በመጪው ሚያዝያ ለሚካሄደው ምርጫ የምርጫ ቁሳቁሶች ሊከፋፈል ነው


አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2005(ዋኢማ) - በመጪው ሚያዝያ 6 እና 13 ለሚካሄደው የአካባቢና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ የምርጫ ቁሳቁሶችን ከዛሬ ጀምር ማሰራጨት እንደሚጀምር የምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ ወይዘሮ የሺ ፍቃዱ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ለምርጫው የሚያስፈልጉ የምርጫ ቁሳቁሶችን ቦርዱ በማዘጋጀት በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት ቀናት ለሁሉም ክልሎች ለማሰራጨት ዝግጅቱን አጠናቋል።
ቦርዱ ካሁን በፊት የመራጮች መመዝገቢያና የምርጫ ካርዶችን በአማርኛ ብቻ ያሳትም እንደነበረ ጠቁመው፤ በዘንድሮው ምርጫ ግን ከአማርኛው በተጨማሪ  በኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛና ሶማሊኛ ቋንቋዎች ማዘጋጀቱን ገልፀዋል።
የዘንድሮው ምርጫ ፍትሀዊነቱ የተረጋገጠ ለማድረግም ለባለድርሻና ለአስፈፃሚ አካላት ስልጠና መሰጠቱን ተናግረው፤ በቅርቡም ከ100 በላይ ለሚሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጥ ወይዘሮ የሺ ገልፀዋል።
ምርጫውን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ለማድረግም በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በተለያዩ ቋንቋዎች ትምህርት በመሰጠት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የምርጫ ክልል የምርጫ አስፈፃሚዎችን የመመልመሉ ስራም መጠናቀቁን ጠቁመው፤ በዚህም 2ሺ የሚሆኑ አስፈፃሚዎች በቋንቋቸው ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል ብለዋል።
የምርጫ አስፈፃሚዎች ገለልተኛ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ወይዘሮ የሺ የስራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት እንዲኖራቸው በተለይም የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎ ከባለፈው ምርጫ የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ ወይዘሮ የሺ ገለፃ የመራጮችና የእጩዎች ምዝገባ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከታህሳስ 22 ጀምሮ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ሚያዝያ 6 እና 13 ለሚካሄደው ምርጫም እስከ አሁን 26 የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክቶቻቸውን መምረጣቸውን ወይዘሮ የሺ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር