የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀን በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከትናንት ጀምሮ በድምቀት አየተከበረ ነው


ሃዋሳ ህዳር 22/2005 ህገ መንግሰቱ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የተጀመረውን የፀረ ድህነት ዘመቻና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ራዕይ ከዳር ለማድረስ ህብረተሰቡ በጋራ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት አስገነዘቡ ። ለሰባተኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዩኒቨርሲቲው ግቢ ከትናንት ጀምሮ በተለያየ ዝግጅት በድምቀት እየተከበረ ነው ። ፕሬዚዳንቱ ዶክተር ዮሰፍ ማሞ በአሉን አስመልክቶ የተዘጋጀውን የፓናል ውይይት ሲከፍቱ እንደተናገሩት ህገ መንግስቱ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ድህነትን ለማስወገድና በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተቀየሱ የልማት ራዕዮችን ለማሳካት ሁሉም በጋራ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል። የክልሉ ህዝብና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በህገ መንግሰቱ የተጎናፀፈውን ራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነት በመጠቀም ባለፉት ሃያ አንድ አመታት በርካታ የልማት ድሎችን ሊያስመዘግብ መቻሉን አስታዉቀዋል ። በሀገሪቱ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ልማት በማስመዝገብ ድህነት ለማስወገድ ለተያዘው እቅድ መሳካት ሁሉም በየተሰማራበት ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል። በአሉ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ሲያነሱት የነበረው የነፃነትና የእኩልነት መብት ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ዕለት በመሆኑ በአሉ ለዘላለም ሲዘከር ይኖራል ብለዋል ። የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፌ ጉባኤ አቶ መሃመድ ረሽድ በበኩላቸዉ በሀገሪቱ ሁሉም አከባቢ እየተካሄዱ ያሉትን የልማት ጅምሮች በማፋጠን ዋንኛ ጠላት የሆነውን ድህነት ድል ለመንሳት የሁሉም አካላት የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል። የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀር ላይ የመሰረቱትን አንድነታቸውን በማጠናከር ባለፉት አመታት በድህነት ላይ በጋራ በከፈቱት ዘመቻ በርካታ አኩሪ ድሎችን ማስመዝገብ መቻላቸውን ተናግረዋል። በሀገሪቱ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች የመሰረተ ልማት ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶች ህገ-መንግስቱ ያስገኛቸው ትሩፋቶች በመሆናቸው እነዚህ ድሎች ሳይቋረጡ ለማስቀጠል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ አመራር፣ ተማሪዎችና የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡ በትናንትናው የፓናል ውይይት የተለያዩ የልማት ስኬቶችና በህገ መንግሰቱ ዙሪያ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን በዓሉ ዛሬም ቀጥሎ የደቡብ፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የትግራይና የታዳጊ ክልል የብሄር ብሄረሰቦች አልባሳትና ባህላዊ ትዕይንትና ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ከወጣው መርሀ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር