንያቱ ይሄው ነው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሰማዕታት አደራ ተበራተንና ነገ ለልጆቻችን የምናስተላልፈውን ተስፋ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከራስወዳድነትና ፍርሃት መንፈስ ፍጹም ተላቀን፣ በምንም ጫና ሳንንበረከክና በተለያዩ ጊዜያዊ ድለላና ማታለያዎች ሳንበገር እስከጫፍ እንድንታገል ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡ ጫፍ ማለት ጥያቄዎቻችን የሚመለሱበት ወቅት ማለት ነው፡፡
4. ቅድሚያ ከተሰጠው የትግል ስትራቴጂ አንጻር የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች የትግል አጋሮቻቸውን በንቃት መምረጥ ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ከተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ሲአንን ጨምሮ ግንኙነት ማድረጉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሲአንም ቢሆን ይሄንን እውነታ መረዳት መቻል አለበት፡፡ 
5. ከሲዳማ አብራክ ወጣን የሚሉ የደኢህዴን ካድሬዎች መካከል አብዛኛው የሲዳማ ህዝብ ፍላጎት የሚጋሩ ስለሆነ እነዚህን ከሆድ አምላካቸው ካድሬዎች በጥንቃቄ በመለየት ከተላላኪዎች ጋር ተዳምረው ተወግዘው ስሜታቸው እንዳይጎዳ ውስጥ ውስጡን የመግባባት ስራ ማካሄድና  ሁሉም የብሔሩ ተወላጆች አንዳንድ ለሆዳቸው ብለው ለሙሰኛ አመራሮች ተላላኪ የሆኑ ያሉ ቢሆንም በጥንቃቄ ለይቶ በማወቅ በዘመድ አዝማድ አስመክሮ ከለመዱት መሰሪ ድርጊት እንዲታቀቡ ማድረግ፡፡
6. ይህ የሲዳማ ህዝብ መብት የማስከበር እንቅስቃሴ በሚደረግበት ጊዜ ገጠር ካልሆነ በስተቀር በሀዋሳ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ወይም መንግስት ፈቃድ ባልሰጠው ቦታ መሰብሰብ ደም ለመጠጣት እንደሚያገሳ አንበሳ ያፈጠጡ  የሲዳማ ህዝብ ደመኞች ግርግር ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥርላቸውና ዘመኑ በስሜት ሳይሆን በስሌት የሚመራ ስለሆነ ምንም ሰላማዊ ሰልፍና ሁከት ሳያስፈልግ ደኢህዴን አንድ ለአምስት ወይም 1፡5 ጥምርታ ስለሚጠቀም የሲዳማ ህዝብ ሰላማዊ ትግል አንድ ለአንድ ብቻ ሆኖ በመንገድ ሲኬድ፣ በካፊቴሪያዎች፣ በስልክ በተለያየ ኮድ እያቀያየሩ አእምሮንና ሀሳብን ብቻ በማሠራት የሚካሄድ መሆኑን ሁሉም ልብ ሊል ይገባል፡፡
7. ነገሩ እያደር የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ እንዳይመለስ ለመገደብ ሳይታክቱ አቅደው የሚንቀሳቀሱ ጥቂት የክልል ቁልፍ አመራር ጎሳዎች መሆናቸው እየታወቀ መጥቶአል፡፡ እነሱም ቢሆኑ እግዚአብሔር እውነተኛውን ጉዳይ እንዲረዱና እንዲያምኑ እንዲረዳቸው እየጸለይን ለሌሎች ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ባለመኖር ወይም በሲዳማ ህዝብ የሚደርሰው ጫና ባለመደገፍ ዝም ያሉ ካሉ እነሱ በትክክል ተረድተው የህዝባችንን ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ባይደግፉ እንኳን በጭፍን እንዳይቃወሙ እውነታውን የማስረዳት ሥራ ሳይታክቱ መስራት ይገባል፡፡
8. የደኢህዴን ቁልፍ አመራሮች መንግስትንና የሲዳማን ህዝብ በማጋጨት በተለይ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ እንዲቀየር በማድረግ በህዝብና በመንግስት ንብረትና ገንዘብ ላይ ያደረሱት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተድበስብሶ እንዲቀር ስለሚፈልጉ ውዝግቡ ተባብሶ እንዲቀጥል ሳይታክቱ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም የሙስናን ወንጀል የፈፀሙበት በቂ ማስረጃ  ተጠናቅሮ ፍትህና ርትህ የሚፈልጉ የህግ ባለሙያዎች ተመካክረው በመደበኛ ፍርድ ቤት /ፀረ ሙስና ኮሚሽን/ በኩል ክስ እንዲመሰረት ማድረግ፡፡ 
9. አሁን ባለው ሁኔታ ያመጡትን ሰነድ ለሰፊው ህዝብ ውይይት ማቅረብ በመፍራት ሰነዱን መልሰው ሸሽገውታል፡፡ ይሁን እንጂ አረሳስተው በሀዋሳ ከተማ ባሉት መዋቅር በሚስጢር ሌላ ሤራ እንዳይተገብሩ በከተማው ያሉ ሀቀኛ የብሔሩ ተወላጆች  እየተከታተሉ መረጃውን ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡
10.  በመጨረሻም በዚህ ሰላማዊ ትግል ወቅት አሉታዊ ተግዳሮቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ መታሰር ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ከሆነ ግን የተበዳዩን/የታሳሪውን ወገን መጠየቅ፣ ታሳሪውን መጠየቅ በገንዘብ ቀጣይነት ባለው መልኩ መርዳት፣ እስከሚወጣም ድረስ ሳያቋርጡ ለአሳሪው ወገን ጥያቄ ማቅረብና ሠላማዊ ጫና መፍጠር፡፡ ከሁሉም በላይ የታሰሩ እስከሚፈቱ “ይፈቱ” የሚል ትግል ያለማቆም፡፡ እስራትና ሞት እንዳይመጣ ግን እግዝአብሄር እንዲረዳን በኢየሱስ ስም እንጸልያለን፡፡ አሜን፡፡


ኢህአደግ የህዝባችንን ውሳኔ የማያከብር ከሆነና እንደወትሮው ሁሉ ህገ-መንግስታዊ ባልሆነ መልኩ ጥያቄውን የሚያፍን ከሆነ ብቻ (worest case senario) የሚከተለውን የትግል ስልት እንከተላለን፡ -
11. ሴረኛው የደኢህዴን አመራር ሁለት ዓላማ ይዞ እንደሚታገል ይታወቃል - 1ኛ) የሀዋሳን ከተማ መለየትና የህዝቡን ውሳኔ ማምከን ሲሆን 2ኛ) የመጀመሪያው ዓላማቸው ተሳካም አልተሳካ ሁለተኛው ህዝቡን ከመንግሥት ለመለየት ሆን ብሎ በታቀደና በተቀነባበረ መንገድ እየሠራ ያለ መሆኑን በማወቅ ትግሉ እጅግ ሰላማዊ እንዲሆን ማድረግ፡፡ ምናልባት የህዝባችን ውሳኔ ባይከበር ሰላማዊ ትግሉን በተደራጀ መልኩ መቀጠል ግድ ይላል፡፡ ለዚህም ነባራዊ ሁኔታዎች ከሚፈለገው በላይ የተሟሉ ሲሆን ሥነ-ልቡናዊ ሁኔታና  እንቅስቃሴውን የሚመራ የተጠናከረ የፖለቲካ ድርጅት አስፈላጊነት ግልጽ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ሲአን ከእንቅልፍ ነቅቶ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ቁመና እንዲኖረው እራሱን የማጥራት ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ትግሉን በግንባር ቀደምትነት የማስተባበርና የመምራት ሚና መጫዎት ይገባል፡፡
12. ሲአን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ፈጥኖ እራሱን ማዘጋጀት የማይችል ከሆነ የሲዳማ ብሔር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና እውነተኛ የህዘብ ተወካዮች  ፎረም ትግሉን የመምራት ታሪካዊ የበኩርነት ድርሻ እንዲወጡ መደረግ ይኖርበታል፡፡
13.  ኢህአዴግ የሲዳማ ጥያቄ የማያስተናግድና በሰበብ አስባቡ የሚያዘገይ ከሆነ ሰላማዊ ትግሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሌሎች መብታቸውና ህልውናቸው ስላልተከበረላቸው ከሚታገሉ በመላው ሀገራችን ከሚገኙ የህዝብ እውነተኛ ወገኖችና ታጋዮች ጋር ግንባር ፈጥረን መታገል እንዳለብን ይታመናል፡፡ 
ሠላማዊ ትግሉ ይፋፋም ድልና ስኬት ለሠላም ወዳዱ ህዝብ!!!

ከማህበሩ ማህበራዊ መረብ ላይየተገኘ