ሹመት ብቻ ሳይሆን ሽረትም እንጠብቃለን


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለፓርላማ ያቀረቡትን ሹመት ፓርላማው አፅድቆታል፡፡ ተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችም ተሹመዋል፡፡
እያንዳንዱ ሹመት በፓርቲ ውስጥ ተሳትፎን ያረጋገጠ፣ አመኔታ ያሳደረ፣ የሕዝብ ጥቅምና ክብርን ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ መሆኑን አደራ በማለት ልዩ ትኩረት ሰጥታችሁ አረጋግጡ፣ ወስኑ፣ ፈጽሙ፣ ከማለት በስተቀር ለምን ሾማችሁ አንልም፡፡ ተሿሚዎች ኃላፊነታቸውን በሚፈለገው ብቃት፣ ሥነ ምግባርና ፍጥነት ሲወጡ ለማየት እንጓጓለን እንጂ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በአጠቃላይ ለመንግሥት፣ መንግሥታዊ ሥልጣን ለያዘው ኢሕአዴግ አንድ ዓብይና ጠቃሚ እንዲሁም አስቸኳይ የሆነ የምናቀርበው ጥያቄ ግን አለን፡፡

ጥያቄያችንም ስለመሾም ስታስቡ ስለሚሻሩም ታስባላችሁ ወይ? የሚል ነው፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥ ከተፈለገም ክፍት ቦታ ላይ መሾም ብቻ አይደለም ቁም ነገሩ፡፡ የተያዘ የሥልጣን ወንበር ካለና ወንበሩ ላይ የተቀመጠው ሹምም ብቁ ካልሆነ፣ ከሥልጣኑ በማንሳት የተሻለ መሾም አስፈላጊ መሆኑን አምናችሁ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ናችሁ ወይ? የሚል ነው፡፡

መሾም አለባቸው ከሚለው ጎን ለጎን መሻር አለባቸው የሚባሉ እንዳሉም መታመን አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የኃላፊነትና የሥልጣን ወንበሮች ላይ ተቀምጠው ሥራቸውን በሕግ፣ በግልጽነት፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ መወጣት ያልቻሉ አሉ፡፡ በአቅም ማነስ፣  በሥነ ምግባር ጉድለትና በፖለቲካዊ አመለካከት ምክንያት፡፡

መንግሥትም ሆነ ኢሕአዴግ ይህንን ሁኔታ በድፍረትና በቆራጥነት አይተው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት የማይወጡትን ከኃላፊነት ማንሳት አለባቸው እንላለን፡፡

ብቁዎችን ሾሜያለሁ ከማለት ጎን ለጎን ብቃት የሌላቸውን ሽሬያለሁ ወይም እሽራለሁ መባል አለበት፡፡ ስለሚኒስትሮችና ኮሚሽነሮች ብቻ አይደለም እያነሳን ያለነው፡፡ በተለያዩ የሥልጣን እርከኖች ያሉትን በሙሉ በመፈተሽና በመገምገም ብቃትና ሥነ ምግባር የሌላቸውን መሻር ወይም ማባረር ያስፈልጋል እያልን ነው፡፡ ያውም በአፅንኦት!!!

በፌዴራል ደረጃ ብቻ ስላለው ሥልጣን አይደለም እየተነጋገርን ያለነው፡፡ በክልሎችም እንደዚሁ ብቁዎችን እንሾማለን ሲባል ብቃት የሌላቸውን እንሽራለን በሚል መታጀብ አለበት፡፡ ክፍት ቦታ ሲኖርና ሲገኝ እንሾማለን መባል ብቻ የለበትም፡፡

እከሌ ወይም እከሊት ብቃት ስላለው ወይም ስላላት የተሻለ ኃላፊነት እንስጥ ሲባል፣ እከሌና እከሊት ግን ሕዝቡን እያገለገሉ ስላልሆኑ እንሻራቸውና በምትካቸው የተሻለ ይሾም የሚለው መኖር አለበት፡፡

መፈራራት ካልሆነ በስተቀር ኢሕአዴግ አቅምና ብቃት የሌላቸው፣ በጉቦና በሙስና የተዘፈቁ ሹሞች እንዳሉት አያውቅም አንልም፡፡ ያውቃል፡፡ መንግሥትም አያውቅም አንልም፡፡ ያውቃል፡፡ ያውቃል ብቻ ሳይሆን የግል ሌቦች ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥት ሌቦችም አሉ ብሎ በይፋ መናገሩ ይታወሳል፡፡

ስለዚህ ጥያቄያችን የመንግሥት ሌቦች ይነሱ፣ የመንግሥት ሌቦች ይሻሩ፣ የመንግሥት ሌቦች ለፍርድ ይቅረቡ፣ የመንግሥት ሌቦች ተጠያቂ ይሁኑ ነው፡፡ ሕዝብም እያየ፣ እያስተዋለ፣ እየታዘበና እያዘነ ነው፡፡ ሕዝብን ለማገልገል ቃለ መሀላ ፈጽመው መንግሥት ከሾማቸው በኋላ ሕዝብንና አገርን ትተው ለግል ሀብትና ንብረት የሚሯሯጡ ሹሞች እንዳሉ ሕዝብ እያየ ነው፡፡

አገርንና ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ግለሰብንና ባለገንዘብን የሚያገለግሉ ሹሞች እንዳሉ ሕዝብ በዓይኑ እያየ በጆሮው እየሰማ ነው፡፡ አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁሌም፡፡ ሌላውን ሕግ አክብር፣ ሥነ ሥርዓት ይኑርህ፣ በአገርና በሕዝብ አትቀልድ እያሉ እየወነጀሉና መግለጫ እየሰጡ፣ እነሱ ራሳቸው ግን ሕግ ሳያከብሩ፣ ሥነ ሥርዓት ሳይኖራቸው፣ በአገርና በሕዝብ ሲቀልዱና ሲያስቀልዱ ይታያሉ፡፡

‹‹ሹሞች›› ተብለው ተቀምጠው ‹‹ተላላኪዎች›› መባልን የመረጡም አሉ፡፡ ተላላኪዎች ደግሞ ከሹመት ይሻሩ፣ ይባረሩ ነው እያልን ያለነው፡፡ በተግባር እነዚህን ሰዎች ለመሻር ቀላል እንዳልሆነ ይገባናል፡፡ ለኢሕአዴግም ለመንግሥትም ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹የመንግሥት ሌቦች›› የያዙት የሥልጣን ስፋት በካሬ ሜትር ሲለካ ‹‹የሕዝብ አገልጋዮች›› ከያዙት ይዞታ በላይ ሊሰፋ ይችላል፡፡ ከላይ ከላይ በቀላሉ ቢታወቅም ውስጥ ለውስጥ ያላቸው ኔትዎርክ ግን ሰፊና የተወሳሰበ ነው፡፡ የተበላ ቢቃወማቸውም የበላ ይደግፋቸዋል፡፡

በመሆኑም ትግሉ ቀላል ነው ማለት አይደለም፡፡ ትግሉ ቀላል ባይሆንም ግን ግዴታ ነው፡፡ በፍላጎትና በእምነት ደረጃ ሕዝብና መንግሥት ዕድገት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ ይመኛሉ ይፈልጋሉ፡፡ በተግባር ግን እንቅፋት አለ፡፡ እንቅፋቶቹም በሕዝብ የሚቀልዱና በአገር የሚነግዱ፣ ብቃት የሌላቸው፣ ሥነ ምግባር የጎደላቸው፣ የአገርና የሕዝብ ፍቅርና ወገናዊነት የሌላቸው ሹሞችና ኔትዎርኮቻቸው ናቸው፡፡

ፍላጎትን ዳር ለማድረስ፣ ዕቅዶችን በብቃት ለማሳካት ከተፈለገ ምርጫው አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ፀረ ሕዝብ ሹሞችን፣ ሙሰኛ ባለሥልጣናትን፣ ተላላኪዎችንና አስመሳዮችን ከሥልጣን ማንሳት፣ ተጠያቂ ማድረግ፣ ለፍርድ ማቅረብ የግድ ነው፡፡

የብቁዎችን ሹመት እንደግፋለን፡፡ የደካሞችን፣ የሙሰኞችንና የመንግሥት ሌቦችን ሽረት ደግሞ እንጠብቃለን፡፡
 http://www.ethiopianreporter.com/editorial/294-editorial/8693-2012-12-01-08-49-39.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር