ሹመት ችግር ካልፈታ ፋይዳ ቢስ ነው!

ሰላም! ሰላም! ለዛና ጨዋታ ናፈቀን አይደል ጎበዝ? የድርቅ ታሪካችንን ለማጥፋት ስንረባረብ ሳይታወቀን የጨዋታ ድርቅ እየወረሰን መጣ መሰለኝ። የሚወራው፣ የሚሰማው፣ የሚዘፈነው፣ የሚታየው ሁሉ ለዛ በማጣት ድርቅ ከተመታ ምን ይውጠናል? እንዴ መኖር እየጠላን እንዴት እንዘልቃለን? እውነት እውነት ስላችሁ! ሳቅና ጨዋታ ከአታካቹ ኑሯችን ከተባረረ መሀል ላይ ስንዋልል ጥሩ አይመስለኝም። ‹‹አይ አንተ ሁሌም አንድ ሐሳብ አያጣህም?›› አለችኝ ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ሳቅ አላማረሽም?›› ብዬ ብጠይቃት። በነገራችን ላይ ማንጠግቦሽ ከት ብላ ከሳቀች ድንበር ተሻጋሪ ድምጿን ማንም ነው ሚሰማው። አሁን ታዲያ በገባሁ በወጣሁ ቁጥር ‹‹ምነው ሰላም አይደላችሁም?›› የሚለኝ ሠፈርተኛ በዝቷል። 

ይኼኔማ አንዳንዱ ተጣሉም ብሎ ያስወራ ይሆናል። ሰው እንዴት የሰውን ጓዳ ጎድጓዳ እየተከታተለ እንደሚኖር ሳስብ በእጅጉ ይደንቀኝ ጀመር። በነገራችን ላይ ከመሬት እየተነሳ ባለፀጋ የሚሆነው አልበዛባችሁም? መጠቃቀም በሕዝብ ሀብት ባይሆን ጥሩ ነው እያልን ብንመክር ብናስመክር ማን ከመጤፍ ቆጠረን? ‹‹ምርጫ ሲደርስ ብቻ የሚቆጠረው ድምፃችን ከወዲሁ ሰሚ ቢያገኝ ኖሮ የሌባው ቁጥር እንዲህ ባልበዛ ነበር፤›› ይለኛል የባሻዬ ልጅ በአንድ ጀንበር የሚከብሩ ሲበዙበት። መክበራቸው ሳያንስ ተፈርተው መኖራቸው የሚያበሳጨን አደባባይ ይቁጠረን። እናም ሳቅ ጠፋ የምለው በየትኛውም ሥፍራ እያረሩ መሳቅ የደስታ ምልክት ነው ተብሎ ስለማይቆጠር ነው። 

ለነገሩ ዝም ብላችሁ ብትታዘቡ እንኳን መሳቅ ይቅርና እሪ ብሎ ማልቀስስ ተወዷል። (ቆይ የማይወደደው ምን ይሆን?) ‹‹ይኼ ለብ ማለት ደግ አይደለም አንበርብር፤›› ይሉኛል ባሻዬ ጋቢያቸውን እያጣፉ። ኑሯችን ከአንዱ ወደ አንዱ እንደኳስ እየጠለዘ ሲጫወትብን መሳቅና ማልቀስ ማቆማችንን ባሻዬ አይወዱትም። ‹‹ሰው ቢያንስ ወይ ስቆ ወይ አልቅሶ፣ ወይ ደስ ብሎት ወይ ከፍቶት ስሜቱን ካልገለጸ ትልቅ ችግር አለ፤›› ይሉኛል ባገኙኝ ቁጥር። ‹‹አይ ባሻዬ! ማልቀስም መሳቅም የከበደን እኮ ኑሮ እየጠነዛ ስላቸገረን ነው። በሐሳብ እኮ እንኳን ትልልቆቹ ሕፃናቱ ሸበቱ፤›› እላቸዋለሁ መሸበትን ቀለል አድርጌ። ዘንድሮ የዕድሜና የጤናን ፀጋ የሚያቃልለው መብዛቱ እጅግ እያሳዘነኝ። አይ ሰውና ድፍረቱ! በራሱ ተደግፎ ይኖር ይመስል የሚንቀውንና የሚያከብረውን ለይቶ ሳያውቀው ያልፋል። እንዴት ግን ሞኝ ነን እናንተዬ? ሥልጣኔ የድፍረትንና የመገዳደርን ካባ በጋበዘው ቁጥር የሰው ልጅ ፈጣሪን ሲንቅ ገደብ እያጣ ስንት አሳዛኝ አወዳደቅ ወደቀ! ያሉበትን እየረሱ የተነሱበትን አላውቅ እያሉ ስንት ኃያላን በሕዝባቸው ላይ የግፍ ቁማር ሲጫወቱ እንዳይሆን እየሆኑ አለፉ! የሕዝብን ቅሬታና አስተያየት አንሰማም አናይም ሲሉ ስንት መንግሥታት ውድቀታቸው ሲፋጠን አየን! እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሁላችንም የቆምንበትን መርሳት፣ የተነሳንበትን መዘንጋት ይብቃን እላለሁ!

እና ባሻዬ ‹‹ሰው ትቶት ሊሄድ ለምድራዊ ነገር እንዲህ ሲባላ ማየት ያሳዝነኛል፤›› እያሉ መተናነቅን ኮንነው ሲያወሩ ያልሰማሁ መስዬ ሹልክ እላለሁ። ሆሆ ሆድን የሚያክል ነገር ሰው ተሸክሞ እየኖረ ባሻዬ እንደሚሉት ስለሰማይ ቤት ብቻ በማሰብ ምድራዊውን ትግል ማን ሊቋቋመው ይሆን? ባሻዬን የቄሳርን ለቄሳር ማለት እኮ የምድሩን ለምድሩ ነው ልላቸው አስብና በወሬ የማጠፋው ጊዜ ይታሰበኝና ወደ ሥራዬ እሮጣለሁ። ያለ አግባብ በሰው ላብ የሚከብሩትን እንጂ ሰው በላቡ ቢያተርፍ ፈጣሪን ምን ያስከፋዋል? ብቻ ዋናው ነገር አንዱ ለአንዱ መድረሱ ላይ ነው። እናላችሁ ይህን በማሰብ የደላላ ሰዓቴን ማበከን ስለማልፈልግ እንዳልኳችሁ ሳያዩኝ ሹልክ ብዬ እጠፋለሁ። የጊዜ ጥቅም ቀድሞ እኔን ገባኝ ብዬ ሳስብ ቀድሞ ሊገባቸው ይገባ ነበር ለምላቸው እያዘንኩ ስራመድ ነፍሴን አላውቅም። ‹‹በየጉራንጉሩ የምናጠፋው ጊዜ ቢደማመር ሌላ ሦስት የህዳሴ ግድብ በሠራልን ነበር፤›› የሚል ወዳጅ አለኝ። ታዲያ ተከራካሪ አያጣውም። ‹‹ምን ትቀልዳለህ! ታላቋ ኢትዮጵያ ተሠርታ ታልቃለች እንጂ፤›› ይለዋል። ‘ታላቋ’ ሲባል ልቤ ትርክክ እያለ እንደሚያስደነግጠኝ መቼም አጫውቻችሁ ይሆናል። ‘ታላቋ’ ሲባል አዕምሮዬ ለሁለት ይከፈልና በፍልስፍና፣ በመንፈሳዊ ጥበብ፣ በፈጠራ ሌሎችን መምራት የሚገባት ኢትዮጵያ የት ናት? በምግብ ራሷን ችላ፣ ከተሞቿ በሕንፃ ተንቆጥቁጠው፣ ከዕርዳታ ፈላጊነት ወደ ረጂነት ተሸጋግራና ኑክሌር ታጥቃ ያዙኝ ልቀቁኝ ባዩዋ እያለ ልቤ ይብሰለሰላል። 

ታዲያ ከአንዱ ፈጣሪ በቀር እኛ ራሳችን ወዴት እንደምናመራ ለማወቅ ግራ የገባን እንመስላለን። ‹‹የይድረስ የይድረሱ ላይ ስንበረታ ሩቅ ተመልካችነታችን አቅሙ ተዳከመ፤›› ይለኛል የባሻዬ ልጅ ስልችት ባለው ድምፅ። እናላችሁ እንዲህ ታካች ድምፅ ስሰማ በእውነት ፍርኃት ሰውነቴን ይወረዋል። እንዴት አልፈራ? ትውልዱ ገና ለገና በሐሳብ ተስፋ ቆርጦ በደባል ሱስ ሲሰቃይ ሳይ እንዴት አልፈራ? የ‹‹ሺ ዓመት አይኖር!›› ፈሊጥ ትልቁ ግባችንን መብላትና መጠጣት ሲያደርገው እንዴት አልበረግግ? ደግሞ ምናለ በነባሻዬ ቢሆን በታዳጊው እኮ ሥር ሰደደ! እንጃ! እንዲህ ያለውን ስንፍና የሚዘራ ስሜት ሳንገድብ ዓባይን ገድበን ረጅም ርቀት መጓዛችንን እንጃ!

ቅድም እንደ ኳስ ስል የኳሳችን ነገር ትዝ አለኝ። ልጆቻችንን በአፍሪካ ዋንጫ መድረክ ቀርበው ልናያቸው እያሟሟቅን ነው። የባሻዬን ልጅ ግን አሟሟቂዎቹ እኛ ብቻ መሆናችን ደስ አላሰኘው ብሏል። እንዲያውም ሰሞኑን በቁጭት፣ ‹‹አንበርብር ምን እንደሚሻለን እንጃ! የእኛዎቹ ቁጭ ተደርገው እሳት ሲሞቁ ተፎካካሪዎቻችን ዝግጅታቸውን በኃይለኛው እያጧጧፉ መሆኑን ፌዴሬሽንኑ ልብ ያለው አይመስልም። 

ለነገሩ የገንዘብ ነገር ባለበት መቼ ልብ ይገኛል ብለህ ነው?›› አለኝ አንዴ መሬቱን አንዴ እኔን እያየኝ። እንዴት ስለው ትንሽ እንደማሰብ ብሎ፣ ‹‹ሁሌ መቀበል የለመደ እጅ ለመሥራት መለገሙ ሳይታለም የተፈታ ነው። ፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ በመንግሥት ሥር ያሉ ተቋማት የፋይናንስ አቅማቸውን ለማጎልበት ደፋ ቀና ሲሉ አላይም። አየር መንገዱን እያየ ሌላው እንዴት መማር ያቅተው? ያውም ስፖርት ንግድም ጭምር በሆነበት በዚህ ዘመን፤›› አለኝ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹ደስታችንና ዝማሬያችን እኮ ገና ለአፍሪካ ዋንጫ ጭምር እንጂ ለክልላዊ ዋንጫ ብቻ አይደለም፤›› እያለ የባሻዬ ልጅ ሲቀጥል እኔን የሚወቅስ መሰለኝ። ጨንቆኝ ጨዋታውን አቋርጬ፣ ‹‹ተረጋጋ! እኔ እኮ አይደለሁም ቡድናችን የወዳጅነት ጨዋታ እንዳያደርግ ችግር የፈጠርኩት፤›› እስክለው ድረስ መዓት ወረደብኝ። እያንዳንዳችን በገዛ መንገዳችን የምንወጣውን መወጣት ካልቻልን የሚወርድብን መዓት ማባሪያ እንደሌለው ድንገት ባስብ በቅጡ ሳልሰናበተው ድለላዬን ለማጧጧፍ ከነፍኩ። ሳይሠሩ መብላት እንደሌለ፣ ብቁ ተወዳዳሪ ሳይሆኑ ዋንጫ እንደማይገኝ በትክክል ቢገባን ምን አለበት!?

ታዲያላችሁ አየሩን ሳስስ ወሬውን ስለቃቅም አዳዲስ ዋጋ ሳጣራ ከደላሎች መሰብሰቢያ ቆያይቼ አንድ ሬስቶራንት አከራይቼ ያልተቀበልኩትን ሒሳብ ለመቀበል አሰብኩ። ‹‹ገንዘብና ሚስት ውጭ ካደሩ ያንተ አይደሉም›› የምትለኝ ራሷ ማንጠግቦሽ ናት። ‹‹አይ ተረትና ኑሮ አሁን ሳልቀበል ሁለት ቀን የሆነኝን ገንዘብ ይቅርና 20 ዓመት ቢሞላኝስ ልምረው ነው?›› አለኝ የማንጠግቦሽን አባባል ያጫወትኩት ደላላ ወዳጄ። ‹‹ኧረ ልክ ነህ!›› አልኩታ፤ ታዲያ ምን ልለው ኖሯል? እኛ ገንዘብን ብንምረው ኑሮ መቼ ይምረናል ብላችሁ ነው? ግን ሰው በራሱ ጥረት ያላገኘው ገንዘብ ላይ ተርብ ሲሆን በጣም ያስተዛዝባል። እንዲህ በየጊዜው ዋጋው የሚወርደው ብራችን ሰውን ደም ሲያቃባ፣ እልህ ሲያያይዝ ሳይ የምለው ይጠፋኛል። የሆነው ሆኖ ለአንድ አፍታ ማንጠግቦሽ እንዳለችው ላቤን ጠብ ያደረኩበትን ገንዘብ የእኔ አይደለም ብዬ ስተው ታሰበኝና ከት ብዬ ሳቅኩ። አስቡት እስኪ? እንኳን በዚህ ጊዜ ይቅርና ሰው ለሰው መድኃኒቱ በነበረበት በደጉ ጊዜ የማን አንጀት ይሆን በገንዘብ ጨካኙ? ‘ያልሰበሰበ አያከማችም’ ሲባል አልሰማችሁም? ታዲያ በተሳሳተ መንገድ የተረጎማችሁትን አይጨምርም!

የማይመስል ነገር እያልኩ ቪላ ተከራይቶ እንደ አዲስ የምግብ ሥራውን የጀመረውን ደንበኛዬን ለማግኘት ሄድኩላችሁ። ‘በአዲስ መልክ ምግብ ጀምረናል’ የሚል ማስታወቂያ ከቤቱ በር ላይ ተለጥፏል። ‘አዲስ የሚባል በጠፋበት ዘመን ያውም አዲስ ዓይነት ምግብ እንዴት ያለ ይሆን?’ እያልኩ ሳስብ ደንበኛዬ ከሩቅ አይቶኝ መጣ። ‹‹እንዴት ያለ ጥሩ ቤት እንዳገኘህልኝ ማወቅ አትፈልግም?›› እያለ ለወሮታዬ ምግብ ጋብዞ ጭምር እንጂ ገንዘቤን ብቻ ሰጥቶ እንደማይለቀኝ ነገረኝ። ‹‹ይሁና›› አልኩና በዚያውም በአዲስ መልክ የተጀመረውን ምግብ ልቀምስላችሁ ተዘጋጀሁ። ማስታወቂያቸውና ሥራቸው የማይገናኙትን እያሰብኩ ሳልጨርስ ምግቡ መጣ። 

ወይ አዲስ? እንዴት ብዬ ላስረዳችሁ? በቃ ኮሜዲ ነው ተብላችሁ ትራጄዲ የሚሆንባችሁ ፊልም አለ አይደል? (መቼም የፊልሞቻችን ነገር እንደ ተመልካችም እንደ ባለሙያም ገና ብዙ ሳያባብለን አይቀርም) ምን አለፋችሁ አዲስ የተባለውን ምግብ ከወትሮው ያልተለየ ሆኖብኝ ሰፍ ሳልል እንደነገሩ ቶሎ ቶሎ ተመገብኩ። ‹‹እዚህ አገር በአዲስ መልክ እንዲጀመር የተነደፈው ብዙ ነው። ችግሩ ተግባራዊ እናደርጋለን የሚሉት ሰዎች አሮጌ አስተሳሰብ ይመስለኛል፤›› ያለኝ የባሻዬ ልጅ ትዝ አለኝ። ‹‹ልማታዊው መንግሥታችን ምነው በየተቋማቱ በአዲስ መንፈስና በአዲስ ወኔ የሚሠሩ ሰዎችን መልምሎ ማስቀመጥ አቃተው? ንቅዘት እኮ ከምንለው በላይ እየጎተተ አስቸገረን፤›› ያሉት ባሻዬ ውልብ አሉብኝ። አዲሱ አሮጌ አሮጌው እንዳዲስ እየተቀያየረ በከንቱ ለፍተን እንዳንቀር ብቻ ሰጋሁ!   

ሥራዬን ጨርሼ ወደ ሠፈሬ ስመለስ ያጋጠመኝን ላጫውታችሁ። የባሻዬ ልጅ የተለያየንበት ቦታ ላይ ቆሞ ራሱን እየነቀነቀ ብቻውን እንደማውራት ሲቃጣው ደንግጬ ተጠጋሁት። እንዳስቀመጡት የሚገኝ ነገር የለም አይደል? አንዳች ነገር የሆነ ስለመሰለኝ ‹‹ምነው ምን ሆንክ?›› አልኩት ክፉ እንዳልሰማ እየተመኘሁ። ‹‹ኧረ ጉድ ነው የዚህች ዓለም ነገር!›› ሲለኝ እንደመናደድም እንደማኩረፍም ያደርገኝ ጀመር። ‹‹የዓለምን ነገር ዛሬ እንደ አዲስ ሰማሁ እንዳትለኝ?›› ስለው ቆጣ ብዬ፣ ‹‹የእውነት ግን አንበርብር የግብፅን ሕዝብ ዳግም የተቃውሞ ድምፅ ማሰማቱን ስትሰማ ምንም አልተሰማህም?›› ሲለኝ እንደተናደድኩ ‹‹ምን ሊሰማኝ ኖሯል?›› አልኩት። ‹‹ይህቺ ሥልጣን የምትባል ነገር ምን ትሆን? በማን አለብኝነት ደረት አስነፍታ በፍቅሯ የምትለክፍ ከእሷ ወዲያ ማን ይገኝ ይሆን?›› እያለ ሲቀጥል ንዴቴ እየበረደ በቅጡ የሚለውን ማውጠንጠን ጀመርኩ። ‘ለፖለቲከኛ ትዳሩ ሹመት ትመስለዋለች’ የምትል ጥቅስ የሆነ ቦታ ማንበቤ ትዝ አለኝ። ሕዝብ መሆንና ፍዳው ሲሰማኝ ፖለቲከኛና ሹመት ፍቅራቸው ገረመኝ። ወይ የሥልጣን ፍቅር? ስንቱን ያሰማናል። 

የሹመት ጉዳይ ሲነሳ የበቀደሙ የፓርላማ ውሎ ትዝ አለኝ፡፡ በሬዲዮ ቀጥታ ሥርጭት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዳዲስ ተሿሚዎችን ስምና ኃላፊነት በፓርላማ ሲያፀድቁ ስሰማ እኔም ሐሳብ አለኝ አልኩ፡፡ ምንም እንኳ እንደኔ ዓይነቱ ደላላ ምክሩ ተቀባይነት ባይኖረውም፣ አዳዲስ ተሿሚዎች ሲመጡ ዝም ብሎ መቀበል አይሆንልኝም፡፡ ሹመት ያዳብር ብሎ ጠጋ ጠጋ ማለት ሳይሆን፣ በተሰጣችሁ ሥልጣን ሥሩበት ማለት ይገባል፡፡ 

ሙስና እንደ ሸረሪት ድር በየቦታው አድርቷል፡፡ መልካም አስተዳደር ጠፍቷል፡፡ የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ፍትሕ ርቋል፡፡ በሕገ መንግሥት የተረጋገጡ መብቶች ተጨፍልቀዋል፡፡ ሥርዓቱን ሙስና እንደነቀዝ እየበላው ስለሆነ የመፍትሔ ያለህ እየተባለ ነው፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ተሿሚዎቹ ይህንን ችግር ለማስወገድ ካልሠሩ ሹመታቸው ምንም አይረባንም እላለሁ፡፡ ይህንን ሐሳቤን ለባሻዬ ልጅ ብነግረው በመገረም እያየኝ፣ ‹‹አስተያየትህን በአስቸኳይ ለኢቲቪ ለምን አትልክም?›› አለኝ፡፡ እኔስ ምኔ ሞኝ ነው? ‹‹ኢቲቪ ሐሳቤን ቆራርጦ በ‹‹አበረታች›› ሊተካው ስለሚችል ፌስቡክ ላይ ለጥፈዋለሁ፤›› ስለው አንገቱን እየወዘወዘ ሳቀብኝ፡፡ ወደ ግሮሰሪያችን ስናመራ፣ ‹‹ሹመት ካልሠሩበት ምን ይፈይዳል?›› ስለው፣ ‹‹ምንም! ነገር ግን ያስተዛዝባል፤›› አለኝ፡፡ ሹመት ችግር ካልፈታ ፋይዳቢስነቱ ገዝፎ ታየኝ፡፡ መልካም ሰንበት! 
http://www.ethiopianreporter.com/component/content/article/304-delalaw/8720-2012-12-01-09-38-08.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር