የነጭ ሪቫን ቀን በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ


አዋሳ ታሀሳሰ 03/2005 የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህራን፣ ተማሪዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችን ለማስቆም የተቀናጀ ጥረት እንደሚያደርጉ አስታወቁ፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከዩኒቨርስቲ ጋር በመቀናጀት ያዘጋጀው አለም አቀፍ የነጭ ሪቫን ቀን ትናንት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡ ቀኑን አስመልክቶ በዩኒቨስርቲው በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለፀው በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃቶችን ማሰቆም ሰብአዊ መብቶች በማስተባበር ልማትና እድገትን ለማፋጠን ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ የዩኒቨርስቲው ሶስቱም ካምፓስ መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሰራተኞች በውይይቱ መጨረሻ በተቋሙ ውስጥም ሆነ ውጭ በሴቶች ላይ የሚፈፀመውን ማንኛውንም ጥቃት እና ትንኮሳዎችን ለመከላከል ግንዛቤ በመፍጠር የበለጠ ትኩረት ሰጥተው እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ የሃይል ጥቃቶች የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በመሆናቸው ከተለያዩ ማህበራት፣ መንግስታዊ ከሆነ ተቋማትና ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ችግሩን ለመግታት ግንባር ቀደም ሚና ለመጫወት ዝግጁ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የስርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ በዛ ነገዎ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት መንግስት የብሄር ብሄረሰቦች መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር የሴቶችን አኩልነት ፣ የሃይማኖት ነፃነትን ያረጋገጠ በመሆኑ ሁሉም ተገንዝቦ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ኮሚሽነር አቶ አስማሩ በሪሁን በበኩላቸው ፆታዊ ጥቃትና ትንኮሳዎች ሴቶች ለሀገር ልማትና እድገት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ የሚገድብ፣ በትምህርት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያቀጭጭ፣ የሀገሪቱ የሰብአዊ መብት የሚያጎድፍ እንዲሁም የልማትና ዕድገት ጐዳናን የሚያደናቅፍ በመሆኑ ምሁራን ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ አለባቸው ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመግታት ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች፣ ከኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማትና ማህበራት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በቀጣይ የሰብአዊ መብት ክበብ ለማቋቋም እንዲያስችል ከመምህራን፣ ከተማሪዎችና ከአስተዳደር ሰራተኞች የተውጣጡ አባላት ተመርጠዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=3918&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር