POWr Social Media Icons

Sunday, April 22, 2012

የደቡብ ክልል መንግሥት ነዋሪዎቹ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ገንዘብ እያዋጡ በመሆኑ ላለማስጨነቅ ሲል በራሱ ወጭ የአዲስ ስታዲየም ግንባታ አስጀመረ፡፡ ክልሉ ለስታዲየሙና ለተያያዥ ግንባታዎች ትናንት ሐሙስ ሚያዝያ 11 ቀን 2004 ዓ.ም. ሳትኮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ በ548 ሚሊዮን ብር እንዲገነባለት ውል ተፈራርሟል፡፡ ከዚህ በጀት ውስጥ 80 ሚሊዮኑን በዚህ የበጀት ዓመት ለሚሠሩ ሥራዎች የሚውል ሲሆን፣ ይህንን ጨምሮ በ2005 በጀት ዓመትም ለሥራው የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚመድበው ክልሉ ነው፡፡ ይህ የተወሰነው ሐዋሳ ከተማ ላይ ስታዲየሙን ጨምሮ የሚገነባውን ግዙፍ የስፖርት ኮምፕሌክስ እንዲያሠራ የተሰየመው ምክር ቤት ከክልሉ መንግሥት ጋር ከመከረ በኋላ መሆኑ ታውቋል፡፡

የስፖርት ኮምፕሌክስ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበርያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ አመሎ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ2004 እና በ2005 በጀት ዓመት ክልሉ ከራሱ ካዝና እየመደበ ያሠራል፡፡ በ2006 በጀት ዓመት ሕዝብ ለግንባታው አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ይጠይቃል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሥራውን ሐሙስ ተረክቦ በዕለቱ ቁፋሮ የጀመረው ሳትኮን ኮንስትራክሽን ይህንን ፕሮጀክት ለማሸነፍ ከስምንት ኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ጋር ተወዳድሯል፡፡ ከስምንቱ ውስጥ ሦስቱ በቴክኒካል ጨረታ ሲወድቁ፣ አምስቱ ጨረታውን አልፈው በፋይናንስ ጨረታ ተወዳድረዋል፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ ሳትኮንን ጨምሮ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን፣ ሚድሮክ ኮንስትራክሽንና ቫርኔሮ ይገኙበታል፡፡

ከአምስቱ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ውስጥ ዝቅተኛውን 548 ሚሊዮን ብር ለመጀመርያው ዙር የስታዲዮም ግንባታ በማቅረብ ሳትኮን አሸንፏል፡፡

ከፍተኛ የሆነውን የጨረታ ገንዘብ 564 ሚሊዮን ብር ያቀረበው ቫርኔሮ ሲሆን፣ ሦስቱ ኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በ548 ሚሊዮንና በ564 ሚሊዮን ብሮች መካከል መወዳደርያ ገንዘባቸውን አቅርበዋል፡፡ ስታዲዮሙ የሚገነባው ከሐዋሳ ከተማ ወደ ዲላ ከተማ በሚወስደው ዋና መንገድ፣ ደቡብ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ በሚገኘው ቦታ ላይ ነው፡፡ 

ስታዲየሙ 40ሺሕ ሰው የመያዝ አቅም ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ ልዩ ልዩ ቢሮዎችንና አዳራሾችን የሚይዝ ነው ተብሏል፡፡ ይኸ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ በሁለተኛው ዙር ጂምናዚየሞችንና የተለያዩ ስፖርታዊ ሥራዎች የሚካሔድባቸው ግንባታዎች ይከናወናሉ፡፡ 

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙ ስታዲዮሞች ሕዝብ በቴሌቶንና በመሳሰሉት ገቢ ማሰባሰቢያ ዓይነቶች የተሳተፈባቸው መሆናቸው ይታወቃል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/component/content/article/315-sport/6064-2012-04-21-11-30-00.html

ለወላጅ አጥና ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ሁሉ አቀፍ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተገለፀ::በሀዋሣ ከተማ የምሥራቅ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የከፍተኛ ሁለት ዐ3 ቀበሌ መረዳጃ እድርና ልማት ማህበር ከእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ከሳውዲን ተራድኦ ድርጅት ኘሮጀክት ጋር በመተባበር ለ145 ወላጅ አጥና ችግረኛ ህፃናት የፋሲካን በዓል ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል::
የኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት የሀዋሣ ቅርንጫፍ ሥራ አስያኪጅ አቶ ማስረሻ ክብረት እንዳሉት ህፃናቱ ቀደም ሲል የትምህርት ፣ የጤናና የስነ ልቦና ድጋፍ ሲሰጣቸው የቆዩ ናቸው::ከፍተኛ ሁለት ዐ3 መረዳጃ እድርና ልማት ማህበር ከድርጅታቸው ጋር በመተባበር የሚያደርግላቸውን ድጋፍ በመጠቀም ህፃናቱ በትምህርታቸው ውጤታማ ለመሆን መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል::
የምሥራቅ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ ወይዘሮ ዘውዲቱ ገ/መስቀል በበኩላቸው የመረዳጃ እድርና ልማት ማህበሩ ከረጂ ድርጅቶች ጋር በመተባበር  በክፍለ ከተማው በዓላትን ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ ለወላጅ አጥና ችግርተኛ ህፃናት የተለያዩ ድርጋፎችን  እንደሚያደርግ ተናግረዋል::
የአሁኑ ተረጂ ህፃናት በሚደረግላቸው ድጋፍ ተግተው ከተማሩ የነገይቱ አገር ተረካቢና የተሻለ ዜና መሆን እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡ ባልደረባችን ጌታሁን አንጭሶ እንደዘገበው::