አሞራ ገደልና የዓሳ ገበያው


በሔኖክ ረታ
ቀደም ሲል አካባቢውን ለሚያውቀው ጎብኚ የአሞራ ገደል አሰያየም በቀጥታ ከአካባቢው ተፈጥሯዊ ሁኔታ ጋር ስለመዛመዱ መናገር ይችላል፡፡
ከከተማዋ ፈጣን ዕድገትና በየአቅጣጫው ከተስፋፋው የሥራ ዕድል ጋር ተያይዞ ግን ለከተማዋ ጀባ የተባለው ትኩረት ለዚህም የሐይቁ ታዋቂ ስፍራ እንደ ፀበል ደርሶ በመጠኑም ቢሆን የአጥር መከለያ ተሠርቶለትና ከዚህ በፊት እዚህም እዚያም ይጠባበስ የነበረው የዓሳ ምግብ በወጉ እየተዘጋጀ ለተመጋቢው መቅረብ ጀምሯል፡፡

እንደዚያም ሆኖ ግን ይህ ዝነኛ የሐይቁ ክፍል አሁንም ቢሆንም እንደሌላኛው የሐይቁ መዳረሻ በሰንደቅ ዓላማና በቀለማት ባሸበረቁ ጀልባዎች፣ አበቦችና የማስታወቂያ ሰሌዳዎች የደመቀ አይደለም፡፡ ይልቁንም ዓሳ ጎርጓሪ ወፎች፣ እነ አባ ኮዳ፣ አባጆፌዎችና ሌሎቹም ዓሳ ተመጋቢ ወፎች እንደትናንቱ ግቢውን ወረው፤ ከዓሳ አጥማጆች የሚያፈተልኩትን ጥቃቅን ዓሶችንና ከበላተኛው ተርፈው የተጣሉ ትርፍራፊዎችን እየተሻሙ ሲለቅሙ የሚታዩበት እንጂ፡፡

ለሁለት በተከፈለው ሰፊ ግቢ በአንደኛው በር የመግቢያ ትኬት እየተቆረጠበት በፓርክ (መናፈሻ) ውስጥ ፎቶግራፍ ለመነሣት የሚቻል ሲሆን በሌላኛው በር ደግሞ የዓሳ ጥብስና ሾርባን ለመመገብ ብቻ ታስቦ በነፃ የሚስተናገዱበት በር ይገኛል፡፡

በዚህ በር በስተግራ በኩል መደዳውን እንደ ሱቅ የተደረደሩት ደሳሳ ቤቶች እንደዋዛ በደረደሯቸው የመመገቢያ ጠረጴዛና ወንበሮች ተኮልኩሎ ለሚጠብቃቸው ተመጋቢ ፊሌቶ የተሰኘውን የአካባቢውን ተወዳጅ ዓሳ የሚጠበስባቸውና ሾርባው የሚዘጋጅባቸው ኩሽናዎች ናቸው፡፡ ‹‹ኧረ እባካችሁ! ቆየ እኮ!....›› ‹‹ሾርባው ይቅደም!›› ወዘተ የሚሉ የደንበኞች አቤቱታ በጭብጨባ ታጅበው ከዚህም ከዚያም ይሰማሉ፡፡ ጫጫታውና ግርግሩ በአንድ የሐይቅ ዳር ዙርያ እየተዝናኑ ሳይሆን በአንድ የደራ የገበያ መንደር ውስጥ ዘልቀው እንደገቡ ያስታውስዎት ይሆናል፡፡

የእነዚህ ዓሳ ቤቶች ዋነኛ ደንበኞች የአካባቢው ነዋሪዎች ይሁኑ እንጂ ማንኛውም የከተማው ነዋሪም ሆነ ከተማውን ለመጎብኘት እግር ጥሎት ብቅ ያለ ጎብኝ ሳይቀር በብዛት ይስተናገድበታል፡፡ ከዓሳ ነጋዴዎችም ሆነ ወደ ስፍራው ጎብኝዎችን ከሚያመላልሱ የባጃጅ ሾፌሮች መረዳት እንደተቻለው የተለመደ ነው፡፡ ታዲያ የእነዚህ ፀጉረ ልውጦች ዋናው መስህብ በስፍራው የሚታዩት ዓሳ በሊታ ወፎች ወይም ደግሞ በእርጅና ብዛት የወላለቁትና ዓሳን ከሐይቁ ዳር ለማጥመድ የሚያገለግሉት ጀልባዎች አይደሉም፡፡ በእነዚያ ደሳሳ ጓዳዎች በፍጥነት ተጠብሰውና ሾርባ ሆነው በርካሽ ዋጋ የሚቀርቡት ዓሳዎች እንጂ፡፡ በአንደኛው ዓሳ ቤት ውስጥ ዓሳ ሲጠብስና እንግዶቹን መለስ ቀለስ እያለ ሲያስተናግድ ያገኘነው ዓለማየሁ የተባለ ወጣት የሰውን ትዕዛዝ መቀበሉና ወዲያውም ደግሞ በመጥበሻ ላይ የተጣዱትን ዓሳዎች ማገለባበጡ የተለመደ ውሎው እንደሆነ ገልጾ የጥብሱንም ሆነ የሾርባውን ጣዕም በጠበቀ መልኩ ደንበኞቹን ለማስደሰት እንደሚጥር ነግሮናል፡፡

ከማብሰያዎቹ ደጃፍ ፊት ለፊት ካሉት የጥላ ዛፎች ሥር ቁጭ ብለው ትኩስ ዓሳዎቻቸውንና የዓሳ ሾርባቸውን ከሚመገቡት እንግዶች መካከል ፀጉረ ልውጦቹ የስፔንና የስዊድን ዜግነት ያላቸው ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ እንደ አገሬው በላተኛ ሁሉ እነሱም አቅማቸው በፈቀደ መልኩ የቀረበላቸውን ማዕድ ሲመገቡ ለተመለከታቸው ለአካባቢው እንግዶች ሳይሆኑ የዘወትር ደንበኞች ነበር የሚመስሉት፡፡ ‹‹እንዴ! በጣም ነው የሚጣፍጠው እኮ፡፡ እኔ በበኩሌ የትም ቦታ እንዲህ ዓይነት ጣፋጭ ዓሳ በልቼ አላውቅም፡፡ ልዩ ነው፤›› ስትል አስተያየቷን ለሪፖርተር ያካፈለችው ስፔናዊቷ ሊንዳ ሙር ጠግባ የምትተው እስከማይመስል ድረስ ዓሳን በብልሃት ሳይሆን በትኩሱ ስትሰለቅጠው ነበር፡፡ ተጓዳኟ ላርሰንም የኢትዮጵያ ዓሳን ሲመገብ የመጀመርያው አለመሆኑን ገልጾ እንደዚህኛው ጣፋጭ የዓሳ ጥብስ ግን በየትም ቦታ እንዳልተመገበ በኩራት ‹‹በጣም ጣፋጭ!›› ሲል ነበር ምላሹን የሰጠው፡፡

በደጅ የሚበላውና የሚጠጣው ማዕድ በእንዲህ መልኩ እያለ የተወሰኑ ዓሳዎችን በትከሻው ላይ ባነገበው ዱላ (በትር) ጫፉ በገመድ አንጠልጥሎ ከአንደኛው የዓሳ መጥበሻ ጓዳ የገባውን ወጣት ማንነት ለመጠየቅ አብረነው ዘለቅን፡፡ ወጣቱ ሰሎሞን ይባላል፡፡ ዋናተኛና ዓሳ አጥማጅ መሆኑን ካወጋን በኋላ ያለንበት ክፍል የደንበኛው ዓሳ መጥበሻ መሆኑን ካስተዋወቀን በኋላ ዓሳውን በምን ያህል ዋጋ እንደሚሸጥለት ከደንበኛው ጋር መደራደሩን ቀጠለ፡፡ ከተወሰነ ንግግር በኋላም በአሥር ብር ሊሸጥለት ተስማምቶ በትከሻው ላይ ያንጠለጠላቸውን ዓሳዎች በአንደኛው የክፍሉ ጥግ ከነበረ የቅርንጫት ወንፊት ላይ ጣላቸው፡፡ ‹‹ብዙም አትራፊ አይደለም፡፡

ከእኛ እነሱ ናቸው በደንብ የሚያተርፉት፡፡ በዚያ ላይ የዓሳ እጥረቱም አለ፤›› ሲል ነበር ሰሎሞን ስለገበያው አስተያየቱን የሰጠው፡፡ በሌላ በኩል የዓሳ ሾርባና ጦሮሾ (ቂጣ) በሦስት ብር ገዝቶ ሲመገብ ያገኘነውና ማንነቱን ለመግለጽ ፈቃደኛ ያልነበረው ወጣት በሸንኮራ አገዳ ሻጭነት እንደሚተዳደር ገልጾ በአካባቢው እንዳደገና ዕድሜ ልኩንም የአሞራ ገደልን ዓሳና የዓሳ ሾርባ ሲመገብ መኖሩን ከጠቆመ በኋላ አሁን ላይ ግን የዓሳ ገበያውን መድራት ተከትሎ በተፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ከዓሳ ተመጋቢነት ወደ ዓሳ ሾርባ ተጠቃሚነት እንደተለወጠ አብራርቷል፡፡ ‹‹በቀን ሁለትና ሦስት ጊዜ ለዓሳ አሥራ አምስት ብር መክፈል ስለማይቻል ነው ሾርባውን የምጠጣው፤›› ብሎን ሸንኮራ አገዳውን ወደሚቸረችርበት ዛፍ አመራ፡፡

በእርግጥም ከላይ የተጠቀሰው ወጣት ብቻ ሳይሆን ሌሎች መሰሎቹም ተወልደው ባደጉበት አካባቢ እንደ ልብ የሚገኘውን ዓሳ መመገብ አልቻሉ ይሆናል፡፡ የከተማዋ እንግዶች ግን ጠዋትም ሆነ ማታ አሞራ ገደል ብለው መጥተው እዚያው ተመርቶ እዚያው የሚበላውን ዓሳና የሚጠጣውን ሾርባ ሳይቀምሱ የሚመለሱ አይመስሉም፡፡ ይህን የአካባቢውን የቆየ አሉታዊ ስያሜን በተሻለ ሁኔታ የሚቀይረው የዓሳ ጠባሾች የደራ ገበያና የአካባቢውን መሻሻል እንደ መልካም ሥራ የሚቆጥሩት እንዳሉ ሁሉ በአካባቢው ያለውና አሁንም ድረስ ያልተለወጠው የጽዳት ሁኔታ ከምግብ ቤቶቹ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ለጤናም ሆነ ለአካባቢ ብክለት መንሥኤ እንዳይሆን ‹‹የጽዳቱ ነገር ይታሰብበት›› ሲሉ አስተያየታቸውን ለግሰዋል፡፡ በሌላ በኩል የአካባቢውን ነዋሪ የመግዛት አቅምንም ያገናዘበ ገበያ ይሁን ሲሉም ያሳስባሉ፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com/life-art-culture/299-life-art-culture/8586-2012-11-21-07-05-20.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር