POWr Social Media Icons

Tuesday, May 8, 2012አዋሳ, ሚያዝያ 29 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - ሰብአዊ መብት እንዲጎለብት ከትምህርት ሚኒስቴርና ከ18 ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ለሶስት ቀናት ያዘጋጀው 4ኛ ብሄራዊ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የህግ ተማሪዎች የአምሳለ ፍርድ ቤት የክርክር ውድድር ትናንት ተጠናቋል፡፡ በውድድሩም የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል፡፡
የኮሚሽኑ የሴቶችና ህጻናት ኮሚሽነር ወይዘሮ አስማሩ በሪሁን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ሰብኣዊ መብቶች በየደረጃው በሚገኙ የትምህር ተቋማት በስርዓተ ትምህርት እንዲካተት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ተግባራዊ እንቅሳቃሴ ተጀምሯል፡፡
እንዲሁም ከ18 የህግ ትምህርት ከሚሰጡ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ጋር ለመስራት ስምምነት ላይ በመደረሱ ከ110 በላይ ነጻ የህግ ማዕከላትን ከፍተው አቅም ለሌላቸው በተለይም ለሴቶች፣ ለህጻናት፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለሌሎችም የህብረተስብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የህግ ትምህርት ከሚሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የሰብአዊ መብት ግንዛቤን የማስፋት ስራዎች እየተከናወነ ከመሆኑም በላይ በህግ ተማሪዎች መካከል የአምሳለ ፍርድ ቤት የክርክር ውድድር በመቀሌ ፣ በጅማና በባህር ዳር ዩኒቨርስቲዎች አዘጋጅነት በተለያዩ ርዕሶች ላይ ላለፉት ሶስት አመታት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡
ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር " የባህል መብቶችና የሴቶች መብት " በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ መካሄዱንና በተለይ በሴቶች መብት ላይ ተማሪዎች መሰረታዊ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ መንገድ በማሳየት ለተግባራዊነቱ እንዲንቀሳቀሱ ለማበረታታት አላማ ያለው ነው ብለዋል፡፡
ውድድሩ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ ከማስፋት በተጨማሪ ለጥናትና ምርምር ለአስፈላጊ እርምጃ መነሻ ሀሳብ የተገኘበት፣ ሰፊ የመከራከሪያ ሃሳቦችን በማንሳትና በማሸራሸር ለኮሚሽኑ አላማ መሰካት አስተዋጽኦ ላደረጉ ተማሪዎች፣ ምሁራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ኮሚሽነሯ አመስግነዋል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው የኮሚሽኑን አላማና ፕሮግራም የሚደግፉ በርካታ የመማር ማስተማር ስራዎች እንዳላቸው አመልከተው በተለይ የአምሰለ ፍርድ ቤት የህግ ውድድር ከኮሚሽኑ ጋር የበለጠ ለመስራት ዕድል የሚፈጥር፣ በተወዳዳሪ ተማሪዎች መካከል የልምድና የዕውቀት ልውውጥ ብሎም የደቡብና የሀዋሳን ገጽታና እሴቶች የሚጎበኙበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን በመግለጽ ተሳታፊዎችን አመስግነዋል፡፡
የሴቶች ፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማው መንግስቴ በበኩላቸው ሰብአዊ መብቶችን አስመልከቶ ባሉት የፍርድ ቤቶች አፈጻጸም ዙሪያ በምሁራን መካከል የክርክርና የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ተማሪዎች በንደፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር ማዋልን እንዲለማመዱ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም ተማሪዎቹ ከተመረቁም በኋላ በተለይ በሴቶች ላይ የሚከሰቱ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከልና ጎጂ ልማዳዊ ድረጊቶችን ለማስወገድ መብትን መሰረት ያደረገ አሰራር እንዲከተሉና በአሰራር ያሉ ክፍተቶችን በመለየት እንዲሻሻሉ የበኩላቸውን እንዲወጡ የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የሚካሄደው ይሄው ፕሮግራም በሀገሪቱ ያለው የፍትህ ስርዓት ለማሻሻልና ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ ዕገዛ እንዳለውና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስትር ዴኤታ አሳስበው ለኮሚሽኑ አላማ መሰካት አብረው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡
በፉክክሩ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በአጠቃላይ አሸናፊነት አንደኛ ሲወጣ መቀሌ ሁለተኛ የሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ደግሞ ሦስተኛ በመሆን አሸንፈዋል፡፡
ለተሳታፊ ዩኒቨርስቲዎችና አሸናፊዎች እንዲሁም ለውድድሩ መሳካት አስተዋጾኦ ላደረጉ ድርጅቶች የምስክር ወረቀት፣ ዋንጫ፣ የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ከዕለቱ የክብር እንግዶች ተሰጥቷል፡፡
በስነስርዓቱ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡