አማራጭ ሐሳብና አማራጭ ጥንካሬ ያለው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ይፈለጋል!



አገራችን ኢትዮጵያ ምን እንድትሆን ትፈልጋላችሁ ብንባል ቀጥተኛውና ቀልጣፋው መልሳችን የበለፀገችና ዲሞክራሲያዊት አገር እንድትሆን እንፈልጋለን ነው፡፡ ልማትና ዲሞክራሲ ጐን ለጐን ተያይዘውና ተሳስረው የሚታዩባት አገር እንድትሆን እንፈልጋለን፡፡
ልማት እንጂ ዲሞክራሲ አንፈልግም የሚለውን አንቀበልም፡፡ ዲሞክራሲ እንጂ ልማት አንፈልግም የሚለውንም አንቀበልም፡፡ ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ መንግሥትና ፖለቲካ እንፈልጋለን፡፡

ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንፈልጋለን ስንል አንዱ መገለጫው የተለያዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት ሥርዓት እውን ማድረግ ነው፡፡ ለአገር የሚጠቅም የተሻለ ሐሳብ አለን የሚሉ ኃይሎች የሚሰባሰቡበትና የሚደራጁበት የፖለቲካ ፓርቲ መፍጠርና ሥልጣን ለመያዝ መወዳደር መብት መሆኑን የሚያረጋግጥ ሥርዓት እውን ማድረግ ማለት ነው፡፡

ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር ለአንድ አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ወሳኝ ነው፡፡ ሐሳቦች እርስ በርስ ይወዳደራሉ፤ ይታገላሉ፡፡ ሕዝቡም የተሻለውን ሐሳብ ይመርጣል፡፡ በሕዝብ ድምፅ የተመረጠውም አገሪቱን እንዲመራ ኃላፊነት ይሰጠዋል ማለት ነው፡፡

በዚህ ዙሪያ ሕዝብም፣ መንግሥትም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሥነ ሐሳብ ደረጃ ልዩነት የላቸውም፡፡ ሕዝብ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ኖረው ይወዳደሩ ብሎ ያምናል፡፡ በሕገ መንግሥቱም ሰፍሯል፡፡

በተግባር ግን የጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ትግል፣ ፉክክርና ውድድር ማየት አልቻልንም፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ እውን ማድረግ አልተቻለም፡፡ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ የሆነው ጠንካራ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ በተግባር በኢትዮጵያ እውን መሆን አልቻለም፡፡

ለምን?
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ መሆን ያልቻልነው ገዥው ፓርቲ እንዳንጠናከር ስላደረገን ነው የሚል መከራከሪያ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ይህንን በተመለከተ ንፁህ ነው ብለን አንከራከርም፡፡ የፈጠረው ችግርና ጫና የለምም አንልም፡፡ ነገር ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያልተጠናከሩበት ዋነኛው ምክንያት በራሳቸው ድክመት፣ ጉድለትና የብቃት ማነስ ነው እንላለን፡፡ ከማንም በፊት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ላለመኖሩ ተጠያቂ የምናደርገው ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ራሳቸውን ነው፡፡

ለምን?
1.    ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ፣ ግልጽና፣ ይፋ የሆነ አማራጭ ሐሳብ ለሕዝብ አላቀረቡም፡፡
2.    ጠንካራ ሐሳብ አለመኖር ብቻ ሳይሆን ጠንካራ አደረጃጀትና ጠንካራ እንቅስቀሴም አያሳዩም፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙና እንዲከበሩ አማራጭ ሐሳብ ማቅረብ አለባቸው፡፡

ገዥው ፓርቲ ትክክልም ይሁን ስህተት ለእያንዳንዱ ጉዳይ በፖለቲካ መስመር፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፎች ዕቅዶች አሉት፡፡ ግብርናን፣ ኢንዱስትሪን፣ ትራስፖርትን፣ ዲፕሎማሲን፣ መገናኛ ብዙኅንን፣ ምርጫን፣ ዲሞክራሲን፣ ልማትን፣ ወዘተ እንዲህ አደርጋለሁ፤ ዕቅዴን እንዲህ እፈጽመዋለሁ፤ በዚህ ዓመት ይህ ይከናወናል ብሎ በግልጽ አቅርቧል፡፡

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የለም እኛ ሥልጣን ብንይዝ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በፕሬስ፣ በዲሞክራሲ፣ በዲፕሎማሲ፣ ወዘተ እንዲህ እናደርጋለን፤ ይህንን ፖሊሲ እንከተላለን፤ አፈጻጸሙም እንዲህ ይሆናል፤ ውጤቱም እንዲህ እንዲሆን እንታገላለን ማለት ነበረባቸው፡፡

ስለዚህ አንዱና ትልቁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድክመት አማራጭ ሐሳብ፣ አማራጭ ፕሮግራምና አማራጭ ስትራቴጂ በግልጽ ለሕዝቡ አለማቅረባቸው ነው፡፡

ሁለተኛው ድክመታቸው አማራጭ አደረጃጀትና የእንቅስቃሴ ጥንካሬ አለማሳየታቸው ነው፡፡ ለመሆኑ ተቃዋሚ ድርጅቶች አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ምን ያህል ይሆናሉ? ለመሆኑ ዓመታዊ ጉባዔ ያካሂዳሉ ወይ? ለመሆኑ በፓርቲያቸው ውስጥ ወቅቱን የጠበቀ ምርጫና ግምገማ ይካሄዳል ወይ? የውስጥ ኦዲት ይደረጋል ወይ? ግልጽነት አለ ወይ? ፓርቲውን ሁሌም የሚመራው አንድ ዓይነት ኃይል ነው? ወይስ መተካካት አለ? ወጣቶች በፓርቲው ውስጥ ምን ሚና አላቸው? ወዘተ የሚለው መታየት አለበት፡፡ 

ሌላው ትልቁ ድክመት ይህ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውስጣቸው ጥንካሬ አይታይም፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሕይወት አይንፀባረቅም፡፡ መተካካት የሚባለው ፈጽሞ አይታወቅም፡፡

ይህ የሚያሳየን አማራጭ ሐሳብ መኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ አማራጭ ሐሳብ ተይዞም ወደ ድርጅታዊ እንቅስቃሴና ጥንካሬ ካልተቀየረ በሲዲና በወረቀት ብቻ ማሳየት አቅም አለመኖሩን ማሳያ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆንና ጥንካሬ ሲባል ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ባለመኖሩ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ላይ ቅሬታ ያለው ወገን በግራም በቀኝም ሲያይ ጠንካራ ተቃዋሚ ስለማያገኝ፣ ኢሕአዴግን የሚተካ ኃይል ይኖራል ብሎ መተማመን አልቻለም፡፡ ምን ተቃዋሚ አለና እያለ ተስፋ እየቆረጠ ነው፡፡

በመሆኑም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሌላ ወገን ሳያሳብቡ መጀመሪያ ውስጣቸውን ይፈትሹ፤ ድክመታቸውን ይመኑ፡፡ ብቁ ተቃዋሚ ለመሆን ይጣሩ፡፡ ድክመታቸው ሲነገራቸው ለጥንካሬያቸው ስለሚበጅ በእጅጉ ያስቡበት፡፡ የብቁ ተቃዋሚ የጥበብ መጀመሪያም አማራጭ ሐሳብና አማራጭ ጥንካሬ ለሕዝብ ማቅረብ ነው፡፡
ይፈለጋል! 
http://www.ethiopianreporter.com/editorial/294-editorial/8839-2012-12-12-09-02-10.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር