የነፃ ገበያ ውድድሩ ወዴት?


በዳዊት ታዬ
የዜጎችን የመኖርያ ቤት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደው የጋራ መኖርያ ቤቶች ግንባታ አተገባበር ሲያወያይ መሰንበቱ ይታወቃል፡፡
ማወያየት ብቻ ሳይሆን ብዙ ውዥንብር መፍጠሩንም ከሁለት ሳምንታት በፊት በየቀበሌው ደጃፍ የተመለከትነው ግርግር ይመሰክራል፡፡

የ40/60 የመኖርያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለመሆን የነበረው ጉጉት ከልክ በላይ መሆኑንም የምንረዳበት ነው፡፡

የ40/60 የቤቶች ፕሮጀክት አተገባበር አሁንም ድረስ ብዥታ እንደፈጠረ ነው፡፡ ከዛሬ ነገ ምዝገባው ይጀመራል እየተባለ አሁንም ድረስ እየተጠበቀ ቢሆንም ነገሩ በእንጥልጥል ላይ ቀርቷል፡፡ ምዝገባው ለምን አልተጀመረም? ለሚለው ጥያቄ በቂ መልስ አልተገኘም፡፡ ሌሎች ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮችም እስካሁን ጥርት ብለው አልተገለጹም፡፡

በ40/60 የመኖርያ ቤቶች ፕሮጀክት እየተስተዋለ ያለው ሽፍንፍን ያለ አካሄድ እንደተጠበቀ ሆኖ ፕሮጀክቱን መሬት ላይ ለማውረድ ቤት ፈላጊው እንዲያሟላ የሚጠበቅበት የ40 በመቶ የቅድሚያ ክፍያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በሚካሄድ ቁጠባ ስለመሆኑ ግን ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡

ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ የግንባታ ወጪውን ከባንክ ጋር አስተሳስሮ ግንባታውን ለማከናወን መቻሉ የሚደገፍ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራር እስካሁንም መዘግየት አልነበረበትም፡፡

ሆኖም የጋራ መኖርያ ቤቶችን ለመገንባት ወይም አሁን እንደታሰበው በ40/60 የመኖርያ ቤቶች ግንባታ ከባንክ ጋር በማስተሳሰር የሚሠራውን ሥራ ለአንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ መስጠቱ እንደ ትክክለኛ ዕርምጃ ሊወስድ ግን አይችልም፡፡

በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ያሉትን የመኖርያ ቤት ፈላጊዎችን ትተን በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ብቻ ወደ በሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎች የራሳቸው የመኖርያ ቤቶች የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ በየወሩ ገንዘብ ቆጥበን ተጠቃሚ እንሆናለን የሚሉ ወይም አቅም ይኖራቸዋል የተባሉ ዜጎች ቁጥርም እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ካልተጋነነ በዚህ ዕድል ለመጠቀም እንችላለን ብለው ሊመዘገቡ የሚችሉ ዜጎች ከአንድ ሚሊዮን በታች አይሆኑም፡፡ ለዚህም ከስምንት ዓመታት በፊት የኮንደሚኒየም ቤት ባለቤት ለመሆን የተመዘገቡትን ወደ ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በ40/60ው ፕሮጀክት ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ዜጋ ቁጥሩ ሳይገደብ ይመዝገብ ቢባል እያንዳንዱ የቤት ፈላጊ ወደ ንግድ ባንክ ሄዶ የሚያስቀምጠው ገንዘብ በብዙ ቢሊዮኖች የሚገመት ይሆናል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩን ተቀማጭ ገንዘብ ምን ያህል እንደሚያሳድግለት መገመት አያዳግትም፡፡

ባንኩ ከሌሎች የአገሪቱ ባንኮች በተለየ ያገኘው ዕድል ከሚያስገኝለት ጥቅም ባሻገር የተወዳዳሪ ባንኮችን ጥቅም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንካቱም አይቀርም፡፡

በተለይ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ሌሎች ባንኮች የተቀማጭ ገንዘባቸውን መጠን ለማሳደግ ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት የ40/60 ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትልቅ ሲሳይ ሆኖም ይወሰዳል፡፡

በውዴታ ግዴታ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ሰተት ብሎ መግባቱ ለአንድ ባንክ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ይህም ከዚህም ቀደምም ቢሆን በመንግሥት ደረጃ ከሌሎች ተወዳዳሪ ባንኮች በተለየ ድጋፍ እየተደረገለት እንደሚያገኝ ስለመሆኑ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የ40/60 አጋጣሚ የበለጠ እንዲልቅ ወይም የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርገው በር እንደተከፈተለት ይቆጠራል፡፡

በእርግጥም ባንኩ ከሌሎች የተሻለ አቅም ያለው በመሆኑ ሲታሰብ ለ40/60 ፕሮጀክት የፋይናንስ አቅራቢ መሆኑ ብዙም ላይገርም ይችላል፡፡ ሆኖም እንዲህ ዓይነቱን ዕድል የግል ባንኮች መስጠት አይችሉም ነበር ወይ? የሚለውን ተገቢ ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡

በ40/60 ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልግ ሰው እንደሚፈልገው የቤት ዓይነት በየወሩ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ለሚቆጥበው ገንዘብ 5.5 በመቶ ወለድ ያገኛል፡፡ ቆጣቢው የሚያጠራቅመው ገንዘብ ደግሞ እስከ አምስት ዓመት በዚሁ የወለድ መጠን እየተሰላ ይቀመጥለታል፡፡ ባንኩ አርባ በመቶውን የቁጠባ ገንዘብ እየተጠራቀመለት ለቤቶች ግንባታ የሚሆነውን ቀሪ ገንዘብ ወይም 60 በመቶውን በብድር ለቆጣቢው ይሰጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ላበደረው ገንዘብ ቆጣቢው የ7.5 በመቶ ወለድ እንዲከፈል ይደረጋል፡፡ ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ይህ አሠራር መልካም ነው፡፡ ለባንኩም ሲሳይ ነው፡፡ ሲሳይ የሚሆንበት ዋናው ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በጊዜ ገደብ የሚያስቀምጡትን በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ ሁለት ሦስት ጊዜ እያበደረ በባለሁለት አሃዝ የወለድ መጠን እያበደረ ይጠቀምበታል፡፡ እየሰበሰበ ለሌሎች ያበድራል፡፡

በአንዴ ይህንን ያህል ብር የሚገኝበት አጋጣሚም ባለመኖሩ፣ በ40/60 ፕሮጀክት ቤት ለማግኘት ተጠቃሚ ከሚሆነው በላይ ባንኩ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡

የተጠቀመው አገልግሎት በመስጠቱ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ የጠቀመ ይጠቀም፡፡ ግን ይህንን ዓይነቱን ዕድል ለአንድ ባንክ ብቻ መስጠቱ ለምን አስፈለገ? የሚለው ጉዳይ ሁሉንም የሚያነጋግር ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ባንኮች የተቀማጭ ገንዘባቸውን ለማሳደግ ከመደበኛ የወለድ ምጣኔ በላይ ክፍያ በመፈጸም ብር እንዲቀመጥላቸው እያደረጉ ባሉበት ወቅት ያለምንም ውጣ ውረድ እንደ 40/60 ባለው ፕሮጀክት ምክንያት ወደ ባንክ የሚመጣ ገንዘብ መቼም የሚገኝ ያለመሆኑን የባንክ ባለሙያዎች አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ፡፡

ከዚህም በላይ የ40/60 ፕሮጀክት የሚቆጠብ ገንዘብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ መሆኑ ሌሎች የግል ባንክ አስቀማጮች ለቤት ግንባታ ቁጠባ ብለው አካውንታቸውን ወደዚያ ሊያዞሩ ይችላሉ የሚልም ሥጋት አላቸው፡፡ በዚህ ፕሮጀክት አፈጻጸም ዙሪያ መንግሥት የወሰደው ውሳኔ ምንን ታሳቢ አድርጎ እንደሆነ ባይታወቅም፣ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለው የውድድር ሜዳ የተደላደለ እንዲሆን አላደረገውም፡፡ ቢያንስ በግል ባንክ በመቆጠብ ዕድሉ እንዲገኝ ማድረግ ተገቢም ነበር፡፡ የባንክ ባሕሪ ከሌሎች ሰብስቦ ማበደር እንደመሆኑ መጠን፣ የንግድ ባንክ ያህልን አቅም ባይኖራቸው እንኳን የግል ባንኮች ተመሳሳይ አገልግሎት ሊሰጡ ይችላሉ፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ ባንኩ መጠቀሙ አይቀርም፡፡ እንደ ግል ባንክ ሲታሰብ ደግሞ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እየተሰጠ እንዳለው ዓይነት ዕድል ቢያገኙ፣ ያለማቅማማት የሚጠቀሙበት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ከዚህ ቀደም ባንኮች ከእያንዳንዱ ብድር 27 በመቶ ለቦንድ ግዥ አውሉ የሚለው መመርያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንዳይመለከተው ተደርጓል፡፡ አንዳንድ የወጪ ንግድ ምርቶች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ብቻ እንዲከናወኑ ተወስኗል፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራሮች በነፃ ገበያ ውድድር ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ አስተዋጽኦ ያሳርፋል፡፡

ለአንዱ የሚሰጥ ዕድል ለሌላው ካልተሰጠ ወይም ተጠቃሚዎች በሚፈልጉት አገልግሎት መስጫ ተቋም መስተናገድ እንዳይችሉ ከተደረገ ፍትሐዊ ውድድር አይኖርም፡፡

አሁንም በባንኮች ዙርያ የሚታየው ሁኔታ ይህንኑ ነው የሚያሳየው፡፡ የግል ባንኮች ልክ እንደ 40/60ው ዓይነት ፕሮጀክቶችን እንዲያስተናግዱ ማድረግ ከባድ አይሆንም፡፡

ምናልባት የብድር መክፈያ ጊዜውን ባያራዝሙ እንኳን አሳጥረውም ቢሆን አቅሙ የሚችል በእነርሱ ቢገለገል ምን ክፋት አለው? ለማንኛውም የነፃ ገበያ ውድድር ሲታሰብ ለሁሉም እኩል ዕድል ይሰጥ፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/component/content/article/311-shemach-trade-business-shopping/8337-2012-11-03-09-58-12.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር