“ገዥውን ፓርቲ የሚጠቅሙ እየመሰላቸው በምርጫ ወቅት ችግር የሚፈጥሩ አስፈጻሚዎች አሉ”


አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ የፍትሕና የአስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ
ከአራት ወራት በኋላ ሚያዝያ 6 እና 13 ቀን 2005 ዓ.ም. በመላ አገሪቱ የአካባቢና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ይካሄዳል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ግልጽና ተዓማኒ ለማድረግ ደፋ ቀና ማለት ጀመርኩ ካለ ሰነባብቷል፡፡ ባስቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት የምርጫ ቁሳቁሶችን ከማሳተም፣ ከማዘጋጀትና ከማሠራጨት ጐን ለጐን ደግሞ፣ ቀደም ብሎ ማከናወን ቢገባውም በምርጫው ዙሪያ ውይይትና ሥልጠና በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ቦርዱ እያደረጋቸው ከሚገኙት የምርጫ ክንውኖች መካከል ታህሳስ 7 እና 8 ቀን 2005 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ኤክስኪዩቲቭ ሆቴል ለጋዜጠኞች የሰጠው የሁለት ቀናት ሥልጠና ተጠቃሽ ነው፡፡ ሥልጠናውን የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር ዶክተር ገብረ መድኅን ስምዖንና በተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ የፍትሕና የአስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ናቸው፡፡ አቶ አስመላሽ “የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግና አፈጻጸሙ” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ጥናታዊ ጽሑፍ ዙሪያ የምርጫ ቦርድ አባላትንና ሌሎች የምርጫ ክንውኖችን በሚመለከት ከሥልጠናው ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ አስመላሸ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ታምሩ ጽጌ እንደሚከተለው አዘጋጅቶታል፡፡

ጥያቄ፡- የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አባላት ገለልተኛ ናቸው ብለው ያምናሉ?

አቶ አስመላሽ
፡- የምርጫ ቦርድ አባላት ገለልተኛ ናቸው ወይስ አይደሉም ለማለት ዋናውና አንዱ መሠረታዊ ጉዳይ፣ የሚለዩበትን መሠረታዊ ነገር መፈተሽ ነው፡፡ የምርጫ ቦርድ አባላት ለሕገ መንግሥቱ መከበርና ማስከበር ታማኝ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ በማንኛውም መንገድ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይገባም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማክበርና የማስከበር ግዴታ የሌለው ሰው የምርጫ ቦርድ አባል ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ አንደኛውና የመጀመሪያው መመዘኛ ነው፡፡ ሁለተኛው መመዘኛና መሠረታዊ ነጥብ፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ መሆን አለባቸው፡፡ ነፃና ገለልተኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በመቀጠል የሥነ ምግባርና የሙያ ጉዳይ ይመጣል፡፡ ከዚህ አንፃር ስናየው በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በተገቢው ሁኔታ ተሠርቷል፡፡ ከ97 ምርጫ በኋላ የምርጫ ሕጉ ሲሻሻል በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገኝተው ነበር፡፡

በፓርላማም መቀመጫ ነበራቸው፡፡ “የምርጫ ቦርድ አባላትን በመስፈርቱ መሠረት መመልመል አለብን” የሚል ንዑስ ኮሚቴ ሲቋቋም፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲያስተባብሩ የነበሩት የኦፌዴን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ነበሩ፡፡ ሁሉም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ “ለምርጫ ቦርድ አባል የሚሆኑ ገለልተኛ ሰዎች አሉን” ብለው ዕጩዎችን ከነሙሉ የትምህርት ማስረጃዎቻቸው አቀረቡ፡፡ የጠቆሟቸው ዕጩዎች ለምርጫ ቦርድ አባልነት የተቀመጠውን መስፈርት ማሟላት አለማሟላታቸውን ራሳቸው ፓርቲዎቹ ተቀባብለው ጥናት አድርገዋል፡፡ ከጥናታቸው በኋላ መምረጥ ያለባቸውን መርጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል፡፡ ካቀረቧቸው ዕጩዎች መካከል ዘጠኙን ብቻ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል፡፡ ምክንያቱም ማቅረብ የሚቻለው ዘጠኝ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው የምርጫ ቦርድ አባላት የተሾሙት፡፡

ስለአመላመሉ ጉዳይ ስንናገር ከተቃዋሚ በኩል ስለሆንን ወይም ከገዥው ፓርቲ በኩል ስለሆንን ሳይሆን እውነታው ቀደም ብለን እንዳስቀመጥነው ነው የሆነው፡፡ በመስፈርቱ መሠረት እነዚህ ሰዎች መስፈርቱን አሟልተዋል በማለት ሁሉም ፓርቲዎች ተስማምተው ያቀረቧቸው ናቸው፡፡ መጨረሻ አካባቢ ማለትም የምርጫ ቦርድ አባላት እነማን መሆን እንዳለባቸው ከተስማሙ በኋላ የወጡ ፓርቲዎች አሉ፡፡ በምልመላው ላይ ግን ምንም ዓይነት ልዩነት አልነበረም፡፡ ከዘጠኙ የምርጫ ቦርድ አባላት ሦስቱ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተጠቆሙ ናቸው፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ አባላት አሿሿም በአፍሪካ የምርጫ መገምገሚያ ሪፖርት ላይ እንደ አንድ መሠረታዊ ነገር ተወስዷል ወይም ተቀምጧል፡፡

እኔ እስከማውቀው ድረስ በወቅቱ ከተቃዋሚ ፓርቲዎችም “የኢትዮጵየ ምርጫ ቦርድ ነፃና ገለልተኛ አይደለም” ብሎ የሚከራከር አንድም አባል አልነበረም፡፡ የምታስታውሱት ከሆነ የ2002 ምርጫ የሥነ ምግባር አዋጅ ላይ ውይይት ሲደረግ፣ “ይህንን ውይይት ማድረግ ያለበት ነጻና ገለልተኛ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሆን አለበት” በማለት መድረክ ጭምር ገለልተኛነቱን አረጋግጧል፡፡ አሁን አሁን ግን የሚመጡ አስተያየቶች አሉ፡፡ ምንም ይሁን ምንም የቦርዱን አባላት ለመመልመል በመስፈርቱ መሠረት ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳተፈ ስለነበር በገለልተኝነታቸው ላይ የሚነሳው ጥያቄ ተገቢነት የለውም፡፡

ጥያቄ፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገዥው ፓርቲ አባል ናቸው፡፡ የምርጫ ቦርድ አባላት ምንም እንኳን የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተሳተፉበት የመመልመል ሒደት ተመርጠው ሲቀርቡላቸው ሙሉ በሙሉ ተቀብለው እንዲሾሙ ለፓርላማ ማቅረባቸው እንዴት ሊታመን ይችላል? አባል ለሆኑበት ፓርቲስ አያዳሉም ተብሎ ይታሰባል?

አቶ አስመላሽ
፡- በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ይሾማሉ ማለት የተለመደ አሠራር ነው፡፡ ዳኞችም የሚሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ነው፡፡ በተለይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት የሚሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ነው፡፡ ሌሎቹ ዳኞች እንኳን በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አስተያየት ከተሰጠባቸው በኋላ ነው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርበው የሚሾሙት፡፡ የሁለቱ ግን በቀጥታ በራሱ አቅራቢነት ነው፡፡ ስለዚህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ከመሾማቸው አንፃር፣ ገለልተኛነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል ብሎ ማስቀመጥ ተገቢነት የለውም፡፡ በዓለም ላይ የተለመደው አሠራር ይኸው ነው፡፡ አንድ ጊዜ ስለዳኞች ነፃነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ጥናት ይደረግ ተባለና ለአገር ውስጥ አጥኚዎች ተሰጠ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ “ይህ መንግሥት ጥናት ሲባል የሚሰጠው ለውጭ አጥኚዎች ነው” ስለሚባል ነው እንዲያጠኑ የተሰጣቸው፡፡ የዳኞችን ነፃነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ሲያጠኑ አንድ የሰጡት አስተያየት አሁን ያነሳችሁትን ነው፡፡ “የእኛ ዳኞች ነፃና ገለልተኛ አይደሉም” ከሚል ነው ጥናታቸውን የጀመሩት፡፡

ምክንያታቸው ደግሞ ዳኞቹ የሚሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ ነው፡፡ በሁሉም የአውሮፓ አገሮችም ዳኞች የሚሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ ሲነገራቸው፣ “እነሱ በዲሞክራሲ የበለፀጉ አገሮች ናቸው” የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ፡፡ ጥናቱን ውድቅ አድርገን “ሲዳ” የሚባል የካናዳ ድርጅት መጥቶ እንዲያጠና አደረግን፡፡ ሲዳ በጥናቱ ያረጋገጠው የኢትዮጵያ የዳኞች የአሿሿም ሥርዓት በጣም ጥሩ ልምድ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ በሌላ አገር የሚደረገው ወደኛ አገር ሲመጣ የሆነ ያልሆነ ትርጉም ስለሚሰጠውና የጋራ ስምምነት የሚባል ባህል ስላልተፈጠረ፣ የግንዛቤና የልምድም እጥረት ስላለ እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት የምርጫ ቦርድ አባላት መሾማቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ እንደዚህ ካሰብንማ ፓርላማው ራሱ አብላጫ ድምፅ ያለው የአንድ ገዥ ፓርቲ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ፓርላማውም ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ነው ማለት ነው፡፡

ዋናው ነገር ማየት ያለብን በወቅቱ በፓርቲዎች ጠቋሚነት ቀርበው ከነበሩት ከ40 በላይ ዕጩዎች መካከል የቀረበውን መሥፈርት አሟልተው ገለልተኛ መሆናቸው የተረጋገጠ፣ ብቃት ያላቸው አባላት ዕጩ ሆነው መቅረባቸውንና መሾማቸውን ነው፡፡ ሌላው ይህ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ ብዙ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ይህንን እኛ ብቻ አይደለንም የምንመሰክረው፡፡ “የኢትዮጵያ ምርጫ ትክክል አይደለም” ብሎ ምስክርነት የሰጠው የአውሮፓ ኅብረት ሳይቀር በቦርዱ ነፃነትና ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ አላነሳም፡፡ ከፕሮፌሽን አንፃር ጥሩ መሆናቸውን አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ከገለልተኝነት አንፃር የሚነሳው ጥያቄ ተቀባይነትና ተጨባጭነትም አይኖረውም፡፡ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ገለልተኛ ሆነው እንዲፈጽሙ የተሾሙና ተጠሪነታቸውም ለፓርላማ መሆናቸውን ደማምረን ስናይ፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከገለልተኛነትና ከነፃነት አንፃር አጠያያቂ የሚሆንባት ነጥብ የለም ብለን በአጭሩ ማስቀመጥ እንችላለን፡፡

ጥያቄ፡- ምርጫ ለማስፈጸም የሚመደቡ ምርጫ አስፈጻሚዎችም ገለልተኛ አለመሆናቸው ይነገራል፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ አስመላሽ
፡- በእነሱ ላይ አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ችግር አለ፡፡ እውነታውን መደበቅ አንችልም፡፡ መደበቅም የለበትም፡፡ የሚያጋጥመው ችግር በምልመላ እንቅስቃሴ ላይ ብቻ ሳይሆን ካለን ልምድም ጭምር የሚከሰት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲን የሚጠቅም የሚመስለው ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ከዚህ በመነሳት አንዳንድ ምርጫ አስፈጻሚዎች ችግር ይፈጥራሉ፡፡ የሚጐዱት ግን ገዥውን ፓርቲ ጭምር ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንም ይጐዳሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ከግንዛቤ እጥረት ነው፡፡ በየጊዜው ግን ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡ ለምሳሌ ዘንድሮ ምርጫ ለማስፈጸም ከተመለመሉት ውስጥ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት አዲስ የተመለመሉ ናቸው፡፡ ሕግ በመጣስ አድልዎ ሲፈጽም የሚገኝ የምርጫ አስፈጻሚ ይቀጣል፡፡ የሚታሰሩም አሉ፡፡ የሚባረሩም አሉ፡፡ ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ በአመላመሉና በመስፈርቱ ደረጃ ሲታይ ግን መስፈርቱ ለምርጫ ጣቢያዎችና ለክልል አስፈጻሚዎችም በሚጠቅም መልኩ ባህል፣ ቋንቋንና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ መስፈርቶች ተቀምጠዋል፡፡ በዚያ መሠረት ነው የሚመለመሉት፡፡ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች በአንዳንድ ቦታዎች ችግር እንደሚፈጥሩ ሁሉ እታች ያሉ ምርጫ አስፈጻሚዎችም ችግር ይፈጥራሉ፡፡ ለገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ለተቃዋሚ ፓርቲም በማገዝ ችግር የሚፈጥሩ አሉ፡፡ የሁለቱም ድርጊት ጐጂ ነው፡፡

ጥያቄ፡- የምርጫ ሕጉ ከአራት ጊዜ በላይ ተሻሽሏል፡፡ ከሌሎች ሕጐች በተለየ ሁኔታ በአጭር ጊዜ በተደጋጋሚ ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ አስመላሽ
፡- ትክክል ነው፡፡ የምርጫ ሕጉ ተሻሽሏል፡፡ የተሻሻለበት ምክንያት ደግሞ ከመጀመሪያው ከ1987 ዓ.ም. ምርጫ ስንጀምር የነበረው የምርጫ ሕግ አጠቃላይ ይዘቱ ሲታይ ችግር የለበትም፡፡ ግን አልፎ አልፎ የሚታዩ ክፍተቶች አሉ፡፡ ሁልጊዜ ቅድመ ምርጫ ከተደረገ በኋላ፣ የዳግም ምርጫ ፍተሻ ይደረጋል፡፡ “ምን ምን ጥንካሬዎችና ምን ምን ክፍተቶች ነበሩ?” በሚል በምርጫው ዙሪያ ጥናት ይደረጋል፡፡ በዚህ መሠረት ክፍተቶች ካሉ ይስተካከላሉ፡፡ ይህ ደግሞ እኛ አዲስ ያመጣነው ወይም የጀመርነው ሳይሆን ሌሎች ያደጉ አገሮችም የሚያደርጉት ነው፡፡ ሁልጊዜ መፈተሽና መስተካከል አለበት፡፡ መሠረቱና ይዘቱ ተገቢና ትክክል ቢሆንም መስፈርቶቹ በየጊዜው መሻሻልና መስተካከል አለባቸው፡፡ ከ1997 ዓ.ም. በፊት የነበረው የምርጫ ሕግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባስቡ ያስገድድ ነበር፡፡ ይህ ትንሽ መሰናክል ይፈጥራል፡፡ ከዚህ አንፃር ታይቶ ተስተካክሏል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ፓርቲዎቹ ሲወያዩ ያሻሻሏቸው ነገሮች አሉ፡፡ የፓርቲዎች ተሳትፎ ምን ይሆናል? “አንድ ዕጩ፣ ዕጩ ሆኖ ሲንቀሳቀስ ከባድ ወንጀል ሲሠራ ካልተገኘ በስተቀር የሕግ ከለላ እንዲኖረው፣ እንዳይጠየቅ” የሚሉትና ብዙ ነገሮች ተሻሽለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ነው እየተሻሻለ ያለው፡፡  

ጥያቄ፡- ምርጫ እንዴት መካሄድ እንዳለበት ደንግጐ የሚገኘው ሕገ መንግሥቱ ለምን አይሻሻልም?

አቶ አስመላሽ
፡- ሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ ሕጐችን እንጂ ዝርዝር ሕጐችን አይዝም፡፡ ለምናካሂደው የምርጫ ሥርዓት እንቅፋት የሆነ አንቀጽ ሕገ መንግሥት ውስጥ  የለም፡፡ ቢተፈሽም የለም፡፡ እንቅፋት የሆነ ነገር እስከሌለ ድረስ ሕገ መንግሥቱን ለማስፈጸም በዝርዝር የሚወጡትን ሕጐች ማየት፣ መፈተሽና ማስተካከል የግድ ነው፡፡ “ሕገ መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቦርድ አባላትን አቅርበው እንዲያሾሙ ስላስቀመጣቸውና የፓርቲ አባል በመሆናቸው ምን ያህል ያስኬዳል?” ለሚለው ያስኬዳል፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ የሚያስቀምጠው ጥቅል ነገር ነው፡፡ ሌላውን “በዝርዝር ሕግ ይወሰናል” ብሎ ነው የተወው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ መንግሥቱ የሰጠን ሕግ ስላለ ይህንን ሕግ አላከብርም ማለት አይችልም፡፡ አስገዳጅ ነው፡፡ ፓርላማ ወንበር ያላቸው ፓርቲዎች በሚፈጥሩት መድረክ እንዲመካከሩበት ያደርጋል ይላል አዋጁ፡፡ ስለዚህ የምርጫ ሕግ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚይዝ በመሆኑ በየጊዜው መቃኘትና መሻሻል አለበት፡፡ ተገቢም ነው፡፡

ጥያቄ፡- በፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳና ዘመቻ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

አቶ አስመላሽ
፡- ማንኛውም ፓርቲ ፕሮግራሙንና ፖሊሲውን ለማስረዳት የምረጡኝ ቅስቀሳ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል፡፡ በተለይ በፖርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ላይ የሕዝብ የፋይናንስ ድጋፍ በመንግሥት እንደሚደረግ ተቀምጧል፡፡ የፐብሊክ ፋይናንስ ድጋፍ ሲባል ሦስት ነገሮችን ያካተተ ነው፡፡ የመጀመሪየው በጥሬ ገንዘብ የሚሰጥ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በዓይነት የሚሰጥ ሲሆን፣ ሦስተኛው አገልግሎት ማለትም የሬዲዮ፣ የቴሌቪዥንና የሕትመት ውጤቶች ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃንን እንዲያገኙ የተደረገበት ሁኔታ ነው፡፡ በመጀመሪያ ውይይት ያደረጉ ሰባት ያህል ፓርቲዎች የሰጡት አስተያየት የራሳቸውን ግምት ነው፡፡ ፓርቲዎቹ ከተወያዩ በኋላ የመገናኛ ብዙኃን ክፍፍሉ ምን መሆን እንዳለበት ተስማምተዋል፡፡ ይህ ማለት ግን እነዚህ ሰባት ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም ውሳኔ አስተላልፈዋል ማለት አይደለም፡፡ ቦርዱ ግን ሁሉም አስተያየት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ በአንድ ላይ ሆነው በጋራ ውይይት ያደረጉ አንድ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እንደ መድረክ ያሉት ደግሞ ባመኑበትና በተናጠል ተነጋግረው አስተያየታቸውን ለቦርዱ ሰጥተዋል፡፡ በተናጠል ተነጋግረው መጨረሻ ላይ ቦርዱ የሁሉንም ሐሳብ አሰባስቦ የመሰለውን በመቀበልና ያላመነበትን ውድቅ በማድረግ የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀማቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ሁሉም በቦርዱ የወጡ መመርያዎችና ደንቦች በዚህ መልክ ነው የወጡት፡፡ ነገር ግን ሰባቱ ወይም ስምንቱ ፓርቲዎች ጫና አደረጉ የሚባለው ትክክል አይደለም፡፡  

ጥያቄ፡- መስፈርቱ ምንድን ነው?

አቶ አስመላሽ፡
- መስፈርቱ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው መሆኑ ታውቋል፡፡ የጥራቱ፣ የዕጩ ብዛት፣ በክልሎች ምክር ቤቶችና በፓርላማ ያላቸው የወንበር ብዛት እንደመነሻ ያገለግላሉ፡፡ በጋራ መድረኩ ላይ ብቻ ያሉ ሳይሆኑ ሌሎቹም ተስማምተው ክፍፍል የተደረገበት ሁኔታ አለ፡፡ አጠቃቀሙን በሚመለከት አጀንዳ በመቅረፅና ጽሑፎች በማዘጋጀት የሚደረግ ውስንነት ሊሆን ይችላል፡፡ የባለሙያ እጥረትና ሌሎችም ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እውነታው ግን ሁሉም የገዥውን ፓርቲ ጨምሮ የተቀመጠላቸውን የመገናኛ ብዙኃን እየተጠቀሙበት አይደለም፡፡ እየተሻሻለ መሄዱ ግን ግድ ይላል፡፡

ጥያቄ፡- የፓርቲዎች ክርክር በቀጥታ ሥርጭት መደረግ ሲገባው፣ በስቱዲዮ ከተቀረፀና ከታረመ በኋላ በመገናኛ ብዙኃን መተላለፉን የሚቃወሙ ብዙ ናቸው፡፡ እርስዎ ይህን አስተያየት ይቀበላሉ?

አቶ አስመላሽ
፡- የቀጥታ ክርክር ማድረጉ በወቅቱ አከራክሯል፡፡ በድርድሩ የነበሩ ፓርቲዎች መኢአድን ጨምሮ በፓርላማ ወንበር ያላቸው ድርድር ሲደረግ በመገናኛ ብዙኃን ብሔር ብሔረሰቦችን የሚያጐድፍ ነገር ቢተላለፍ አገር ሊያጠፋ ይችላል፡፡ ቁጥጥር የሚደረግበት ቴክኖሎጂም የለም፡፡ ከዚህ አንፃር የሚተላለፍ ነገር ቀጥታ መሆን የለበትም፡፡ ተቀርጾ ፓርቲዎቹ የቱ መውደቅና የቱ መተላለፍ እንዳለበት ይከራከራሉ፡፡ በስምምነት አላስፈላጊ የሆነውን ያወጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ይተላለፋል፡፡ ከዚህ አንፃር ምንም ችግር የለውም፡፡ ሐሳባቸውን በነፃነት ከመግለጽ መብት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ቀጥታ ባለመሆኑ የሚቀር ነገር የለም፡፡ የሚቀረው ነገር የደጋፊ ጭብጨባ፣ አላስፈላጊ የሆነ ቃልና ሐሳብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተከባብሮ በሚኖር ብሔር ብሔረሰብ መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ሊያደርጉ የሚችሉ ቃላትን ለመቆጣጠር የሚደረግ ነው፡፡ በሁሉም ፓርቲዎች ስምምነት ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ገዥው ፓርቲ መገናኛ ብዙኃንን በፈለገው መንገድ ሲጠቀም ይስተዋላል፡፡ የመንግሥትንና የፓርቲን ሥራ ቀላቅሎ ከመሥራት ባሻገር፣ የመንግሥት ሥራ በማስመሰል የፓርቲውን ሥራ ሲሠራ ይታያል፡፡ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ የመገናኛ ብዙኃንን ሲጠቀም ይስተዋላል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡

አቶ አስመላሽ
፡- የፓርቲዎች መተዳደሪያ ደንብ ገደብ አስቀምጧል፡፡ ጋዜጠኛ መብትና ግዴታው ምንድነው? የመገናኛ ብዙኃን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች መብትና ግዴታ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ የገዥው ፓርቲ አስፈጻሚዎችም ይሁኑ የምክር ቤት አባላት፣ በተለይ ተወዳዳሪ የሆኑት፣ በሚሰጡት መግለጫና ዜና ላይ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ደንቡ አስቀምጧል፡፡ ፍትሕ እንዳይዛባ ጋዜጠኛም ክትትል ማድረግ እንዳለበት በሥነ ምግባር ሕጉም ተቀምጧል፡፡ ይህ ግን መለየት አለበት፡፡ ገዥው ፓርቲ በአጠቃላይ እንደ መንግሥት ሆኖ ከሚሠራው ሥራ ጋር መገናኘት የለበትም፡፡ ለምሳሌ “አሥር ዓመት ከተሐድሶ በኋላ” ተብሎ የሚሠራ ሥራ አለ፡፡ ይህ ቀደም ብሎ የታሰበ ሥራ ነው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊም እያሉ ጀምሮ ከ1994 ዓ.ም. በኋላ፣ “የተሐድሶ መስመሩ ያመጣው ለውጥ ምንድን ነው? ምን ለውጥ አሳይተናል? የታየው ክፍተት ምንድን ነው? እንዴት መቀጠል ይቻላል?” በሚል አጠቃላይ ግምገማ ይደረጋል፡፡ ይህ መሠራቱ ለምርጫ ከሚደረገው ዝግጅት አንፃር የሚታይ አይደለም፡፡ አንዳንድ አገሮች እንዳላችሁት በምርጫ ጊዜ ሆስፒታልና ትምህርት ቤት ሲመረቅ የሚከለክሉ አሉ፡፡ እኛ ግን ይህንን የሚከለክል ነገር የለንም፡፡ ግን በዚህ ምክንያት የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግና የተዛባ የመገናኝ ብዙኃን አጠቃቀም እንዲኖር መደረግ እንደሌለበት ተቀምጧል፡፡ ይህ በጥንቃቄ መታየት አለበት ያላችሁት ነገር ተገቢ ነው፡፡ በተለይ በዜና ጊዜ ሲቀርብ የሚታይ ሠፊ ትንታኔ አለ፡፡ ይህ አግባብ ስላልሆነ ገዥው ፓርቲም ማየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

ጥያቄ፡- መድረክ በሥነ ምግባር አዋጁ ላይ አለመፈረሙ ምን የሚያመጣው ጉዳት አለ? ለሕጉ ተገዥ የመሆን ግዴታ አለበት? ለሕጉ ተገዥ የመሆን ግዴታ እንዳለበት እየታወቀ፣ መፈረም አለበት ወይም ካልፈረመ እየተባለ በተደጋጋሚ ሲነሳ ይሰማል፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ አስመላሽ
፡- በጋራ መድረክ መሥራት ጥሩ ስለሆነ ነው፡፡ ፓርቲዎቹ የጋራ የምክክር መድረክ ሲኖራቸው ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና ለዴሞክራሲ ዕድገቱ ለሁሉም ጠቃሚ ነው፡፡ ችግር ሲኖርም በጋራ እየተወያዩ ለመፍታት ይጠቅማል፡፡ ከዚህ አንፃር ሥርዓቱን ያጠናክረዋል፡፡ ከግጭትና አላስፈላጊ መወዛገብ በትክክለኛ ሕጉን አክብሮ የመሥራት ነገር ለአገር፣ ለሕዝብና ለሁሉም የሚጠቅም ስለሆነ መድረክም ቢገባበት ጥሩ ነው፡፡ መድረክ ወደ ጋራ መድረኩ የሚገባ ከሆነ መፈረም አለበት ይባላል፡፡ የሥነ ምግባር አዋጁ አንድ ጊዜ ፀድቆ ወጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ ግለሰቦችንም ሆነ ፓርቲዎችን የሚገዛ ነው፡፡ ስለዚህ ለምንድነው ለመፈረም የሚገደደው? የሚለው ትክክል ነው፡፡ የሚፈርመው ግን አዋጁን እፈጽመዋለሁ ወይም አልፈጽመውም ብሎ አይደለም፡፡ በአገር አቀፍ መድረክ ከገዥው ፓርቲም ሆነ ከሌላው በጋራ ለመወያየት ወደ መድረኩ ለመግባት ከፈለገ መፈረም አለበት፡፡ ፊርማው እንደ ግዴታ የተቀመጠው የጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ አባል ለመሆን መፈረም አለበት በሚል ነው፡፡ ከዚህ ውጪ አይደለም፡፡ ገዥው ፓርቲ እያለ ያለው ካልፈረምክ ወደ ድርድር አትመጣም ሲባል ለመድረክ ብቻ ተብሎ የተቀመጠ ሳይሆን ለማንኛውም ፓርቲ ነው፡፡ በአገር አቀፍ የጋራ ምክክር መድረክ የሚገባ ከሆነ አዋጁን እቀበለዋለሁ በሚል እንዲፈርም ለማድረግ ብቻ ነው፡፡ 

ጥያቄ፡- የፓርቲዎች ቁጥር 75 እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት የጐላ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እየተስተዋለ አይደለም፡፡ የምርጫ ሰሞን አለሁ አለሁ ይሉና ጥፍት ይላሉ፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን የፖለቲካ ፖርቲዎች እየተዳከሙ ነው የሚሉ አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ አስመላሽ
፡- ዋናውና ማየት ያለብን ነገር ፓርቲዎችን የሚያዳክም ሕግ መኖር የለበትም፡፡ ፓርቲዎቹን የሚያዳክምና የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያጠብ ሕግ ካለ መስተካከል አለበት የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ምኅዳሩ ፓርቲዎቹ እንዳይፈጠሩና እንዳይጠናከሩ እንቅፋት የሚፈጥር አይደለም፡፡ በዚህ አገር 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች የሚይዙትን ፕሮግራም ሕዝቡ እንዴት ይቀበለዋል የሚለው ዋናው ጥያቄ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ከሌሎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች አንፃር ሲታይ በጣም ትንሹ ነበር፡፡ በሒደት አድጐ ምን ያህል ታሪክ እንደሠራ የምታውቁት ታሪክ ነው፡፡ ትንሽ መሆን አለመሆን አይደለም፡፡ ነባራዊ ሁኔታውን የሚቀይር፣ ሕዝቡን ከጐኑ የሚያሠልፍ ፖሊሲ ይዞ መንቀሳቀስ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ የሕዝብን ጥያቄ የመመለስ ጉዳይ ነው፡፡ የአገሪቱን ችግር የመፍታት ጉዳይ ነው፡፡ ፓርቲው ካደገ የገቢ ምንጩም እያደገ ይሄዳል፡፡ ይህንን የሚከለክል ሕግ ደግሞ የለም፡፡ ማየት ያለብን ከዚህ አንፃር ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ እነዚህን ፓርቲዎች ለማዳከም የሚሠራው ሥራ የለም፡፡ ይልቁንም ከገዥው ፓርቲ ጋር አብረው የሚሠሩ ፓርቲዎች በ2002 በተፈጠረው የምርጫ ሁኔታ 99.6 በመቶ የፓርላማ ወንበር የያዘ በመሆኑ የዕለት ተዕለት የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እያከፋፈለ ነው፡፡ ይህንን የሚያደርገው ገንዘብ ስለበዛበት አይደለም፡፡ የገንዘብ እጥረታቸውን ለማቃለል ነው፡፡ ስለዚህ ገዥው ፓርቲ ሌሎች ፓርቲዎችን ለማበረታታት የሚሠራው ሥራ እንዳለም ማየቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ጥያቄ፡- እስካሁን በተደረጉ የምርጫ ውድድሮች የመጨረሻው የውጤት ሲታወቅ ውዝግብ ሲፈጠር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ የተነሳም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ውጤቱን አንቀበልም ሲሉ ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ሊቀረፍ የሚችለው እንዴት ነው?

አቶ አስመላሽ
፡- ውጤት መቀበል አንዱ መሠረታዊ ሕግ ነው፡፡ ውድድር ተደርጐ ውጤት የማይቀበል ከሆነማ ዘለዓለም ትርምስ ነው የሚሆነው፡፡ እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ምርጫም አያስፈልግም፡፡ በትክክለኛ የሕግ ማዕቀፍ ትክክለኛ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ የሚኖረውን ውጤት መቀበል ነው፡፡ ተጭበርብሯል የሚልና ቅሬታ ያለው ከምርጫ ቦርድ ጀምሮ እስከ ፍርድ ቤት ሊሄድ ይችላል፡፡ ፍርድ ቤት ወይም ምርጫ ቦርድ የሚወስኑት ነገር አስገዳጅ ነው፡፡ ቦርዱ አይደገም ቢል እንኳን ፍርድ ቤት መደገም እንዳለበት ውሳኔ ካስተላለፈ ምርጫው ይደገማል፡፡ ሕጋዊ የሆኑ አካሄዶችን ተከትለን ችግሮችን መፍታት አለብን፡፡ ከዚህ ውጪ ውጤት አልቀበልም ብሎ መሄድ ተገቢ አይደለም፡፡ የ97 ምርጫን ማስታወስ ይቻላል፡፡ ተቃዋሚዎች በመጀመሪያ የአዲስ አበባ ምርጫ እንኳን ተጭበርብሯል ነበር ያሉት፡፡ ነገር ግን ከአንድ ወንበር ውጪ ሙሉ በሙሉ ቅንጅት ያሸነፈ መሆኑ ሲገለጽ ደግሞ የአዲስ አበባ ምርጫ ጥሩ ነው አሉ፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ ምንም ይሁን ምንም ውጤትን በፀጋ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የዜጎች ድምፅ ስለሆነ ዋጋ አለው፡፡ ችግር ካለ በአግባቡ መጠየቅ ይቻላል፡፡ 

ጥያቄ፡- በአንዳንድ ሥፍራዎች አንድ ዜጋ ከሁለትና ከዚያም በላይ በተለያዩ ቦታዎች የሚመዘገብበት ሁኔታ ባለፉት ምርጫዎች እንደነበረ ይታወቃል፡፡ አንድ ሰው ስንት ጊዜ ነው መመዝገብ ያለበት? ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ሁለትና ከዚያ በላይ ተመዝግቦ የተገኘበት የምርጫ ጣቢያ ውጤት በምን ሕግ ነው የሚስተናገደው?

አቶ አስመላሽ፡
- የመራጮች ምዝገባ ከአንድ ጊዜ በላይ መሆን የለበትም፡፡ ወይም ምርጫ ጣቢያው መመዝገብ የለበትም፡፡ እንደተባለው አልፎ አልፎ ሁለትና ሦስት ቦታዎች ተመዝግበው የሚገኙ አሉ፡፡ ይህ በወንጀል ያስቀጣል፡፡ የተቀጡም አሉ፡፡ በ2002 ምርጫ ድሬዳዋ አካባቢ የተቀጡ አሉ፡፡ አጭበርብሮ መመዝገብ ወንጀል ነው፡፡ ምዝገባ ካለቀ በኋላ ለአምስት ቀናት ለሕዝቡ ይገለጻል፡፡ የማይታወቅና በዚያ ቀበሌ ነዋሪ ያልሆነ ከስድስት ወር በታች የኖረና ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ተመዝግቦ ከሆነ ለሕዝቡ ይገለጻል፡፡ ችግር ከተገኘ ይታረማል፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ ያጋጠሙ ችግሮች ነበሩ፡፡ ወደፊት እየታረሙ መሄድ አለባቸው፡፡ 

ጥያቄ፡- የግል ተወዳዳሪ ዕጩዎች የመገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ አስመላሽ
፡- የግል ዕጩ እንቅስቃሴ በሕዝብ ገንዘብ ድጋፍ የሚሸፈን አይደለም፡፡ የግል ዕጩ ከተቻለ ወደፊት እንዳይወዳደር መደረግ አለበት፡፡ ግለሰቦች ሳይሆኑ ፓርቲዎች ናቸው ፖሊሲና ፕሮግራም ያላቸው፡፡ ለምሳሌ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫዎች አሉ፡፡ 547 ግለሰቦች አሸነፉ ብለን እናስብ፡፡ ምን ያመጣሉ? ፖሊሲና ፕሮግራም ያለው መንግሥት መመሥረት አይችሉም፡፡ ከዚህ አንፃር ነው መታየት ያለበት፡፡ በእርግጥ የግለሰቦች መወዳደር አልተከለከለም፡፡ የሚከለክሉ አገሮች ግን አሉ፡፡ የሰብዓዊ መብትን ማፈን ነው ተብሎ መከራከር ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን መታየት ያለበት ለዜጎች ከሚያስገኘው ጥቅም አንፃር መሆን አለበት፡፡ በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን እንዳይጠቀሙ፣ የገንዘብ ድጋፍ የማይደረግላቸውና ለፓርቲዎች ማድላቱ ከዚህ የመጣ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙኃንን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙ የሰዓት ድልድሉን የሚያወጣው ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ከሆነ፣ ፓርቲዎች የሚያደርጉትን ክርክር መተላለፍ አስመልክቶ የሚወስነው የጋራ የምክክር መድረኩ ከሆነ፣ የመንግሥትና የፓርቲ ሥራ ተቀላቅሎ ሲሠራ ማስቆም ካልቻለ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በተሸራረፈ ሥልጣን እየሠራ እንዴት ያለማንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት ሥራውን እያከናወነ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ አስመላሽ፡
- ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን የሚሠራው ከምርጫ ቦርድ ጋር በመመካከር ነው፡፡ ውሳኔውን የሚወስነው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ወሳኝ ሚና የለውም፡፡ ነገር ግን የአገሪቱን የመገናኛ ብዙኃንን ሁኔታ የሚከታተለው እሱ ስለሆነ የአየር ሰዓት ክፍፍሉ ምን መምሰል እንዳለበት ተመካክሮ ይወስናል ከሚል አንፃር እንጂ የምርጫ ቦርድን ሥልጣን ለማሳነስ አይደለም፡፡

ጥያቄ፡- የድምፅ መስጫ ሰዓትን ማራዘምና ማሳጠርን በሚመለከት በግልጽ የተቀመጠ ነገር አይታይም፡፡ ቦርዱ እንደፈለገ የማራዘምና የማሳጠር መብት አለው ማለት ነው?

አቶ አስመላሽ
፡- ቦርዱ እንደፈለገ የማስረዘም ወይም የማሳጠር መብት የለውም፡፡ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ብቻ ድምፅ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ለመምረጥ ተሠልፈውና በምርጫ ጣቢያ አጥር ግቢ ውስጥ ያሉ ዜጎች፣ ሰዓቱ ካለፈባቸው እነሱ ድምፅ እስከሚሰጡ ድረስ ብቻ ሊራዘም ይችላል፡፡ አዳዲስ ሰዎችን ግን ሊቀበል አይችልም፡፡ ይህም የሚደረገው በአካባቢው ያሉ አስመራጮች በሚወስኑት ሳይሆን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው የሚወስነው፡፡

ጥያቄ፡- ብዙ ጊዜ ችግሮች ሲከሰቱ የሚስተዋለው ከድምፅ ቆጠራና ውጤት አገላለጽ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እከሌ የሚባለው ፓርቲ ሊያሸንፍ ይችላል ተብሎ ከሚነገር ትንበያ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው፡፡ ከሕግ አኳያ የምርጫ ውጤት አገላለጽን በሚመለከት ቢያብራሩልን? በሌሎች አገሮች ትንበያ እየተሠራበት ከመሆኑ አንፃርስ እንዴት ይታያል?

አቶ አስመላሽ
፡- ትንበያን የሚፈቅዱም የሚከለክሉም አገሮች አሉ፡፡ ይህ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት ጋር የሚጋጭ ነገር የለውም፡ በእኛ አገር ድምፅ ሲሰጥና ሲቆጠር ትንበያ የሚከለከለው የሕዝቡን የዴሞክራሲ ዕድገት፣ ባህልና አጠቃላይ አስተሳሰብን ከግምት ውስጥ አስገብተን ብናየው ጥሩ ነው፡፡ “እከሌ የሚባል ፓርቲ አሸነፈ ወይም እንደሚያሸንፍ ገለጸ” ሲባል የሚሆነው ምንድን ነው? ለሌላው ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት የተሠለፈውና ከቤቱ በመምጣት ላይ ያለው አቋርጦ ይወጣል፣ ይመለሳል፣ ወይም ለማያምንበት ፓርቲ ድምፅ ሰጥቶ ይመለሳል፡፡ ያንን ታሳቢ በማድረግ ነው የማይፈቀደው፡፡

ጥያቄ፡- የምርጫ ሕጉ እንዲሻሻል የተደረገው ምርጫ 97ን ታሳቢ ወይም መነሻ በማድረግ ነው ይባላል፡፡

አቶ አስመላሽ
፡- ሕጉ እንዲሻሻል የተደረገው በ97 ምርጫ ምክንያት በተፈጠረ ግጭት አይደለም፡፡ ሕጉን መጀመሪያ የቀረፅነው የአይዲኢኤን ዶክመንት ይዘን ነው፡፡

ጥያቄ፡- የምርጫ ታዛቢዎችን በሚመለከት ሁሉም ታዛቢዎች ከአገር ውስጥ መሆን እንዳለባቸው ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ እንዳስፈላጊነቱና መንግሥት ካመነበት ብቻ የውጭ ታዛቢዎችን ሊጋብዝ ይችላል ተብሏል፡፡ መንግሥት የሚያምንበትና ሊጋብዝበት የሚችልበት መስፈርት በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ ለምን?

አቶ አስመላሽ
፡- ምርጫ የሚታዘቡት በማኅበራትና በበጎ አድራጐት ኤጀንሲ ሥር ባሉ ማኅበራት ውስጥ የሚሠሩ ናቸው፡፡ መስፈርትም አለው፡፡ ጥቅሙም ምርጫው ነፃና ገለልተኛ ነበር አልነበረም ሲባል ምስክርነት ለመስጠት ነው፡፡ ሌላ ምንም ትርጉም የላቸውም፡፡ ይህ ይጨመር ወይም ይቀነስ ብለው የሚሰጡት አስተያየት ለድኅረ ምርጫ ግምገማ ሊጠቅም ይችላል፡፡ የምርጫ ሕግ ለማሻሻልም የሚሰጡት አስተያየት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ የውጭ አገር ታዛቢን በተመለከተ እንደየአገሩ ይለያያል፡፡ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችን ከእኛ አገር ጋር በንፅፅር ማስተያየቱ የሚከብድ ይሆናል፡፡ ደቡብ አፍሪካና ሩዋንዳ ከእኛ ጋር የሚመሳሰሉት በከፊል ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊና ልማታዊ አስተሳሰብ በተወሰነ ደረጃ የሚከተሉ አገሮች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ስናየው የአፍሪካ አገር ታዛቢዎች የሚገኙት የፈረምነው ነገር ስላለ ነው፡፡ በአፍሪካ የዴሞክራሲና የምርጫ ስምምነት እያንዳንዱ አገር ምርጫ ሲያደርግ ከኅብረቱ ታዛቢ መላክ እንዳለበት ያስገድዳል፡፡ ሌሎችን አገሮች መጋበዝ ግን በአማራጭ ነው፡፡ አስገዳጅ አይደለም፡፡ ሥጋት ስላለም አይደለም፡፡ የሚጠራቸው ምርጫ ቦርድ አይደለም፡፡ መንግሥት ከፈለገ ሊጠራቸው ይችላል፡፡ መንግሥት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ይጠቅማሉ ብሎ ካሰበ ሊጠራቸው ይችላል፡፡ ብጠራቸው ትርምሱና ሁከቱ ይበዛል እንጂ ምንም ፋይዳ የለውም ብሎ ካመነ ላይጠራም ይችላል፡፡

ጥያቄ፡- በፓርቲዎች መካከል በምርጫ ምክንያት በሚነሱ ግጭቶች አፈታት ዙሪያ የሕግ ባለሙያዎች ያላቸው ዕውቀትና ችሎታ እስከምን ድረስ ነው? በሚገባስ ያውቁታል?

አቶ አስመላሽ
፡- ትክክል ነው፡፡ ጥረት እየተደረገ ነው ያለው፡፡ የተለያዩ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ነው፡፡ የፍትሕ አካላትም፣ ዜጎችም፣ የመገናኛ ብዙኃንና ማኅበረሰቡ የምርጫ ሕግንና ተጓዳኝ ነገሮችን በደንብ ማወቅ አለባቸው፡፡ ይህ ከሆነ እንከን የሌለበት ሰላማዊ የምርጫ ሥርዓት ይካሄዳል የሚል እምነት አለኝ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር