POWr Social Media Icons

Friday, January 13, 2012ሀዋሳ ፤ ጥር 04 2004 ዋኢማ - በደቡብ ክልል የመሬት ይዞታ ባለቤትነት የምዝገባ ሥርዓትን በዘመናዊ መንገድ ለማካሄድ የሚያስችለውን የሙከራ ተግባር ማከናወኑን የክልሉ የተፈጥሮ ሀብትና የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበራ ዊላ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል  እንዳስታወቁት የምዝገባ ሥርዓቱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በሙከራ ደረጃ የተካሄደው በሲዳማ ዞን ወንዶ ገነት ወረዳ አባዶ ቀበሌ ውስጥ ነው ፡፡
በቀበሌው የ 2 ሺህ 528 አባወራና እማወራ አርሶአደሮች መሬት ተለክቶ በኮምፒዩተር በመመዝገብ የባለቤትነት ማረጋገጣጫ ሰነድ እንደተሰጣቸው ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

የአርሶአደሮችን የመሬት ባለቤትነት ይዞታ ለማረጋገጥ ቀደም ሲል  የመሬት ልኬት ሥራው በገመድና በሜትር ሲካሄድ መቆየቱን ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ ይህም ሂደቱን አድካሚ ከማድረጉም በላይ የመሬቱን ይዞታ ሙሉ አቀማመጥ ለመለየትና መረጃዎችን በኮምፒዩተር ለማደራጀት አስቸጋሪ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አዲሱ የይዞታ ባለቤትነት ምዝገባ  በሳተላይት ቴክኖሎጂ  በመታገዝ የሚካሄድ በመሆኑ የባለሥልጣኑ ባለሙያዎች የየአንዳንዱን አርሶአደር የመሬት ይዞታ ሥፍራው ድረስ መጓጓዝ ሳያስፈልጋቸው ከቢሯቸው ሆነው ለማወቅ እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል፡፡

በክልሉ በሙከራ ደረጃ የተካሄደው የመሬት ይዞታ ባለቤትነት የምዝገባ ሥርዓት ውጤታማ ስለመሆኑ ከክልልና ከፌዴራል በተውጣጡ ባለሙያዎች በተደረገ ግምገማ መረጋገጡን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ባለሥልጣኑ  በሙከራ የተገኙ ውጤቶችን መሠረት በማድረግ ሙሉ የመሬት ልኬቱን  በከፊል  የክልሉ ዞኖች እና በተመረጡ ወረዳዎች ለመጀመር  የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

የመሬት ልኬት ሥርዓቱ መካሄድ የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት ስሜት ከማጠናከሩም በላይ በመሬት ወሰን ክርክር የሚነሱ አለመግባባቶችን ለማስቀረት እንደሚያስችል ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ምዝገባው ሴት አርሶአደሮችም በመሬታቸው ላይ ከወንዶች እኩል ድርሻ እንዳላቸው ስለሚያረጋግጥ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን  እንደሚያስከብርም ሥራ አስኪያጁ   አብራርተዋል፡፡