POWr Social Media Icons

Thursday, January 5, 2012


አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26 2004 /ዋኢማ/ -የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በአሲዳማ አፈር ላይ የቢራ ገብስና የስንዴን ምርት ለማሳደግ ላለፉት አራት አመታት ሲያካሂድ በቆየዉ ምርምር በሄክታር ከአምስት እጥፍ በላይ ምርት ማግኘት እንደሚቻል ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡
ዩኒቨርስቲው በአሁኑ ወቅት ከ100 የሚበልጡ የምርምር ፕሮጀክቶችን እያካሄደ መሆኑም ተመልከቷል፡፡
የዩኒቨርስቲው የምርምር ልማት ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ አበበ በሲዳማና በጌዴኦ ዞኖች መልጋና ቡሌ ወረዳዎች ሰሞኑን በተካሄደ የመስክ ጉብኝት ላይ እንደተናገሩት አሲዳማ አፈርን ምርታማ ማድረግ የተቻለው በአርሶ አደሩ ማሳና በገበሬ ማሰልጠኛ ማዕከላት በተከናወነ በተግባር የተደገፈ የሙከራ ምርምር ነው ።
አርሶ አደሩን በማሳተፍ ሲከሄድ በቆየዉ በዚሁ ምርምር አሲዳማ አፈርን ከኖራ ፣ ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጋር አቀናጅቶ በማከም የቢራ ገብስን በሄክታር እስከ 34 ኩንታል በማምረት በተለምዶ ከሚገኘው ከ5 እጥፍ በላይ ምርት መገኘቱን ገልፀዋል ።
በስንዴ ምርት ላይ በተካሄደ ምርምርም በተመሳሳይ ከፍተኛ ምርት ሊገኝ መቻሉን ዶክተር ተስፋዬ አስታውቀዋል፡፡
በሲዳማ ፣ በጌዴኦ ፣ በስልጤና ጉራጌ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የምርምር ስራው የተካሄደው ከኔዘርላንድ መንግስትና ከሌሎች የምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በምርምር ስራው ላይ ከ200 የሚበልጡ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውንና ምርምሩ እስከቀጣዮቹ አምስት አመታት እንደሚቆይና የተሳታፊ አርሶ አደሮችን ቀጥርም ከአራት ሺህ በላይ ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።
የምርምሩ ዋነኛ አላማም የገበሬውን ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር መሆኑን የምርምር ልማቱ ዳይሬክተር አስረድተዋል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ በበኩላቸው ከመማር ማስተማሩ ጎን ችግር ፈቺና ህብረተሰብ አሳታፊ የሆኑ የምርምር ስራዎችን ለማስፋፋት ስድስት የቴክኖሎጂ መንደሮች ተቋቁመው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት እየሰሩ መሆናቸዉን ተናግረዋል ።
ከምርምሩ ተሳታፊ አርሶ አደሮች መካከል በሲዳማና ጌዴኦ ዞኖች መልጋና ቡሌ ወረዳዎች የሚገኙት አርሶ አደር ደስታ ዳሌና ጎበና አአሎ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ከአሲዳማ አፈር ላይ በሄክታር ያገኙት የነበረዉን ከአራት ኩንታል በታች ምርት በምርምሩ በብዙ እጥፍ በማሳደግ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በደቡብ ክልል በተመረጡ ስድስት አካባቢዎች ከ100 በላይ ችግር ፈቺ የምርምር ፕሮጀክቶችን እያካሄደ መሆኑን ዶክተር ተስፋዬ አመልክተው የምርምር ስራዎቹም በግብርና ፣ በተፈጥሮ ሀብት ፣ በደን ልማት ፣ በእንስሳት ፣ በጤና ፣ በትምህርትና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ባላቸው ዘርፎች ላይ ማተኮሩን ኢዜአ ዘግቧል፡፡