POWr Social Media Icons

Thursday, February 23, 2012

New


ሃዋሳ, የካቲት 15 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ከጎበኙ የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኝዎች ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የዞኑ ባህል ቱሪዝምና የመንግስት ከሙኒኬሽን መምሪያ አስታወቀ፡፡
በመምሪያው የቱሪዝም ፓርኮች ልማትና አጠቃቀም የስራ ሂደት አሰተባባሪ አቶ ቶሎማ ካቢሶ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ገቢው የተገኘው ባለፉት ስድስት ወራት በዞኑ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን ከጎበኙ 27 ሺህ 452 የሀገር ውስጥና የውጪ ቱሪስቶች ነው፡፡
የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
የጎብኚዎች መጨመር
በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን በተለያዩ ህትመቶችና በድረ ገጽ ማስተዋወቅ በመቻሉ የጎብኝዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን አቶ ቱሉማ ገልጸዋል፡፡
የጎብኚዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱ ማሳያ ከሆኑት በተለይ በሲዳማ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ ዕለት የፊቼ በዓል አከባበርን ለማየት የሚመጡ ጎብኝዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የሚጠቀስ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የዞኑን የመስህብ ስፍራዎች ከጎበኙ ቱሪስቶች መካከል 8 ሺህ 498 የሚሆኑት የውጭ ሃገር ጎብኝዎች መሆናቸውንና የአገር ውስጥ ጎብኝዎችም የአገራቸውን ተፈጥሯዊና ባህላዊ የመስህብ ስፍራዎችን የመጎብኘት ልምድ እያደገ መምጣቱንም አስታውቀዋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ የያሬድ ሆቴል ባለቤትና የሆር አስጎብኝ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ሽብሩ እንደገለጹት የቱሪስት ፍሰቱ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው በተለይ ወጣት የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡
ከተማዋን ለመጐብኘት ለሚመጡና በሆቴላቸው ለሚስተናገዱ እንግዶች መጎብኘት ያለባቸውን ስፍራ የመጠቆም ስራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በሀዋሳ ሀይቅ ዳር በመዝናናት ላይ ከሚገኙ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች መካከል ወጣት በላይ ታምራትና ወይዘሪት ትፍስህት ይስሀቅ እንዳሉት በሀዋሳ ሀይቅ ላይ በጀልባ ለመዝናናትና በተለምዶ አሞራገደል እየተባለ የሚጠራውን የዓሳ ገበያ በመመልከታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ሌሎች ጓደኞቻቸውን አስተባብረው ለመመለስ ማሰባቸውን ገልጸዋል።