POWr Social Media Icons

Tuesday, May 1, 2012

New

አዋሳ, ሚያዝያ 23 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ አባል ሀገራት ተግባራዊ የሚደረገው አዲሱ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና አፋጣኝ ምላሽ ስልት ስትራቴጂክ ዕቅድን ለማዳበር ኢትዮጵያ የበኩሏን አስተዋጾኦ እያበረከተች መሆኗ ተገለጸ፡፡
በስትራቴጅክ ዕቅዱ ላይ ለመምከርና ሀሳብ ለማሰባሰብ የተዘጋጀ አውደ ጥናት ትናንት በሃዋሳ ከተማ ሲጀመር የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ምትኩ ካሳ እንደገለጹት በአፍሪካ ቀንድ በተለይ በኢጋድ አባል ሀገራት የሚከሰቱ ግጭቶች ለልማት፣ለመልካም አስተዳዳርና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት አሉታዊ ተጽልኖና ጫና እያሳረፉበት እንዳለ ይታወቃል፡፡
የግጭቶች መንስኤ እንደ ሰዎች ፍላጎትና ባህሪ ተለዋዋጭ መሆናቸውን ገልጸው ችግሮቹ በኢትዮጵያና በጎረቤት ሀገር በአርብቶ አደር አካባቢ ለጥሎሽ የሚጠየቀውን ከብት ከሌላ ጎሳ ለማምጣት መሞከር፣ውሃና ግጦሽ ፍለጋ ፣የተመጣጠነ የሀብት ጉድለት የመሳሳሉ ችግሮች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ለኢትዮጵያና ለቀሩትም የኢጋድ አባል ሀገራት ትልቁ ጠላት ድህነት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የሚከሰቱ ግጭቶች ከድህነት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ችግሮቹን ከምንጫቸው ለማድረቅ እንደያአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ህብረተሰቡን ባሳተፈ ሁኔታ አዲስ የጋራ ስትራቴጂክ ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቀደም ሲልም ከሌሎች የኢጋድ አባል ሀገራት ጋር በመተባበር የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና አፋጣኝ ምላሽ ስልት እንዲቋቋም ግምባር ቀደም ሚና በመጫወት ድንበር ተሻጋሪ የአርብቶ አደር ግጭቶችን በመከላከልና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ስትንቀሳቀስ መቆየቷን ተናግረዋል፡፡
ላለፉት አምስት አመታት የቆየው ፕሮግራም በቅርቡ በማብቃቱና በኢጋድ አባል ሀገራት እንደገና በቀጣይነት ተግባራዊ ለማድረግ የተዘጋጀው አዲሱን ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማዳበር ኢትዮጵያ የበኩሏን አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኗን ገልጸው ለዚህ ትልቅ ጉዳይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ልምዳቸውን በማካፈልና ጠቃሚ የማዳበሪያ ሃሳብ በማመንጨት ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና ልዩ አማካሪ አቶ አኔሳ መልኮ በበኩላቸው ዕቅዱን ለማዳበር የተዘጋጀው አውደ ጥናት ሃዋሳ ከተማ እንዲካሄድ በመመረጡ ተሳታፊዎቹን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ፣ በደቡብና ሱማሌ ክልሎች አልፎ አልፎ የሚታዩ ድንበር ዘለል የአርብቶ አደር ግጭቶችን ለመከላከል የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከኢጋድ አባል ሀገራት ጋር ግጭቶችን በተመለከተ የመረጃ ልውውጥ በማድረግና ግጭቶችን በጋራ ለማስወገድ ስልቶች በመንደፍ ፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ የመስራት ልምድ በመፍጠር አዲስ ለቀረበው ክፍለ አህጉራዊ የጋራ ስትራቴጂክ ዕቅድን ለማሳካት የበኩሏን እየተወጣች መሆኗን አብራርተዋል፡፡
በኢጋድ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና አፋጣኝ ምላሽ ሜካኒዝም ቢሮ ዳይሬክተር ዶክተር ማርቲን ኪማኒ በበኩላቸው ላለፉት አምስት አመታት የተሰራበት ፕሮግራም አብቅቶ እንደገና እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2012 እስከ 2019 የሚቆይ ስትራቴጂክ ዕቅድ እንዲነደፍ በቅርቡ የኢጋድ አባል ሀገራት ባስተላለፉት ውሳኔ መሰረት ጠቃሚ መረጃ ለማመንጨትና ለማሰባሰብ አውደ ጥናቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ተመሳሳይ አውደ ጥናት ቀደም ሲልም የኢጋድ አባል ሀገራት በሆኑት በጅቡቲ ፣ በኬኒያ ፣ በሱማሊያ፣ በሱዳንና በኡጋንዳ መካሄዱን ዶክተር ማርቲን አስታውቀው በየአባል ሀገራቱ የሚገኙ የችግሩ ተጠቂ አርብቶ አደሮችን በማነጋገር ለግጭት መንስኤ ናቸው ያሏቸውን ሀሳቦች፣ መፍትሄዎችና ፍላጎቶች ያካተቱ መረጃዎች መሰባሰባቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለድርሻ ከሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት የሚሰበሰበው ጠቃሚ መረጃ ስትራቴጂክ ዕቅዱ ለማዳበርና ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጾኦ እንዳለው በማመልከት ለዝግጅቱ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላትና ባለሙያዎች ላደረጉላቸው ትብብርና ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከኢጋድ አባል ሀገራት ጋር በመተባበር በሀዋሳ ከተማ ለሶስት ቀናት ባዘጋጀችው አውደ ጥናት ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ከፌዴራል ጉዳዮች፣ ከውጪ ጉዳይ ፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፣ ከኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ጨምሮ በሀገር አቀፍና ክልል ደረጃ ከሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተወጣጡ የስራ ሃላፊዎች ፣ ከፍተኛ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን የአውደ ጥናቱ አስተባባሪ ሲስተር ትዕግስት ሀይሉ ገልጸዋል፡፡
በቆይታቸው ስትራቴጅክ ዕቅዱን ለማዳበር የቡድንና ተናጠል ውይይት በማድረግ ጠቃሚ ሃሳብ በማሳባሰብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል ያሉት ሲስተር ትዕግስት አዲሱ ስትራቴጅክ ዕቅድ ዳብሮና ተሻሽሎ በኢጋድ አባል ሀገራት ደረጃ በቅርቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡