ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከፍተኛ የመንግሥት ፕሮጀክት ግዥዎችን እመረምራለሁ አለ



-    ስዊስ ባንክ በታምራት ላይኔ ስም የተቀመጠ ስምንት ሚሊዮን ዶላር መለሰ
በውድነህ ዘነበ

በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ ግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ከሚያካሂዷቸው ግዥዎች ጋር በተያያዘ የሙስና ሥጋት በመፈጠሩ፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራ እጀምራለሁ አለ፡፡
ኮሚሽኑ ምርመራ ከሚያካሂድባቸው ፕሮጀክቶች መካከል በስኳር ኮርፖሬሽን አማካይነት የሚካሄዱ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሚካሄዱ ትላልቅ የኃይል ማመንጫ ግድቦችና ጣቢያዎች ግንባታና በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሚካሄዱ ትላልቅ የኢንጂነሪንግ ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡

የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ በትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ እንዲያተኩር መመርያ ተሰጥቶታል፡፡

“ቀደም ሲል ከምናካሂደው በተለየ ሁኔታ በግዙፍ ፕሮጀክቶች ግዥ ላይ እናተኩራለን፤” ሲሉ አቶ ዓሊ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ በመቶ ቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ በርካታ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ መሰማራቱ ይታወቃል፡፡

በእነዚህ ግዙፍ መንግሥታዊ ፕሮጀክቶች ላይ ምርመራ ለማድረግ እየተዘጋጀ ያለው የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ለምርመራው ያለውን የሰው ኃይል እንደሚያሰማራ ተገልጿል፡፡

ጥቃቅን የሙስና ወንጀሎችን እንጂ ታላላቅ ሙስናዎች አይደፍርም በሚል የሚታማው ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ዘግይቶም ቢሆን በእነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ ምርመራ ለመጀመር መዘጋጀቱ መልካም ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሽግግሩ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት አቶ ታምራት ላይኔና የመከላከያ ሚኒስትር ከነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ ወዲህ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በሙስና ባለመጠየቁ ይተቻል፡፡ አቶ ዓሊ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ የአመለካከት ጉዳይ ነው እንጂ ትላልቅ ባለሥልጣናት በሙስና ተጠይቀዋል ሲሉ አቶ ዓሊ ኮሚሽኑ ፍርኀት እንደሌለበት ይከራከራሉ፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ አቶ ታምራት ላይኔ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከመቋቋሙ በፊት ሥልጣንን አለአግባብ በመጠቀም ሦስት ክሶች ተመሥርቶባቸው ነበር፡፡ ከእነዚህ ክሶች በተጨማሪም መንግሥትን ወክለው ከሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ 16 ሚሊዮን ዶላር ለቡና ግዥ ተበድረዋል መባሉ ይታወሳል፡፡ ይህ ገንዘብ ስዊስ ባንክ ውስጥ ይገኛል የሚል መረጃ የደረሰው መንግሥት በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል ገንዘቡን ለማስመለስ ጥረት አድርጓል፡፡  

ከ16 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ስምንት ሚሊዮን ዶላር በስዊስ ባንክ እንደሚገኝ በመረጋገጡ፣ መንግሥት ገንዘቡ እንዲመለስለት ለስዊስ ፍርድ ቤት ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የስዊስ ፍርድ ቤት ገንዘቡ የኢትዮጵያ መንግሥት አይደለም በሚል ለሌላ ግለሰብ እንዲመለስ ወስኗል፡፡

አቶ ዓሊ የተጠቀሰው ገንዘብ ለኢትዮጵያ እንዳልተመለሰ ገልጸው፣ ገንዘቡ የተመለሰለትን ግለሰብ ስም ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደሚገልጹት ከሆነ ግን ገንዘቡ የተመለሰው ለሼክ አል አሙዲ ነው፡፡

ለ12 ዓመት ከሁለት ወራት ታስረው ታህሳስ 2000 ዓ.ም. ከእስር የተፈቱት አቶ ታምራት ላይኔ ከእስር በተፈቱበት ወቅት ስለዚህ ገንዘብ ምንም ማለት እንደማይፈልጉ፣ ከዚህ በኋላ በፕሮቴስታንት እምነት ጥላ ሥር ሰላምና ፍቅርን እየሰበኩ ቀሪውን ዕድሜያቸውን እንደሚገፉ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡   
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8902-2012-12-19-06-30-23.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር