መገናኛ ብዙኃን ምርጫውን በትክክል በመዘገብ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ


ፕሮፌሰር መርጋ በቃና፤
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በ2005 .ም የሚካሄደው የአካባቢና የአዲስ አበባ አስተዳደር ምርጫን ትክክለኛ ገጽታ በመዘገብ አገራዊ ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባቸው ተገለጸ።
በምርጫ ሕጎች አሠራሮችና በምርጫ አዘጋገብ ላይ ለመገናኛ ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት የተዘጋጀ ሥልጠና ትናንት ሲጀመር የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና እንደተናገሩት፤ ባለሙያዎቹ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ለዜጎች በማድረስ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል።
እንደ ፕሮፌሰር መርጋ ገለፃ፤ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በምርጫው ወቅት ለሕዝቡ ከወገንተኝነት የፀዳ መረጃ ይጠበቅባቸዋል። ዜጎች በሕገ መንግሥቱ የተጎናፀፉትን የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዲጠቀሙ ማነሳሳት አለባቸው።
በመሆኑም ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ከምርጫ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጋቸው ይህን ከግቡ ለማድረስ እንደሚያስችል ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል።
የሥልጠናው ዓላማ ጋዜጠኛው በምርጫው ላይ ያለው የአዘጋገብ ክህሎትን የሚያስጨበጥ እንደሆነ አመልክተው፤ እንዲሁም ልምዳቸውን የሚለዋወጡበት መድረክ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ፓርቲዎችም ሆነ የግል ተወዳዳሪዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት መተባበርና መቻቻል እንዲኖራቸው፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴውን ሳያውኩ በሥነ ምግባር ሕጉ መሠረት እንዲያካሂዱ የማድረግ አገራዊ ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
የሥልጠናው ተሣታፊዎች የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ጨምሮ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የየክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ባለሙያዎች እንዲሁም የጋዜጠኞች ማኅበራት ተወካዮች፣ ተሣታፊዎች ናቸው። ሥልጠናው ዛሬም ቀጥሎ ይውላል።
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/national-news/577-2012-12-17-11-49-46

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር