POWr Social Media Icons

Thursday, May 24, 2012


ሚያዝያ መካተቻ ላይ ሐዋሳ ከተማ የዘለቁት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አገራችንን እንወቅ ክበብ አባላት ከተፈጥሯዊና ታሪካዊ መስህብ ቦታዎች ጉብኝታቸው ባሻገር ያከናወኑት ዐቢይ ተግባር ችግኝ ተከላ ነበር፡፡ ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ተግባራዊነትን ከአካባቢ ጥበቃ አንፃር ዕውን ለማድረግ አንዱ መገለጫው ዛፍ ተከላ እንደመሆኑ፣ የሐዋሳ ከተማ ልዩ መገለጫ የኾነው ሐዋሳ ሐይቅ ህልውናውን ለመጠበቅ በራስጌው ያለውን የታቦር ተራራ ደን ለማልበስ ይረዳ ዘንድ የክበቡ አባላት የችግኝ ተከላውን አካሒደዋል፡፡ ችግኙ የተተከለባት ሐዋሳ ከ52 ዓመት በፊት በልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ስትመሠረት ስሟን ያገኘችው ከሐይቁ መጠርያ ነው፡፡ 

በሲዳማ ዞን ውስጥ የምትገኘውና ከአዲስ አበባ 273 ኪሎ ሜትር የምትርቀው ሐዋሳ በምዕራብ ሐዋሳ ሐይቅ፣ በደቡብ ሐዋሳ ዙርያና ሸበዲኖ ወረዳዎችን በምሥራቅ ወንዶገነት ወረዳ፣ በሰሜን ሻሸመኔ ይከቧታል፡፡  

ከባሕር ወለል 1685 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው ሐይቁ የተለያዩ የዓሣ ዝርያዎች እንደአምባዛ ቆሮሶ፣ ቤሩስ ዓይነቶች አሉበት፡፡ አዕዋፋትና የዱር እንስሳትም በአካባቢው ይገኛሉ፡፡ ከአካባቢው ጋር ተስማሚ የሆነ ቱሪዝም ለማስፋፋት፣ ብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ በአካባቢው የሚገኘውን ታቦር ተራራ በደን መሸፈን አስፈልጓል፡፡ በየጊዜው እንክብካቤ እየተደረገለት በመሆኑም ተራቁቶ የነበረው ታቦር አሁን መልክ እየያዘ ነው፡፡ 

“ለፍቅር ሐይቁ ውበት ዋስትና የታቦር ገላ በዕጸዋት መሸፈን አለበት” የሚለውን የኅብረተሰቡ አገላለጽ ይበልታ ለመስጠት የተካሔደውን የሚያዝያ 28 ቀን 2004 ዓ.ም. የችግኝ ተከላ ያስተባበረው በሐዋሳ ከተማ የሚገኘው አፊኒ ኢኒሼቲቭ ዴቨሎፕመንት ፎረም ነው፡፡ ችግኝ ተከላውን ሲያስተባብር የነበረውን የፎረሙን ዳይሬክተር አቶ አራርሶ ገረመውን የ“አፊኒ” ምንነት ጠየቅነው፡፡ መለሰልንም፤ “አፊኒ ቃሉ ሲዳምኛ ነው፡፡ በቁሙ ሲተረጐም ‘ሰማችሁ’ ማለት ነው፡፡ ቃሉ የዘርም፣ የሃይማኖትም፣ የጾታም ልዩነት ሳይኖረው ሁሉን ያማክላል፡፡ በሲዳማ ባህል ይህንን ቃል ችግሮች ሲፈጠሩ ለመፍታት፣ የተለያዩ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ብሔሩ ይጠቀምበታል፤ ይህን ስም አፊኒን ልማትን ለማቀጣጠል እየተጠቀምንበት ነው፡፡”

በአፊኒ ስም ከአምስት ዓመት በፊት በ12 ወጣቶች የተቋቋመው ፎረሙ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ በጤናና ኤችአይቪ በሥራ ፈጠራ ላይ ያተኮሩ ዓላማዎችንም ሰንቋል፡፡ ከአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና አንድ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የሚማርን ተማሪ ጨምሮ በርካታ ወጣቶችን አቅፏል፡፡

በፎረሙ ዓላማ መሠረት “ሰዎች ይህን ሰማችሁ ወይ? የትምህርት ጥራት እየደከመ ነው? ወይስ እየተጠናከረ ነው? አያችሁ ወይ ለማለት ገዢ ቃል የኾነውን የሲዳምኛውን “አፊኒ” ለፎረማችን መጠርያ አደረግነው፤ ቃሉ ራሱ አሳታፊ ነው በማለት አቶ አራርሶ ያብራራል፡፡ ፎረሙ ጉልህ ተግባር አከናውኛለሁ የሚለው በትምህርት መስክ ነው፡፡ በደቡብ ክልል በሲዳማ ዞን ሁሉም ወረዳዎችና በሐዋሳ ከተማ የማጠናከርያ ትምህርት ለተማሪዎች በየጊዜው እየሰጠ ይገኛል፡፡ 

በርካታ ተማሪዎችንና ወጣቶችን በፎረሙ ሥር ተደራጅተው በመንቀሳቀሳቸው በአካባቢው ሰፊ ዕውቅናና የሕዝብ ተቀባይነትን ማግኘቱን፣ የአካባቢ ጥበቃ ሥራውንም የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) በመደገፉ ሦስት ማኅበራትን በመመሥረት የደን ተከላውንም ሆነ እንክብካቤ የማድረጉም ሥራ እየተሳካለት መሆኑንም አቶ አራርሶ ያወሳል፡፡ “በአካባቢ ጥበቃ  ላይ ያለው የኅብረተሰባችን ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል” የሚለው አቶ አራርሶ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አገራችንን እንወቅ ክበብ አባላት ከአዲስ አበባ ሐዋሳ መጥተው በታቦር ላይ ችግኝ መትከላቸው ለኅብረተሰቡ አርአያነት እንደሚኖረው ያምናል፡፡ 

“እዚህ ያለው ሰው እነርሱን ሲያይ በጣም ይነሣሣል፡፡ ስለ አካባቢ ጥበቃ ያለውንም ግንዛቤም ሆነ ስሜቱ ይጨምራል፤”

አፊኒ አገር በቀል ዕውቀት ጎልቶ እንዲታወቅ ትውልዱም በቅጡ እንዲያውቀው ለማድረግ ራዕይ አለው፡፡ ነባርና ጠቃሚ ባህሎች ተጠብቀው እንዲቆዩ ትልቅ ሥራ ለመሥራት መነሣቱንም ዳይሬክተሩ ይናገራል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/component/content/article/300-social/6436-2012-05-23-07-51-16.html