በኢትዮጵያ ''ሃሎ ዶክተር'' የተሰኘ የምክር አገልግሎት መስጫ አገልግሎት ተጀመረ

አዲስ አበባ ታህሳስ 8/2005 በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ሕሙማን ከሐኪሞች ምክር የሚያገኙበት ''ሃሎ ዶክተር'' የተሰኘ አገልግሎት በይፋ ተጀመረ። አገልግሎቱ በኦሮምኛ፣በትግሪኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ለመጀመርም ታቅዷል። የቴሌ ሜዲስን የሕክምና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ዮሐንስ ወዳጄ ዛሬ ለኢ ዜ አ እንዳስታወቁት ለ24 ሰዓት የሚሰጠው አገልግሎት በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ሆነው ምክር የሚፈልጉ ሕሙማንን ለመርዳት ያስችላል። በተጨማሪም ቤታቸው ሆነው የሐኪም ድጋፍ የሚፈልጉ ሕሙማንን እንደሚያግዝም አስረድተዋል። እንዲሁም በሕመም ወይም በአደጋ ለተጎዱ ሰዎች የአምቡላንስ አገልግሎት በማቀናጀት እገዛ እንደሚያደርግ ዶክተር ዮሐንስ አስታውቀዋል። ''ሕሙማን ካሉበት ሆነው በሞባይል ስልካቸው አማካይነት ወደ 8896 መደወል የሐኪም ምክር ሲጠይቁ በመሥመር ላይ ያለው ሐኪም ከሕመማቸው እንዲፈወሱ ተገቢውን ምክር በመስጠት ይረዳቸዋል።ለዚህም ከስልካቸው ሂሳብ ተቀናሽ የሚሆን መጠነኛ ሂሳብ ይቆረጣል'' ሲሉም አብራርተዋል። በአገሪቱ የሞባይል አገልግሎት መስፋፋትና የወደፊት አቅጣጫው አገልግሎቱን ለማስጀመር ጥሩ መሠረት እንደሆነም ዋና ሥራ አስኪያጁ አመልክተዋል። አገልግሎቱ ለጊዜው በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች በ10 ሐኪሞች መጀመሩንም ተናግረዋል።በያዝነው ዓመትም የሐኪሞቹን ቁጥር ወደ 50 ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል። አገልግሎቱን በኦሮምኛ፣በትግሪኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ለመጀመርም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። አገልግሎቱ ቀደም ሲል በአውሮፓና በአሜሪካ፣በቅርቡ ደግሞ በደቡብ ምሥራቅ አገሮችና በላቲን አሜሪካ እንዲሁም በአፍሪካ እየተስፋፋ መምጣቱን ዶክተር ዮሐንስ አስረድተዋል። በአገሪቱ እየተተገበረ ያለው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለጤናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረትና የጤና አገልግሎትን በጥራት ለማዳረስ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እገዛ እንዳለው ማህበሩ ያሰራጨው ዘገባ ያመለክታል። የኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ሽፋን 89 ከመቶ የደረሰ ቢሆንም፤ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ከሕሙማን ጋር ያለው ምጣኔ የዓለም ጤና ድርጅት ካወጣው መስፈርት ባለማሟላቱ ግን ችግሮች እንዳለበት መረጃው እንደሚያሳይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር