3ቱ የኑሮ ችግሮች


የኢህአዴግና የተቃዋሚዎች 3 የምርጫ አጀንዳዎች
የተመራቂዎች ሥራ አጥነት
በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ተመራቂዎች ሥራ አጥ ሆነዋል፤ በየአመቱ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ወጣቶች በቴክኒክና ሙያ ይመረቃሉ።
የኑሮ ውድነት ሸክም የዋጋ ንረት በአስር አመት በአምስት እጥፍ ጨምሯል። የደሞዝተኛ ሰራተኞች የኑሮ ደረጃ ደግሞ በግማሽ አሽቆልቁሏል።
የአነስተኛና ጥቃቅን ችግር
በሺ የሚቆጠሩ ወጣቶች በገበያ እጦትና በመንግስት የተንዛዛ ቢሮክራሲ ሳቢያ ከስረዋል፤ የተበደሩትን ሳይመልሱ ጠፍተዋል
በመጪው ግንቦት የሚካሄደው የአዲስ አበባ አስተዳደር ምርጫ ምን አይነት መልክ ሊኖረው እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ይከብዳል። በዚያው ጊዜ በመላ አገሪቱ በሚከናወኑት የወረዳና የቀበሌ ምርጫዎች፤ ከሞላ ጎደል ኢህአዴግና አጋሮቹ በዘጠና ምናምን ፐርሰንት እንደሚያሸንፉ አያጠራጥርም። የአዲስ አበባውም ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ግን ላይሆንም ይችላል።
የሆነ ሆኖ፤ ከምርጫው ጋር ተያይዞ፤ ለረዥም ጊዜ ጠፍቶ የነበረው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፅ ሰሞኑን ብቅ ብቅ ማለት ጀምሯል። የገዢው ፓርቲ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውዝግብም ሞቅ ሞቅ ማለቱ አይቀርም - ፉክክር መሆኑ ነው። ግን ምን ዋጋ አለው? ፉክክራቸውና ውዝግባቸው ሁሉ ያን ያህልም ከዜጎች ተጨባጭ የኑሮ ችግር ጋር ግንኙነት የለውም።
የምርጫ ንትርክና ውዝግብ
ለግለሰብ ነፃነት የተሻለ ክብር እየሰጡ፣ በስልጣኔ ጎዳና ደህና የተራመዱ አገራት ውስጥ የምናየው ፉክክር ኢትዮጵያ ውስጥ ከምናየው ውዝግብ በእጅጉ ይለያል። የአሜሪካና የእንግሊዝ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በምርጫ ወቅት የሚያነሷቸው አጀንዳዎች፣ ከዜጎች ኑሮ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። በዜጎች ኑሮና ፍላጎት ዙሪያ እየተከራከሩ፣ በዜጎች ችግርና በመፍትሄ ሃሳቦች ላይ እየተፎካከሩ የምርጫ ውድድር ያካሂዳሉ። “ያኛው የዜጎች ችግር፣ ቅድሚያ ትኩረት ያሻዋል... አይ ይሄኛው ችግር ይቀድማል” እያሉ ይከራከራሉ። “እኔ ያቀረብኩት የመፍትሄ ሃሳብ ይበልጣል ... አይ፤ የኔ ሃሳብ ይሻላል” እያሉ ይፎካከራሉ። ፓርቲዎቹ በምርጫ ውድድራቸው አብዝተው የሚከራከሩትና የሚፎካከሩት፤ በዜጎች የኑሮ ችግርና በመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ነው። በአጭሩ፤ የምርጫ ውድድሩ ዋነኛ አጀንዳ፣ “የዜጎች ኑሮ” ይሆናል - በሰለጠኑት አገራት።
በእርግጥ በኛ አገርም፤ ለምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች እንደነገሩ ለወጉ ያህል አነሰም በዛም “ይከራከራሉ፤ ይፎካከራሉ” ይባል ይሆናል። ነገር ግን፣ “ክርክራቸውና ፉክክራቸው”፣ በዜጎች ኑሮና ችግር ላይ ወይም በመፍትሄ ሃሳቦች ዙሪያ አይደለም። በራሱ በምርጫ ጉዳይ ነው የሚነታረኩትና የሚወዛገቡት። ምርጫውን ራሱ፣ ዋነኛ የምርጫ አጀንዳ ስለሚያደርጉት፤ “ክርክርና ፉክክር” ሳይሆን፤ “ንትርክና ውዝግብ” ገንኖ ይወጣል።
ድሮም፣ በግለሰብ ነፃነት ላይ ያልተመሰረተ ኋላቀር ፖለቲካ፣ ከንትርክና ከውዝግብ ውጭ ሊሆን አይችልም። እንዴት አትሉም? ለግለሰብ ነፃነት ብዙም ክብር የማይሰጥ ገዢ ፓርቲ፤ ነፃ ምርጫዎችን የማካሄድ ፍላጎቱ ዝቅተኛ ነው። ምርጫዎች የስልጣን ማራዘሚያ መሳሪያ ሆኖ የሚታየው ከሆነ፤ ዜጎችን በአፈናም በጫናም ለመቆጣጠር ይጥራል። ተቃዋሚዎችን በዛቻም በወከባም መፈናፈኛ ያሳጣቸዋል። በዚያው ልክ፤ ለግለሰብ ነፃነት ብዙም ዋጋ ለማይሰጡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ የምርጫ ውድድር ምን ሆኖ እንደሚታያቸው አስቡት። የምርጫ ውድድር ማለት፣ እያንዳንዱ ዜጋ በነፃነት ሃሳቡን የሚገልፅበትና ድምፁን የሚሰጥበት መድረክ ነው? ወይስ የምርጫ ውድድር በአመዛኙ የአመፅ ሰበብ ሆኖ ይታያቸዋል?
ያው የምርጫ ውድድር በመጣ ቁጥር፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምሬታቸውን ይገልፃሉ - “የገዢው ፓርቲ አፈናና ወከባ በዛብን፤ ምርጫው ነፃ አይደለም” እያሉ። ገዢው ፓርቲም እንዲሁ ያማርራል - “ተቃዋሚ ፓርቲዎች አመፅ ይሰብካሉ፤ ስርዓቱን ለማፍረስ ይፈልጋሉ” እያለ። ንትርኩና ውዝግቡ እስከ ምርጫው እለት ይቀጥላል።
በእርግጥ፤ ከምርጫው ጋር የተያያዙ የአፈናና የወከባም ሆነ የአመፅ ጉዳዮች አይነሱ ማለቴ አይደለም። መነሳት አለባቸው። ነፃ ምርጫ እንዲካሄድ፤ አፈናና ጫና፣ ወከባና እስር መቆም አለበት። ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ፣ አመፅ መቅረት ይኖርበታል። ለነገሩ አሁን አሁን እንኳ ስለ አመፅ የሚናገር ይቅርና ሰላማዊ ሰልፍ የሚጠራ ተቃዋሚ ፓርቲም ያለ አይመስልም። ቢሆንም ግን፤ ጨርሶ ጉዳዩ መነሳት የለበትም ብሎ መናገር ያስቸግራል። እናም ይሁን ... በምርጫ ውድድር ውስጥ፤ አፈናንና ወከባን እንዲሁም አመፅን በማውገዝ ላይ ያተኮሩ፤ ከምርጫ ጋር የተያያዙ አጀንዳዎች ይኑሩ። ነገር ግን፤ ምርጫው በእነዚህ አጀንዳዎች ታጥሮ የንትርክና የውዝግብ ሰርከስ መሆን አይገባውም። ከዜጎች ህይወት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ሌሎች አጀንዳዎችን የማንሳትና የማስተጋባት ልምድም ሊኖረን ይገባል። ለዚህም ነው፤ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊከራከሩባቸው የሚገቡ ሦስት ዋና ዋና የኑሮ አጀንዳዎችን መርጬ የማቀርበው።

መፍትሄ የናፈቃቸው የኑሮ ችግሮች
ፅሁፌ ውስጥ በርከት ያሉ ቁጥሮችን ስትመለከቱ ቅር እንዳይላችሁ። ደግሞስ ቁጥርን ጠልተን የት እንደርሳለን! ኑሯችንኮ በቁጥሮች የተሳሰረ ነው። የሥራ ሰዓት በቁጥር፤ ግዢና ሽያጭ በቁጥር፤ ደሞዝና አስቤዛ በቁጥር፣ ትርፍና ኪሳራ በቁጥር፣ የዋጋ ንረትና ሥራ አጥነት በቁጥር... ቁጥር ሳንጠቀም ውለን አናድርም። ቢሆንም ግን፤ ሦስቱን አጀንዳዎች አስተሳስረን ለማገናዘብ የሚረዱ መረጃዎችን የማቀርብላችሁ፤ በተቻለ መጠን የቁጥር ጋጋታ ሳላበዛ ነው። ማዕከላዊ የስታትስቲክስ ኤጀንሲ፤ “የምርት ተቋማት”ን በሚመለከት ካሰራጫቸው ሪፖርቶች ልነሳ።
በነገራችን ላይ፤ በኤሌክትሪክ ወይም በነዳጅ የሚንቀሳቀስ አንዳች መሳሪያ ተጠቅሞ የሚያመርትና ለገበያ የሚያቀርብ ተቋም ሁሉ፤ የምርት ተቋም ይባላል። የሰራተኞቹ ቁጥር ከአስር በታች ከሆነ፣ አነስተኛ የምርት ተቋም ተብሎ ይጠራል - በአብዛኛው የሰራተኞቻቸው ብዛት ከሶስት አይበልጥም። መበየጃ ተጠቅሞ የብረት በርና መስኮት የሚሰራ፤ እንጀራና ዳቦ መጋገሪያ፤ ወፍጮ ቤት የመሳሰሉ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ለምሳሌ በ94 ዓ.ም በመላ አገሪቱ ከነበሩት 32 ሺ ገደማ አነስተኛ የምርት ተቋማት መካከል 27ሺ ያህሉ ወፍጮ ቤቶች እንደነበሩ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርት ያሳያል።
ያኔ፣ በአነስተኛ የምርት ተቋማት ውስጥ ይሰሩ ከነበሩ መቶ ሺ ገደማ ሰራተኞች መካከል 45ሺ ያህሉ ያለ ደሞዝ የሚሰሩ ነበሩ - የቤተሰብ አባላት ናቸውና። ደሞዝ የሚከፈላቸው 55ሺ ሰራተኞች በአማካይ 120 ብር የወር ደሞዝ እንደሚያገኙ በወቅቱ የወጣው መረጃ ያመለክታል (የ1994 ዓ.ም REPORT ON SMALL SCALE MAIYUFACTURING INDUSTRIES SURVEY)። ከጠቅላላው ሰራተኛ ውስጥ በቴክኒክና ሙያ ወይም በከፍተኛ ትምህርት የተመረቁ ሰራተኞች፤ 2ሺ አይሞሉም ነበር (ገፅ 28)።
እንግዲህ፤ በ1994 ዓ.ም የአነስተኛ የምርት ተቋማት ብዛት፤ የሰራተኞቻቸው ቁጥር፤ የትምህረት ብቃታቸው ደረጃ፤ የደሞዛቸው መጠን አየን። “ከስድስት አመት በኋላስ የአነስተኛ የምርት ተቋማት እድገት የት ደረሰ?” ብለን እንጠይቅ። የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርት ላይ ምላሹን እናገኛለን - (የ2000 ዓ.ም REPORT ON SMALL SCALE MANUFACTURING INDUSTRIES SURVEY)።
በስድስት አመታት፣ የተቋማቱ ቁጥር በአስር ሺ ስለጨመረ 43ሺ ደርሷል። የሰራተቹ ቁጥር ደግሞ 140ሺ ሆኗል። በእርግጥ ስልሳ ሺ ያህሉ ደሞዝ የማይከፈላቸው የቤተሰብ አባላት ናቸው። ሰማኒያ ሺዎቹ ደግሞ፣ ቋሚ ወይም ጊዜያዊ ደሞዝተኞች ናቸው - በአማካይ በወር 240 ብር የሚከፈላቸው። በቴክኒክና ሙያ ወይም በከፍተኛ ትምህርት የተመረቁ ሰራተኞች ቁጥር ከአርባ ሺ በላይ ሆኗል።
ግራ አያጋባም? በቴክኒክና ሙያ ተመርቆ በሶስት መቶ ብር በታች ደሞዝ የሚከፈለው ወጣት ይታያችሁ። በስድስት አመታት ውስጥ በቴክኒክና ሙያ ወይም በዩኒቨርስቲ የተመራቁ ሰራተኞች ቁጥር፣ ከሃያ እጥፍ በላይ ቢጨምርም፤ የሰራተኞች አማካይ የወር ደሞዝ ግን በ120 ብቻ ነው የጨመረው (ከ120 ወደ 240 ብር)። ለነገሩ ይህንን የደሞዝ ለውጥ፣ እንደ ጭማሪ ከቆጠርነው ተሳስተናል።
ለምን ቢባል፣ በእነዚያ ስድስት ዓመታት ውስጥ የዋጋ ንረት በእጥፍ ጨምሯል። ስለዚህ፤ በ1994 ዓ.ም የነበረው 120 ብር የወር ደሞዝ እና በ2000 ዓ.ም የነበረው 240 ብር የወር ደሞዝ እኩል ናቸው። የሰራተኞቹ ኑሮ አልተለወጠም ማለት ነው። የተለወጠ ነገር ቢኖር፤ አብዛኞቹ ደሞዝተኛ ሰራተኞች የቴክኒክና ሙያ ወይም የዩኒቨርስቲ ምሩቃን መሆናቸው ብቻ ነው። ነገር ግን ምሩቃን በመሆናቸው ምክንያት ከቀድሞዎቹ ሰራተኞች የተሻለ ክፍያና የተሻለ ኑሮ አላገኙም። ቢሆንም፤ ቢሆንም... “ደሞዝ አነስ፣ ተምረን እንዳልተማረ ሆንን” ብለው ባያማርሩ ይሻላቸዋል። የባሰምኮ አለ። ብዙ ተመራቂዎች ስራ አጥ ሆነዋላ። በዚያ ላይ በየአመቱ በቴክኒክና ሙያ የሚመረቁ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የሥራ አጡን ጎራ ይቀላቀላሉ። በእርግጥ ትምህርቱና ስልጠናው አስተማማኝ ስላልሆነ፤ “መመረቅ” ማለት የሙያ ባለቤት መሆን ማለት አይደለም። ከተመረቁት መካከል ሩብ ያህሉ ናቸው የሙያ ብቃት መመዘኛ የሚያልፉት። ለማንኛውም፣ በስድስት አመት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በቴክኒክና ሙያ ተመርቀዋል። ነገር ግን፤ ቢበዛ ቢበዛ አርባ ሺ ያህሉ ብቻ ናቸው በአነስተኛ የምርት ተቋማት ውስጥ ስራ ያገኙት (በአማካይ በአመት ሰባት ሺ ተመራቂዎች ብቻ ማለት ነው)። ታዲያ ሌሎቹ ተመራቂዎችስ ሌላ ምን እድል አላቸው? ምናልባት መካከለኛና ትላልቅ የምርት ተቋማት ውስጥ ሥራ ያገኙ ይሆን?

የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት
እንግዲህ አነስተኛ የሚባሉትን የምርት ተቋማት አይተናል - ከአስር በታች ሰራተኞችን የያዙ ናቸው። መካከለኛና ትላልቅ የምርት ተቋማት የሚባሉት ደግሞ አስር ወይም ከዚያ በላይ ሰራተኞች የያዙ ተቋማት ናቸው። እነዚህ ተቋማትስ በስድስት አመታት ውስጥ ለምን ያህል ሰራተኞች የስራ እድል ፈጠሩ? የማዕከላዊ ስታትስቲክስ የ1994 ዓ.ም ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ መካከለኛና ትላልቅ ተቋማት ውስጥ መቶ ሺ ሰራተኞች ነበሩ - በአማካይ በወር 630 ብር የሚከፈላቸው (ገፅ 24)።
ከስድስት አመት በኋላ በ2000 ዓ.ም ግን የሰራተኞቹ ቁጥር በ30 ሺ ገደማ ጨምሯል - ወደ 130 ሺ። በወር የሚያገኙት አማካይ ደሞዝ 1060 ብር እንደነበረም የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን የ2000 ዓ.ም ሪፖርት ያመለክታል (ሰንጠረዥ 3.6)።
ሁለት ነገሮችን አስተውሉ። አንደኛ ነገር፤ በስድስት አመታት ውስጥ የሰራተኞች አማካይ ደሞዝ የጨመረ ይመስላል እንጂ፤ በተቃራኒው የሰራተኞቹ የኑሮ ደረጃ ወደ ታች ወርዷል። ለምን ቢባል፤ በስድስቱ አመታት ውስጥ የዋጋ ንረት በእጥፍ ጨምሯል። የሰራተኞቹ አማካይ የወር ደሞዝ ግን በእጥፍ አልጨመረም። እናም ኑሯቸው በዚያው ልክ ዝቅ ብሏል ማለት ነው።
ሁለተኛ ነገር፤ በስድስት አመታት ውስጥ ለ30 ሺ ተጨማሪ ሰዎች ብቻ ነው የሥራ እድል የተፈጠረው (በአመት 5ሺ ያህል ማለት ነው)። ከ2000 ዓ.ም ወዲህ ያለውን መረጃ ስንመለከትም ተመሳሳይ ውጤት ነው የምናገኘው። ነሐሴ ወር ላይ በማእከላዊ ስታትስቲክስ የተለቀቀውን የመካከለኛና የትላልቅ አምራች ተቋማት የ2003 ዓ.ም ሪፖርት ተመልከቱ። የተቋማቱ የሰራተኞች ቁጥር ወደ 170 ሺ አድጓል። አማካይ የሰራተኞች የወር ደሞዝ ደግሞ ወደ 1330 ብር ጨምሯል። የደሞዛቸው መጠን ከ1994 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር በአስር አመት ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል ማለት ይቻላል። ነገር ግን በእነዚያ አስር አመታት ውስጥ የብር የመግዛት አቅም ክፉኛ ተሸርሽሮ የዋጋ ንረት በአራት እጥፍ ጨምሯል። ምን ማለት ነው አትሉም?
ያኔ በ1994 ዓ.ም ገበያ ወጥተን በ630 ብር እንገዛቸው የነበሩ ነገሮች፤ በ2003 ዓ.ም ዋጋቸው ከ2400 ብር በላይ ሆኗል። በሌላ አነጋገር፤ የሰራተኞች ደሞዝ በእጥፍ ቢጨምርም እንኳ የዋጋ ንረት በአራት እጥፍ ስለጨመረ፤ የሰራተኞቹ የኑሮ ደረጃ በግማሽ ቀንሷል ማለት ነው። ብር ስለረከሰ የዛሬ ደሞዛቸው ... ከአስር አመት በፊት ከነበረው 300 ብር ጋር እኩል ነውና።እንግዲህ የዜጎች ኑሮ፤ በተለይ ደግሞ የሙያተኞችና የከተሜዎች ኑሮ ባለፉት አስር አመታት ምን ያህል እንደተደቆሰ ለማየት፤ ከዚህ የማዕከላዊ ስታትስቲክ መረጃ የተሻለ ግልፅ ማስረጃ የሚገኝ አይመስለኝም። የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፣ ዋነኛው የምርጫ አጀንዳ መሆን የሚገባውም በዚህ ምክንያት ነው። ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የኑሮ ውድነትን ዋነኛ አጀንዳ ካላደረጉት፤ ከዚያም ግልፅና አሳማኝ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማቅረብ ካልሞከሩ... በእርግጥም ከዜጎች ኑሮ በእጅጉ ተራርቀዋል ማለት ነው።ሁለተኛው አጀንዳ፤ ከኑሮ ችግር ጋር የተያያዘው የሥራ አጥ ተመራቂዎች ጉዳይ ነው። የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲሁም የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሄድም፤ ያንን የሚመጥን የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ እድገት ስላልተፈጠረ ብዙዎቹ ተመራቂዎች ሥራ አጥ እየሆኑ ነው። የመንግስት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ሰነድ እንደሚያሳየው፤ በ97 ዓ.ም መቶ ሺ ገደማ የነበረው የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞች ቁጥር፣ በ2002 ዓ.ም ወደ ሰባት መቶ ሺ ደርሷል። በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች 80ሺ ገደማ የነበረው የተማሪዎች ቁጥርም ወደ 190ሺ የሚጠጋ ሆኗል። ባለፉት ሦስት አመታትም በቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲሁም በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የተማሪዎች ቁጥር ስለጨመረ፤ የቴክኒክና ሙያ ተመራቂዎች ቁጥር በአመት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ሆኗል። የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች ቁጥርም በተመሳሳይ መንገድ በአመት ወደ መቶ ሺ እየተጠጋ መጥቷል።የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲሁም የዩኒቨርስቲ ትምህርት፤ በአብዛኛው ለምርት ተቋማት በሚያመች መንገድ (ለአነስተኛ፣ ለመካከለኛና ለትላልቅ አምራቾች የሚጠቅም መንገድ) እየተቃኘ እንደሆነ ይናገራል መንግስት። የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ገፅ 74 መመልከት ትችላላችሁ። አብዛኞቹ ተመራቂዎችም በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ለሥራ ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ማለትም በአነስተኛ፣ በመካከለኛና በትላልቅ አምራች ተቋማት ውስጥ የስራ እድል ያገኛሉ፤ ወይም ተመራቂዎቹ ራሳቸው ተቋማቱን በመመስረት የስራ እድል ይፈጥራሉ። ታዲያ እንዲህ በእቅድ የሰፈረው ሃሳብ፤ በተጨባጭ እውን ሆነ? አልሆነም። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ አመታዊ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በእነዚህ ተቋማት ውስጥ በአማካይ በየአመቱ የሚፈጠረው የሥራ እድል ቢበዛ ከ20ሺ አይበልጥም። ለአብዛኛው ተመራቂ የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብለው የሚጠበቁት የምርት ተቋማት፤ እንዲህ 5 በመቶ ያህሉን ተመራቂ እንኳ ማስተናገድ አልቻሉም ማለት ነው። ታዲያ በየአመቱ እየተመረቀ የሚወጣው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ወጣት የት ይገባል? ከአመት አመት ሥራ አጥ ተመራቂ በተበራከተ ቁጥር፤ የዚያኑ ያህል አደጋው እያበጠ ይመጣል። አብጦ አብጦ ከመፈንዳቱ በፊት መፍትሄ ሊበጅለት ስለሚገባ፤ በመጪው ምርጫ ትልቅ የመከራከሪያና የመፎካከሪያ አጀንዳ መሆን ይገባዋል።
ሦስተኛው አጀንዳ፣ የኑሮ ችግርንና ሥራ አጥነትን እንደሚያቃልሉ የሚነገርላቸው ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ላይ ማተኮር አለበት - በከፍተኛ ችግሮች የተከበቡ ናቸውና። በእርግጥ፣ የተወሰኑ ሰዎችና ተቋማት እንደየትጋታቸው ሲሳካላቸውና ሲመነደጉ ይታያል። ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት እንዲስፋፉ፣ መንግስት በየአመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር በጀት፣ ብድር እና ድጋፍ ሲመድብ መቆየቱም አይካድም። ነገር ግን፤ የተወራላቸውን ያህል ጉልህ ለውጥ አላስገኙም።
አልፎ አልፎ ከሚታየው የጥቂት ታታሪ ሰዎች ስኬት በስተቀር፤ እቅዱ እንደታሰበው አለመሳካቱንና በርካታ ገንዘብ መባከኑን መንግስት ራሱ ያምናል። መንግስት የማምረቻ መሳሪያዎች ገዝቶ ለበርካታ ወጣቶች ቢያከፋፍልም፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በየቦታው ተጥለው ባክነዋል። በአንድ ቀበሌ ብቻ፤ ብድር ወስደው ያልመለሱ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ሥም ዝርዝራቸው በአደባባይ ተለጥፎ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። ከሳምንት በፊት በፓርላማ በተካሄደ ስብሰባ፤ ብድር ለማስመለስ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት የፓርላማ አባላት ማሳሰቢያ ሲሰጡ የተመለከትነው ለምን ሆነና!
ድሮም ቢሆን መንግስት ብድርና ድጋፍ እሰጣለሁ ብሎ የቢዝነስ ስራ ውስጥ ሲገባ፤ የገንዘብ ብክነት መፈጠሩ አይቀሬ ነው። በዚያ ላይ፤ የመንግስትን ድጎማና ድጋፍ የለመደ እጅ፤ እድሜ ልክ በጥገኝነት ለመቀጠል ይመኛል እንጂ ራሱን ችሎ የመስራት ልምድ አያዳብርም። ይህም ብቻ አይደለም። የመንግስት አሰራር በተፈጥሮው በተንዛዛ ቢሮክራሲ የተተበተበ በመሆኑ፤ ወቅቱንና ጊዜውን ጠብቆ ክፍያ አይፈፅምም። የሥራ መንፈስን ይደገድላል። እናም እንደታቀደው አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ተስፋፍተው አልተጠናከሩም። ታዲያ በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ዙሪያ የሚታየውን የገንዘብ ብክነት፤ ጥገኝነትና ስራ አጥነት ማስወገድ የለብንም? ዜጎች የሥራ መንፈሳቸው ተነሳስቶ የሥራ እድል እንዲፈጥሩና በራሳቸው ጥረት ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ መንገዱን ማስተካከል አይኖርብንም? የመጪው ምርጫ ሶስተኛ አጀንዳ፤ በአነስተኛና ጥቃቅን የቢዝነስ ተቋማት ዙሪያ መሆን ያለበትም በዚህ ምክንያት ነው።
http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=5262:3%E1%89%B1-%E1%8B%A8%E1%8A%91%E1%88%AE-%E1%89%BD%E1%8C%8D%E1%88%AE%E1%89%BD&Itemid=22

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር