የማይዝል ክንድ


በምሕረት አስቻለው
ጥቂት የማይባሉ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች የቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መገኘት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የመሥራት አቅማቸው፣ ወይም ሌሎች የዕለት ተዕለት ክንዋኔአቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ይሰማቸዋል፡፡ በሌላ በኩል አብረዋቸው የሚሠሩ በዙርያቸው ያሉ ስለ እነዚህ ሰዎች ኤችአይቪ ፖዘቲቭ መሆንና የመሥራት አቅምና ተመሳሳይ አመለካከት ሲያንፀባርቁ ይስተዋላል፡፡

እያንዳንዷን ቀን መርካቶ ጭድ ተራ እየተባለ ከሚጠራው ቦታ ላይ ለሚያሳልፈው ወጣት የቀን ሠራተኛ ቫይረሱ በደሙ ውስጥ የሚገኝ ነገር ግን የሥነ ልቦና ጥንካሬ ያለው ሰው ጉልበት ፈታኝ በሆነው የቀን ሥራ ላይ ቢሰማራ ምንም የሚገርም ነገር እንደሌለው ይናገራል፡፡

ባደረገው የኤችአይቪ ምርመራ የቫይረሱን በደሙ ውስጥ መገኘት ካወቀ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የመጀመርያዎቹን ሁለት ዓመታት ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት መውሰድ አላስፈለገውም ነበር፡፡ አራቱንም ዓመታት ግን የጉልበት ሥራ ሠርቷል፡፡

የትውልድ ቀዬው ቂጨሞን ጥሎ እንደ ብዙዎቹ የቀዬው ወጣቶች ሠርቶ ለመለወጥ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ከአሥር ዓመታት በፊት የ18 ዓመት ወጣት እያለ ነበር፡፡ የሆቴል መስተንግዶ፣ ጀብሎን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ እዚህም እዚያም እያለ የጉልበት ሥራ እየሠራ ኑሮውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና ሲል በነበረበት ወቅት ከተዋወቃት ጓደኛው ጋር በትዳር ተሳስሮ አንድ ልጅ ማፍራት ችሏል፡፡

ለወጣቱ በምን አጋጣሚ የኤችአይቪ ምርመራ እንዳደረገ ጥያቄ አቅርበንለት ነበር፡፡ ከጓደኛው ጋር በጋብቻ ተሳስረው መኖር እንደጀመሩ ሳንባ መታመም ጀመረ፡፡ ይኖሩ የነበረው የባለቤቱ አክስት የሚያከራዩት አንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ነበር፡፡

ሕመሙን የተመለከቱት አክስቷ በግልጽ ኤችአይቪ መሆኑን ባይነግሩትም ልጃቸው (ባለቤቱ) በአንድ ወቅት ሲያስመረምሯት የሚተላለፍ በሽታ መያዟ መታወቁን ገልጸው እሱም እንዲመረመር ይነግሩታል፡፡ ነገሩን ለቅርብ ጓደኛው ሲያማክር ምናልባትም አክስትየው ማለት የፈለጉት ኤችአይቪ ተመርመር ሊሆን ይችላል የሚል ፍንጭ በማግኘቱ ወዲያው የኤችአይቪ ምርመራ አደረገ፡፡ ቫይረሱ በደሙ ውስጥ እንደሚገኝም አወቀ፡፡ ድንጋጤ፣ ግራ መጋባትና ‹‹እያወቀች እንዴት አትነግረኝም›› የሚል ቁጭት ስሜቱን ስለረበሸው ጨርቄን ማቄን ሳይል ቤቱን ጥሎ ወጣ፡፡ በዚህ ከባድ ስሜት ውስጥ ሆኖ ሁለት ወራትን ጎዳና ላይ አሳለፈ፡፡

ባለቤቱም ምርመራ እንድታደርግ በሕክምና ባለሙያዎች የተነገረውን አስታውሶ እሷም እንድትመረመርና ውጤታቸው ተመሳሳይ ከሆነ ከመለያየት ይልቅ አብረውን እንዲኖሩ ከራሱ ጋር ተስማማ፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የጎዳና ላይ ጓደኞቹም ይህን እንዲያደርግ በመወትወታቸው ጭምር ነበር፡፡

ኤችአይቪ ፖዘቲቭ መሆኗን በምርመራ ያወቀችው ባለቤቱ ቀደም ሲል ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ስለመገኘቱ ምንም የምታውቀው ነገር እንዳልነበር፤ ነገር ግን አክስቷ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ መሆናቸውንና በጠና ታምመው በነበረበት ወቅት ሳለ ካለጥንቃቄ ማስታመሟን ገለጸችለት፡፡ ነገሩ ሙሉ በሙሉ ባያሳምነውም በቁጭት ተለያይቶ መኖር እንደማይጠቅም በመረዳት ከእሷው ጋር አብሮ መኖርን መረጠ፡፡ ሲዲ ፎሯ ወርዶ ስለነበር እሷ ወዲያው ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት እንድትጀምር ተደርጓል፡፡

ዛሬ ላይ እሷም እሱም ተሯሩጠው እየሠሩ በመተሳሰብ ኑሯቸውን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በወር ለቤት ኪራይ 400፣ ለሦስት ዓመቱ ሕፃን ልጃቸው ትምህርት ቤት ደግሞ 60 ብር ይከፍላሉ፡፡ ኑሮ የቱን ያህም ቢከብዳቸው ሳይማረሩ ሁለቱም እዜያ መርካቶ ውስጥ የጉልበት ሥራ ሠርተው ያድራሉ፡፡ በተለይም እሱ ለምን ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሆንኩ ወይም ባለቤቴ በድላኛለች የሚል አንድም ቁጭት እንደሌለበት ይናገራል፡፡

‹‹እኔ ራሴን አልደብቅም፣ ግልጹን እናገራለሁ፡፡ ሌሎችንም እንዲጠነቀቁ እመክራለሁ፡፡ የትም ብሆን የት ሰው እየኝ አላየኝ ሳልል መድኃኒቴን እወስዳለሁ፤›› በማለት ባለቤቱ ግን ቫይረሱ በደሜ ውስጥ መኖሩን ሰዎች ያውቁብኛል በሚል ሥጋትና በሌሎችም አላስፈላጊ ሐሳቦች ራሷን እንደምታስጨንቅ ይናገራል፡፡

መድኃኒት በምትወስድበት ሰዓት ላይ እንግዳ በአጋጣሚ ቤታቸው ውስጥ ከተገኘ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቱን ትተወዋለች፡፡ በተመሳሳይ ምክንያት ሰዓት የምታሳልፍባቸው አጋጣሚዎችም ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም በተደጋጋሚ እንደምትታመም፤ ከምትሠራበት የማትሠራበት ጊዜ እንደሚበጥል ይናገራል፡፡

‹‹እሷ ብቻ ሳትሆን አክስቷ ከጤና ጣቢያ የሚያመጡትን መድኃኒት ገና ለገና እቤት የሚመጣ ሰው በአጋጣሚ ቢያየውስ በሚል ፍርሐት ትቦ ውስጥ ይጨምራሉ፡፡ ሁሌም እንደዚህ ስለሚያደርጉ መጀመርያ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቱን ለምን እንደሚያመጡ ይገርመኛል፤›› ይላል፡፡

እንዲህ ዕለት በዕለት የጉልበት ሥራ እየሠራ፤ ይህ ነው የሚባል ምግብ በማያገኝበት ሁኔታ ፍጹም ጤናማ የመሆኑ ምስጢር የሥነ ልቦና ጥንካሬው እንደሆነ ያምናል፡፡ እሱም ባለቤቱም አባል ከሆኑበት ኦሳ የኤችአይቪ ድጋፍ ድርጅት የሚያገኘው የሥነ ልቦናና ድጋፍ ሌሎች እገዛዎችም ትልቅ ዋጋ የሚሰጣቸው ነገሮች እንደሆኑ ይሰማዋል፡፡

‹‹ከመሸከም፣ መሀል መርካቶ ላይ ዕቃ ሲያወርዱና ሲጭኑ ከመዋል የሚከብድ ሥራ የለም፡፡ እኔ ግን ፍጹም ጤናማ ነኝ፡፡ ትልቁ ነገር የአእምሮ ሰላምና መረጋጋት ነው፡፡ በእርግጥም መቋቋም ብችል እንደዚህ ያለውን ከባድ ሥራ ከምሠራ እንደ ጀብሎ ወይም ሌሎች ቀላል ሥራዎችን ሠርቼ ባድር እመርጥ ነበር፡፡››

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር